
የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከአስር ዓመት በፊት ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው በተለያዩ ዓለምአቀፍ የስፖርት መድረኮች ስፖርተኞች በዘርና በቆዳ ቀለማቸው መገለል የተለመደ እንደሆነ ያትታል። ይህ እውነታ አሁን ላይ አደጉ በምንላቸው አገራት ስፖርት ላይ እንኳን ነቀርሳ መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች እንመለከታለን። በተለይም እንደ አሜሪካ፤ አውስትራሊያና አውሮፓ የመሳሰሉ አገራት ላይ ጥቁር ስፖርተኞች አሁንም ድረስ በዘረኝነት ሲዘለፉ፤ ሲንቋሸሹና ዝቅ ተደርገው የሚታዩባቸው አጋጣሚዎች እየተበራከቱ መምጣታቸው ከዘር፤ ከሃይማኖትና ከፖለቲካ ነፃ መሆን የሚገባው ስፖርት ላይ መጥፎ አሻራ እንዲያርፍ እያደረገ ይገኛል።
በስፖርት ጥቁሮች አሁን ላይ በየትኛውም ዓለምአቀፍ መድረክ ተፎካካሪ እንዲሆኑ ከማስቻል ባሻገር በትልቅ ደረጃ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ለማሳየት በርካታ ጥቁር ከዋክብት ብዙ ችግሮችን ተጋፍጠዋል። በተለይም ጥቁር አሜሪካውያን አትሌቶች በዚህ ረገድ ያዩት ፈተና ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም። አፍሪካውያንም ቢሆኑ በርካታ መከራዎችን ተጋፍጠው ለታላቅ ክብር በመብቃት ለአሁኖቹ አትሌቶች ፋና ወጊ ሆነው እኩልነትን ማንፀባረቃቸው አይካድም። ለዚህም ታሪካዊውን ኢትዮጵያዊ የማራቶን ኮከብ አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ በትልቁ የሚነሳ የጥቁር ህዝቦች ኩራት ሆኖ እናገኘዋለን። ኢትዮጵያውያን በስፖርቱ ብቻም ሳይሆን በዓደዋ ድል የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌትና የመዓዘን ድንጋይ ሆነዋል። የጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነው የዓደዋ ድል የሚዘከርበት የካቲት ወር በመላው ዓለምም የጥቁር ህዝቦች መታሰቢያ ሆኖ ይከበራል። በስፖርቱ ዓለም ለእኩልነት የታገሉ ቁንጮ አትሌቶችም በዚህ ወር ሳይዘከሩ አይታለፉም። በእርግጥ በስፖርት መድረክ ዘረኝነትን የታገሉ፤ እኩልነትን ያንፀባረቁና በድላቸው የጥቁር ህዝቦችን አንገት ያቀኑ በርካታ ጥቁር ከዋክብቶች መኖራቸው አይካድም። ከእነዚህ ከዋክብቶች ግን ተፅዕኗቸው ከፍተኛ የነበረ፤ ድላቸው በርካታ ትርጉም የነበረውና በትልቅ ደረጃ የሚነሱትን ሦስት ጀግኖች ብቻ በዓድዋ ድል ዋዜማ ላይ ሆነን በስፖርት ማህደር አምዳችን እንመልከት።
አበበ ቢቂላ
1928 ፋሺስት ጣሊያን በአምባገነኑ ቤኒቶ ሞሶሎኒ ኢትዮጵያን ወረረ፤ ምስጋና ለማይዘነጉት ጀግኖቹ አርበኞቻችን ይግባና ሞሶሎኒና ግብረአበሮቹ ብዙም ሳይደላደሉ ከአገር ቤት በቅሌት ተባረሩ። ከሃያ አራት ዓመታት በኋላ ታላቁ አበበ ቢቂላ ሮምን በባዶ እግሩ ወሮ ዓለምን ጉድ አሰኘ፤ የምን ጊዜም የማራቶን ንጉሡ የአፍሪካውያን ኩራትና የነፃነት ተምሳሌት እንዲሁም፤ የመጀመሪያው ጥቁር የማራቶን ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ በጥቁሮቹ በጀግኖቹ መታሰቢያ ወር የካቲት የጥቁር ህዝቦች ኩራት ሆኖ ከሃምሳ አምስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት ዋዜማ በሮም ኦሊምፒክ የፈፀመው ታሪካዊ ጀብድ በመላው ዓለም ያሉ ጥቁር አትሌቶችን በእጅጉ ያኮራና ያነሳሳ ነበር። ጷግሜ 5ቀን 1952 አስራ ሰባተኛው የሮም ኦሊምፒያድ በታላቋ ሮም ጎዳናዎች አንድ ተዓምር ታየ፤ በርካቶች ዓይናቸውን ለማመን ተቸገሩ፤ በአንባገነኑ ሞሶሎኒ አገር በበርካታ ነጮች መሃል አንድ ጥቁር በባዶ እግሩ ታየ። የጥቁር ህዝቦች ተዓምርን ለመቀበል የሚተናነቃቸው ዘረኝነትን በደማቸው ያሰረፁ ነጮች እንዴት ይህ ሊሆን እንደቻለ ግራ ተጋቡ። አፍሪካውያንን ያኮራ ኢትዮጵያውያንን ከልብ ያስፈነጠዘ ታሪካዊ ድል። የአራት ዓመት ታዳጊ ሆኖ እናት አገሩ ኢትዮጵያ በጣሊያን ፋሺስት ስትወረር መጥፎውን ጊዜ ገና ባልጎለበተ የሕፃን አዕምሮው የሚያስታውሰው አበበ ቢቂላ ሃያ ስድስት ዓመታት ጠብቆ ታላቁን የሮም ጎዳና በባዶ እግሩ ወሮ የማይደገመውን ታሪክ ሠራ። ከአራት ዓመት በኋላም 1956 በድጋሜ ጫማ አጥልቆ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር አሸንፎ ጥቁሮች በማይደፈረው ርቀት አሁን ላይ ቁንጮ እንዲሆኑ መሰረቱን አኖረ። እሱ በከፈተው በርም ቁጥር ስፍር የሌላቸው የማራቶን አትሌቶች ለዘመናት ርቀቱን የግላቸው አድርገው አሁን ድረስ ዘልቀዋል።
ጄሴ ኦውንስ
ታላቁ የስፖርት መድረክ ኦሊምፒክ እንደ 1936ቱ በዘረኝነት የተጨማለቀበትን ወቅት ማስታወስ ከባድ ነው። ገና ከጅምሩ አይሁዶችንና ጥቁሮችን ከኦሊምፒኩ ለማግለል እንዲሁም የነጮችን የበላይነት አስተሳሰብ የመደገፍ አባዜ የተጠናወተው ዘረኛው የናዚ መሪ አዶልፍ ሂትለር ውድድሩ በአገሩ ጀርመን እንደሚካሄድ ካወቀ አንስቶ ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም። ይህ ኦሊምፒክ ብዙ ተቃውሞ ቢገጥመውም ከውድድሩ ራሳቸውን ያገለሉና እንዳይሳተፉ የተደረጉ አይሁዳውያን ነበሩ። በውድድሩ የተሳተፉትም ቢሆኑ በሂትለር ትዕዛዝ የተገለለ የመለማመጃ ሜዳና የውድድር ቁሳቁስ እንዲጠቀሙ ተደርገዋል። ጥቁሮችም በዚህ ኦሊምፒክ ተመሳሳይ ዕጣ ፋንታ የገጠማቸው ሲሆን የበታች እንደሆኑ ለማሳየት ያልተደረገ ጥረት አልነበረም። ይህን ጥረት ሁሉ ውድቅ አድርጎ የሂትለርን ቆሽት ያሳረረ አንድ ክስተት ግን በጥቁሩ አሜሪካዊ አትሌት ጄሴ ኦውንስ ተፈፀመ። ኦውንስ በዚህ የበርሊን ኦሊምፒክ በመቶ፤ በሁለት መቶ፤ በረጅም ዝላይና አራት በመቶ የዱላ ቅብብል ውድድሮች አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ጠራርጎ በመውሰድ ጥቁሮች አንገታቸውን ያቀኑበት ነጮች ደግሞ የተሸማቀቁበትና ለመቀበል ያቃራቸውን ድል አጣጣመ። ይህ አልዋጥለት ያለው ሂትለር ግን በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ ኦውንስን ላለመጨበጥና ለድሉም እውቅና ላለመሰጠት ራሱን አሳምኖ ስቴድየሙን በድንፋታ ለቆ ወጣ። የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልትም ቢሆኑ ለኦውንስ ድል እውቅና ሳይሰጡት ቀርተዋል። ኦውንስ ይህ ገድሉ በዘረኛ ነጮች እውቅና ይነፈገው እንጂ ነጮች ወደዱም ጠሉም ከጥቁሮች እኩል እንደሆኑ ልቦናቸው እንዲያምን አስገድዷቸዋል። በአንድ አገር ውድድሮች የነጭና የጥቁር ተብሎ ተከፍሎ በሚካሄድባት አሜሪካም በወቅቱ የኦውንስ ድል ትልቅ ትርጉም ነበረው። በዚህም ኋላ ላይ እኤአ 1976 የአሜሪካውያን ትልቁ ሽልማት የሆነውን የነፃነት ሜዳሊያ ሊሸለም በቅቷል። ኦውንስ ህይወቱን በሙሉም የጥቁሮች መብት እንዲከበር ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ጥብቅና ከመቆም ባሻገር የእሱን ፋና ተክለው ለመጡ ጥቁር አትሌቶች ሁሉ ትልቅ የመንፈስ ብርታት በመሆን ከጎናቸው ሲቆምና ሲሟገት ኖሯል።
መሐመድ አሊ
የምን ጊዜም የቦክስ ስፖርት ንጉሡ መሐመድ አሊ የዓለም የቦክስ ቻምፒዮንና ታላቅ የቡጢ ተፋላሚ ብቻ አልነበረም። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፤ የጥቁር ህዝቦች ሰንደቅ፤ በመላው ዓለም በስፖርትና በታላቅ ስብዕና ተምሳሌትም ጭምር ነው። ብዙዎች ቦክስ ስፖርት ሳይሆን የጥጋበኞች ድብድብ አድርገው ከመሳል አስተሳሰብ አውጥቶ የቦክስን ስፖርት ጥበባዊ ገፅታ በማላበስ ተወዳጅና አሁን ላይ በዓለማችን በአንድ ጊዜ በርካታ ሚሊየን ዶላሮች የሚያሳቅፍ ግንባር ቀደም ስፖርት እንዲሆን ተፅዕኖውን አሳርፏል። መሐመድ የትውልድ ስሙ ካሴስ ክሌይ ቢሆንም በ19ኛው ክፍለ ዘመን ባሮችን ነፃ ለማውጣት በታገሉ ታላቅ ሰው መታሰቢያነት የወጣለት ስም ነበር፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ የዓለም ከባድ ሚዛን ቻምፒዮን ከሆነ በኋላ በማግስቱ ስሙን ለመቀየር ወሰነ፡፡ የነፃነት ታጋዩን ማልኮለም ኤክስ ከጎኑ አድርጎ በሰጠው መግለጫ «ዘ ኔሽን ኦፍ ኢስላም» የተባለውን ተቋም መቀላቀሉን በማሳወቅ የባርያ ስም ይለው የነበረውን ካሴስ ክሌይ በመቀየር በቀድሞ ስሙ ላለመጠራት ወሰነ። በወቅቱ «ኔሽን ኦፍ ኢስላምን» ይመራ የነበረው ኤልጅያህ መሃመድ እኤአ በ1964 ላይ መሐመድ አሊ የሚለውን ስም ካወጣለት በኋላ እሱን በማፅደቅ እስከ ህይወት ዘመኑ መጨረሻ ተጠራበት። ታሪካዊው ኢትዮጵያዊ አትሌት አበበ ቢቂላ በ196o የሮም ኦሊምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ ለጥቁር ህዝቦች የመጀመሪያውን የማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ሲያስመዘግብ መሐመድ አሊም በቦክስ የወርቅ ሜዳሊያ አጥልቆ ነበር። ሁለቱ ታሪካዊ የጥቁር ህዝቦች ከዋክብት ፊርማቸውን ተለዋውጠውም ነበር። ይሁንና መሐመድ አሊ ይህን የወርቅ ሜዳሊያውን ለአገሩ ከማበርከት ይልቅ በሊውስ ቪል ግዛት በሚገኘው የኦሃዮ ወንዝ ጨምሮታል። ሜዳሊያውን ለአሜሪካና ለትውልድ ከተማው ሊውስ ቪል ቢቀዳጅም በርገር የመግዛት መብት ባለመኖሩ ተቃውሞውን ለመግለፅ ነበር ይህን ርምጃ የወሰደው። በ1996 አገሩ አሜሪካ ባስተናገደችው የአትላንታ ኦሊምፒክ ችቦውን እንዲለኩስ ከመደረጉ ባሻገር ወንዝ የጨመረው የወርቅ ሜዳሊያ ምትክ ሌላ ሜዳሊያ በአንገቱ ተጠልቆለታል። በ1970 የዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ መታሰቢያ ሽልማት የተቀበለው መሐመድ አሊ፤ የዓለም አቀፋዊ ወዳጅነት ተምሳሌት ሆኖም ያውቃል። የተባበሩት መንግሥታት የሰላም መልዕክተኛ ሆኖም ከ1998 እሰከ 2008 በታዳጊ አገራት በመዘዋወር አገልግሏል። ታላቁን የደቡብ አፍሪካ ነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ከእስር እንደተፈቱ በአካል ተገኝቶ ደስታውን ለመግለፅ መሐመድን የቀደመው አልነበረም።
አዲስ ዘመን የካቲት 22/2012
ቦጋለ አበበ