በመንግሥት ውሳኔ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የካቲት 17 ቀን 2012 ዓ.ም የ63 የወንጀል ተጠርጣሪ ሰዎችን ክስ ማቋረጡን ይፋ ማድረጉ በሕዝብ ዘንድ ትልቅ የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ከርሟል፡፡
በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መግለጫ መሠረት ክሱ የተቋረጠው ለሀገራዊ አንድነት እና ለለውጡ የሚኖረው ፋይዳን ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ለህዝብ እና ለሀገር ጥቅም ሲባል ነው።
ክሳቸው እንዲቋረጥ ከተደረጉ ግለሰቦች መካከልም የሜቴክ ሰዎች እና ከሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ባህርዳር እና በአዲስ አበባ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ እንዲሁም በሲዳማ ዞን ተከስቶ ከነበረው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ግለሰቦች እንደሚገኙበትም መነገሩ የሚዘነጋ አይደለም፡፡
ይህ ከተሰማ በኋላ በመገናኛ ብዙሃን ሳይቀር “መንግሥት ምህረት እና ይቅርታ አደረገ” የሚሉ የተምታቱ መግለጫዎች ሲደመጡ ተሰምቷል፡፡ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተነገረው ግን በሰዎቹ ላይ ሲካሄድ የነበረው ክስ መቋረጡን ብቻ ነው፡፡ ለመሆኑ የወንጀል ተጠርጣሪ ክስ መቼና እንዴት ነው የሚነሳው? ይቅርታ ምንድነው? ምህረትስ? አንዳንድ ጉዳዮችን እንመልከት፡፡
ክስ ስለማቋረጥ፣
ውብሸት ሙላት፤ አቢሲኒያ ሎው በሚል ድረገጽ ላይ እንዳሰፈሩት ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክስ እንዳይጀመር ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ሊያዝ እንደሚችል ከወንጀልኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ በተጨማሪ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 ላይም ተደንግጓል፡፡ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 6(3)(ሀ) ላይ ስለጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ሥልጣንና ተግባር ሲገልጽ ‹‹በሕዝብ ጥቅም መነሻ… የወንጀል ምርመራ እንዲቋረጥ ወይም የተቋረጠው የወንጀል ምርመራ እንዲቀጥል ያደርጋል፤›› ይላል፡፡
በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 42(1) (መ) መሠረት ዓቃቤ ሕግ ለሕዝብ ጥቅም ሲል ክስ የመመሥረት ሒደቱን ሊያቋርጥ እንደሚችል መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ የሚሆነው ፖሊስ ምርመራውን አጠናቅቆ ሪፖርቱንም ለዓቃቤ ሕግ አስተላልፎ ነገር ግን ክስ ከመመሥረቱ በፊት ነው፡፡ ክስ ተመሥርቶ ከሆነ ግን በዚሁ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 122 አማካይነት የክስ ሒደቱን ማቋረጥ ወይም ማንሳት ይቻላል፡፡ የክሱ ሒደት እየተከናወነ እንደሆነ ዓቃቤ ሕግ ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት ክሱን ሊያነሳ ይችላል፡፡ ክሱ የሚነሳው በፍርድ ቤቱ ፈቃድ ነው፡፡
ዓቃቤ ሕግ ክስ ሲያነሳ ፍርድ ቤቱ ከመፍቀዱ በፊት ማረጋገጥ ያለበት ነገር ቢኖር ክሱ ላይ የተገለጸው የወንጀል ድርጊት በዓቃቤ ሕግ ክሱ የማይነሳ አለመሆኑን፣ እንዲሁም ዓቃቤ ሕጉ ክሱን እንዲያነሳ ከመንግሥት የታዘዘ መሆኑን ነው፡፡ በዚሁ አንቀጽ ላይ እንደተገለጸው በከባድ የግፍ አገዳደልና በከባድ የወንበዴነት ተግባር የተከሰሱ ሰዎችን ክስ ማቋረጥ ወይም ማንሳት አይቻልም። ተራ የሰው ግድያ ወይም በቸልተኝነት ሰው የመግደል ወንጀሎችን በሚመለከት ክስ ማንሳት ይቻላል፡፡
ሌላው መንግሥት ክሱ እንዲቋረጥ የወሰነ መሆኑን ማረጋገጥ የሚያስችል ማስረጃ የመኖር አስፈላጊነት ነው። የክሱን መነሳት ሲፈቅድም ወይም ሲከለክል ፍርድ ቤቱ ለውሳኔው ምክንያት የሆኑትን ነጥቦች መግለጽና መመዝገብ ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረት መንግሥት ክስ የሚያነሳበትን ምክንያት የመመርመር ሥልጣን ፍርድ ቤት የለውም፡፡ መንግሥትም በምን በምን ምክንያት ክስ ማቋረጥ እንደሚችል አልተገለጸም። በዚህ ሁኔታ የተቋረጠ ክስ አንድም በሌላ አንቀጽ መልሶና ወዲያውኑ ክስ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ከዚህ ሌላ ደግሞ የተነሳውን ክስ መልሶ በሌላ ጊዜ በዚያው ክሱ ተመሥርቶበት በነበረው አንቀጽ ክሱን መቀጠል ይቻላል። በሌላ ጊዜ የክስ ሒደቱን ማንቀሳቀስን አይከለክልም፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት ከሆነ መንግሥት ክሳቸውን በቅርቡ ያቋረጠላቸውን ሰዎችና ወደፊትም የሚያቋረጥላቸውን የዚህ ዓይነት ዕጣ ፋንታ ሊያጋጥማቸው ይችላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ክስ አለመመሥረትም ማንሳትም ቢሆን ከዚህ ሥጋት ውጭ አይደሉም፡፡
እዚህ ላይ መንግሥት ክሱ እንዲቋረጥ ዓቃቤ ሕጉን ማዘዙን ፍርድ ቤቱ ማረጋገጥ አለበት ብለናል፡፡ ለመሆኑ መንግሥት የሚለው የሚያመለክተው ማንን ነው? መንግሥትንስ ወክሎ ትዕዛዝ የሚሰጠው? የሚለውን መመለስ ተገቢ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ፍርድ ቤቱ መንግሥት ትዕዛዝ እንዳስተላለፈ የተረጋገጠ መሆኑን ለመረዳት ትዕዛዙ የተሰጠው በማን ሲሆን ነው?
ከላይ ለተገለጹት ጥያቄዎች መልስ የምናገኘው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6(3)(ሠ) ላይ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ‹‹የፌዴራል መንግሥትን በመወከል… ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ክስ ያነሳል፤ የተነሳውን ክስ እንዲቀጥል ያደርጋል፡፡ ሆኖም ጉዳዩ አገራዊ ይዘት የሚኖረው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩን በማማከር ክስ ስለሚያነሳበት አግባብ መመርያ ያወጣል፡፡›› ከዚህ ድንጋጌ የምንረዳው ክስን የሚያነሳው መንግሥት ነው ቢልም በሕግ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ውክልና መሰጠቱን ነው፡፡
ይሁን እንጂ ሁኔታው አገራዊ ይዘት ካለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመመካከር እንጂ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ብቻ ማንሳት አይቻልም፡፡ እዚህ ላይ ሁለት አይቀሬ ጥያቄዎች አሉ፡፡ አንዱ ‘ለሕዝብ ጥቅም’ ማለት ምን ማለት የሚለው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ‘አገራዊ ይዘት ያለው የሕዝብ ጥቅም’ ምን ማለት ነው የሚለው ነው። በእርግጥ ስለሁለተኛው ጉዳይ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ መመርያ ማውጣት ስለሚጠበቅበት መልሱን የምናገኘው ከሚያወጣው መመርያ ይሆናል፡፡
የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ክስ ላለመመሥረት ‘ለሕዝብ ጥቅም’ የሚል ቅድመ ሁኔታ ሲያስቀምጥ ክስ ለማንሳት ግን ምንም የተገለጸ ቅድመ ሁኔታ የለም፡፡ በአዋጁ ላይ ግን ክስ ማንሳት ወይም ማቋረጥ የሚቻለው ‘ለሕዝብ ጥቅም’ ሲባል እንደሆነ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጧል አለ፡፡ ይሁን እንጂ አዋጁም ቢሆን የሕዝብ ጥቅም ማለት ምን እንደሆነ ትርጓሜም ይሁን ማሳያዎችን አልያዘም፡፡ ስለሆነም ክሱ ላለመመሥረትም ይሁን ለማንሳት ምክንያት የሆነው ጉዳይ የሕዝብ ጥቅም ነው ወይስ አይደለም የሚለውን የሚወስነው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ነው፡፡ ክስ በሚነሳበት ወቅት ፍርድ ቤቶች የሕዝብ ጥቅም አለ ወይስ የለም የሚለውን የማጣራት ሥልጣን አልተሰጣቸውም፡፡
ከላይ እንዳየነው ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ምርመራን ለማቋረጥ በሕግ የተቀመጡ መሥፈርቶች የሉም፡፡ ክስን ለማንሳትም እንዲሁ፡፡ ነገር ግን በርካታ ተከሳሾች ክሳቸው የተቋረጠ መሆኑን እናውቃለን፡፡ በተመሳሳይ ወንጀል እንደውም በአንድ ክስ ከተከሰሱ ሰዎች ውስጥ የተወሰኑት ክሳቸው ተነስቶ የሌሎቹ ደግሞ ያልተነሳም አለ፡፡ ምናልባት ያልተነሳላቸው ለአገራዊ መግባባትና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የሚኖራቸው ሚና አነስተኛ ነው ተብሎ እንደሆነም የታወቀ ነገር የለም፡፡ እንዲህ ተብሎ ከሆነም ያው ሌላ አገራዊ አለመግባባትን ማስከተሉ አይቀርም፡፡
ረቂቅ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ ይኼንን ክፍተት በመረዳት ይመስላል ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክስ የማይመሠረትባቸውን ሁኔታዎች ዘርዝሯል፡፡ ክስ ማንሳትን በተመለከተ ግን በምን በምን ምክንያቶች ዓቃቤ ሕግ ክስ ሊያነሳ እንደሚችል ረቂቅ ሕጉም ላይ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ በረቂቅ ሕጉም ላይ ቢሆን ለአገራዊ መግባባት ወይም የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የሚሉት ወይም እነዚህን የሚመስሉ አገላለጾች በሕዝብ ጥቅም ሥር አልተካተቱም፡፡
የሕዝብ ጥቅም ምንነት ግልጽ ካልሆነ ይኼንን የመለየትና የመወሰን ፍቃድ ሥልጣን (discretion) ያለው ያው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ነው ማለት ነው፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ውሳኔ ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተቋቋመበት አዋጅ በመግቢያው ላይ ካስቀመጣቸው ግቦች ውስጥ ወጥነት ያለው አገልግሎት መስጠት፣ የሕዝብ ተዓማኒነት ያለው ለሕዝባዊ ተጠያቂነት የሚገዛ እንዲሁም በግልጽነት የሚሠራ የዓቃቤ ሕግ ተቋም ማደራጀት አስፈላጊ የመሆኑ ጉዳይ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በአዋጁ መሠረት የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተቋም ሲቋቋም ማሳካት ካለበት ግቦች መካከል ጥቂቶቹ ከላይ የተገለጹት ናቸው፡፡
ወጥነት ያለው አገልግሎት መስጠት ከተጓደለ ሕዝብ በተቋሙ ላይ የሚኖረው አመኔታ መቀነሱ አይቀሬ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ተቋሙ የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ሕዝቡ ይህ ተቋም በምን መልኩ እንደወሰናቸው የሚያውቅበት ሥርዓት ከሌለ ግልጽነት የለም ማለት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር ደግሞ አዋጁ ሲወጣ በግብነት ያስቀመጣቸው የሚፃረሩ ይሆናሉ፡፡
በዚሁ በአዋጅ አንቀጽ 11(3)(ሀ) ላይም ይህንኑ ሁኔታ አስፍሮት እናገኛለን፡፡ ዓቃቤ ሕጋዊ አሠራር ለሕዝብ ተጠያቂነትን በሚያሰፍን መልኩ መደራጀት፣ የሥራ አመዳደብ፣ የሥራ ዓይነቶቹ፣ ሥራዎቹ የሚመሩባቸው ሥርዓት ሁሉ ለሕዝብ ተጠያቂ መሆንን በሚያሰፍን መንገድ መሆን እንደሚጠበቅበት ተደንግጓል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በማይኖሩበት ወይም በሚድበሰበሱበት ወቅት ለሕዝብ ተጠያቂ አለመሆንን ያስከትላል፡፡ አንዳንድ ጉዳዮችን በሚመለከትም ሥርዓት የለሽነትም ሊያስከትል ይችላል ማለት ነው፡፡
የፍቃድ ሥልጣን አጠቃቀም በሕዝብ ዘንድ የማይገመት ሲሆን፣ ሕዝባዊ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን አሠራር እየመነመነ ሲሔድ ሕዝብ በተቋሙ ላይ የሚኖረው አመኔታ እየቀነሰ መሔዱ አይቀሬ ነው፡፡ ከላይ የጠቀስነው አዋጅ ይኼንን ሁኔታ አስቀድሞ ከግምት በማስገባት የዓቃቤ ሕግ አስተዳደር ምን መምሰል እንዳለበት በሚዘረዝርበት አንቀጽ 11(3)(ለ) ላይ እያንዳንዱ ዓቃቤ ሕግ የሥራ አፈጻጸሙ ሁሉ ሳይቀር ከሚመዘንባቸው መሥፈርቶች አንዱ በሕዝብ ዘንድ በጎ ተፅዕኖ መፍጠሩ እንዲሁም በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ያለው መሆኑ ነው፡፡
በአንቀጽ 11 ላይ የተዘረዘሩት የዓቃቤ ሕግ የውስጥ አሠራርን የሚመለከቱ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ በሚባልበት ጊዜ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉንም ምክትሎቹም እንደሚጨምር አዋጁ አንቀጽ 2(8) ላይ ተገልጿል፡፡ ስለዚህ በየትኛውም የሥልጣን ደረጃ ላይ የሚገኝ ዓቃቤ ሕግ እነዚህን አሠራሮች አበክሮ መከተል እንደሚጠበቅበት ሕጉ አስቀምጧል፡፡
ለማጠቃለል ያህል የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉን አንቀጽ 42(1)(መ) ላይ ተመርኩዞ ክስ እንዳይመሠረት የማድረጉ ሒደት እንዲሁም በአንቀጽ 122 መሠረት ደግሞ ክስን የማንሳቱ ሥራ በተመሳሳይ የወንጀል ተግባር የተጠረጠሩን፣ የተከሰሱን በአንድነት ሳይለያይ፣ ሳይነጣጥል እየተተገበረ ነው ማለት አይቻልም። ይህ ደግሞ ‹‹ከልጅ ልጅ ቢለዩ…›› ዓይነት አሠራር መሆኑ ነው። ከዚህ አንፃር የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ያስተላለፈውን አገራዊ መግባባትና የዴሞክራሲ ምህዳሩን የማስፋት ውሳኔ እንዳይሳካ እንቅፋት መሆኑ አይቀርም፡፡ የታሰበለትን ዓላማም እንዳያሳካ ጋሬጣም ይሆናል፡፡
ስለምህረት አሰጣጥ
አቶ ውብሸት ሙላት፤ በወንጀል ተከሰው የተፈረደባቸው ሰዎች ለይቅርታ ሲያመለክቱ ለይቅርታ ቦርድ ቀርቦ ካጸደቀው በኋላ በፌዴራል ደረጃ ለፕሬዚዳንቱ፤ በክልል ደግሞ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ቀርቦ እንደሚጸድቅ ያስቀምጣሉ። ምህረት ለማድረግ ግን ዝርዝር ህግ የለም። የወንጀል ህጉ አንቀጽ 230 ላይ በባለቤቱ ምህረት ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ አንድ ዓይነት ወንጀል ለፈጸሙ ወይም ደግሞ በተመሳሳይ ሁኔታ ለሚገኙ ወንጀለኞች የሚሰጥ እንደሆነ ተቀምጧል። ይሄ ሲደረግ ግን መጀመሪያ ምህረት መስጠቱ ለሀገሪቱ አስፈላጊ መሆኑ መታወቅ አለበት።
ምህረት የሚደረገው ለፖለቲካ ዓላማ ነው። በሀገር ውስጥ የፖለቲካ አለመረጋገት አልያም ሌላ ችግር በሚኖር ጊዜ ያንን ተከትሎ የሚመጣውን ቀውስ ለማስቀረት ምህረት ሊሰጥ ይችላል፡፡ ምህረቱ በቅድሚያ ታሳቢ የሚያደርገውም ለሠላም፣ የሀገር አንድነትና ብሄራዊ መግባባት ለማስገኘት ነው። የወንጀል ሕጉም ቃል በቃል የሚለው ሁኔታዎች ሲገመገሙ የእርምጃው አስፈላጊነት ጠቃሚ ሲሆን ነው። ምህረት የሚደረገውም ሕግ ወጥቶ በሕጉ መሰረት ነው። ምህረት የሚያደርገውም አካል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ምክር ቤቱ ይሄንን ሲያደርግ አንድን ግሩፕ አሸባሪ ብሎ እንደሚሰይመው ሁሉ አንድ ዓይነት ተመሳሳይ ወንጀል ለፈጸሙ ቡድኖችም ምህረት የሚያደርግበት ህግ ያወጣል። ምክንያቱም በህግ ወንጀል የተባለ ነገር አለ፤ ነገር ግን ወንጀሉን ቢፈጽሙም አይከሰሱ የሚለው ራሱ ህጉን ያወጣው አካል መሆን ስላለበት ነው። ይሄ ሲፈጸም ግን ህጉ ዓላማውን ማስቀመጥ እንዳለበትም ተደንግጓል፡፡ በዚህ ውስጥም የተጠቃሚዎችን ማንነትና የተፈጻሚነቱን ወሰን በግልጽ ማስቀመጥ አለበት። ምህረት ከተደረገ ምህረት የተደረገለት ምንም ዓይነት ወንጀል እንዳልፈፀሙ ተቆጥሮ በሙሉ ይሰረዛል ሲሉ አብራርተዋል።
ስለይቅርታ
በወንጀል ተከሰው የተፈረደባቸው ሰዎች ለይቅርታ ቦርድ በራሳቸው፣ በቤተሰቦቻቸው፣ በጠበቃቸው… በኩል ሲያመለክቱ ማረሚያ ቤቱ ተቀብሎ ለይቅርታ ቦርድ ያቀርባል፡፡ የይቅርታ ቦርዱ ካጸደቀው በኋላ በፌዴራል ደረጃ ለፕሬዚዳንቱ፤ በክልል ደግሞ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ቀርቦ ሲጸድቅ ይቅርታው ይሰጣል፤ ታሳሪውም ከማረሚያ ቤት ይወጣል፡፡ ይቅርታ የሚሰጠው በቅድመ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ ስለሆነ ይቅርታ የተደረገለት ሰው በወንጀል ድርጊት ውስጥ ቢገኝ ይቅርታው ተነስቶ መጀመሪያ የቀድሞ ቅጣቱን እንዲጨርስ ይደረጋል፡፡
ይቅርታም ምህረትም የማይደረግላቸው ወንጀሎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የዘር ማጥፋት ወንጀል፣ አስገድዶ ሰው መሰወር፣ ያለ ፍርድ ሰው መግደል፣ በሰብዓዊነት ላይ ለሚፈጸሙ ወንጀሎች ምህረትም ይቅርታም አይሰጥም።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 21/2012
abebeferew@gmail.com
ፍሬው አበበ