– በ6 ወራት 101 የገጠር ቀበሌዎችና ከተሞች ኤሌክትሪክ አግኝተዋል
– እንደሀገር ኤሌክትሪክ የሚያገኘው ህዝብ 44 በመቶው ብቻ ነው
አዲስ አበባ፡- ከኢትዮጵያ ህዝብ መካከል የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያ ገኘው 44 በመቶው ብቻ መሆኑን እና አገልግሎቱን ለማዳረስ በስድስት ወራት 101 የገጠር ቀበሌዎች እና ከተሞች ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ማድረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ 56 ከመቶው ህዝብ ኤሌክትሪክ አያገኝም። ችግሩን ለመቀነስ በተከናወኑ ሥራዎች በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ለ101 የገጠር ቀበሌዎች እና ከተሞች አዲስ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ተካሂዶ ኤሌክትሪክ አግኝተዋል።
እንደ አቶ መላኩ ገለጻ፤ ከ101 አዲስ የገጠር ቀበሌ እና ከተሞች ውስጥ 93ቱ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ተከናውኖላቸው አገልግሎቱን ያገኙ ሲሆን የተቀሩት 12ቱ ደግሞ በፀሐይ ብርሃን አማካኝነት ኃይል እንዲያገኙ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል። በአጠቃላይ ተቋሙ በስድት ወራት ውስጥ ለ55ሺ 914 አዳዲስ ደንበኞች ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሰጠ ሲሆን፤ በሀገር አቀፍ ኤሌክትሪክ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ደግሞ ለ13ሺ 399 አዳዲስ ደንበኞች ኤሌክትሪክ ማቅረብ ጀምሯል።
ኤሌክትሪክ የማያገኘውን ከግማሽ በላይ ለሚሆነው ኢትዮጵያዊ አገልግሎቱን ለማዳረስ በየዓመቱ ለአንድ ሚልዮን አዳዲስ ደንበኞች አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ የገለጹት አቶ መላኩ፤ በግማሽ ዓመቱ ማዳረስ የተቻለው ግን ለ68 ሺ 313 አዳዲስ ደንበኞች ብቻ መሆኑ ሲታይ ዕቅዱን ለማሳካት የማይቻል መሆኑን እና ዝቅተኛ አፈጻጸም መሆኑን ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ችግር የኤሌክትሪክ ቆጣሪ፣ የተለያዩ የኤሌክትሪክ ሽቦዎችን እና ማገናኛዎችም እንዲሁም ግብዓቶችን በውጭ ምንዛሬ ገዝቶ ለማሟላት አዳጋች ሁኔታ በመፈጠሩ እንደሆነ አብራርተዋል። በተለይ እንደሀገር ያጋጠመው የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የተቋሙ የፋይናንስ አቅም ማነስ ግብዓቶቹን በወቅቱ ለማሟላት እንዳላስቻለ እና የሀገር ውስጥ አቅራቢዎችም በውጭ ምንዛሬው እጥረት ምክንያት ግብዓት ማቅረብ አለመቻላቸውን ተናግረዋል።
እንደ ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ከሆነ፤ የኢትዮያ ኤሌክትክ አገልግሎት አዳዲስ ደንበኞችን ከማዳረስ በዘለለ፤ ያረጁ እና ሳይቀየሩ የቆዩ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮችን በከፍተኛ ወጪ እያስቀየረ ይገኛል። በተለያዩ ከተሞች እየተከናወኑ በሚገኙ የኤሌክትሪክ መስመር ማሻሻያዎችም የማይቆራረጥ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለማዳረስ ትልቅ አቅም ይፈጠራል።
እንደ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መረጃ፤ በኢትዮጵያ ከ14 ዓመታት በፊት ኤሌክትሪክ የሚያገኙ ከተሞች ቁጥር ከ600 አይበልጥም ነበር፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ 7ሺህ ከተሞች እና የገጠር መንደሮች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እያገኙ ነው። ተቋሙ እ.አ.አ በ2025 ሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማዳረስ ይቻላል የሚል ግብ አስቀምጧል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 21/2012
ጌትነት ተስፋማርያም