አዲስ አበባ፡- ለሴቶችና ሕፃናት የአዕምሮ ህክምና አገልግሎት የሚውል ሕንፃ በ4ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በቅ/ አማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ተገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነ።
ሕንፃውን ገንብቶ ያስረከበው ሄኒከን አፍሪካ ፋውንዴሽን በተባለ ድርጅት አማካኝነት ሲሆን ለሕፃናትና ሴቶች የአዕምሮ ህክምና አገልግሎት የሚሰጡ 23 ክፍሎችን የያዘ ነው። ሕንፃውንም ገንብቶ ለመጨረስ አራት ወር መፍጀቱንም በትላንትናው ዕለት የሕንፃው ምርቃት በተከናወነበት ወቅት ተገልጽዋል።
በዚህ የምርቃት ስነስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የአማኑኤል ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢደኦ ፊጆ እንዳገለጹት ከተቋቋማ 80 ዓመትን ያስቆጠረው የቅ/አማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአሁኑ ወቅት በተመላላሽ፤በድንገተኛ፤በአስተኝቶ ህክምና፤ በሱስና ተያዥ ግዳዮች ፤በአዕምሮ ህመም፤በእናቶችና ሕፃናት እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶችን ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ልዩ ልዩ ህክምናዎችን እየሰጠ ነው።
ሆስፒታሉ ከዚህን ቀደም የእናቶችና ሕፃናት ጤና አገልግሎት ይሰጥ የነበረው በጣም ጠባብ በሆነች አንድ ክፍል ውስጥ ነበር ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ አሁን ከሄኒከን አፍሪካ ፋውንዴሽን ተሠርቶ የተበረከተው ሕንፃ ሆስፒታሉ አገልግሎቱን በተሳለጠ መልኩ ለማከናወን እንደሚያስችለው ገልጸዋል፡፡
የሄኒከን አፍሪካ ፋውንዴሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ዴቪድ ሄኒከን በበኩላቸው ሄኒከን አፍሪካ ፋውንዴሽን ከኢትዮጵያውያን ጋር አብረን እናድጋለን የሚል አስተሳሰብ ይዞ በሀገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው ፋውንዴሽኑ በሆስፒታሉ ያለውን ችግር ተረድቶ ይህንን ሕንፃ ለሴቶችና ለሕፃናት አዕምሮ ታማሚዎች አገልግሎት ብቻ እንዲውል ሠርቶ በማስረከቡ ከፍተኛ ደስታ እንደሚሰማው ገልጸዋል፡፡
ፋውንዴሽኑ በጤና ዘርፉ ላይ በርካታ ድጋፎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው በቂሊንጦ ጤና ጣቢያ ለእናቶችና ሕፃናት የሚውል የአምቡላንስ፣ የላብራቶሪ መሳሪያዎችና አልትራሳውንድ መሳሪያዎችን ማበርከቱንም አስታውሰዋል፡፡ ፋውንዴሽኑ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎችም መሰል አገልግሎቶችና ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝም ሚስተር ዴቪድ ተናግረዋል፡፡”
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 21/2012
ሃይማኖት ከበደ