ደሴ፡- በአማራ ክልል ከሚገኙ ከተሞች ውስጥ የደሴ ከተማን ሦስተኛዋ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተገለጸ። ከተማዋ ባለፉት ስድስት ወራት ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች ፍቃድ ሰጥታለች።
የደሴ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ ገብረመስቀል ዓሊ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት በአማራ ክልል የኢንቨስትመንት መዳረሻ በመሆን ከሚታወቁት ደብረብርሃንና ኮምበልቻ ቀጥሎ ደሴን ሦስተኛዋ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ከተማ ለማድረግ ልዩ ልዩ ኢንቨስትምንት ዕምቅ ሀብቶችን የመለየት፤ መሬት የማዘጋጀት፤የብድር አቅርቦት ማመቻቸትና ባለሀብቶችን የማወያየት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
የደሴ ከተማ በተራሮች የተከበበች ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ሆነ መሬት አቅርቦት ችግር መኖሩን የጠቆሙት ከንቲባው ይህንን ችግር ለመፍታትና በቀጣይ ከተማዋ ለምትፈልገው ሰፊ የመሬት ፍላጎት አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር የከተማዋን ማስተር ፕላን የመከለስ ሥራዎችም እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል።
ደሴ በርካታ ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤት ከመሆኗም ባሻገር የተለያዩ ሃይማኖቶችና ብሄር ብሄረሰቦች ተዋደውና ተስማምተው የሚኖሩባት የፍቅር ከተማ መሆኗም በርካታ ባለሀብቶችን ወደ ከተማዋ ለመሳብ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ ከንቲባው ጨምረው ገልጸዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በተደረገው የኢንቨስትመንት ማነቃቂያ ሥራዎች በማዳበርያ ከረጢት፤ በፓይፕ፤ በፕላስቲክ ውጤቶች፤ በሳሙና፤ በሆቴልና በከተማ ግብርና ልማት የተሰማሩ 1ነጥብ 24 ቢሊዮን ብር ላስመዘገቡ 52 ባለሀብቶች ፍቃድ መሰጠቱንም ጠቁመዋል።
የደሴ ከተማ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምርያ ኃላፊ አቶ ሰለሞን አለሙ በበኩላቸው ደሴ ባላት የኢንቨስትመንት አዋጭነትና ሰላም ምክንያት ከመላ ሀገሪቱ በርካታ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት
ዘርፎች ለመሰማራት ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጻው፤ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ100 በላይ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ጥያቄ ቢያቀርቡም ከተማዋ ያላትን አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት 75 ባለሀብቶችን ብቻ ለመቀበል እንደተቻለ ጠቁመዋል፡፡
የመሬት፤የ መንገድና የመብራት ችግሮች የሚቀርቡ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎችን በሙሉ ተቀብሎ ለማስተናገድ ማነቆ እንደሆነባቸው የገለጹት የመምርያ ኃላፊው እነዚህንም ችግሮች ለመቅረፍና ደሴን የኢንቨስትምንት የስበት ማዕከል ለማድረግ ከክልሉ እና ከፌዴራል መንግሥት ጋር በጋራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በስድስት ወራቱ የተሰጡት 52 የኢንቨስትመንት ፍቃዶችም ለ266 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ያስታወሱት አቶ ሰለሞን በቀጣይም ሰፊ ሥራ ዕድል የሚፈጥሩና ከተማዋንም የኢንዱስትሪ ፓርክ ባለቤት ለማድረግ የሚያስችል የኢንዱስትሪ ፓርክ የማካለል ሥራ መከናወኑንም አስታውቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 21/2012
እስማኤል አረቦ