አዲስ አበባ፡- ኢትዮ ሊዝ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በ150 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በኢትዮጵያ ግብርና ላይ ልዩነት የሚያመጡ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን ለአርሶ አደሩ በኪራይ (በካፒታል ዕቃዎች ፋይናንስ ሊዝ) እንደሚያቀርብ ገለጸ።
የኢትዮ ሊዝ ሊቀመንበር አቶ ግርማ ዋቄ ኢትዮ ሊዝ፣ ግብርና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ትናንት በግብርና ሚኒስቴር አደራሽ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ውል ሲፈራረሙን እንደገለጹት፤የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ድርጅቶች በፋይናንስ ሊዝ መሳተፍ እንዲችሉ በፈቀደው መሰረት ኢትዮ ሊዝ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የኢትዮጵያን ግብርና ለማሻሻል በ150 ሚሊዮን ዶላር ለአርሶ አደሩ የእርሻ ትራክተሮችን፣ጀኔረተሮችና ኮባይነሮችን በኪራይ (በፋይናንስ ሊዚንግ) ያቀርባል።
ለአርሶ አደሩ የዘመናዊ ግብርና መሳሪያዎችን ተደራሽ ለማድረግ ብዙ ካፒታልና ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች የሚያስፈልጉ መሆኑን የገለጹት አቶ ግርማ ኢትዮ ሊዝ ከግብርና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር በመሆን በአንድ ዓላማ የኢትዮጵያን ግብርና ለማሻሻል ለአርሶ አደሩ የእርሻ ትራክተሮችን፣ጀኔረተሮችና ኮምባይነሮችን በኪራይ ለአገልግሎት የሚያቀርብ መሆኑን ተናግረዋል።
“የኢትዮጵያ ግብርና የአገሪቷ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ቢሆንም በሚፈለገው መልኩ አላደገም፤አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን በበሬ አርሰው እኛን መግበው አሳድገዋል። በወቅቱ የኢትዮጵያ ህዝብ 20ና 30 ሚሊዮን ነበር። ይህን ህዝብ እንደምንም አጥግበው አሳልፈዋል። የሚያሳዝነው ዛሬም አርሶ አደሩ በበሬ ነው የሚያርሰው” ያሉት ሊቀመንበሩ “ኢትዮ ሊዝ የእርሻ መሳሪያዎችን ለአርሶ አደሩ በኪራይ (በፋይናንስሊዝንግ) ሲያቀርብ ቤትህን፣መሬትህን አስይዝ አንለውም፤ይልቁንም መሳሪያውን በደንብ ያዝ ፣በመሳሪያው በደንብ ተጠቀም ምርትህን አሳድገህ ከምርቱ ዕዳህን ክፈል ስለምንለው ለእሱም ይቀለዋል፤ እኛም ለማስፋፋት ይረዳናል” ብለዋል።
አርሶ አደሩ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን በአግባቡ የሚጠቀም ከሆነ ምርትና ምርታማነት የሚጨመር መሆንኑ ገልጸው፣ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ምግብ የምትልክበት ደረጃ ትደርሳለች የሚል ህልም አለን ብለዋል። ይህ የሦስት ዓመት መርሐ ግብር ውጤታማ ከሆነ ቀጣይነት እንደሚኖረው አስታውቀዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ በበኩላቸው ኢትዮ ሊዝ ፣የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲና ግብርና ሚኒስቴር በጋራ በህብረት ስሥራ ማህበራት፣ በግል ድርጅቶችና በተደራጁ ወጣቶች አማካኝነት አርሶ አደሮች ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች እንዲያገኙ ለማድረግ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ገልጸው፤ አብረው መሥራት የሚያስችላቸው የጋራ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
አቶ ሳኒ እንዳሉት አርሶ አደሩ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች በአገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች አማካኝነት ማግኘት ከቻለ በወቅቱ መሬቱን ያርሳል፣ይዘራል፣ፀረ ተባይ ይረጫል፣ምርት ሳይባክና ጥራቱ ሳይጓደል ይሰበስባል። በአጠቀላይ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ገበያ የሚፈልገውን ምርት ለማምረት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል። የአርሶ አደሩን ህይወት በመቀየርና የአገሪቷን የወጪ ገቢ በማሻሻልም ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
ግብርና ስር ነቀል ለውጥ እንዳያደርግ ተግዳሮት ከሆኑት መካከል ዋናው ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎች መጠቀም አለመቻሉ መሆኑን የገለጹት የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የምርትና ምርታማነት ከፍተኛ ዳይሬክተር ዶክተር ጨምዶ አንጫላ፤ ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን ለአርሶ አደሩ የማቅረብ ሥራ ትልቅ ኢንቨስትመንት የሚፈልግ መሆኑን በመንግሥት ብቻ የሚሠራ አለመሆኑን ጠቁመዋል።
መንግሥት በፋይናንስ ሊዝ ዘርፍ የግሉ ሴክተር እንዲሳተፍ በመፍቀዱም ኢትዮ ሊዝ ለአርሶ አደሩ ከመጪው የመኸር እርሻ ዝግጅት ጀምሮ ውቂያ ድርስ የሚያስፈልጉትን ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎች እንዲያቀርብ የሚያስችል የሦስትዮሽ ስምምነት ውል መደረጉን ተናግረዋል።
የአሜሪካ ኩባንያ የሆነው ኢትዮ ሊዝ ነሐሴ ወር በ2011 ዓ.ም ፈቃድ አግኝቶ ሥራ መጀመሩን ታውቋል። እስከአሁን ድረስም ዘጠኝ ትራክተሮች፣ ስምንት ትላልቅ ጀኔተሮችና የህክምና ቁሳቁሶች ለአርሶ አደሩ በማህበራት በኩል እንዲደርሳቸው ያደረግ ሲሆን 48 ትራክተሮችና የህክምና ቁሳቁሶች ተገዝተው በጉዞ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 21/2012
እስማኤል አረቦ