ኮምበልቻ፡- በጨርቃጨርቅ ዘርፍ ላይ አተኩሮ እየሠራ የሚገኘው ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ውጭ ከሚልካቸው ምርቶቹ የተሻለ የውጭ ምንዛሬ እያገኘ መሆኑን አስታወቀ።
የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ መኮንን ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት የኢንዱስትሪ ፓርኩ ወደ ሥራ ከገባበት ከሀምሌ 1/2009 ዓ.ም ጀምሮ የስደስት ሀገራት ኩባንያዎች ወደ ምርት ሂደት ውስጥ በመግባት ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ፤ አውሮፓና እስያ ሀገራት እየላኩ ይገኛሉ። ኩባንያዎቹ ከካናዳ፤አሜሪካ፤ቻይና፤ጣሊያን፤ደቡብ ኮርያ እና እንግሊዝ የመጡ ሲሆን በዋነኝነትም የተሰማሩባቸው ዘርፎች የአልባሳትና የቆዳ ምርቶች ናቸው።
ከእነዚህ ኩባንያዎች መካከል በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ላይ የተሰማራው ፑንግ ኮክ የተሰኘው እና ከ900 በላይ ኢትዮጵያውያንን ቀጥሮ የሚያሠራው የደቡብ ኮርያው ኩባንያ የሴቶችን ቦርሳ በማምረት ወደ አሜሪካ፤አውሮፓና ጃፓን በመላክ የውጭ ምንዛሬ እያስገባ እንደሚገኝ ሥራ አስኪያጁ ገልጸው፤ ምርቶቹም በውጭ ገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸውና በቀጣይም የሀገር ውስጥ ቆዳን በመጠቀም ምርቱን ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት ለመላክ በዝግጅት ላይ የሚገኝ ኩባንያ መሆኑን አስታውቀዋል።
ሳይቴክስ የተባለው የቻይና ኩባንያ ደግሞ ወደ ሁለት መቶ ኢትዮጵያውያንን ቀጥሮ የሚያሠራ ኩባንያ ሲሆን ክርና የክር ውጤቶችን በማምረት ምርቱን ወደ ቻይና በመላክ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ላይ የሚገኝ እና አሁን በውስን መልኩ እየተጠቀመ ያለውን የሀገር ውስጥ የጥጥ ምርትን ጥራቱን በመጨመር በስፋት በመጠቀም ምርቶቹን ወደ ውጭ ሀገራት ለመላክ ፍላጎት ያለው ኩባንያ መሆኑን አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል።
ሥራ አስኪያጁ አክለውም ካርቢኮ የተሰኘው የጣሊያን ኩባንያ ለስፖርት የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን በማምረት ለናይክና አዲዳስ ምርቶቹን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማቅረብ ላይ እንደሚገኝና በተመሳሳይም በኢትዮጵያውያን፤ አሜሪካውያንና ቻይናውያን በጥምረት የተቋቋመውና የወንድ ልብሶችን በማምረት ወደ ውጭ የሚልከው ትራይባስ የተባለው ኩባንያ ምርቶቹን ወደ አሜሪካ በመላክ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱን አመልክተዋል። ፉአላይ የተሰኘው የቻይና ኩባንያ ደግሞ ደረጃቸውን የጠበቁ የእግር ካልሲዎችን በማምረት ወደ አሜሪካ በመላክ ላይ የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት ላይ ከሚገኙት ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ መሆኑንም አስታውሰዋል።
እነዚህ ኩባንያዎች ሰኔ 2010 ላይ የነበራቸው ኤክስፖርት መጠን ከ33 ሺ ዶላር የዘለለ እንዳልነበረ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ በአሁኑ ወቅት የእነዚህ ኩባንያዎች ኤክስፖርት መጠን 1 ሚሊዮን 187 ሺ ዶላር መድረሱን አስታውቀዋል። እነዚህ ኩባንያዎች ያላቸውን ውጤታማነት በመመልከትም ሌሎች የውጭ ባለሀብቶችም በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ለመሰማራት ጥያቄ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙም አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል።
የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ገብቶ ለመሥራት ጥያቄ የሚያቀርቡ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ በዋነኝነትም የፓርኩ ለጅቡቲ ወደብ ቅርብ መሆን ፤ለምርት ሂደቱ በቂ የሆነ የከርሰምድር ውሃ እንደልብ መገኘት ፤ለኤርፖርት ቅርብ መሆኑ፤በቀጣይም የባቡር መስመሩ ፓርኩን አቋርጦ መሄዱ፤ባንክና ቴሌን ጨምሮ ሁሉም አገልግሎቶች በአንድ መስኮት በተቀላጠፍ መንገድ መሰጠቱና በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም መኖሩ የኢንዱስትሪ ፓርኩን ተመራጭ እንዳደረገው አብራርተዋል።
በኢንዱስተረሪ ፓርኩ ውስጥ የተሰማሩት በሙሉ የውጭ ኩባንያዎች እንደመሆናቸው ከፍተኛ የሆነ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርም ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን አቶ ሙሉጌታ ጠቁመዋል።
እነዚህ የውጭ ኩባንያዎች በአሁኑ ወቅት 2260 ሠራተኞችን ቀጥረው እያሠሩ ሲሆን ከእነዚህ ሠራተኞች ውስጥ 90 በመቶው ሴቶች ሲሆኑ 65 የሚሆኑት ደግሞ የውጭ ሀገራት ዜጎች ናቸው። በቀጣይም የኢንዱስትሪ ፓርኩ በሙሉ አቅሙ መንቀሳቀስ ሲጀምር እስከ 13 ሺህ ሠራተኞችን ቀጥሮ የማሠራት አቅም አለው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 21/2012
እስማኤል አረቦ