አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት ላሳዩ እና ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 163 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ፈቃድ መስጠቱን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ኃይሉ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በ2012 በጀት ግማሽ ዓመት ብቻ ለ163 አዳዲስ የኢንቨስተመንት ፍላጎት ላሳዩ ፈቃድ ተሰጥቷል። በተለይ ከእስያ፣ አሜሪካ፣ አውሮፓ እና ዩናይትድ አረብ ኢሚሬትስ የመጡ ኢ ን ቨ ስ ት መ ን ቶ ች ፍቃድ ካገኙት መካ ከል ሰፊውን ድርሻ ይይዛሉ።
እንደ ሕዝብ ግንኙነቱ ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት በግማሽ በጀት ዓመቱ ለ163 ኢ ን ቨ ስ ት መ ን ት ፕሮጀክቶች ፈቃድ ከመስጠቱ በተጨማሪ በመንግሥት እና በግል ሊገነቡ ስለታቀዱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ55 የውጭ ሀገራት ባለሀብቶች ጋር ውይይት ተደርጓል። ኢንቨስተሮቹ በተመረጡ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው መዋዕለነዋያቸውን ቢያፈሱ ለእራሳቸውም ሆነ ለኢትዮጵያ የተሻለ ጥቅም እንደሚያገኙም ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ከዚህ በተጨማሪ በየሀገራቱ ከሚገኙ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች ጋር በመተባበር ለ215 የውጭ ሀገራት ኢንቨስተሮች እና ለ482 የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንት አማራጭ እንዲሁም በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ስለሚያስፈልጉ መስፈርቶች መረጃ ተሰጥቷል። በመሆኑም በቀጣይ ጊዜያትም ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ይጠበቃል።
በግማሽ ዓመቱ ከተሰጡት ፈቃዶች በአጠቃላይ አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መገኘቱን የተናገሩት አቶ መኮንን፤ መጠኑ በተቋሙ ከተያዘው ዕቅድ አንጻር 71 በመቶ መሆኑን ገልጸዋል። አፈጻጸሙ ዝቀ እንዲል ካደረጉ ችግሮች መካከል በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች እና የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ዋነኞቹ ምክንያቶች መሆናቸው ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለአፈጻጸሙ ማነስ የእራሱ የሆነ አሉታዊ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስረድተዋል። ነገርግን በቀጣይ ወራት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቱን የሚጨምሩ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረው፤ በመንግሥት ይዞታ ስር የነበሩ የተለያዩ ተቋማትም ወደግል ኢንቨስተሮች የሚዞሩበት ወቅት በመሆኑ እስከ 2012 በጀት ዓመት ማጠናቀቂያ ድረስ የኢንቨስትመንት መጠኑ በእጅጉ እንደሚጨምር ገልጸዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ከሆነ፤ አንድ የውጭ ኢንቨስተር ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ መዋዕለ ንዋዩን ማፍሰስ ከፈለገ ቢያንስ በአማካይ 200 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ካፒታል ማስመዝገብ አለበት። እንደየኢንቨስትመንት ፕሮጀክቱ ሁኔታ ግን ለውጭ ኢንቨስተሮች የሚጠየቀው አነስተኛ የካፒታል መጠን ሊጨምርም ሆነ ሊቀንስ ይችላል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 21/2012
ጌትነት ተስፋማርያም