አዲስ አበባ፡- የጸደቀው የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት አዋጅ ሥራ ከጀመረበት የሰኔ ወር ጀምሮ 14 ሺህ 411 ሠራተኞች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት መሄዳቸው ተገለጸ፡፡ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አዋጅ 923/2008 ከፀደቀ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች እስከ ሰኔ 2011 ዓ.ም ድረስ ሳይተገበር ቆይቷል፡፡
አዋጁ የማስፈፀሚያ ደንብና መመሪያ የማዘጋጀት፣ የማፅደቅና ስምሪቱን ለመተግበር የሚያስችል አደረጃጀት የመፍጠር፣ የአሠራር ስርዓቱን የመዘርጋት፣ የዳታ አድሚኒስትሬሽን ሲስተም የማሳደግ፣ በስምሪቱ ውስጥ የሚገቡ ሠራተኞች የሙያ ስልጠና የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ ማዕከላትን ማዘጋጀት፣ ከሠራተኛ ተቀባይ ሀገራት የጋራ የሆነ የሁለትዮሽ የሥራ ስምሪት ሰምምነት የማድረግና ሌሎች ዝግጅቶች ከተጠናቀቁ በኋላ ባለፈው ሰኔ ወር ሥራ ጀምሯል፡፡
በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የኮምኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ደረጀ ታየ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ሠራተኞቹ የሚላኩት ስምምነት ወደተደረገባቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አ ገራት ነው፡፡
ጆርዳን፣ ኳታር፣ ሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢሜሬቶች የሁለትዮሽ ስምምነት የተደረገባቸው አገራት ሲሆኑ ሠራተኞችን ወደነዚህ አገራት ለመላክ እየተሠራ ያለው ከህጋዊ ወኪሎች ጋር ነው፡፡
እንደ አቶ ደረጀ ገለጻ፤ የተላኩት ሠራተኞች ምን ላይ እንዳሉ በየጊዜው ሪፖርት ይደረጋል፡፡ ከወኪሎቻቸው ጋር የመረጃ ልውውጥ እየተደረገ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ በህገ ወጥ መንገድ የሚሄዱት ላይ ነው ችግር እየደረሰ ያለው፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 21/2012
ዋለልኝ አየለ