የተወለዱትና ያደጉት በቀድሞ ስሙ የረርና ከረዩ አውራጃ ናዝሬት ከተማ (አዳማ) ውስጥ ነው። የመጀመሪያ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩትም እዚያው ከተማ ውስጥ ባለው አፄ ገላውዲዮስ ትምህርት ቤት ሲሆን በተለይም ደግሞ አባታቸውም የትምህርት ቤቱ መምህር ስለነበሩ በትምህርትና በስነ ምግባር ተኮትኩተውና ታንፀው እንዲያድጉ ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጉላቸው እንደነበር ይገልፃሉ። ወላጅ እናታቸውን ገና 3ዓመት ጨቅላ እያሉ ከማጣቸው ጋር ተያይዞ ከአባታቸው ጋር የተለየ ቀረቤታ የነበራቸው በመሆኑ የእርሳቸውን ባህሪና ጥንካሬ ይዘው እንዲያድጉ ምክንያት ሆኖቸዋል። ይህም ታዲያ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ «የአባቱ ልጅ» የሚል ቅፅል ስም አሰጥቷቸው ነው ያደጉት። በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ከክፍል ክፍል በመሸጋገር የትምህርት ቤታቸውን ስም በመልካም ዝና ያስጠሩ እንደነበርም ይነገርላቸዋል። እሳቸውም ሆኑ የትምህርት አቅማቸውን ያየ ሁሉ ወደፊት ከፍተኛ ትምህርት ቤት ገብተው በመማር በትምህርቱ ዘርፍ የአገራቸውን ስም እንደሚያስጠሩ ህልም ነበራቸው።
ይሁንና 11ኛ ክፍል ሲደርሱ ካሰቡበት አቅጣጫ የሚመልሳቸው ሁኔታ በህይወታቸው ተከሰተ። ይኸውም ከወላጅነት ባለፈ እንደጓደኛ ቅርባቸው የነበሩትን አባታቸውን በሞት ማጣታቸው ነው። ያን ጊዜ ታዲያ ምንም እንኳ የአባታቸው ብቸኛ ወራሽ በመሆናቸው የኢኮኖሚ ችግር ባይኖራቸውም የህይወት አቅጣጫቸውን መቀየር እንዳለባቸው አመኑ። በአጋጣሚ ደግሞ በአካባቢያቸው ያለ የባህር ኃይል አባል ለዕረፍት መለዮውን እንደለበሰ በሚመጣበት ጊዜ በአለባበሱ ይማረኩ ስለነበር ባህር ኃይል የመሆን ፍላጎት አጫረባቸው። በዚህም አልበቁ ፤እንዳሰቡትም ባህር ኃይሉን ተቀላቀሉ። በባህር ኃይሉም በወታደራዊ ግብረ ገብና በመልካም ስነምግባር ተቀረፁ። ያቋረጡትንም ትምህርት በግል ተፈትነው አጠናቀቁ። በባህር ኃይሉ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ሲያገለግሉ ቆይተው ከ1966ቱ ዓብዮት መምጣት ጋር ተያይዞ የለውጡ አካል እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል በሚል እሳቤ በወታደራዊ ፖለቲካ ትምህርት ቤት እንዲሰለጥኑ ተደረገ። በቀጣይም በፖለቲካ መምሪያ የባህር ኃይል ሰራዊት አንቂ የፖለቲካ ካድሬ ሆኑ። ይሁንና የነበረው የፖለቲካ አዝማሚያ አላምር ስላለቸው በሙያቸው ሌላ ቦታ ላይ ተመድበው እንዲሠሩ ጥያቄ አቅርበው ወደ አስመራ ተዘዋወሩ። በአስመራም ለሁለት ዓመት ከቆዩ በኋላም ችግሩ እየተባባሰ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ከባለቤታቸውና ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ሆነው የሚወዷትና አገር ለቀው ወደ ሱዳን ተሰደዱ። ከሱዳን ጥቂት ወራት ቆይታ በኋላም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ በአስተርጓሚነት ተቀጠሩ፤ በኋላም ወደ ስውዲን የመሄድ እድሉን አገኙ። ስዊድን ስቶኮልምስ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ከተሙ። ከቋንቋ ጀምረው በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያዙ። እዚያው ዩኒቨርሲቲ ውስጥም በምምህርነት አገለገሉ። በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥም ገብተው በሙያቸው ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የሠሩ ሲሆን በአገሪቱ በበጎ ፈቃድ አገልሎት ላይ በሚሠራ ፌኒክስ በሚባል ድርጅት ውስጥም ለ20 ዓመታት በነፃ በሙያቸው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። በእዚያው አገር ውስጥ እያሉም ለቅንጅትና አንድነት ፓርቲዎች ድጋፍ በማሰባሰብ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በቅርቡ ደግሞ ወደ ተወለዱባት ምድር በመመለስ በሲውዲን የጀመሩትን መፅሐፍ «የባህር ኃይሉ ራስወርቅ» በሚል ርዕስ ፅፈው በማጠናቀቅ ለህትመት አብቅተዋል። ይህንን በባህር ኃይሉ የነበራቸውን ህይወት የሚዳስሰውን መፅሐፍም የቀድሞ ባልደረቦቻቸውና ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት አስመርቀዋል። በእለቱም ግለሰቡ ለሠሩት ሥራ የክብር ማስተር ቺፍ ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል። ከዛሬው እንግዳችውን ማስተር ቺፍ ራስ ወርቅ መንገሻ ጋር በሙያቸውና በተለየዩ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገናል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- የባህር ኃይል ቆይታዎ ምን ይመስል እንደነበር ያስታውሱንና ውይይታችንን ብንጀምር?
ማስተር ቺፍ ራስወርቅ፡- እኔ እንግዲህ ወደ ባህር ኃይል የገባሁት በ1958 ዓ.ም ነው። ስንቀጠር ድርጅቱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገስት የባህር ኃይል በሚል ስያሜ ነበር የሚጠራው። ያንጊዜ ታዲያ የነበረው ሁኔታና አመለካከቱ ሉላዊነት የሚያሰኝ መልከ መልካም፤ጥሩ አቋም ካላቸው፤ ደረታም ከሆኑ ወጣቶች መካከል ተመርጬ ነው የተቀጠርኩት። አሰልጣኞቻችንና መምህራኖቻችን ግብረገብ የተላበሱ ነበሩና እኛን አንፀው ያዘጋጁን ነበር። በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በዓለም የሚደነቅና ከአፍሪካም በአንደኝነት ደረጃ የሚቀመጥ ተቋም ነበር። በዚህ ተቋም ውስጥ በማገልገሌ ዛሬም ድረስ ኩራት ይሰማኛል። በተለይም በንጉሡ ጊዜ በባህር ላይ የነበረው መስተንግዶና የካምፕ ኑሮ ሁልጊዜም ከአዕምሮዬ የማይጠፋ ነው። ከዚያም በ1966ዓ.ም ለውጡ መጣ። ሁላችንም የለውጡ አካል እንድንሆን ተደረግን። በነፃ አመለካከታችን ሳይሆን በአዛዦቻችን ፍቃድ ብቻ ሆነ የምንንቀሳቀሰው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን ለፖለቲካ ትምህርት ቤት ታጨሁኝና የካቲት 66 ፖለቲካ ትምህርት ቤት ገባሁ። በዚያም ከፍተኛ ምሩቅ ተማሪ ሆኜ አጠናቀቅሁኝ። ከማሰልጠኛው ከወጣሁ በኋላ እዚያው ባህር ኃይል ውስጥ በፖለቲካ መምሪያ የባህር ኃይል ሰራዊት አንቂ የፖለቲካ ካድሬ ሆንኩ። በእርግጥ የማሰልጠኛው አመራሮች እዚያው እንድቀር ፈልገው የነበረ ቢሆንም ባህር ኃይሉ ግን እኛ የላክነው ለትምህርት ብቻ ነው በማለት ተምልሼ አዲስ ምልምል የባህር ኃይል ሰራዊቶችን እንዳሰለጥን ተመደብኩ። አዲስ ምልምል ሰልጣኞችም በፖለቲካው ርዕዮት ዓለም እንዲታነፁ የማድረግ ኃላፊነት ተጣለብኝ።
በነገራችን ላይ በወቅቱ ከነበሩት ድርጅቶች መካከል የወዛደር ሊግ አባል ነበርኩኝ። እየዋለ ሲያድር ግን የፖለቲካው ሁኔታ በጣም አስጊ እየሆነ መጣ። በተለይም ሰርጎ የገባ ኃይል አለ ትብሎ ይታመን ስለነበር ሰዎችን የማፅዳት ዘመቻ ማካሄድ ተጀመረ። ማፅዳት የጀመሩትም ከየካቲት 66 ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ጀምሮ ኮረኔል ሽታዬ ደስታ፥ ሻለቀ ወልደማርያም፥ ነጋሽ ታደሰ እንዲሁም የቅርብ ጓደኛዬ የነበረው ኮማንደር ድንቁ የመሳሰሉትን ሰዎች ነው። እነዚህ የቅርቤ የምላቸው ሰዎች እዚያው ጊቢ ውስጥ ተመትተው ሳይመለሱ መቅረታቸውን ሳውቅ ዘመቻው ወደ እኔ እንደሚቀጥል ተገነዘብኩ። በወቅቱ የማደርጋቸውንም አንዳንድ ነገሮች በመጠራጠር የግሉን አባላት እየመለመለ ነው የሚል ውንጀላ ውስጥ እንደገቡ ተረዳሁ። እኔ ግን የወዛዳር ሊግ አባል እንጂ የራሴን ሰዎች የምመለምል አለመሆኔን ብገልፅለትም ሊያምነኝ ስላልቻለ ሁኔታውም የሚያዛልቀኝ ስላልመሰለኝ በወቅቱ የባህር ኃይሉ አዛዥ ለነበሩት ሰው ከካድሬነት ሥራ ውጪ የሆነ ቦታ በባህር ኃይል ውስጥ እንዲመድቡኝ ጠየኳቸው። በእሳቸውም አማካኝነት ከአንድ ቀን በኋላ የባህር ኃይል የሲቪል ሰርቪስ ፐርሶኔል መኮንን ሆኜ አስመራ ተመደብኩ።
በአስመራም ከ1971 እስከ 1972 ዓ.ም ብቻ ነው የቆየሁት። እዚያም ሆኜ ሰዎችን የመያዝና የማሰር እንቅሳቀሴ ተጀመረ። በተለይም ጓደኞቼ እየተያዙ ሲታሰሩ ስመለከት ይህ ጉዳይ ደግሞ ወደ እኔም እያዘነበለ እንደመጣ ተገነዘብኩኝ። ስለዚህ የምወዳትን አገር ለግለሰቦችና ለራሳቸው ሃሳብ ብቻ በሚሮጡ ሰዎች ተገፍቼ ሀገሬን ጥዬ እንድጠፋ ተገደድኩኝ። ከኤርትራዊቷ ባለቤቴና ከሁለት ልጆቼ ጋር በመሆን በግመል ሱዳን ገባን።
አዲስ ዘመን፡- የመያዝ እድል አላገጠሞትም?
ማስተር ቺፍ ራስወርቅ፡- በኢትዮጵያ መንግሥት አልተያዝንም፤ ግን ሻብያዎች ያዙንና ሦስት ወር አቆዩን። ባለቤቴ ኤርትራዊት ስለነበረችና ከእኔ ምንም እንደማያገኙ ስለተረዱ ምንም አልነኩንም። እዚያ በጥሩ እንክብካቤ ሦስት ወር ከቆየን በኋላ በሰላም አሸጋገሩን። በዚያን ጊዜ ደግሞ ብዙ የጦር ሰራዊት ምልምል የሆነን ሰው ተቀብለው ወደ ሌላ አገር የሚያሸጋግሩ ስለነበር እኔም በሦስት ወር ጊዜያት ውስጥ እድሉ ደረሰኝና ሱዳን ገባሁ። በሱንዳን የማውቀው ሰው ስላልነበረኝ ከነቤተሰቤ በቀጥታ በረንዳ ነበር ያረፍኩት። ሲመሽ አጥር ጥግ ካርቶን ከልለን ነበር የምናድረው። ጠዋት ስንነሳ ደግሞ አጥር ጥግ ካርቶኑን ሸጉጠን ነበር የምንውለው። ይሁንና ብዙውን ጊዜ ማታ ላይ ስንመጣ ካርቶኑን ቤተሰብ የሌላቸው ዱርዬ ፍየሎች በልተውብን ነው የምናገኘው። ከዚያ እንደገና የሰዎችን ቤት እያንኳኳን ካርቶን እንለምን ነበር።
በዚያ ሁኔታ ውስጥ እያለን ታዲያ ሥራ ከማፈላለግ አልቦዘንኩም ነበር። ለማንኛውም ሥራ የሚመጥን እውቀት ቢኖረኝም አረብኛ ቋንቋ ስለማልችል እንዳሰብኩት ቶሎ ሥራ ማግኘት አልቻልኩም ። በመሆኑም በፍጥነት ቋንቋውን ለመልመድ ጥረት አደረኩኝና ሥራ ማፈላላጌን ቀጠልኩ። አንድ ቀን ጋደም ብዬ ከምውልበት ሜዳ ፊት ለፊት የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት ነበርና የድርጅቱ ሠራተኞች እኔንና ሌሎች ስደተኞች ትግርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋ የሚችል ካለ እንዲያስተረጉም ጠየቁ። እኔም ፈጠን ብዬ እኔ እችላለሁ አልኳቸው። አንዲት የድርጅቱ ሠራተኛ መጣችና እንዳስተረጉም ጠየቀችኝ። ባስተረጎምኩላቸው በማግስቱ ስደተኞችን የሚረዳና ትራንስፖርት የሚቆርጥ ቢሮ ሊከፍቱ በመሆኑ እዚያ ሊቀጥሩኝ እንደሚፈልጉ ነገረችኝ። እኔም በደስታ ተቀበልኩ። ከዚያም በኋላማ እንደቀልድ በአንዲት ጀምር ከካርቶን ቤት የአየር መቆጣጠሪያ ወደአለው ቤት ገባን። ደመወዜም በዶላር ይከፈለኝ ጀመር። ከራሴ አልፌም ሌሎች ስደተኞችንም መርዳት ቻልኩ።
ይሁንና ሱዳን ውስጥ መቆየት ፍላጎት ስላልነበረኝ ወደ ሌላ አገር ለመሄድ ብዙ ሙከራ አደረኩ። አርዕስቶች እየቀያየርኩ በየኤምባሲው አስገባ ስለነበር በአንድ ጊዜ ሦስት አገሮች ተቀበሉኝ። ያን ጊዜ ደግሞ የመምረጥ ፈተና አጋጠመኝ። አንደኛው ካናዳ አልበርታ የሚባል ቦታ፥ ሁለተኛው ዩናይትድስቴት ኦሃዮ፥ ሲዊድን ደግሞ ስቶኮልም ነው የደረሰኝ። ሁሉም አገሮች ሰዎች ሊሄዱባቸው የሚጓጉባቸው አገሮች በመሆናቸው መወሰን በጣም አቃተኝ። እንግሊዝኛ ተናጋሪ አገር ብሄድ ከትምህርቴም ጋር አብሮ ይሄዳል የሚል ሃሳብ በአንድ ወገን ያዘኝ። በሌላ በኩል ደግሞ የርዕዮተ ዓለም ሰው ስለነበርኩ እነሲ.አይ. ኤ የተባሉ ተቋማት ችግር ከሚፈጥሩብኝ ወደ ሲዊዲን ብሄድ ይሻላል የሚል ሃሳብ መጣብኝ። በመሆኑም እነዚህን አገራት ስም እንደቆሎ ተማሪ ወረቀት ጠቅልዬ እጣ ሳወጣ በተደጋጋሚ የሚደርሰኝ ሲዊዲን ነበር። ስለዚህ ልቤም ወደ ሲዊድን አዘነበለና ቤተሰቤን ይዤ ወደዚያው አቀናሁ። ኑራችንንም እዚያው አደረግን። እዚያ እንደደረስኩም ከአገሩ ጋር ለመላመድ ስል በቀጥታ ቋንቋ ተማርኩ። ከቋንቋ ትምህርት ቤት በኋላ በቀጥታ ወደ ስቶክሆልም ዩኒቨርሲቲ ገብቼ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪዬን ወስጃለሁ። በዚያው ዩኒቨርሲቲ ተቀጥሬ ለ11 ዓመት በአስተማሪነት አገለገልኩኝ። የተሻለ ደመወዝ ለማግኘት ደግሞ በሌላ ተቋም ውስጥ ተቀጥሬ በጊዜያዊና በቋሚ ሠራተኝነት እያገለገልኩ እገኛለሁ። እስከአሁን ድረስ እዚያው ሲውዲን ውስጥ ነው የከተምኩት።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ሀገርዎ የማምጣት እድሉን አላገኙም?
ማስተር ቺፍ ራስወርቅ፡- ወደ ሀገሬ የመመለስ እድሉን ልክ ኢህአዴግ እንደመጣ አግኝቼ ነበር። የመጣሁት ግን እዚሁ ለመቅረት ሳይሆን ሁኔታዎችን ለማጥናት ነበር። በወቅቱ ሁኔታውን ሳጠናው ደህና ይመስላል። ወደሲዊድን ከተመለስኩ በኋላም ስቶክሆልም የነበረው የኢትዮጵያ ኤምባሲን ኮምፒውተራይዝድ በማድረጉ ሂደት የበኩሌን አስተዋፅኦ አበረከትኩኝ። ሆኖም በወቅቱ የራሳቸውን ሰው ይፈልጉ ስለነበር እኔ የሠራሁትን እንኳ በራሳቸው ባለሙያ ማስፈተሽ ይፈልጉ ስለነበር በሁኔታው አልተደሰትኩም። በአገር ውስጥም ዜጎችን የማሰር ሁኔታ ስመለከት ወደዚህ አገር መምጣቱ እንደማያዋጣና ከእነሱ ጋር ተደጋግፎ መሥራት አስፈላጊ አለመሆኑን ተገነዘብኩኝ። ስለዚህ በተቃውሞ ጎራ ውስጥ ገባሁኝ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በተቃውሞ
ሲሉ ምን ማለትዎ ነው? ለምንስ ወደ ተቃውሞ ጎራ መቀላቀል አስፈለገዎት?
ማስተር ቺፍ ራስወርቅ፡- የኢህአዴግ ርዕዮተ ዓለም ለአገሪቷ መፍትሔ የማይሰጥና ሰዎችን እያሰረ የሚያሰቃይ ጨቋኝ ስርዓት ነው። ዘረኝነት እየተጠናከረ ሲመጣ፤ በኋላም በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የሚደርሰውን ጫናና ወከባ ስመለከት በተቃውሞ ጎራ መሰለፍ እንዳለብኝ አመንኩ። በዚህም መሰረት በ1997 ዓ.ም ቅንጅት ሲቋቋም የቅንጅት የድጋፍ ኮሚቴ አባል ሆኜ በገንዝብ ያዥነት ካገለገልኩ በኋላ የቅንጅት ቸርማን ሆኜ ተመረጥኩኝ። እዚያው ሆኜ ፓርቲውንና የታሰሩ ሰዎችን በገንዘብ የማገዝ ሥራ እሠራ ነበር። ሲዊዲን ያለነው አብዛኞቹ ሰዎች የቅንጅት የጀርባ አጥንት ሆነን ነው ስንሠራ የነበረው። ከቅንጅት ወደ አንድነት ሲሻገርም ቸርማን ሆኜ ስሠራ ነበር። በነገራችን ላይ ድጋፉ እስካሁንም አልቆመም። አንድነት ሲከስም እኛ ራሳችን አልከሰምንም፤ ፓርቲ ውስጥ ያልገቡትን በመያዝ ወርሐዊ ግኑኝነትና ሰብዓዊ እርዳታም እንዳይቋረጥ እስከአሁን ድረስ እየሠራን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ወደአገሮ የመጡበት አጋጣሚ ምንድን ነው?
ማስተር ቺፍ ራስወርቅ፡- እዚህ ለመምጣት ሃሳብ አልነበረኝም ነበር። ሆኖም አሁን ከተፈጠረው እድል ጋር ተያይዞ እኔም የጡረታዬ ጊዜ በመድረሱ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት አስቤ ዳግም የአገሬን መሬት መርገጥ ችያለሁ። እኔ የመጣሁበትን ሂደት በመፃፍ ከእኔ ህይወት ትውልዱ እንዲማር አስቤ ነው የመጣሁት። መፅሐፉን እዚያ ጀምሬው ስለነበር እዚህ ከመጣሁ በኋላ ነው የጨረስኩት። ህትመቱ አልቆ በቀድሞው የባህር ኃይል መኮንኖችና በአዲሱ የባህር ኃይል አዛዥ በሪአድሚራል ክንዱ ገዙ በይፋ ጥር 16 ቀን 2012 ተመረቀ። በነገራችን ላይ እኚህ ግለሰብ በጣም ጥሩ ዕውቀት ያላቸውና ማዕረጋቸውም ከሜጀር ጀነራል ማዕረግ እኩል ነው። እኚህ ሰው ታዲያ በመፅሐፉ ምረቃ ላይ ይህንን ታሪክ በመፃፌ ከልብ መደሰታቸውና ወደፊት የሚቋቋመውን ባህር ኃይል እንዳግዝ ጠይቀውኛል። በእለቱም ማስተር ቺፍ የተሰኘ የክብር ማዕረግ ተሰጥቶኛል።
አዲስ ዘመን፡- እኔ የሰማሁት ግን እዚህ የመጡት በዶክተር አብይ ግብዣ የባህር ኃይሉን እንዲደግፉ መሆኑን ነው፤ ይህ ምን ያህል እውነት ነው?
ማስተር ቺፍ ራስወርቅ፡- አይ ይህ እወነት አይደለም፤ እስከአሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩን አላገኘኋቸውም፤ ነገር ግን ወደፊት የራሴን አስተዋፅኦ ለማድረግ ፍቃደኛ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የባር ኃይሉን ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል፤ አንዳንዶች የባህር በር ሳይኖር ባህር ኃይሉን ማቋቋም አስፈላጊነት የለውም ይላሉ፤ እርሶ ይህንን ሃሳብ ይቀበሉታል?
ማስተር ቺፍ ራስወርቅ፡- ብዙ አገሮች ወደብ ሳይኖራቸው የባህር ኃይሎች አሏቸው። ወደብ ባይኖርም የባህር ኃይል ማቋቋም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት ብዬ አምናለሁ። ደግሞም በእርግጠኝነት የኢትዮጵያ መንግሥት በቁርጠኝነት ይጠቀምበታል ብዬ አምናለሁ። አሁን ባለው ሁኔታም ቀይባህር አካባቢ ላይ ወደብ ማግኘት የምንችልበት ዕድል እንዳለ ይሰማኛል። ምንአልባት የሁለቱ መንግሥታት ስምምነት ቢሆንም እነዚህ አገሮች ወደፊት የተሻለ ሥራ በጋራ ለመሥራት ያሰቡ ይመስለኛል። ሆኖም ለጊዜው የተገኘው ቦታ ጅቡቲ ነው፤ ያም ቢሆን ሩቅ አይደለም፤ ባህርዳር ላይ ማሰልጠኛ ተቋሙ እንደሚዘጋጅ ሰምቻለሁ።
በነገራችን ላይ
ድሮም ቢሆን እኮ ባህር ኃይል የራሱ ባጀት ያለው ተቋም ነበር። ባህር ኃይል ማለት በጦር ኃይሎች
ውስጥ የታቀፈ አይደለም። ስለዚህም በቀጥይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በጅምር ደረጃም ቢሆን ወደ ውጭ ተማሪዎች ለስልጠና መላካቸውን ሰምቻለሁ። ሲመጡ ግን ሌሎች እንደሚያወሩት ለወታደራዊ አገልግሎት መዋል የለበትም። ምናልባት የመንግሥት ፖለቲካ ውስጥ ዘልቆ መግባት እንዳይሆንብኝ ግን እሰጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
ማስተር ቺፍ ራስ ወርቅ፡- መንግሥት ይህንን ባህር ኃይል ዳግም ማቋቋም ያስፈለገበት የራሱ ዓላማ ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ። አመራሮቹ እንደሰማሁት በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ ቶሎ ተቋቁሞ ሥራ እንደሚጀምር ነው። ስለዚህ መንግሥት ይህንን ዓላማ ሲይዝ ወደብ ባይኖረውም በሌሎች ወደብ ላይ ሆኖ ሊሠራው ያሰበው ነገር ይኖራል የሚል እምነት አለኝ ።
አዲስ ዘመን፡- በምን መልኩ ነው ታዲያ እርሶ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚፈልጉት ?
ማስተር ቺፍ ራስወርቅ፡- በምችለው ሁሉ ለማገልገል ፍቃደኛ ነኝ። በተለይ በአስተዳደራዊና በአደረጃጀት ሥራ ላይ ባህር ኃይሉን ለማገዝ ፍቃደኛ ነኝ። ባህር ኃይሉ እንዴት እንደሚደራጅ ያደግንበት ስለሆነ ከእኛ የሚወስዱት ልምድ ይኖራል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- እንደው የአሰብን ነገር ሲያነሱ ያኔ ሲመላለሱበት የነበረ ወደብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚፈጠርብዎት ቁጭት ይኖር ይሆን?
ማስተር ቺፍ ራስወርቅ፡- አስቀድሜ እንዳልኩሽ በመሰረቱ አሰብ የኢትዮጵያ አካል እንጂ የኤርትራ ሆና መካተት አልነበረባትም። ይህ ሆን ተብሎ በክፋት የተሠራ ነው እንጂ በትክክል እውነታ ላይ ተመስርቶ የተሰጠ ፈትህ አይደለም። እንዳልሽው አዎ በደንብ የሚቆጭ ጉዳይ ነው። ወደብን፤ ባህርን ያክል ነገር ማጣት ቀላል አይደለም። ሁልጊዜም ሲያስቡት ያናድዳል፤ ይቆጫል። ግን የተሠራው የተንኮል ሥራ ስለነበር ችግሩ እስከአሁን ዘልቆ እዚህ ደርሷል፤ አሁን ደግሞ እንዴት እንደሚሆን መጠበቅ ነው የሚያሻው። መንግሥትን ውስጡን ባላውቀውም ያሰበው ነገር አለ ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- እንደሚያውቁት ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ተቀይሮ ህዝቡ የለውጥ ብርሃን እያየ ነው፤ በዚህ ለውጥ ላይ ያሎትን አመለካከት ይንገሩን እስቲ?
ማስተር ቺፍ ራስወርቅ፡- እኔ እንግዲህ እንደማየው ዶክተር አብይ በጥሩ ሁኔታ ለሁሉም በራቸውን ከፍተዋል። ህዝቡ ደግሞ ተባብሮ እሳቸውን ማገዝ ተገቢ ነበር። ሆኖም የፀጥታው ሁኔታ በጣም የሚያሰጋ ነው። ይህንን የማረጋጋት ሥራ ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ አይደለም የሚጠበቀው። እስከታች ያለው መዋቅርና ህዝቡም ቢሆን ሰላምን ማስከበር ይገባው ነበር። በእኔ በኩል የፀጥታው ሁኔታ ያሰገኛል። ፀጥታን ፈርቶ ደግሞ አብዮትን አለማካሄድ አይቻልም። ከጸጥታው ስጋት ውጪ ያለው ሁኔታ ግን በጣም ቆንጆና የሚበረታታ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ በተለይም ባሰለፏቸው ሁለት የቀድሞ መንግሥታት ዘመን ይህ በብሔርና በሃይማኖት ለይቶ የመጋጨት ሁኔታ እንዳልነበር ይታወቃል። አሁን ላይ ይህንን ሁኔታ ሲመለከቱ ምንአይነት ስሜት ይፈጥርብዎታል?
ማስተር ቺፍ ራስወርቅ፡- አው ልክ ነሽ፤ በዚያን ዘመን ሃይማኖት የግል ነው፤ አገር የጋራ ነው ነበር የሚባለው። ድሮ ገመቹ ወይም ግርማ ደግሞም ሃጎስ የሚል ልዩነት አልነበረም። በአንድ ሰንደቅ ዓላማና በአንድ አስተሳሰብ የምንኖር ሰዎች ነበርን። ቋንቋችንም ቢሆን በመላው 14 ግዛት ሁሉ በአማርኛ ነበር የምንግባባው። አገር ሲወረር እከሌ ኦሮሞ ነው እከሌ አማራ ነው ሳይባል በጋራ «ሆ» ብለን ነበር የምንሰለፈው። ነገሩ ፌዳራሊዝም በሚባለው አካሄድ ስመለከተው ደግሞ ትንሽ ያማል። ዛሬ የሆነ ብሄር አባል ብሆን «የእኔ ዘመን ነው» እያሉ ጦርነቶችን እያነሳሱ እርስበርስ ሰዎችን መከፋፈል ተጀምሯል። ሌሎችም ጠላቶቻችን ደካማ ጎናችንን በማየት ሰርገው ገብተው ይሠራሉ። በእኔ እምነት «የእኛ መንደር እኛን ካልመሰለ በሜንጫ ነው የምንመታህ» ማለት የሚደገፍ ነገር አይደለም። ያሳዝናልም። እኛ እንደዚህ ተባብለን አልኖርንም። እኔ ለምሳሌ ናዝሬት( አዳማ) ነው ተወልጄ ያደኩት ዛሬ የኦሮሞ አገር ነው ሲሉኝ በጣም ነው የሚገርመኝ። የምንግባባው በአማርኛ ነበር። አሁን ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ይህንን ለማስወገድ ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን ከልብ መቀበል ያስፈልጋል። አገሪቱ በቋንቋችን ልክ ትሸነሸን አይገባም። መከፋፈሉ ለወደፊቱም ቢሆን ጥሩ አያመጣም።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ሲሉ አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት አሁን ያለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ልክ እንደሶርያና የመን ትሆናለች እንደሚሉት አይነት ስጋት ይሰማዎታል ማለት ነው?
ማስተር ቺፍ ራስወርቅ፡- አይ እንደሱ ማለቴ አይደለም፤ ኢትዮጵያ በፍፁም እንደሶርያና የመን አትሆንም፤ ህዝቦቿም አይበታተኑም። በመሰረቱ ህዝቡም በጉልበት የመጣን መሪ የመሸከም ጫንቃ ይኖረዋል ብዬ አላስብም። የህዝቡ ተቻችሎ የመኖር ባህል አገሪቱን እንድትበታተን እድል አይሰጥም። ስለዚህ ለእኔ ኢትዮጵያ እንደሶርያና የመን ትሆናለች የሚለው ነገር ዘበት ነው። ኢትዮጵያ እንደኢትዮጵያዊነቷ ትቀጥላለች። ቀስ በቀስ ሊሠሩ የሚገባቸው ሥራዎች ሊሠሩ ይገባል። ሃይማኖታዊውም ሆነ የነገድ ግጭቶች ሊከስሙ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- መንግሥት በአፋጣኝ ሊፈታ ይገባል የሚሉት ሃሳብ አሎት?
ማስተር ቺፍ ራስወርቅ፡- በአገራዊ ሁኔታዎች ሃሳብ መስጠት የምፈልገው አገሪቷን ከነመዋቅሯ ፌዴራሊዝም ስርዓት ቀርቶ ለአንዲት አገር የቆመ መንግሥት ሊኖረን ይገባል። በሌላ በኩልም ያሉት ፓርቲዎች ብዙ ቢሆኑም የተለየዩ ፓርቲዎች ለምርጫ መቅረባቸው እንደስጋት መታየት የለበትም። ምህዳሩ ሰፍቶ የሁሉንም ህዝብ ፍላጎት ማስተናገድ የሚቻልበት እድል ሊፈጠር ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ሰዎች በአሁኑ ወቅት ስለአንድነት ማውራት አህዳዊ ስርዓትን መመለስ እንደሆነ የሚያስቡ አካላት አሉ፤ ይህ ባለበት ሁኔታ እርሶ የሚሉት አንድነት በምን መልኩ ነው ሊመጣ የሚችለው?
ማስተር ቺፍ ራስወርቅ፡- እስካዛሬ እኔ የማውቃት ኢትዮጵያ ሁሉንም ብሄር ያሳተፈች አገር መሆኗን ነው። ለምሳሌ እኔ ባህር ኃይል በምገባባት ጊዜ ኦሮሞ፤ አማራ፤ ትግሬ፤ ኤርትራዊ ሳይባል ነው ይቀጠር የነበረው። ሁሉንም ያሳተፈ ነው። የአሁኑም በዚያ መልኩ ነው ሊሆን የሚገባው። ሹመትና ስልጣን በዘርና በነገድ ከሚሆን ይልቅ ኢትዮጵያዊያን ተወዳደረው የሚቀጠሩበት መሆን አለበት የሚል እምነትም አለኝ። ስለዚህ ይህንን ስርዓት መዘርጋት ማለት አሀዳዊ ስርዓትን ይመጣል ብሎ እንደስጋት ይታያል ብዬ አላምንም።
አዲስ ዘመን፡- በሌላ በኩል በኢህአዴግ ድርጅቶች መካከል የነበረው ልዩነት ሰፍቶ እስከመለያየት በደረሱበት ሁኔታ በተለይም የህወሓት አመራሮች ለብቻቸው ተሰልፈው በቆሙበት ሁኔታ እንዴት የአገር አንድነት ይታሰባል ብለው የሚጠይቁ አካላት አሉ?
ማስተር ቺፍ ራስወርቅ፡- እኔ እስከማውቀው ድረስ አንድ ጠቅላይ ግዛት( ክልል ) ብቻ ነው በልዩነቱ የቀጠለው። እነሱም በዘመናቸው እኛ ያልነው ካልሆነ መንግሥት አይኖርም ከሚል መንፈስ እንጂ ከአገራቸው ይገነጠላሉ ብዬ አላምንም። ቢያስቡም የሚሆን ነገር እንዳልሆነ እረዳለው። አይመስለኝም፤ ግን ኢትዮጵያዊነታቸውን ማንም አይወስድባቸውም። ከሌላው ጠቅላይ ግዛት( ክልል) እነሱ የታጠቁ ፥ እነሱ ገንዘብ ያላቸው፤ የድሮ ስልጣን የነበራቸው ሆነው ራሳቸውን ችለው ልዩ ልዩ ሰልፎችን ሲያሳዩ ነበር። ይህም ለእኔ በጣም አሳዛኝ ተግባር ነው። ግን በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የትም አይደረስም። የተናገሩት ሁሉ እውነት ይሆናል ብዬ ባላስብም አንዳንድ ጊዜ የሚናገሩት ነገርም በኋላ የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም እንደሚባለው ተረቱ እውን እንዳይሆንባቸው እሰጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ የባህር ኃይል ውስጥ በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያና ኤርትራ አንድ አገር ነበሩ፤ ይሁንና ካለፈው 20 ዓመት ወዲህ ኤርትራ ራሷን ችላ ከመገንጠሏም ባለፈ ጦርነትም ሰላምም በሌለበት ሁኔታ ህዝቦቿ ተራርቀው ኖረዋል። አሁን ደግሞ ወደ ስምምነት መጥተዋል። ታዲያ ይህ ስምምነት አድጎ ወደአንድነት ያመጣቸዋል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ?
ማስተር ቺፍ ራስወርቅ፡- አዎ! ተስፋ አለኝ፤ ድሮም ቢሆን እንደእዚህ አይነት ፍላጎት አልነበረም። ከጃንሆይ ጊዜ ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ጀብሃና ሻዕቢያ አንድ ላይ ሆነው አገራችንን ነፃ እናወጣለን የሚል እቅድ ነበራቸው። ሆኖም ግን የአገሪቱ አንድነት እንደተጠበቀ ሰላሙን ለመፍጠር ይፈልጉ ነበር። እናም በእኔ እምነት ድሮም ቢሆን ሰላሙ ሩቅ አልነበረም። ግን ኃይል በዚያና ሰራዊቱ ውስጥ የነበሩት ኃይሎች ሳይቀሩ እጃቸውን እየሰጡ ወደሻዕቢያ ጦርነት ውስጥ ገቡ። ጦርነቱ ተስፋፋ፤ ነገር ግን ወደዚያ የገቡት ወደውት እንዳልነበር እሙን ነው። ህዝቡ ግን አሁንም አብሮ የመኖር ፍላጎት እንዳለው አውቃለሁ። እንደነገርኩሽ ባለቤቴም ኤርትራዊት ነበረች ሦስት ልጆችን አፍርተናል፤ በተመሰሳይ የሁለቱ አገር ዜጎች ተጋብተዋል፤ ተዋልደዋል። ስለዚህ ይህ ህዝብ በዚህ ሁኔታ ተለያይቶ ይኖራል ብዬ አላስብም። በእኔ እምነት ምንአልባት ተለያይተው ሊቆዩ የሚችሉት የአንድ መሪ ዕድሜ ዘመን ብቻ ሊሆን ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ ህዝቡ አብሮ መኖርን ያን ያህል የሚናፍቅ ከሆነ ሁለቱ መንግስታት ምን መሥራት አለባቸው ብለው ያምናሉ?
ማስተር ቺፍ ራስወርቅ፡- እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ትንሽ አስቸጋሪ የሚሆነው። በእኔ እምነት ዳግም አንድ አገር መመስረትም ሆነ በአንድ መንግሥት ለመመራት ከባድ ነው። ይልቁንም ኤርትራን በፌዴሬሽን ማስተዳደር ነው አመቺ የሚሆነው። ኤርትራም የራሷ ህልውና ኖሯት ወደቡን ለሁለት መጠቀም የሚቻልበት ዕድል ይኖራል። በተለይም አሰብ ድሮም በወሎ በኩል የሚዋሰን በመሆኑ መሰጠት አልነበረበት፤ ይህ ከሆነ በኋላ ደግሞ ከኤርትራውያን ይልቅ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ የሚሆን ይመስለኛል። በዚህ ሁኔታ የአንድ ወንድማማች ህዝቦች አገር ሆኖ መኖር ይቻላል። ኤርትራውያን ግን በራሳቸው ፍላጎት ወደ ኢትዮጵያ መመለሰ እንፈልጋለን ካሉ የተለያየ የአስተዳደር ስርዓት መቀረፅ አለበት ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም ፓርቲዎችን ይደግፉ እንደነበር ገልፀውልኛል በአሁኑ ወቅት የፖለቲካ ድርጅት አባል ነዎት?
ማስተር ቺፍ ራስወርቅ፡- እስከአሁን የትኛውም ፓርቲ ውስጥ አልገባሁም፤ የመግባትም እቅድ የለኝም።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ ቀጣይ እቅዶ ምንድን ነው?
ማስተር ቺፍ ራስወርቅ፡- እንዳልኩሽ እኔ የጡረታ ጊዜዬን ኢትዮጵያ ውስጥ ማሳለፍ ነው የምፈፈልገው። ነገር ግን የመሥራት አቅም ስላለኝ አሁንም አገሬን ማገልገል እፈልጋለሁ። ከተቻለም አዲስ በሚቋቋም የባህር ኃይል ውስጥ በሙሉ ልቦና የማገልገል ፍላጎት አለኝ። ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም ተወያይተናል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ማስተር ቺፍ ራስወርቅ፡- እኔም አክብራችሁ እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 21/2012
ማኅሌት አብዱል