በሥነ ቃል (ፎክሎር) ዘርፍ ከሚመደቡ ጥበባት ውስጥ አንዱ ክብረ በዓል ነው። ክብረ በዓል ሰዎች የተለያዩ ጉዳዮችን ምክንያት አድርገው በጋራ በመሰብሰብ የሚያከብሩት በዓል ነው። ክብረ በዓል የበዓል ክብር፣ ገናን፣ ጥምቀትን፣ ትንሣኤን፣ ጰራቅሊጦስን፣ መስቀልን፣ ፍልሰታን፣ ኅዳር ሚካኤልን፣ ሚያዝያ ጊዮርጊስን ለመሰለ በዓል የሚደረግ ማህሌት፣ ዘፈን፣ ንግስ እልልታና ደስታ፣ ሥራ አለመስራት፣ መንገድ አለመሄድ… በማለት ደስታ ተክለ ወልድ ክብረ በዓልን ያብራሩታል።
እንደ ደሰታ ተክለወልድ አገላለፅ፤ ክብረ በዓላት እንደ ገና ወይም ጥምቀት እንዲሁም አረፋና መውሊድ የመሳሰሉት በዓሎችን ምክንያት በማድረግ መንፈሣዊ እርካታን ለማግኘት የሚከናወን ድርጊት መሆኑ ነው። ድርጊቱም በምስጋና፣ በዘፈን፣ በጭፈራ፣ በሆታና በመሳሰሉት የሚገለፅ እንደሆነም መገንዘብ ይቻላል። በደስታ ማብራሪያ ላይ ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች አሉ። አንደኛው በማህበረሰቡ ውስጥ ትኩረት የተሰጣቸው እንደ ትንሣኤ፣ መስቀል፣ ኢድአልፈጥር የመሳሰሉ ዕለታት መኖራቸውንና ሁለተኛው ደግሞ ዕለታቱ የሚከበሩት እንደ ዘፈን፣ ንግስ፣ ነሺዳና መንዙማ በመሳሰሉት መንገዶች መሆኑን ነው።
ደስታ ተክለወልድ ካነሷቸው ክብረ በዓላት በተጨማሪ ቀለበት፣ ሠርግ፣ ክርስትና፣ ተዝካር፣ ማህበር የመሳሰሉት ድግስን መነሻ ያደረጉ ሁነቶች በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚታወቁ ናቸው። የዛሬው ትዝብት የበዓላቱን ምንነት መግለጥ ሳይሆን በበዓላትና በዝግጅቶች ሰበብ ምክንያት ስለሚደረጉ አላስፈላጊ ወጪዎች ነው።
ከተጠቀሱት ክብረ በዓላት በተጨማሪ ያሉ እንደ ሠርግ የመሳሰሉት ባህላዊ ክንውኖች በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተለመዱና እንደ ትውፊትም የሚታዩ ሲሆን አሁናዊ ገጽታቸው ግን ፈር ለቅቆ በአዳዲስ መጤ ባህሎች ተወርረው እናስተውላለን። በተለይም የበዓላትና የዝግጅት ፕሮግራሞች በቁጥር አድገው በወጪም ጨምረው ደጋሹን አፈር ድሜ ሲያበሉ የምናስተውልበት አጋጣሚ ብዙ ነው።
በእርግጥም እነዚህን ክብረ በዓላትና ዝግጅቶችን አስታከው የሚደረጉ ድግሶች ማህረሰብን በማቀራረብና ግንኙነትን በማጠናከር ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው። ነገር ግን ከማን አንሼነት የሚባለው መንፈስ በሁሉም ሰው ስለሰረጸ ሰው እንደ ቤቱ መኖር ትቶ እንደ ጎረቤቱ ለመኖር እየቃጣው ነው።
አሁን አሁን በዓላትና ዝግጅቶችን ተከትሎ የድግስ አደጋገስ ባህላችን ‹‹ከማን አንሼ›› በሚል ፈሊጥ የታጀበ መሆኑን ተከትሎ አላስፈላጊ ለሆኑ ኪሳራዎች መዳረግ ተለምዷዊ ድርጊት እየሆነ ይገኛል። በተለይ የኑሮ ውድነት ጣራ በነካበት ዘመን የሚደረግ ከአቅም በላይ የሆነ ድግስ ትልቅ ጫና መፍጠሩ አይቀርም። በዘመኑ ትልቁን የኢኮኖሚ ቀውስ በሰው ጫንቃ ላይ እየጣለ የሚገኘው ከአቅም በላይ ድግስ ስንቱን ባለ ዕዳ አድርጓል። ንብረትን አሽጧል። ድግስ የቃሉ ጥፍጥና ብቻ በቂ ነበር፤ ግና ምን ያደርጋል የድግሱ ምሬት አንገት አስደፊ እየሆነ ነው።
ኢትዮጵያ አሉኝ ከምትላቸው የማይዳሰሱ ባህላዊ ትውፊቶች አንዱ ሠርግ ነው። ታዲያ ተወዳጁ የሠርግ ባህላችን በሀገራችን በሁሉም ማህበረሰቦች ዘንድ የተለመደ ሲሆን፤ ድግሱም ‹‹ያለው ማማሩ›› በሚለው ብሂል አራማጆች ዘንድ የሚተገበር ነው። ነገሩ ትውፊታዊ ወግ ማዕረግ የሚታይበት ቢሆንም፤ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስን የሚያስከትልም ነው።
ሦስት ጉልቻ ያቆሙት ጓደኞቼ ከጥቂት ቀናት በኋላ አንደኛ ዓመት የጋብቻ በዓላቸውን ያከብራሉ። የሠርጋቸውን ድግስ ለእንግዶች ለማብላት የጓጉትን ያህል በዓመታቸው የመጀመሪያ ልጃቸውን ለማየት በጉጉት ሜዳ ላይ ዱብ ዱብ እያሉ ነው።
መቼም የትዳር ሕይወት ቀላል እንዳልሆነ የገባበት ያውቀዋል። ለዚያም ይመስለኛል ከፊሉ ሲያማርር የተቀረው ደግሞ የሚደሰትበትን አጋጣሚ የማስተውለው። በትዳር በተለይ የመጀመሪያ የሠርግ ቀን ደስታን በሰማያዊ ሚዛን ካልሰፈረው በቀር በምድር ልኬት እንዴት ተብሎ ሊገለጽ እንደሚችል ባለ ትዳር የሆኑት ጓደኞቼ ቃላት ያጡለታል። ደስታውን ምን ብለው እንደሚገልጹት አያውቁም። ይህንን ልዩ ደስታቸውን ከወዳጅ ዘመድ ጋር በድግስ ለማጣጣም ሽር ጉዱና ጎንበስ ቀናው እንዳጣደፋቸው የቅርብ ተመልካቾቻቸው መስካሪዎች ነን። (ለድግስ የሚደረገው ሩጫ ግን አቅምን ያላገናዘበ እንደነበር ልብ ይሏል)
መቼም እኛ ሀገር ከማን አንሼ የምትባል በማይክሮስኮፕ እንኳን የማትታይ ቫይረስ አይሏት ፈንገስ ነገር አለች አይደል? እናም በዚች ደዌ የተመቱት እነዚህ ሠርገኞች ይህን ድግስ እንደነ እንትና ልዩ ለማድረግ ሲባል ባልየው በምክር፣ አባቱ በብድር፣ እናቱ በእቁብ እህቱ በመላ፣ ወንድሙ በቅፈላ ያገኙትን ገንዘብ አሰባሰቡና ድግሱ ተጀመረ።
ተጀምሮም አልቀረ ከእንግዶች ጋር ተከበረ። ‹‹የዛሬ ዓመት የማሙሽ አባት..›› እያሉ ከማዜም በተጨማሪ ምርቃቱም ለጉድ ጎረፈ። በነገራችን ላይ ይህች የሙዚቃ ግጥም ትንቢት ልትሆን ትንሽ ነው የቀራት።
እንደ ጉድ ተበላ ተጠጣ የተስተናጋጁ ምርቃት ተሰብስቦ በክሬዲት ሀወር ተካፍሎ ማስተርስ ይሆናቸው ይመስል አዥጎደጎዱት። በጣም የሚገርመው የተሰበሰበው ምርቃት ሁሉ ከምግብ ጋር የተገናኘ ነው። አንዱ ተነስቶ ‹‹ክርስትናን ለመብላት ያብቃን›› ‹‹የልጃችሁን ልደት ለመብላት ያብቃን››… ይላል። ደስ ስንል ምክንያት እየፈጠርን በሰው ድካም እና እንግልት መብላት ብቻ፤ ሠርገኞቹ ስቃያቸውን በልተው ደግሰው ያበላሉ፤ ታዳሚዎች እየሳቁ ይበላሉ።
በድግስ ምክንያት የወጣውን ወጪ ያላገዛቸውና በሰቀቀን ዘመን ዞሮ ያለያቸው የመጀመሪያ ክርስትና መብላት ይመኛል፤ ድግሱ አልቆ እስከመጨረሻው የድስት ጥራጊ ህቅታ ድረስ ሁሉም ነበሩ። ከድንኳን ማፍረስ እስከ ብድር መመለስ ግን ማንም ከጎናቸው አልነበረም።
አሁን ላይ ሆነው ሲያስቡት ሁሉንም ነገር አየር ላይ በተንጠለጠለ ተስፋ ሳይሆን እንደ አቅማቸው አድርገው ቢሆን ኖሮ ቢያንስ ብድር የመመለስ ጭንቀትና እቁብ የመክፈል ውጥረት አይኖርባቸውም ነበር። ለድግስ ያባከኑትን ገንዘብ አንዴ አሰባስበው የራሳቸውን ሥራ ጀምረውበት ቢሆን ኖሮ ቢያንስ ነገ ላይ ለልጃቸው የዳይፐር መግዣ አይቸገሩም ነበር።
በሀገራችን ባህል ከአቅም በላይ በሆነ ድግስ ሠርግ፣ክርስትና እና መሰል የደስታና የኀዘን ዝግጅቶችን በሞቀና በደመቀ ሁኔታ ማድረግ የተለመደ ተግባር ነው። በፍላጎት ብቻ ያለ እቅድ በመመራት በአራጣና በብድር ከአቅም በላይ የሆነ ወጪ በማውጣት በደስታቸው ማግስት በሀሳብ ውጥረት የሚያዙት ጥቂቶቹ አይደሉም።
በማህበረሰባችን ዘንድ በሚፈፀም ከልክ ያለፈ ድግስ እየባከነ ያለውን ሀብት ያሳዝናል። ማህበረሰቡ እሴቶችን ጠብቆ በመያዝ እና ለትውልድ እንዲተላለፉ የሚያደርገው ጥረት ጠንካራ ቢሆንም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት የሆነውን ከልክ ያለፈ ድግስ ግን መቅረት የሚገባው ነው።
ማህበረሰቡ ዓመቱን ሙሉ ለፍቶ የሚያገኘውን ከላይ ለተጠቀሱት ክብረ በዓላትና ዝግጅቶች የተንዛዛ ድግስ የሚያውልበት አባዜ ከዕለት ዕለት እየጨመረ ነው። ታዲያ በዚህ ዓይነት በባህል ወረርሽኝና በባህላዊ ልምዶች አለአግባብ የሚወጣውን ወጪ ለማስቀረት ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መሰጠት አይኖርበትም ትላላችሁ፤ተገቢ ያልሆነን ነገር ወደ ጎን በመተው በእቅድና በአቅም መመራት የኑሮ መሠረት የደስታ ምንጭ በመሆኑ ለአቅማችን ሚዛን ቢኖረን ይመረጣል።
‹‹የሀገር ምድሩን ሠርግ በልቼ ልጄን ካልዳርኩ ምኑን ሰው ሆንኩ!፤ ልጄ በቬሎ ካልወጣች ሞቻለኋ!›› በሚል ተለምዷዊ ካቴና ታስረው ከአቅም በላይ ለደገሱና ለሚደግሱ፤ አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው፤ ታላቅ ችሎታ ነው የምትለዋን ዜማ ጀባ ማለት ነው።
ከሠርግ ወጣ ስንል ደግሞ ለቀብርና ተዝካርም ድል ያለ ድግስ ተጀምሯል። በየአካባቢው በልቀሶ ሥነ ሥርዓት ላይ ከቀብር መልስ የሚዘጋጀው ብፌ የባለ አምስት ኮከብ ሆቴልን ያስንቃል። እነዚህ ሰዎች የሚደግሱት ኪሳቸው ስለሞላ አይደለም። አገሌ የሚባል ጎረቤታቸው የሞተ ጊዜ ከሠርግ የማይተናነስ ድግስ ተደግሶለት ለምን የእኛ ዘመድ ሲሞት ይቀርብን በሚል ፉክክር ነው። (ሲደክሙ እንጂ ሟች መች ቀና ብሎ ያያቸዋል) እኔ በምኖርበት አካባቢ ተዝካር ለማውጣት ለብዙ ዘመናት ያካበቱትን ሀብት ለድግስ በማዋላቸው ለብድር የተዳረጉ ሰዎች በርካታ ናቸው። የሟች ተዝካር እንዲዘከር እና ሥርዓቱ እንዲፈጸም በትንሹ እስከ 120ሺህ ብር ወጪ ያወጡ ሰዎችም አይጠፉም።
ከመጠን ያለፈ ድግስ በሁሉም ቦታ መቅረት ይኖርበታል። ምክንያቱም በማህበረሰቡ ዘንድ የበታችነት ስም እንዳይሰጥ እየተባለ እንጂ የልጆች ማሳደጊያ የሚሆነው ገንዘብ የሚጠፋበት አጉል ልማድ ነው።
ከላይ ደስታ ከዘረዘሩልን ክብረ በዓላት በተጨማሪ አሁን ላይ ደግሞ ከየት እንደመጡ የማይታወቁ ለተጨማሪ ወጪና ድግስ የሚዳርጉ እንደ ልደት ፕሮግራም፣ ቤቢ ሻዎር፣ ብራይዳል ሻወርና የመሳሰሉ ድግስ ተኮር ሁነቶች እየተለመዱ መጥተዋል።
መጤ ብለን ከምንጠራቸውና ላልተፈለገ ወጪ ከሚዳርጉ አዳዲስ ክስተቶች አንዱ ‹‹ቤቢ ሻዎር›› የሚባል የድግስ ፕሮግራም ነው። ልጅ ሲወለድ የሚደሰቱ ወላጆች ብቻ ባለመሆናቸው ይህ ፕሮግራም አንድ ሕፃን ለመወለድ በመንገድ ላይ በሚሆንበት ጊዜ እናቱና የቅርብ ሴት ጓደኞቿ ተሰብስበው የሚያከብሩት ነው። በዚህ ፕሮግራም ላይ የወደፊቱ አያቶች፣ አክስቶች እና አጎቶች፣ የአጎት ልጆች፣ ጓደኞች እና ሌሎች የሚወዳቸው ሰዎች አዲሱን የቤተሰብ አባል ለመቀበል ፈቃደኞች መሆናቸውንም ያሳያሉ። ጓደኛሞች እና ቤተሰቦች ከሚወለደው ልጅ ወላጆች ጋር ጊዜ የሚያጋሩበት ፕሮግራም ላይ ይነስም ይባዛም ለወጪ ይዳረጋሉ። ተመሳሳይ አልባሳትን በውድ ከማሰራት ጀምሮ እንደ ቢራ፣ ወይን፣ ኬክ፣ ምግብ…. ያሉት ደግሞ የፕሮግራሙ ማድመቂያ ናቸው። (ያው የሌለው በብድርም ቢሆን መደገሱ አይቀርም)
ሌላኛው ‹‹ብራይዳል ቱ ቢ›› የሚባል ፕሮግራም የሙሽራዋ ሠርግ መቃረብ አስመልክቶ ሙሽራዋን ለማክበርና ለሙሽራዋ ስጦታና ድግስ የሚዘጋጅ ሲሆን በዚህ ፕሮግራም ላይ ወይን፤ ኬክ፣ ከተቻለም ውስኪና መሰል ውድ የአልኮል መጠጦች…. ይቀርባል።
ወገኖቼ በብድር ዕድሜ ላይ የብድር ገንዘብ ተጨምሮበት እንዴት ነው መኖር የሚቻለው። ሰበብ ፈልገን ብር የምናወጣበት አጋጣሚ አበዛዙ እኮ አይጣል ነው።
ሰፊ ጥናቶች ቢደረጉ የድግስ ወጪ በማህበረሰብ አኗኗርና ኢኮኖሚ ፈጣን ለውጥ እንዳይመጣ ተጽእኖ መፍጠሩ አይቀርም። ለሠርግ፣ ተስካር፣ ልደት፣ ክርስትና፣ ለምርቃት ጨምሮ ለተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች በሚከናወኑ ድግሶች ምክንያት የሚወጡ ረብጣ ገንዘቦች የአንድን ግለሰብ ኑሮ ምን ያህል በዘላቂነት እንደሚጠግን መገመት አያዳግትም። ይብዛም ይነስም በድግስ የሚባክን ከፍተኛ ወጪ በግለሰብም ሆነ በማህበረሰብ አኗኗርና ኢኮኖሚ ላይ ፈጣን ለውጥ እንዳይመጣ የራሱ የሆነ ተጽእኖ ያሳድራል።
በነገራችን ላይ በመንግሥት ደረጃም የሚደረገው የድግስ ወጪ እንደ አገር ተጽእኖ መፍጠሩ አይቀርም። ከልክ በላይ ለድግስ ወጪ ማድረግ ለኢኮኖሚ እድገት እንቅፋት ነው። መንግሥትም ቢሆን ድግስ በድግስ የሚሆንበት ሰሞነኛ ክስተቶችን ያስተናግዳል። ለእገሌ አቀባበል ድግስ፣ እገሌ ሲሄድ እገሌን በተመለከተ በተዘጋጀው ድግስ የተሳተፉ ሰዎች ምስጋና ማቅረቢያ ሌላ ድግስ ..ከዚያም በዚህኛው የምስጋና ማቅረቢያ ድግስ ላይ ለተሳተፉ ሰዎች ደግሞ ሌላ ምስጋና ማቅረቢያ ድግስ ከዚያም የድግስ እውደት እየሆነ መቀጠሉን ማየት የአደባባይ ምስጢር ነው።
ከመጠን ባለፈ ድግስ የሚባክን ከፍተኛና አላስፈላጊ ወጪ ለመቀነስ ከግለሰቦች በተጨማሪ በማህበረሰብ ውስጥ ተሰሚነት ያላቸው የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው። ይልቁንም ለማህበራዊ ድግሶች የሚባክን ወጪ ለመቀነስና የቁጠባ ባህልን ለማጎልበትና ለማጠናከር የአስተሳሰብ ለውጥ ሥራዎች መስራት አለባቸው። ምክንያቱም ስንት ተለፍቶና ተጥሮ ተወጥቶና ተወርዶ የተገኘን ገንዘብ በድግስ ከማባከን ይልቅ ገቢ ማስገኛ ቀይሮ ሕይወትን መቀየር ተመራጭ ነው እንላለን።
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 20/2012
አዲሱ ገረመው