መጪውን ጊዜ አስቀድመው መተንበይ የሚችሉ ሰዎች በዘመን መካከል ለቅመም ያህል አይጠፉም። ‹‹ተማር ልጄ….›› ያለው ድምጻዊ ለዚህ አስረጂ ነው። የአሁኑን እውነታ ቀድሞ የተረዳ ነው። ብዙ ወላጆች ለአብራካቸው ክፋይ የሚያወርሱት ጥሪት መቋጠር ተስኗቸዋል። ይልቁንም አሁን አሁን በወላጆች ዘንድ ልጅን አስተምሮ ለቁም ነገር ማብቃት እንደ ውርስ እየተቆጠረ መጥቷል። ማህበረሰቡ በተለይም ከተሜው በወጉ በልቶ ማደር ሳይችል መልካም ስም ካለው የግል የትምህርት ተቋም ልጁን ለማስተማር ሲወጣ ሲወርድ ይስተዋላል።
ይሁን እንጂ የትምህርት ተቋማቱ እምነት የተጣለባቸውን ያህል የበሰለ ትውልድ እያፈሩ ነው ወይ የሚል ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖች አሉ? ከዚህ አኳያ አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታው ለግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምን አንድምታ አለው? ምን እድሎች እና ተግዳሮቶች ይዟል? መፍትሄዎቹስ ምን ሊሆኑ ይችላሉ? የሚሉትን ንዑስ ርዕሰ ጉዳዮችን በአዲስ ዘመኗ አስኳላ አምድ ልናስቃኛችሁ ወደድን።
ፍኖተ ካርታው ምን ለውጦችን አምጥቷል?
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እንደገለጹት፤ የትምህርት ሥርዓቱ በክህሎትና በብቃት ተወዳዳሪ ዜጋ በማፍራት በኩል ችግሮች ተስተውለውበታል። በመሆኑም ያሉበትን ችግሮች ፈትሾ መፍትሔ ማበጀት አስፈላጊ ነበር። አጠቃላይ የትምህርት ሥርዓቱን የሚፈትሹ ጥናቶች ተደርገው አመላካች ፍኖተ ካርታ ተቀይሷል። በውስጡም በርካታ የለውጦች (ሪፎርም) የተደረጉ ሲሆን ከእነዚህ ለውጦች መካከልም የትምህርት ተቋማትን በዘርፍ በዘርፍ ማደራጀት ይገኝበታል።
እርሳቸው እንደሚሉት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም የትምህርት ፍኖተ ካርታው ግኝት ነው። ከአጸደ ሕፃናት እስከ ዩኒቨርሲቲዎች ድረስ በአንድ አካል መመራታቸው ዘርፉ ትኩረት እንዳልተሰጠው ጥናቱ በማመላከቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችን (የግሎቹን ጨምሮ) በአንድ ሚኒስቴር፣ አጠቃላይ ትምህርትን ደግሞ በትምህርት ሚኒስቴር እንዲመሩ መደራጀት ተችሏል።
ሥርዓተ ትምህርቱን በጥልቀት ለመፈተሽ ከዩኒቨርሲቲዎች በተውጣጡ እና ውጭ አገር በሚገኙ የዘርፉ ምሁራን ሰፊ ጥናት መካሄዱን ያነሳሉ። ተቋማትን በትኩረት መስክና በተልዕኮ ማደራጀት፣ የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ፣ የአዋጅ፣ መመሪያዎች እና የመስፈርቶች ዝግጅትና ክለሳ መሰራታቸውን ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማርያም በበኩላቸው፤ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የእውቀት፣ የክህሎት እና የአመለካከት ክፍተቶች እንዳሉባቸው በጥናቱ ተለይቷል፤ በመፍትሔነትም የ18 «ኮርሶች ሲለበስ» ተዘጋጅቷል። 14ቱን በጋራ የሚወሰዱ የትምህርት ዓይነቶች (ኮመን ኮርሶች) የ2012 ዓ.ም የዩነቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች እየወሰዱ ይገኛሉ፤ (አስራ አምስተኛው የታሪክ ትምህርት በሁለተኛው አጋማሽ ይጀምራል) ነው ያሉት።
በጥናት የተለዩትን የመምህራንን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የክህሎት፣ የእውቀት፣ የአመለካከት፣ የምክንያታዊነት እና የተቋማት የግብዓት ችግሮችም የሚቀረፉበት አሠራር ይዘረጋል ባይ ናቸው። በ2012 ዓ.ም አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ከአራት መቶ በላይ የግል የትምህርት ተቋማት አስተማሪዎችም በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል ማግኘታቸውን ገልጸዋል ሚኒስትሯ።
«የጥራትና የብቃት ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም» ያሉት የግል ከፍተኛ ትምህርት እና ቴክኒክና ሙያ ተቋማት አሰሪዎች ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተገኝ አለሜ ጌታሁን፤ በዘርፉ እየተደረጉ ያሉ የለውጥ ሥራዎችን (ሪፎርም) መሠረት በአዲሱ የትምህርት ሥርዓት እያስተማሩ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።
የግሉ ዘርፍ ተግዳሮቶች ምን ነበሩ? በሪፎርሙ ይቃለሉ ይሆን?
አቶ ተገኝ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ 242 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይገኛሉ። የትኛውም የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እንደሌሎች ኢንቨስትመንቶች እንዲጠናከሩ በመንግሥት በኩል ድጋፍ አልተደረገም። ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተከራይተው የሚያስተምሩ ናቸው።
ይህም የትምህርትን ጥራት ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጥራል። ለምሳሌ፡-ቤተ-ሙከራዎች፣ቤተ-መጽሐፍት፣የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣የጥናትና ምርምር ማዕከላት እና ሌሎች መሠረታዊ ሰርቶ ማሳያዎች ተቋማቱ አሁን በሚገኙበት ቁመና ላይ ማሟላት አይችሉም። ምክንያቱም የተከራዩአቸው ሕንፃዎችና ቤቶች ለትምህርት ቤት ተብለው የተሰሩ ባለመሆናቸው በተሟላ መልኩ ተማሪዎችን ለማስተማር አይቻልም። በቂም ቦታ የላቸውም። ማህበሩም በ1996 ዓ.ም የተመሰረተ ቢሆንም የራሱ የሆነ ቦታ የለውም። ተቋማቱ ጥናትና ምርምር ሥራዎችን በመስራት ለፖሊሲ አውጪዎች መነሻ የሚሆኑ የምርምር ሥራዎችን ማበርከት የሚገባቸው ቢሆንም ለዚሁ አገልግሎት የሚውል ማዕከል ስሌላቸው አገራዊ ኃላፊነታቸው እየተወጡ አይደለም። እናም አሉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በመስፈርቱ መሠረት የማስተማሪያ ግብዓቶችን (ቤተ ሙከራ፣ የኮምፒዩተር እና ሌሎችም) እንዲያሟሉ በመንግሥት በኩል በተለየ መንገድ ድጋፍ መደረግ ነበረበት ይላሉ።
በተከለሰው ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ከፍተኛ ተቋማት ማሟላት ያለባቸው ጉዳዮች በግልጽ ተጠቅሰዋል። ነገር ግን ብዙ የጋራ ሥራዎች የሚጠይቁ ጉዳዮች መኖራቸውን አስረድተዋል። ለአብነትም በትምህርት ፍኖተ ካርታ የግንዛቤ መድረኮች በአገሪቷ ከሚገኙ ከ240 በላይ የግል ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ውስጥ የተሳተፉት አራት ብቻ ናቸው። ሌሎቹ ሰነዱ እንዲደርሳቸው ቢደረግም የውይይት መድረክ ሊፈጠርላቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።
ቅንጅታዊ ሥራዎችና ትሩፋቶች
የግል የትምህርት ተቋማት ለዘርፉ ችግሮች በጋራ መፍትሄ ለመፈለግ እና መብታቸውን በጋራ ለማስከበር ዓላማ ሰንቀው ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በማህበር መደራጀታቸውን የገለጹት አቶ ተገኝ፣ ማህበሩ 115 የግል የትምህርት ተቋማት በአባልነት ያካተተ ሲሆን ሌሎች ተቋማት አባል ለመሆን በሂደት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት ችግሮች በተጨባጭ በሚስተዋሉባቸው ጊዜ መንግሥት አስፈላጊውን ርምጃ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚወስድ ተናግረዋል። የመንግሥትም ሆኑ የግል የትምህርት ተቋማት ዓላማቸው ብቃት ያለው ትውልድ ማፍራት እንደሆነ የገለጹት አቶ ተገኝ አለሜ፣ የግሉ የትምህርት ተቋማት ወደ ዘርፉ ገብተው የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት ሲያስቡ የመንግሥትን ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በተገቢው መልኩ መተግበር አለባቸው ብለዋል።
እንደ አቶ ተገኝ ገለጻ፤ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ መንግሥት ትውልድን በማነጽ የግሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድርሻ ቀላል አለመሆኑን ተረድቷል። በዚህም እንደ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉ የግል ትምህርት ተቋማት መምህራንም የነፃ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሠራሮች ተዘርግቷል። በ2011 ዓ.ም በሁለተኛ ዲግሪ 48፣ በሦስተኛ ዲግሪ ደግሞ 30 በድምሩ 78 መምህራን የነፃ ትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል።
ሲጠቃለል
ስለዚህ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሰው ልጅ አዕምሮ የሚገነባባቸው ናቸው። ስለዚህ የተቋማቱ አስፈላጊውን የትምህርት ግብዓት እንዲያሟሉ በመንግሥት በኩል ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል። የግሉ የትምህርት ዘርፍ እስከ ወረዳ ከተሞች ድረስ ተደራሽ በመሆኑ ከፍተኛ የተማረ የሰው ኃይል የሚያመርት ነው። የተቋማቱን ክፍተቶች የሚሞሉ ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የሪፎርሙ አካልና ባለቤት ማድረግ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 20/2012
ሙሐመድ ሁሴን