ዛሬ በዓለማችን ላይ ለሰው ልጃች ሰላም ማጣት ለፍትሕና ፍትሐዊነት መጓደል፣ ለምጣኔ ሀብታዊ፣ ለማህበራዊና ለዴሞክራሲያዊ ዕድገቶች መቀጨጭ ዋና ዋና ከሚባሉ ችግሮች መካከል አንዱ ሙስና ነው። ይህን ዓለምአቀፋዊ ችግር ለመከላከል ሀገሮች በተናጠል ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተጨማሪ በጋራ ሊታገሉ የሚያስላቸው ስምምነት እንዲኖር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኩል ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.ኤ.አ ከሚያዝያ 2000 ጀምሮ ስምምነቱን በማርቀቅ ረገድ የተለያዩ ዝግጅቶችን በማድረግ ረቂቅ ስምምነቱ እ.ኤ.አ ህዳር 09 ቀን 2003 በሜክሲኮ ሜሪዳ በተካሄደው የድርጅቱ ጠቅላላ ጎባኤ ላይ ለአባል ሀገሮች ቀርቦ በወሳኔ ቁጥር 58/422 ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ስምምነት ሆኖ ፀድቋል። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ዕለቱ ስምምነቱን በፈረሙ ሀገሮች ዘንድ በየዓመቱ እ.ኤ.አ ታኅሣሥ 09 በኢትዮጵያ ደግሞ ህዳር 30 ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን ሆኖ እየተከበረ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ስምምነቱን በመቀበል፣ በማረቀቅም ሆነ በማጽደቅ ረገድ የራሷን ሚና ከመጫወቷም በተጨማሪ በዓሉን ላለፉት 13 ዓመታት በተለያዩ ዝግጅቶች አክበራለች። በያዝነው ዓመትም በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ15ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ14ኛ ጊዜ «ሁለንተናዊ ልማታችንና ሰላማችንን ለማረጋገጥ በሙስና ላይ እንዝመት፤ ጊዜው የተግባር ነው!» በሚል መሪ ቃል ታኅሣሥ 18 ቀን 2011ዓ.ም ተከብሯል፡፡
በፀረ ሙስና ትግሉ የሚዲያ ተቋማት እና የሲቪክ ማህበራት ሚና፤ የግልጽነት አሠራር ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመዋጋት ያለው ሚና፤ በሚሉ አርዕስቶች ላይ የተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎችና የህብተረሰብ ክፍሎች የሀገራችንን ስር የሰደደ የሙስናና ብልሹ አሠራርን በአዲሱ ለውጥ ለመታገልና ለወደፊት ይህን ችግር ለመፍታት እንደ ሀገር ምን መሠራት እንዳለበት የፓናል ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ስለሙስናና ብልሹ አሠራር ያላቸውን አቋምና ለችግሩም መፍትሔ ይሆናል ያሉትን ሃሳብ እንደሚከተለው አቅርበዋል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፀረ-ሙስናና ስነ-መግባር ኮሚሽን ኮምሽነር አቶ አየልኝ ሙሉዓለም በዕለቱ ባደረጉት ንግግር «ሙስናና ብልሹ አሠራር ሀገርን የሚያፈርስ መሆኑን ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት በሀገራችን በተጨባጭ ዓይተናል፤ በተለይ እንደኛ በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ሙስና ሲንሰራፋ የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም ሆነ የህዝቡ ኑሮ ከድጡ ወደማጡ ይሆናል። በተለይ በሀገራችን አሁን ላይ ተማሪው ምንም ሳያጠና ውጤት የሚዘርፍበት፤ ለፍቶ ጥሮ የሚያድረው ጉሮሮውን ዘግቶ ማደር ሲያቅተው ሌሎች ደግሞ ሳይሠሩ የሚከብሩበት፤ በየዩኒቨርሲቲዎች በማዕረግ የተመረቁት ቁጭብለው ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ገዝተው ወደ ሥራ የሚሰማሩበት፤ በአጠቃላይ የመልካም ሥነ-ምግባር ባለቤቶች የወደቁበትና የከሠሩበት አስከፊ ወቅት ነው፤ ሙስናና ብልሹ አሠራር የሀገራችን ሰላም አውኳል ህዝባችንንም ለከፋ ችግር አጋልጧል» ብለዋል፡፡
ይህን ሁኔታ በፍጥነት መመለስ ካልተቻለ የነገው ትውልድ ይበልጡን ሀገሪቷን ለከፋ ችግር የሚያጋልጥ ነው የሚሆነው። ቀደም ሲል የመልካም ሥነ-ምግባር ባለቤት የሆኑ ልጆችን አሳደጊህ ይደግ፤ እንዲሁም የብልሹ ሥነ-ምግባር ባለቤት የሆኑትን ደግሞ አሳደጊህ አይደግ ይባል ነበር፡፡ እነዚህ አሁን ላይ የደበዘዙ መልካም እሴቶቻችን በማህበረሰቡ ዘንድ እንዲጠነክሩ በማድረግ መሥራት እንደሚጠበቅ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
ሩዋንዳውያን ከትናንት ስህተታቸውን በመማር እኛ ቱትሲና ሁቱ ሳንሆን ሩዋንዳውያን ነን በማለት የትናንት ትውልድ የማይረሳውን ታሪካቸውን ዳግም ላይደግሙት ተማምለው ሀገራቸውን በማልማት ላይ ናቸው፤ ሙስናና ብልሹ አሠራርን አንድ ሆነው በመታገል ሀገራቸውን ለማሳደግ ቆርጠው በመሥራት ላይ ናቸው፤ ታዲያ እኛም ከሩዋንዳዊያን ታሪክ በመማር ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ›› ከሚል የሆዳሞች መርህ ተላቅቀን ሀገራቸን ለነገ የተሻለች እንድትሆን ሙስናና ብልሹ አሠራርን ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል አጥብቆ እንዲዋጋ አፅንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።
«በሀገራችን በመሠራት ላይ ባሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችና በትልልቅ ተቋቋማት ላይ ሲፈጸም የነበረው የተደራጀ ሌብነት በከፍተኛ የመንግሥት አመራር ተዋናይነት ሲተገበር የቆየና ከፀረ-ሙስናና ሥነ-ምግባር ኮምሽኑ አቅም በላይ እንደነበር። ይህን ዘረፋ ኮምሽኑ የሚችለውን ያክል ባይታገል ኑሮ ከዚህም በላይ የከፋ ይሆን እደነበር » ካሉ በኋላ ፤ሙስናና ብልሹ አሠራርን መታገል ለኮሚሽኑ ብቻ የሚተው ሳይሆን እያንዳንዱ ዜጋ ቆርጦ በመነሳት መታገል እንዳለበት አሳስበዋል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ በውይይቱ ወቅት፤ ሀገራችን ከነበረችበት የኋላቀርነትና የድንቁርና ኑሮ ተላቅቃ ወደተሻለ ደረጃ ለመድረስ የብርሃን መንገድን ተያይዛለች፤ ይህ ለውጥ ተሳክቶ ብርሃኑ ለሁሉም እንዳይዳረስ የሚያደርግ የተደራጀ ሌብነት ሀገሪቱን ችግር ላይ እየጣለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ነቀርሳ ከስሩ ነቅሎ ለመጣል በተደራጀ መልኩ መሥራት ይጠበቀብናል፤ የህግ የበላይነት እንዲከበር ማደረግም ዋነኛው ተልኳችን ነው» ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ የአሠራር ክፍተቶችን በመገምገም እሴት በመጨመር አሁን የተጀመረውን የሙስናና ብልሹ አሠራር ትግል እስከ መጨረሻ ድረስ በማዝለቅ፤ የሀገርን ሀብትና ንብረት የዘረፉና በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ ተጠርጣሪዎች በህግ ፊት ቀርበው ተገቢውን ፍርድ እንዲያገኙ በርትተን በመሥራት ላይ ነን በማለት ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ ጠንክሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በውይይት መድረኩ ፤ ሙስና የሀገርንና የማሀበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚገታ ነው። ዓለምም ሆነ ሀገራችን ይህን አጸያፊ ሥራ መዋጋት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። የዓለም ባንክ በተለያዩ ጊዜያቶች ያጠናቸው ጥናቶች እንደሚያሳየው አንድ ትሪሊዮን ዶላር በጉቦ መልክ የሚባክን ሲሆን፤ 2.6 ትሪሊዮን ዶላር የሚሆን ገንዘብ በተለያዩ የሙስና ወንጀል ድርጊቶች እንደሚሰረቅ ጠቁመዋል።
በአፍሪካ ደረጃ ሲታይ በቅርቡ ትራንስፓራንሲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ዘገባ ከ90 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከአህጉሪቱ እንደሚወጣ፣ በኢትዮጵያም በከፍተኛ መጠን የውጭ ምንዛሬን ወደውጭ በማሸሽ ሀገሪቷን ለውጭ ምንዛሬ ችግር እንደዳረጋት፣ በዚህ ምክንያትም 43 በመቶ የሚሆኑ የአህጉሪቱ ነዋሪዎች በከፋ ድህነት ውስጥ እንዲኖሩ መገደዳቸውና ሙስና በአንድ ሀገር ውስጥ ፍትሐዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል እንዲይኖር በማድረግ ባለፉት ዓመታት እንደነ ሴራሊዮን፣ ላይቤሪያ፣ ግብፅ ወ.ዘ.ተ በመሳሰሉት የአፍሪካ ሀገራት ለእርስ በርስ ግጭት መዳረግ ምክንያት መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።
በሀገራችንም ሙስናና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈፀሙ ሰዎች ብሄርንና ዘርን መደበቂያ በማድረግ ሀገርን ይበልጥ ለማተራመስ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉበት ወቅት ላይ ነው ያለነው። በመሆኑም ሙስናና ብልሹ አሠራርን የምንከላከለው የፀረ ሙስና ተቋም ስላቋቋምን አይደለም። ይልቁንም ይህን አስፀያፊ ተግባር መታገል የሁሉም ዜጋና የበርካታ ተቋማት ኃላፊነት ነው። ስለዚህ ሁሉም ዜጋና ተቋማት ቁርጠኛ አቋም ይዘው መታገል ይኖርባቸዋል። እንዲሁም ሚዲያዎች፣ የመንግሥትና የግል ተቋማት ሙስና ሲፈፀም ለህብረተሰቡ ማጋለጥ ኖርባቸዋል። ህብረተሰቡም ሙሰኛ ዘር፣ ብሄርና ሃይማኖት ስለሌለው በዙሪያቸው ያሉትን ሌቦች በማጋለጥ ህግ ፊት እንዲቀርቡ ማድረግ ይጠበቅበታል።
በከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት የተቀመጡ ኃላፊዎች ሙስናና ብልሹ አሠራርን ቁርጠኛ አቋም ወስደው መታገልና አለመታገላቸውን፤ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ሪፖርት የሚያደርጉበትን የአሠራር ስርዓት በመዘርጋት ተጠያቂ የሚሆኑበትን ስርዓት እንዘረጋለን ያሉት አፈ ጉባዔው፤ የፌዴራል ፀረሙስና ኮሚሽን ሕፃናትንና ወጣቶችን በስነምግባር የታነጹና ሙስናን የሚጸየፉ ትውልድ እንዲሆኑ የሚሠራውን ሥራ አጠናክሮ መሥራት እንደሚጠበቅበት አመላክተዋል።
በአጠቃላይ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የሃይማኖት አባቶች የህሌና ቁረጠኝነት ማነስ፤ እንዲሁም የሲቪክ ማህበራት ለይስሙላ የተቋቋሙ መሆናቸው አሁን ላይ ለምናየው ከፍተኛ ኪሳራና ሁከት ተጋልጠናል። በመሆኑም ዛሬ ከሁሉም ጊዜ በተሻለ ሙስናና ብልሹ አሠራርን የምንታገልበት የተሻለ አስተዳደራዊ ለውጥ ላይ በመሆናችን ሁሉም በየፈርጁ ሊታገል ይገባል በማለት አፈ ጉባዔው አሳስበዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች አቶ ጸጋዬ ወጁ በበኩላቸው «አሁን ላይ በሀገራችን የምናየው የሙስናና የብልሹ አሠራርን ሁሉም በተባበረ ክንድ ካልታገለ በስተቀር ነገ አገሪቱ ሁሉም ዜጋ የማይጠቀምባት የወንበዴዎች መፈንጫ ትሆናለች። ስለዚህ እነዚህ በሚዲያ የሰማናቸው የሙስናና ብልሹ አሠራሮች ከዚህ በላይ ሀገር እንዳያጠፉ ሁሉም ዜጋ ሊረባረብ ይገባል።
«ከአሁን በፊት በሀገራችን ኤች አይቪ ኤድስ ወጣቱ ኃይልን እንደ ሰደድ እሳት ሲለበልበው ሁሉም ሰው ዘርና ሃይማኖት ሳይለያየው ሁሉም የሃይማኖት፣ የመንግሥትና የግል ተቋማት በተለይ ትምህርት ቤቶች መምህራን፣ አርቲስቶችና የሲቪክ ማህበራት በጋራ በመረባረብ የበሽታውን አስከፊነት በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ እንዲፈጠር በማድረግ፤ በህመሙ ተጎድተው ለነበሩ ወገኖቻችንም ተገቢውን እንክብካቤና ህክምና እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡
«ዛሬ በሀገራችን ኤች.አይ.ቪ ኤድስን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት ባንችልም ትልቅ ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ችለናል። ስለዚህ ሙስናና ብልሹ አሠራር ደግሞ ከኤች.አይ.ቪ የበለጠ ሁሉንም ሰው የሚያጠፋ ነቀርሳ በመሆኑ፤ በፀረ-ሙስና ኮሚሽኑ ትግል ብቻ ልናቆመው የማንችለው የሀገራችን ወቅታዊ ችግር በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ሊታገል ይገባል» በማለት ሃሳባቸውን ገልጸዋል።
አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው፤ ስለሙስናና ብልሹ አሠራር ሁሌም በየቦታው እና በየሚዲያው ይነገራል። የፀረሙስና ኮሚሽኑ በደርግ ጊዜ እራሱ ጠቋሚ እራሱ ፈራጅ ነበር። አሁን ባለው መንግሥትም ተመሳሳይ ነገር ነው የምናየው። በሀገራችን መንግሥት የህዝብን ድምፅ ወይም የምርጫ ኮሮጆ በመስረቅ የሚመራ መሪ ባለበት ህዝብን ምን ፍጠር ነው የምንለው። መጀመሪያ ሙስናና ብልሹ አሠራር የሚመጣው ከምናስቀምጠው መንግሥት ነው። በህዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት እስካላቋቋምን ድረስ ሙስናን በሀገራችን ለማስቆም የማይቻል ነገር ነው በማለት የመፍትሔ ሃሳብ ያሉትን ጠቁመዋል።
አቶ አብርሃ ደስታ በበኩላቸው፤ ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል በርካታ ዘዴዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገርግን አንድ ቀድመ ሁኔታ ያስፈልጋል፤ እርሱም ገለልተኛና ነፃ የሆነ ተቋማት ያስፈልገናል። የህዝብ ፖሊስ፣ ፍርድቤቶች፣ ሲቪክ ማሀበራት፣ ሚዲያዎች ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉት ተቋማት በሀገራችን በተጨባጭ የመንግሥት ወይም የፓርቲዎች ወገን ናቸው። ስለዚህ እነዚህ ተቋማት ከፖለቲካ ተጽኖ ነፃ ሆነው የህዝብ አገልጋይ መሆን ሲችሉ ሙስናንም ለመዋጋት ያመቻል ብለዋል፡፡
ከቪዥን ኢትዮጵያን ኮንግረስ ፎርድ ዴሞክራሲ አቶ ታደለ ደርሰህ በበኩላቸው፤ በሀገራችን የተፈጠረው ሌብነትና የመብት ጥሰት የሲቪክ ማህበራትና ሚኒስቴር መስሪያቤቶች ዋነኛ ተዋናይ ነበሩ። መንግሥትም ፀረሙስና ኮሙሽኑን ለይስሙላ ነው ያቋቋመው። ስለዚህ በመጣው ለውጥ መንግሥት እነዚህን ተቋማት ከፖለቲካውና ከመንግሥት ተጽዕኖ ተላቅቀው ሙስናና ብልሹ አሠራርን በመታገል ለህዝብ እውነተኛ አገልጋይ እንዲሆኑ ማስቻል ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
ይህንን አስከፊ ችግር በመከላከል የሀገራችንን ልማትና ሰላም ለማረጋገጥ በተለይ የዴሞክራሲና የፍትሕ ተቋማትን እንዲሁም የምጣኔ ሀብት መዋቅሮችን በጽኑ መሰረት ላይ በመገንባት ሙስናና ኢ- ስነ-ምግባራዊ ድርጊቶች በሂደት እየከሰሙ የሚሄዱበትን ዘላቂ አሠራር ማበጀት ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሙስናን በመከላከል ሂደት ውስጥ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ይጠበቃል፡፡በዚህም ዜጎች ሙስናን በመከላከል ለልማት፣ ለሰላምና አገራዊ አንድነት የድርሻቸውን በተግባር ሊወጡ የሚገባበት ጊዜ ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 3/2011
ሰለሞን በየነ