ቅኝ ግዛትና ባለድሉ የአፍሪካውን አንድነት ድርጅት
የመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እና የጋናው ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንኩሩማህ መሪ ሚና የተጫወቱበትና እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ግንቦት 25 ቀን 1963 በአዲስ አበባ የተፈረመው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር በአፍሪካውን ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት ታላቅ የድል መዝገብ ነው። ምክንያቱም በተባበረ ክንድ እናት አፍሪካን ከምዕራባውያን ቅኝ አገዛዝ ነጻ ለማውጣት የሚያግዝ መተባበሪያ መድረክ ለመፍጠር የአፍሪካ መሪዎች ለዓመታት ያደረጉት ጥረት ፍሬ ያፈራበት እና መላ አፍሪካውያንን የሚያስተባብር አንድ አህጉራዊ ድርጅት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ዕውን መሆን በመቻሉ ነው። ያች ቀን በሁሉም አፍሪካውያን ልብ ውስጥ በልዩ ክብር ተጽፋ ትኖራለች።
ትብብርንና አንድነትን መርሁ አድርጎ የተመሰረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ተንሰራፍቶ ህዝቦቿን የበይ ተመልካች አድርጎ ጥቁሯን ወርቃማ አህጉር ሲበዘብዝ የቆየውን የኢምፔሪያሊስቶች የግፍ አገዛዝ ለማስወገድ በተደረገው መራር የነጻነት ትግል ጉዞ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። እንደተጠበቀውም ድርጅቱ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ለአፍሪካ ነጻነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ከቅኝ ግዛት የመውጣትና ነጻነታቸውን የማስመለስ የዘወትር አፍሪካውንን ህልም አሳክቷል።
የነጭ ሰፋሪዎች በብዛት በነበሩባቸው እንደነ ደቡብ አፍሪካ በመሳሰሉ አገራት የነጻነት ትግሉ እጅግ መራራ የነበረ በመሆኑ በራስ ትግል ብቻ ነጻ መውጣት የሚታሰብ አልነበረም። በደቡብ አፍሪካ የነጮች የበላይነትና በጥቁሮች ላይ ከፍተኛ ግፍን ይፈፅም የነበረውን የአፓርታይድ የዘር አገዛዝ በማስወገድና አገሪቱን ከቅኝ ገዥዎች መዳፍ አላቅቆ ነጻነትን በማስገኘቱ ሂደት የአፍሪካውያን አንድነት ድርጅት ግንባር ቀደሙን ሚና ተጫውቷል። በዚህም ደቡብ አፍሪካ ከረጅም ጊዜ እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ በ1994 ነጻነቷን መቀዳጀት ችላለች።
በተመሳሳይ በደቡብ ምዕራብ አፍሪካ(በዛሬዋ ዚምባብዌ)፣ በአንጎላ፣ በሞዛምቢክ፣ በጊኒቢሳው፣ በኬፕቨርድና በሳኦቶሚና ፕሪንስፕ የነጭ ሰፋሪዎች በብዛት የሰፈሩባቸውና በነበራቸው የኃይል የበላይነት ምክንያት በሃገራቱ ለረጅም ዓመታት ገንግኖ የቆየው የቅኝ ግዛት የብረት መዳፍ በአፍሪካውያን የተባበረ ክንድ እንዲሰባበር ድርጅቱ የማይተካ ሚና ተጫውቷል።
ነጻነት፣ የቅኝ ግዛት “ሌጋሲዎች” እና አፍሪካውያን “ወራሲዎች”
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አፍሪካውያንን በማስተባበር ህዝቦቿን ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁና ነጻነታቸውን እንዲጎናጸፉ በማድረግ ረገድ ዘመን አይሽሬ አኩሪ ታሪክ የሠራ ቢሆንም ከነጻነት በኋላ አህጉሪቱ የገጠሟትን ሌሎች አዳዲስ አሳሳቢ ችግሮች በመፍታት ረገድ ግን ውጤታማ መሆን አልቻለም። ከነጻነት በኋላ አህጉሪቱን ከገጠሟት ፈታኝ ችግሮች መካከል ዋነኛው የምዕራባውን ቅኝ ገዥዎች የ”የከፋፍለህ ግዛ” የቅኝ አገዛዝ መርህ ሌጋሲ የሆነው ድንበር አከላለልን ተከትሎ በአገራት መካከል የተከሰተው ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት ነው። ከነጻነት በኋላ የተፈጠረውና አህጉሪቱን አሁንም ድረስ ከባድ ዋጋ እያስከፈላት የሚገኘው ሌላው ፈታኝ ችግር ደግሞ በየሃገራቱ የፖለቲካ ስልጣን የሚይዙ አፍሪካውያን መንግስታት የምዕራባውያን ቅኝ ገዥዎችን ተክተው የራሳቸው ቅኝ ገዥ ሆነው ብቅ ያሉት አፍሪካውያን የጭቆና ወራሲዎች የፈጠሩት አንባገነናዊ አገዛዝ ነው።
መላ አፍሪካውያንን በአንድ አስተባብሮ እናት አፍሪካን ከቅኝ ገዥዎች መዳፍ ማላቀቅ የቻለው ታላቁ የአንድነት ድርጅት ይህን ጊዜ ግን ጥርስ የሌለው አንበሳ ሆነ። በሃገራት መካከልም ሆነ በአንድ ሃገር ውስጥ በመንግስትና በተቃዋሚ ቡድን መካከል የሚነሱ እርስ በእርስ ጦርነቶችን ጣልቃ በመግባት መፍትሔ የሚፈጠርበትን መንገድ ማምጣት እየቻለ በርካታ ሃገራት በጦርነት ሲወድሙ ዝም ብሎ ተመለከተ።
ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ድርጅቱ በመተዳደሪያ ቻርተሩ ላይ ያስቀመጠው “በሃገራት የውስጥ ጉዳይና ሉዓላዊነት ውስጥ ልቃ አለመግባት” የሚለው መርሁ መሆኑን የአፍሪካን ስተዲስ ሴንተር መረጃ ያመላክታል። በአባል አገራት መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን የሚገላግልበትና የሚዳኝበት ፍትህ መዋቅር የሌለው መሆኑም በሃገራት መካከል የሚፈጠሩ ችግሮችን ጣልቃ ገብቶ ለመፍታት የሚያስችል ህጋዊ ስልጣን እንዳይኖረው ተጨማሪ አስተዋፅኦ አበርክቷል። ከዚህም በአሻገር የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአደረጃጀቱ ውስጥ የኢኮኖሚ ኮሚሽን ቢኖረውም ሥራውን የሚያከናውንበት የሃብት ምንጭ አልነበረውም። ይህም አህጉሪቱ ውስጥ ያሉትን ውስብስብ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታትና የፖለቲካ አለመረጋጋትን ጨምሮ ለበርካታ ችግሮች መንስኤ የሆነውን ሥር የሰደደ ድህነት ለመቀነስና ህዝብን ወደ እድገት ጎዳና ለመምራት በአባል አገራት መካከል ኢኮኖሚያዊ ትብብር መፍጠር እንዳይችል እንቅፋት በመሆኑ ድርጅቱን የበለጠ አቅመ ቢስ እንዲሆን አድርጎታል።
የቀደሙ ድክመቶችን ለማረም የተወለደ አዲስ ሕብረት
ዘወትር በአፍሪካውን ልብ ውስጥ በማይጠፉት ቀደምት ታሪካዊ ስኬቶቹ እየተወደሰ ሠላሳ ስምንት ዓመታትን በክብር ከአፍሪካውያን ጋር የዘለቀው አንጋፋው ድርጅት በእርግጥም አሁን ላይ አዳዲሶቹን የአፍሪካ አገራት ፈታኝ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል አቅም እንዳጠረው የአፍሪካ መሪዎች ተረዱ። በአውሮፓውያኑ 2001 እንደዛሬው ሳይሆን ዜጋ ስለሆኑ ብቻ የዜግነት እንደምትከፍል በሚነገርላት “አፍሪካዊቷ ዩናይትድ ስቴትስ” እየተባለች ትሞካሽ በነበረችው አፍሪካዊት ባለፀጋ ሃገር፣ በሞአመር ቃዳፊዋ ሊቢያ አፍሪካውያን መሪዎች ተሰበሰቡ። እናም ከላይ የተጠቀሱትን ድክመቶች ለማረምና ከነጻነት ማግስት አህጉሪቱ ለገጠሟት አዳዲስ ችግሮች በአግባቡ ምላሽ ለመስጠት የሚችል፣ የአህጉሪቱን አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታዎች ግምት ውስጥ ያካተቱ መርሆዎችንና አደረጃጀቶችን ያቀፈ፣ ከጊዜው ጋር አብሮ የሚሄድ ዘመኑን የሚዋጅ አዲስ ድርጅት ታሪካዊውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተክቶ መቋቋም እንዳለበት መሪዎቹ ስምምነት ላይ ደረሱ።
ከዓመት በኋላ በደቡብ አፍሪካ በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2002 ላይ በተደረገው የመጨረሻው አፍሪካ አንድነት ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ አሮጌው አንድነት ድርጅት ፈርሶ አዲሱ ሕብረት በይፋ መመስረቱ በይፋ ተበሰረ። ስሙም “የአፍሪካ ሕብረት” ተባለ። እነሆ ከአንጋፋው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተወለደው “አዲሱ” የአፍሪካ ህብረት እንደዋዛ አስራ ስምንት ዓመት ሞላው፤ ከአባቱ ሊደርስ ሃያ ዓመት ብቻ ቀረው።
ለሕብረቱም ድክመት ሆነው የቀጠሉ የቆዩ ችግሮች
ሕብረቱ በምስረታው ጊዜ እንደተባለው ዙፋን አውራሹ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የነበሩበትን ድክመቶች ማረም ችሎ ይሆን? ወይንስ የአባት ስለሆነበት ድክመቶችንም ጭምር ወርሶ ቀጥሎ ይሆን? የአፍሪካ ሕብረትን በተመለከተ እናንተ የምትሉትን አላውቅም፣ እኔ ግን ሁለተኛውን ሆኗል ብዬ አምናለሁ። አረ እኔ ብቻ አይደለሁም፣ እርሱ ራሱም ብሏል። አዎ፣ ሰሞኑን በዋና መቀመጫው በእኛዋ በአዲስ አበባ ባካሄደው 33ኛው መደበኛ ጉባኤው ላይ “አሁንም በአህጉሪቱ ውስጥ የሚቀሰቀሱ የእርስ እርስ ግጭቶችን ማስቆም አልቻልኩም” ብሏል። በተጨማሪም የመሰረተ ልማት አለመስፋፋት፣ ድህነትና ኋላ ቀርነት አሁንም የአፍሪካ ዋነኛ ችግር ሆነው መቀጠላቸውንም ሕብረቱ አልደበቀም። ታዲያ የአፍሪካ ሕብረት እስካሁን ድረስ እነዚህን ችግሮች መፍታት ካልቻለ ምኑን “ድክመት አራሚ” ሆነ? ልብ በሉ እነዚህ ችግሮች እኮ ከዛሬ ሃያ ዓመታት በፊትም ነበሩ፣ ዛሬም አሉ።
ከላይ እንዳየነው በቅኝ ግዛት ድንበሮች በግዛት ይገባኛል በጎረቤት አገሮች መካከል የሚፈጠሩ ጦርነቶችና በአንድ አገር ውስጥም ሆኖ በአንባገነን መንግስታትና ስልጣን ይገባኛል በሚሉ ተቃዋሚ ኃይሎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችንና የእርስ በእርስ ጦርነቶችን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ማስቀረት ባለመቻሉ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ታስቦ ነበር የአፍሪካ ሕብረት የተቋቋመበት ዋነኛ ምክንያት። የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋነኛ ድክመት ተደርጎ የቀረበውና የአፍሪካ ሕብረት ይፈታዋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ሌላውና ትልቁ ችግር ደግሞ በአህጉሪቱ ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ትብብር መፍጠርና ማጠናከር አለመቻሉ፣ ይህም አፍሪካ ውስጥ ሥር የሰደደ ድህነትና ኋላ ቀርነት እንዲንሰራፋና በርካታ ውስብስብ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዲፈጠሩ ገፊ ምክንያት ሆኖ ማገልገሉ ነበር።
ታዲያ ከአስራ ስምንት ዓመታት በኋላ ዛሬም እነዚህ ችግሮች የአፍሪካ ስጋት ሆነው ከቀጠሉ “መፍትሔ” ይሆናል ተብሎ የተቋቋመው አዲሱ የአፍሪካ ሕብረት ምን እየሰራ ነበር? “የአንባገነኖችን ጉተና እያበጠረ?” አላልኩም። ይሔ እንኳን የህብረቱ ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገትና ልማት ያልተዋጠላቸው እና የአህጉሪቱን ሰላምና ብልጽግና የማይፈልጉ አንዳንድ ጠብ-መንጃ ተኳሽ አካላት የሚያስወሩት ሊሆን ይችላል።
ልክ ነኝ እነዚህን ፀረ ሰላም አካላት አከርካሪያቸውን ለመስበርና እስከ 2020 ድረስ ሰላም የሰፈነባት የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ ሕብረቱ “የጥይት ጩኸት የማይሰማባት አህጉር ዕውን የማድረግ” ዘመቻ ያስጀመረውስ ለዚህ አይደል። የክፍለ ዘመኑ ምርጥ ስትራቴጂ ወይም በዘመቻ ስሙ “አፍሪካን ሊደርስ ኮሜዲ” ይሏችኋል ይሄ ነው። (የዘመቻ ስሙ ሲባል ግር እንዳይላችሁ፣ ለነገሩ ለምን ግር ይላችኋል፣ የቤተሰብ ስም፣ የአያት ስም፣ የፈረስ ስም፣ የበረሃ ስም…ስንት ስም ባለበት ሃገር የዘመቻ ስም ምን ይከብዳል)።
ያም ሆኖ ሕብረታችን ከተመቋቋመበት መርህ አኳያ ዋነኛ ዓላውን ማሳካት አልቻለም ነው እንጅ ምንም የሠራው ሥራ የለም ማለት በእርግጥም ስም ማጥፋት ነው፣ የተሠሩ መልካም ሥራዎችን አለማበረታታትም ጨለምተኝነት ነው። ለአብነትም ህብረቱ ከአውሮፓውኑ 2002 እስከ 2009 በነበሩት ሰባት ዓመታት ብቻ የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ የነበሩ ሃያ ስምንት ሃገራትን ችግሩ ተባብሶ የከፋ ውጤት ከማስከተሉ በፊት የሚቃለልበትን መንገድ መፍጠሩን በ33ኛው መደበኛ ጉባኤው ገልጿል። ይህንንም እናደንቃለን። ሆኖም የቀደመው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ማድረግ ያልቻለውና እንደ ትልቅ ድክመት የታየበት አንዱና ዋነኛው ጉዳይ በአገራት ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አልገባም በሚል “የአጉል ገለልተኝነት” መርህ በርካታ ሃገራት በእርስ በእርስ ጦርነት ከባድ ውድመት ሲደርስባቸው ዝም ብሎ ማየቱ መሆኑ ይታወሳል። በዚህ ረገድ “ችግሮችን አቃልያለሁ” ከማለቱ ውጭ ተተኪው የአፍሪካ ሕብረትም የረባ ሥራ ሲሰራ አለመታየቱ በብዙዎች ዘንድ ትዝብት ውስጥ ጥሎታል። ኢኮኖሚያዊ ትብብርን በመፍጠር ረገድም ያለው ድክመት ዛሬም ድረስ የዘለቀ በመሆኑ ዙፋን አውራሹ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአህጉሪቱን ህዝቦች በማስተባበር ቅኝ ግዛትን በማስወገድና ነጻነትን በማቀዳጀት ያስመዘገበውን ስኬት ጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብርን በመፍጠርና ከድህነት ነጻ የሆነች የበለጸገች አፍሪካን ዕውን በማድረግ አፍሪካ ሕብረት ሊደግመው አልቻለም። እንዲያውም ባለፉት አስራ ስምንት ዓመታት አህጉሪቱ ውስጥ የአፍሪካ ሕብረት ከፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ትብብር ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ የፈጠሩት ሳይሻል አይቀርም። እናም ሕብረቱ የእሳት ልጅ አመድ ሆኗል። ከአባቱ የወረሰው ጥንካሬውን ሳይሆን በአመዛኙ ድክመቱን ነው ማለት ይቻላል።
የጥይት ጩኸትን ለማስቆም የሕዝብ ጩኸትን ማዳመጥ
የአፍሪካ ሕብረትም ሆነ የአፍሪካውያን መሪዎች ትልቁ ችግር ከቀደምት አቻዎቻቸው ወይም ከታሪክ አለመማራቸው ነው። ካስተዋሉ እና ከልብ ለመመለስ ካሰቡ ከመልካም ነገር ብቻ ሳይሆን ከመጥፎ ተሞክሮም መማር ይችላል። ከዚህ መርሆ አኳያ ስንመዝናቸው አብዛኞቹ የአፍሪካ አንባገነን መሪዎች ጅሎች ናቸው። ከሌሎች አቻዎቻቸው ስህተት ትምህርት አልወሰዱም፣ ከታሪክ አልተማሩም፤ መሰሎቻቸውን እንዳልነበሩ ያደረገው የጥፋት ውሃ እነርሱንም ጠራርጎ እስኪወስዳቸው ቆመው እየተጠባበቁ ናቸውና።
ለዚህም አብነት የሆኑ የህዝብን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ተቀብሎ ህዝብ የሚፈልገውን ከማድረግ ይልቅ በተለመደው የአፈናና የግድያ ስልት የጭቆና ቀንበራቸውን ለማጥበቅ ላይ ታች እያሉ የሚገኙ በርካቶች የአፍሪካ አንባገነን ዛሬም ድረስ አሉና። በቅርቡ ፕሬዚዳንት ቡተፋሊካና ኦማር አልበሽር ላይ የተከሰተውን እናውቃለን።ፕሬዚዳንት አብድላዚዝ ቡተፍሊካ በአልጀሪያ የፕሬዚዳንቱን መንበር ከተረከቡ ሁለት ድፍን አስርታት ሞልቷቸዋል። በአውሮፓውኑ 1989 በመፈንቅለ መንግስት በጠብ መንጃ ታግዘው ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር በበኩላቸው የሱዳን መሪ (ገዥ የሚለው የበለጠ ይስማማቸዋል) ከሆኑ የአንድ ትውልድ ዕድሜን አስቆጥረዋል።
ቡታፍሊካም ሆኑ ጥቁሩ ፈርዖን ህዝብ በግድ ካላስወረዳቸው በስተቀር ከስልጣን ላይ መውረድን እንደ ሞት ቆጥረውት ተመልክተናል። ሁለቱ አይጠግቤ መሪዎች ለዘመናት የታፈነና የተጨቆነ የህዝብ ቁጣ እንደ ማዕበል ፈንድቶ ዙሪያቸውን አስኪከባቸው ድረስ ከወንበራቸው መውረድ አልፈለጉም። ሞቴን ከስልጣን ጋር ያድርገው ብለው ዙፋን ላይ የሙጥኝ ተጣብቆ መቅረቱን መርጠዋል። እናም ከዛሬ ነገ ያሻሽላሉ በሚል አንባገነን መሪዎቹን በጨዋነት ሲያስታምም የኖረው ህዝብ የመሪዎቹ ልብ እንደ ፈርዖን ቢደነድንበት የለውጥ ቀንም እንደ ምፅአት ቢረዝምበት ትግስቱ አለቀ። በአንባገነኖቹ ንቀት ህዝብ ተቆጣ። ስልጣን በኃይል ጨብጠው በግዴታ ሲገዙት የኖሩትን ጨቋኝ መሪዎቹን በግዴታ ለማውረድና ነጻነቱንና እኩልነቱን ለማወጅ በሁለቱም አገራት ህዝብ ወደ አደባባይ ይወጣል፣ በጠብ መንጃ ስልጣን የያዙ መሪዎች በጠብ መንጃ ይወርዳሉ፣ ተረኛው ባለ ጠብ መንጃ እንደዚሁ ህዝቡን እየረገጠ ይቀጥላል። ይኸው ነው የድህረ-ነጻነት የአፍሪካ ታሪክ።
እንደ መሪዎች ሁሉ ከቀደመ አቻው መማር ያልቻለው በመሪዎቹ ፍላጎት ተጠፍጥፎ በአምሳያቸው የተሰራው አፍሪካ ህብረትም ይህንን ታሪክ ለመቀየር ከመሰረታዊው መንስኤ መጀመር ሲገባው “የጠብ መንጃ ድምጽ የማይሰማባት አፍሪካን ዕውን ለማድረግ” እያለ ሲያላዝን መሰማቱ በእርግጥም ጉዳዩን የክፍለ ዘመኑ ታላቅ ስላቅ ያስመስለዋል። ጠብ መንጃ የሚጮህበትን ምክንያት ሳይፈቱ ጠብ መንጃ የማይጮህባት አህጉርን መገንባት አይቻልም። ከእነርሱ አልፈው ለእኛ ጠብ መንጃ የሚሸጡልን አንዳንዴም የሚረዱን አውሮፓና አሜሪካ እኮ ለዓለም የሚበቃ ጠብ መንጃ አላቸው፤ ግን እንደ እኛ አይገዳደሉበትም፣ ይነግዱበታል እንጅ!
የአፍሪካም ችግር ጠብ መንጃ መኖሩ አይደለም፤ በጠብ መንጃ ስልጣን የሚይዙ እና በጠብ መንጃ ከስልጣን የሚወርዱ ራስ ወዳድ አንባገነኖች መኖራቸው ነው ዋነኛው የአፍሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት፣ የድህነትና የኋላ ቀርነት መንስኤ! ህዝብ “የምንፈልገው እርገጤን በእርገጤ መቀየር አይደለም፤ የእናንተ የጭቆና መሳሪያ የሆነው የፖለቲካ ሥርዓት እንዲለወጥ ነው የምንፈልገው፤ ስልጣን ከእናንተ ወደ እኛ እንዲሸጋገር ህዝብ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን እንፈልጋለን” ይላል።
አድሮ ጥጃዎቹ የአፍሪካ አንባገነኖች በበኩላቸው “ስልጣኔን ለምክትሌ አስተላልፋለሁ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማሻሻያ አደርጋለሁ፣ ምርጫ እስኪደረግ ታገሱን ወዘተ…” በሚሉ ማታለያዎች የስልጣን ዕድሜያቸውን ለማራዘም አበክረው ሲጥሩ ይስተዋላሉ። እንዲያም ሲል ለተቃውሞ የወጡ ዜጎችን በግላጭ በአደባባይ በጥይት ያስረሽናሉ። ከዚህም ባሻገር የህዝቡን የለውጥ ጥያቄ ለመቀልበስና ስልጣናቸውን ለማስቀጠል በርካታ ሴራዎችንና ስራዎችን ሲሰሩ ይስተዋላሉ። ለምሳሌ ሰማንያ በመቶ የሚሆነው የሱዳን አጠቃላይ ገቢ የሚመደበው ከህዝብና ከሃገር ጠባቂነት ወደ የአልበሽር የጭቆና አገዛዝ ዋና አስፈጻሚነት ለተለወጠው የሃገሪቱ መከላከያና ጦር ሰራዊት እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ። የአፍሪካ ህብረትም በእርግጥ ጥይት የማይጮህባትና የበለጸገች ሰላማዊት አፍሪካን ዕውን የማድረግ ከልብ የመነጨ ፍላጎት ካለው ከጥይት ጩኸት በፊት የህዝብ ጩኸትን ያስቀር!
ኢኮኖሚን በሚመለከትም ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርም “አደህይቶ መግዛት” እንዳሉት ዳቦ የጠገበ ህዝብ ነጻነት እንዳይጠይቃቸው አብዛኞቹ የአፍሪካ ጅል አንባገነኖች (አልበሽርን የበላው የሱዳን አመጽ በዳቦ ጥያቄ የተጀመረ መሆኑን ልብ ይሏል) በሰፊው ህዝብና በ “መንግስታውያን ቤተሰቡ” መካከል እንደሰማይና መሬት የተራራቀ የሃብት ልዩነት እንዲኖር ዘመናቸውን ሁሉ የሚለፉ ናቸው። ስለሆነም የናጠጠ ሃብታም መንግስትና የተራቆተ ድሃ ህዝብ ፈጥረዋል። ከቀደመ አቻው ተምሮ ኢኮኖሚያዊ ትብብርን በመፍጠርና በማጠናከር አፍሪካን ሌላኛውን የአህጉሪቱን የግጭትና ጦርነት መንስኤ ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ይፈታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የአፍሪካ ሕብረት ይህኛውን ዓላማውንም ማሳካት ያልቻለበት ምክንያት ይኸው የአንባገነኖች ህዝብን አደህይቶ የመግዛት ሴራ ነው።
እናም የተከበርከው አፍሪካ ህብረት ሆይ አፍሪካ ውስጥ ብልሹ የሴራ ፖለቲካ እና ብልሹ አንባገነኖች የሚስተካከሉበት እና የህዝብን ጩኸት የሚሰሙ ትክክለኛ የፖለቲካ መሪዎች ወደ ፊት የሚመጡበትን መንገድ እስካላመቻቸህ ድረስ የጠብ-መንጃ ድምጽ የማይሰማባት የበለጸገች አፍሪካን ዕውን ማድረግ አይቻልምና ትኩረትህን ሁሉ እዚህ ላይ እንድታደርግ በስልጣን፣ በማዕረግ ብትበልጠንም አሻቅበንም ቢሆን እንመክርሀለን። እግዚአብሔር አፍሪካንና ሕብረቷን ይባርክ!
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2012
ይበል ካሳ