በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የሚካሄደው ዓመታዊው ፔፕሲ የአዲስ አበባ ክለቦች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለ37ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ስታዲየም በመካሄድ ላይ ይገኛል።ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን የያዘው ውድድሩ በተለያዩ ርቀቶች የሩጫና ሜዳ ተግባራት አትሌቶችን በማፎካከር በርካታ ክብረወሰኖች እየተሻሻሉበት ይገኛል።
በውድድሩ ሁለተኛ ቀን ውሎ ትናንት በተካሄደው የሴቶች አንደኛ ዲቪዚዮን አስር ሺ ሜትር ውድድር ክብረወሰን ተሰብሯል።በኢትዮጵያ ቻምፒዮና በአትሌት ለተሰንበት ግደይ 32፡10፡90 ተይዞ የነበረው የርቀቱ የኢትዮጵያ ክብረወሰን ዘንድሮ በአትሌት ዘይነባ ይመር በስድስት ሰከንድ ሊሻሻል ችሏል።
በቻምፒዮናው ላይ በአንደኛ ዲቪዚዮን ከታቀፉ አምስት ክለቦች የተሳተፉ ሲሆን በሁለተኛ ዲቪዚዮን ከታቀፉ ሃያ ክለቦች የተውጣጡ በአጠቃላይ አንድ ሺ አትሌቶች ተሳታፊ ሆነዋል።ውድድሩ ክለቦች የአትሌቶቻቸውን አቅም ከመለካት ባሻገር በሃገር አቀፉ የአትሌቲክስ ቻምፒዮና ተሳታፊ ለመሆን የሚያስችላቸውን ምዘና የሚያደርጉበት እንዲሁም ስልጠናቸውን በመገምገም ራሳቸውን የሚያጎለብቱበት መድረክም መሆኑ ተነግሯል።
ትናንት በተካሄደው የሁለተኛ ቀን ውሎ የተለያዩ የማጣሪያ እና የፍጻሜ ውድድሮች ተካሂደዋል።በሁለተኛ ዲቪዚዮን የ100 ሜትር ሩጫ በሁለቱም ፆታ የፍፃሜ ውድድሮች የተከናወነ ሲሆን፤ በሴቶች ትዝታ ደጋ ከአራዳ ክፍለ ከተማ እንዲሁም ሜሮን ተመስገን እና ፍቅርተ ሽፈራው ከዳሎል ክለብ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።በወንዶች በኩል ኤርሚያስ ሻጠው ከኮልፌ ቀራኔዮ ክፍለ ከተማ አንደኛ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያውን ወስዷል።የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲው አትሌት ሲሳይ አየሁ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ክለብ አትሌቱ ዘገየ ለገሰ ደግሞ ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን ተከታትለው ገብተዋል።በተመሳሳይ በ10ሺ ሜትር በወንዶችና ሴቶች ውድድር ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ፤ በ1ሺ500 ሜትር፣ በአሎሎ ውርወራ እና በከፍታ ዝላይ አሸናፊ የሆኑ አትሌቶች የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ነገ ቀጥሎ በሚውለው ቻምፒዮና የተለያዩ የፍጻሜ ግማሽ ፍጻሜና የማጣሪያ ውድድሮች የሚካሄዱም ይሆናል።በ5ኪሎ ሜትር በሴቶች እንዲሁም በ10ኪሎ ሜትር የወንዶች እርምጃ ውድድሮች ፍጻሜያቸውን ከሚያገኙት መካከል ይጠቀሳል።በሁለተኛ ዲቪዚዮን የሱሉዝ ዝላይ በሴቶች የማጣሪያ፣ በዲስከስ ውርወራ ወንዶች ግማሽ ፍጻሜ፣ በሁለቱም ጾታ የ400 ሜትር ፍጻሜ፣ 5ሺ ሜትር ሴት ግማሽ ፍጻሜ፣ 100ሜትር መሰናክል የሴቶች ግማሽ ፍጻሜ እና በ110ሜትር መሰናክል ሴት ግማሽ ፍጻሜ ይከናወናሉ።በአንደኛ ዲቪዚዮን ደግሞ በ100 ሜትር ሴትና ወንድ ግማሽ ፍጽሜ እንዲሁም በ110 ሜትር መሰናክል የወንዶች ግማሽ ፍጻሜ ውድድሮች በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት ይካሄዳሉ።
ይህ ዓመታዊ ቻምፒዮና በ1975 ዓ.ም መካሄድ የጀመረ ሲሆን፤ በፌዴሬሽኑ የተመዘገቡ ብዛት ያላቸው ክለቦች ሲሳተፉበት መቆየታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።ከ1991ዓ.ም ጀምሮም ፌዴሬሽኑ አቅሙን በማጎልበት ከሞሐ የለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር ጋር በመተባበር ውድድሩ ለዓመታት በቋሚነት በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ፍጻሜያቸውን ባያገኙ ውድድሮች በቀዳሚነት ለሚያጠናቅቁ አትሌቶችም የወርቅ፣ ብርና ነሃስ ሜዳሊያ የሚበረከትላቸው ይሆናል።ውድድሩ ከትናንት በስቲያ የተጀመረ ሲሆን በመጪው እሁድ 22/2012 ዓ.ም የሚጠናቀቅም ይሆናል።
በቻምፒዮናው ከ1ሺ በላይ
አትሌቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ፣
ኢትዮጵያዊው ብስክሌተኛ በቱር ደ ሩዋንዳ አሸነፈ
በሩዋንዳ በተካሄደ የ‹‹ቱር ደ ሩዋንዳ›› የብስክሌት ውድድር ኢትዮጵያዊው ሙሉ ኃይለሚካኤል አሸነፈ። ብስክሌተኛው 120 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር በሸፈነውና ከዋና ከተማዋ ኪጋሊ ወደ ሁዬ ዲስትሪሲ የነበረውን ርቀት ለመሸፈንም 3ሰዓት ከ3ደቂቃ ከ21 ሰከንድ የሆነ ጊዜ እንደፈጀበት ዘ ኒው ታይምስ ዘግቧል።ለ12ኛ ጊዜ የሚካሄደው ውድድሩ እስከ መጪው እሁድ በተለያዩ ፉክክሮች የሚቀጥል ይሆናል።
አትሌቶች ለቻምፒዮናው አልፈዋል
ሰባት ዙሮች ያሉት የዓለም የቤት ውስጥ የዙር ውድድር የተጠናቀቀ ሲሆን ለዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና በቀጥታ ማለፍ የቻሉት 11 አትሌቶችም ተለይተዋል።ከእነዚህ አትሌቶች መካከልም የ3ሺ ሜትር ተወዳዳሪው ጌትነት ዋለ በወንዶች እንዲሁም በሴቶች ጉዳፍ ጸጋዬ 1ሺ500 ሜትር ማለፋቸውን ያረጋገጡ አትሌቶች ሆነዋል።ይሁን እንጂ የቻምፒዮናዋ አዘጋጅ የሆነችው ቻይና ከኮረና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ውድድሩ ወደ ሚቀጥለው ዓመት (እአአ 2021) መሸጋገሩ የሚታወስ ነው።በዙር ውድድሩ ቀዳሚ በመሆን ያጠናቀቁት አትሌቶች 20ሺ የአሜሪካ ዶላር ተሸላሚ መሆናቸውንም የዓለም አትሌቲክስ በድረ ገጹ አስነብቧል።
ሊጉ ከሁለት ሳምንት በኋላ ይመለሳል
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዙር የካቲት 29 እና 30/2012 ዓ.ም የሚጀመር መሆኑ ታውቋል።የግማሽ ዓመት ውድድር ከትናንት በስቲያ በቅዱስ ጊዮርጊስና አዳማ ከተማ መካከል በተደረገ ጨዋታ መጠናቀቁ ይታወቃል።ይህንንም ተከትሎ ሊጉን የሚመራው አቢይ ኮሚቴ ከሁለት ሳምንት እረፍት በኃላ ፕሪሚየር ሊጉ እንዲጀመር ውሳኔ ላይ መደረሱ ተረጋግጧል።
የወርልድ ቴኳንዶ ቡድኑ አቀባበል
ሰሞኑን ሞሮኮ ላይ ሲካሄድ በነበረው የወርልድ ቴኳንዶ የኦሊምፒክ ማጣሪያ ላይ ኢትዮጵያን የወከለው ቡድን ትናት አዲስ አበባ ሲገባ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፣የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፣ የአዲስ አበባ የወርልድ ቴኳንዶ አሰልጣኞች ማህበር እና የስፖርቱ ቤተሰብ ቡድኑ አዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ ሲደርስ ልዩ አቀባበል አድርጓል። ሰለሞን ቱፋ በማጣሪያ ውድድሩ በወርልድ ቴኳንዶ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ለመሳተፍ የሚያስችለውን ውጤት ማስመዝገቡ ይታወሳል።
ለሴት መምህራን ስልጠና ሊሰጥ ነው
ለሴት የስፖርት ሳይንስ መምህራን የአሰልጣኝነት ስልጠና ሊሰጥ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የ ‹‹ዲ ላይሰንስ›› አሰልጣኞች ስልጠና ለተመረጡ ሃገራት የሚሰጥም ይሆናል። ከሁሉም ክልሎች ለተወጣጡ 30 መምህራን የሚሰጠው ስልጠናው ከዛሬ ጀምሮ እስከ የካቲት 25/2012 ዓ.ም የሚቆይም ነው። ስልጠናው የሴቶች እግር ኳስ ልማትን ለማሳደግና ብቃታቸውን ለማሳደግ እንዲሁም አዳዲስ አሰልጣኞችን ለማፍራት የሚጠቅምም ይሆናል። በንድፈ ሃሳብና በተግባር የተደገፈው ስልጠናው በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ኢንስትራክተር ሰላማዊት ዘርዓይ እና በተጋባዦች የሚካሄድ መሆኑንም የፌዴሬሽኑ የቴክኒክና ልማት ዳይሬክቶሬት በመረጃ ጠቁሟል። ስልጠናው ከተጠናቀቀ በኃላም እድሜያቸው 15 ዓመት በታች በሆኑ 10 የሴት ተማሪዎች ቡድን መካከል ውድድር ይካሄዳል።
ቀነኒሳ በዓለም የግማሽ ማራቶን
የሃገር አቋራጭ ንጉሱ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በዓለም የግማሽ ማራቶን ቻምፒዮና ለአሸናፊነት ይጠበቃል። ከቀናት በኃላ በፖላንድ በሚካሄደው ቻምፒዮና በማራቶን የሁለተኛው ፈጣን ሰዓት ባለቤት የሆነው አትሌት ተሳታፊ እንደሚሆን የቢቢሲ ዘግቧል። አትሌቱ በውድድሩ ከእንግሊዛዊው አትሌት ሞ ፋራህ ፈታኝ ፉክክር ይገጥመዋል በሚል ቢጠበቅም፤ አትሌቱ በጉዳት ምክንያት የማይሳተፍ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የአሸናፊነት ግምቱን አግኝቷል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 18/2012