በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የሚካሄደው ዓመታዊው ፔፕሲ የአዲስ አበባ ክለቦች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለ37ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ስታዲየም በመካሄድ ላይ ይገኛል።ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን የያዘው ውድድሩ በተለያዩ ርቀቶች የሩጫና ሜዳ ተግባራት አትሌቶችን በማፎካከር በርካታ ክብረወሰኖች እየተሻሻሉበት ይገኛል።
በውድድሩ ሁለተኛ ቀን ውሎ ትናንት በተካሄደው የሴቶች አንደኛ ዲቪዚዮን አስር ሺ ሜትር ውድድር ክብረወሰን ተሰብሯል።በኢትዮጵያ ቻምፒዮና በአትሌት ለተሰንበት ግደይ 32፡10፡90 ተይዞ የነበረው የርቀቱ የኢትዮጵያ ክብረወሰን ዘንድሮ በአትሌት ዘይነባ ይመር በስድስት ሰከንድ ሊሻሻል ችሏል።
በቻምፒዮናው ላይ በአንደኛ ዲቪዚዮን ከታቀፉ አምስት ክለቦች የተሳተፉ ሲሆን በሁለተኛ ዲቪዚዮን ከታቀፉ ሃያ ክለቦች የተውጣጡ በአጠቃላይ አንድ ሺ አትሌቶች ተሳታፊ ሆነዋል።ውድድሩ ክለቦች የአትሌቶቻቸውን አቅም ከመለካት ባሻገር በሃገር አቀፉ የአትሌቲክስ ቻምፒዮና ተሳታፊ ለመሆን የሚያስችላቸውን ምዘና የሚያደርጉበት እንዲሁም ስልጠናቸውን በመገምገም ራሳቸውን የሚያጎለብቱበት መድረክም መሆኑ ተነግሯል።
ትናንት በተካሄደው የሁለተኛ ቀን ውሎ የተለያዩ የማጣሪያ እና የፍጻሜ ውድድሮች ተካሂደዋል።በሁለተኛ ዲቪዚዮን የ100 ሜትር ሩጫ በሁለቱም ፆታ የፍፃሜ ውድድሮች የተከናወነ ሲሆን፤ በሴቶች ትዝታ ደጋ ከአራዳ ክፍለ ከተማ እንዲሁም ሜሮን ተመስገን እና ፍቅርተ ሽፈራው ከዳሎል ክለብ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።በወንዶች በኩል ኤርሚያስ ሻጠው ከኮልፌ ቀራኔዮ ክፍለ ከተማ አንደኛ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያውን ወስዷል።የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲው አትሌት ሲሳይ አየሁ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ክለብ አትሌቱ ዘገየ ለገሰ ደግሞ ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን ተከታትለው ገብተዋል።በተመሳሳይ በ10ሺ ሜትር በወንዶችና ሴቶች ውድድር ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ፤ በ1ሺ500 ሜትር፣ በአሎሎ ውርወራ እና በከፍታ ዝላይ አሸናፊ የሆኑ አትሌቶች የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ነገ ቀጥሎ በሚውለው ቻምፒዮና የተለያዩ የፍጻሜ ግማሽ ፍጻሜና የማጣሪያ ውድድሮች የሚካሄዱም ይሆናል።በ5ኪሎ ሜትር በሴቶች እንዲሁም በ10ኪሎ ሜትር የወንዶች እርምጃ ውድድሮች ፍጻሜያቸውን ከሚያገኙት መካከል ይጠቀሳል።በሁለተኛ ዲቪዚዮን የሱሉዝ ዝላይ በሴቶች የማጣሪያ፣ በዲስከስ ውርወራ ወንዶች ግማሽ ፍጻሜ፣ በሁለቱም ጾታ የ400 ሜትር ፍጻሜ፣ 5ሺ ሜትር ሴት ግማሽ ፍጻሜ፣ 100ሜትር መሰናክል የሴቶች ግማሽ ፍጻሜ እና በ110ሜትር መሰናክል ሴት ግማሽ ፍጻሜ ይከናወናሉ።በአንደኛ ዲቪዚዮን ደግሞ በ100 ሜትር ሴትና ወንድ ግማሽ ፍጽሜ እንዲሁም በ110 ሜትር መሰናክል የወንዶች ግማሽ ፍጻሜ ውድድሮች በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት ይካሄዳሉ።
ይህ ዓመታዊ ቻምፒዮና በ1975 ዓ.ም መካሄድ የጀመረ ሲሆን፤ በፌዴሬሽኑ የተመዘገቡ ብዛት ያላቸው ክለቦች ሲሳተፉበት መቆየታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።ከ1991ዓ.ም ጀምሮም ፌዴሬሽኑ አቅሙን በማጎልበት ከሞሐ የለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር ጋር በመተባበር ውድድሩ ለዓመታት በቋሚነት በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ፍጻሜያቸውን ባያገኙ ውድድሮች በቀዳሚነት ለሚያጠናቅቁ አትሌቶችም የወርቅ፣ ብርና ነሃስ ሜዳሊያ የሚበረከትላቸው ይሆናል።ውድድሩ ከትናንት በስቲያ የተጀመረ ሲሆን በመጪው እሁድ 22/2012 ዓ.ም የሚጠናቀቅም ይሆናል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 18/2012
ብርሃን ፈይሳ