የሕሊና ጉዳት ምንድን ነው?
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
ጉዳት የሚባለው ሁኔታ ጠቅለል ባለ አገላለጽ በአንድ ሰው ጥቅም ላይ የሚደርስ ኪሣራ (Loss) ነው። ይኸውም የግለሰቡን ኢኮኖሚያዊ (የገንዘብ) ወይም የሕሊና (የሞራል) ጥቅምን የሚነካና የሚጎዳ ሊሆን ይችላል። ጉዳቱም ከውል ወይም ከውል ውጪ በተነሳ ችግር ይከሰታል።
ኢኮኖሚያዊ (የገንዘብ) ጉዳት የሚባለው የተጎጂውን ኪስ የሚጎዳ ነው። ይህ ጉዳት ደግሞ አሁኑኑ የደረሰ ወይም ገና ወደፊት የሚደርስ ሊሆን ይችላል።
ንብረቱን በማከራየት የዕለት ጉርሱን፣ የዓመት ልብሱን የሚሸፍን ባለንብረት ይህ ንብረቱ ቢወድምበት ኪሣራ ደርሶበታል። ለዚህ ካሣ ይገባዋል። የመስራት አቅሙን የሚጎዳ የአካል ጉዳት የደረሰበት ሰው ኪሣራ ደርሶበታል። ጉዳቱ ባይደርስበት ኖሮ የመስራት አቅሙ እስከሚቀጥል ድረስ ላለው የዕድሜው ዘመን ሁሉ ታስቦ ካሣ ሊከፈለው ያስፈልጋል።
የሕሊና ጉዳት ደግሞ የተጎጂውን ስሜት የሚነካ ጉዳት ነው። ንጋቱ ተስፋዬ “ከውል ውጭ አላፊነትና አላግባብ መበልጸግ ሕግ” በሚል ባሰናዳው መጽሐፍ ውስጥ እንደሚያብራራው በተበዳዩ ላይ የተፈጸመው አድራጎት ሕመምና ሥቃይ፣ ንዴትና ብስጭት፣ ሀዘንና ጸጸት ወይም የበታችነት ስሜት ሊፈጥር ይችላል።
ለእንዲህ ዓይነቱ ስሜትን ለሚነካ ጉዳት ታዲያ የሚከፈለውን ካሣ በገንዘብ መተመን ያስቸግራል። ይሁንና የሕሊና ጉዳቱ በገንዘብ ሊተመን አይቻልም ተብሎ በዳዩ ለፈጸመው በደል ተበዳይን እንዳይክስ ማድረግ አይቻልም። ይልቁንም የሕሊና ጉዳት ካሣ እንዲከፍል በማድረግ የተጎጂውን የስሜት ጉዳት መካስ ያስፈልጋል።
እኛም በዚህ ጽሑፋችን ከውል ውጭ በሆነ አላፊነት በሚደርስ ጉዳት አማካኝነት ሊከፈል የሚገባውን የሕሊና ጉዳት ካሣ በተመለከተ ጠቃሚ ነጥቦችን እንዳስሳለን።
የሕሊና ጉዳት ካሣ በጥቅሉ
ካሣ (የጉዳት ኪሣራ) ለማግኘት ጉዳት መድረሱን ማስረዳት ያስፈልጋል። የጉዳት ኪሳራ (Compensation for Damage) ከውልም ሆነ ከውል ውጭ በሚመጣ አላፊነት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይችላል።
ይኸውም በአንድ ሰው ጥቅም ላይ የሚደርስን በደል ለማካካስ ሲባል በጉዳት አድራሹ ትከሻ ላይ የሚጣል ግዴታ ነው። በሌላ አገላለጽ የጉዳት ኪሳራ ተጎጂው በድርጊቱ የደረሰበትን የጥቅም መቅረት ወይም መቀነስ ለማካካስና ለጉዳቱ መነሻ የሆነው ድርጊት ባይፈጸም ኖሮ ተጎጂው ይገኝ የነበረበትን ኢኮኖሚያዊ አቋም ለማስጠበቅ ወይም የሕሊናውን ስብራት ለመጠገን ያለመ ነው።
ለጉዳት የሚከፈል ኪሳራ በተጎጂው ላይ የሚደርሰውን ቁሳዊ (የማቴሪያል) ወይም ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ብቻ ሳይሆን የሕሊና (የሞራል) ጉዳትንም እንደሚያጠቃልል የፍትሐብሔር የሕገ-ፍልስፍና ልሂቃን ያስረዳሉ። የጉዳት ኪሳራ ኪስንና ስሜትን ለሚጎዱት ቁሳዊም ሆነ ሞራላዊ ጉዳቶች ሊከፈል እንደሚገባው ፕሮፌሰር ጆርጅ ችችኖቪች “The Ethiopian Law of Compensation for Damage” በተሰኘው ጽሑፋቸው የሰጡት ማብራሪያ ለዚህ ማሳያ ይሆናል።
እዚህ ላይ የሕሊናም ሆነ የቁሳዊ ጉዳት ኪሣራ ለማግኘት ጉዳቱ የደረሰው በሕጋዊ ጥቅም ላይ መሆን እንዳለበት ልብ ይሏል። ተጎጂው ያገኝ የነበረውና የተቋረጠበት ጥቅም ሕገ-ወጥ ወይም ለሕሊና ተቃራኒ ከሆነ ካሣ ሊጠይቅ አይችልም። ለምሳሌ ገቢው በቁማር፣ በሴተኛ አዳሪነት ወይም በኮንትሮባንድ ንግድ ላይ የተመሰረተ ከሆነ የጉዳት ካሣ መጠየቅ አይቻልም።
የሕሊና ጉዳት ካሣ የሚከፈልባቸው ሁኔታዎች
የሕሊና ጉዳት ካሣን መሰረተ-ሐሳብ ከሚደነግገው የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2105 እንደምናነበው አንድ ጥፋተኛ ያደረሰው በደል ለሚያስከትለው የሕሊና ጉዳት ሁሉ ካሣ ሊከፍል ይገባዋል።
ይሁንና የሕሊና ጉዳት ካሣ የሚከፈለው በሕጉ “ይህ ጉዳት የሕሊና ጉዳት ካሣ ያስከፍላል” በሚል በግልጽ ከተደነገገ ነው። እናም በሕጉ በግልጽ ተለይተው ከተቀመጡት ጉዳዮች ውጪ ዳኞች የሕሊና ጉዳት ካሣ ለማስከፈል አይችሉም ማለት ነው።
እነዚህ የሕሊና ጉዳት ካሣ የሚጠየቅባቸው ሁኔታዎች ናቸው ተብለው በሕጉ በግልጽ የተመለከቱት ጉዳዮች በርካታ ሲሆኑ፤ እነዚህንም አንድ በአንድ በዝርዝር እንመለከታቸዋለን።
የሕሊና ጉዳት ካሣ የሚጠየቅበት የመጀመሪያው ምክንያት በፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 2106 የተመለከተው ነው። ይኸውም ታስቦ በተደረገ ጥፋት የሕሊና ጉዳት ካሣ የሚከፈልበት ሁኔታ ነው።
ታስቦ የሚደረግ ጥፋት መሰረቱ የሕጉ ቁጥር 2032 ላይ የሰፈረው ድንጋጌ ነው። በዚሁ መሰረት አንድ ሰው የግል ጥቅሙን ለማግኘት ወይም የግል ጥቅም ለመፈለግም ሳይሆን በማናቸውም ሁኔታ ሌላውን ሰው ለመጉዳት በማሰብ በሰራው ሥራና በሚያደርሰው ጉዳት ሁሉ አላፊ ነው።
ስለሆነም ይህ ሰው ሆነ ብሎ በሌላው ላይ የሕሊና ጉዳት ያደረሰበት እንደሆነ ለተበዳዩ ወይም እሱ ላመለከተው በጎ አድራጎት ድርጅት ለሕሊናው ጉዳት ማካካሻ የሚሆን ካሣ እንዲከፈለው ሕጉ ያስገድዳል።
ሁለተኛው የሕሊና ጉዳት ካሣ የሚጠየቅበት ሁኔታ በተበዳይ ሰውነት ላይ ክብረ-ነክ የሆነ ድርጊት ሲፈጸም ነው። በሕጉ ቁጥር 2038 ላይ እንደተመለከተው አንድ ሰው ሆነ ብሎ ሌላው ሰው ሳይፈቅድ ቢነካው ወይም ሕይወት ባለውም ሆነ በሌለው ነገር ቢነካው (ቢያስነካው) ለዚህ መንካቱ ጥፋተኛ ነው።
ይሁንና ሁሉም መንካት የሕሊና ጉዳት ካሣ የሚያስከፍል አይደለም። ይልቁንም በሕጉ አገላለጽ መንካቱ “አስቀያሚ ወይም የሚያስጠላ መጥፎ መንካት” በሆነ ጊዜ ብቻ ነው። በግልጽ ምሳሌ ለማስቀመጥ አንድ ሰው በሌላው ሰው ላይ ሽንቱን ቢሸናበት ወይም ምራቁን ቢተፋበት ይህ የሕሊና ጉዳት ካሣ የሚያስከፍል ጥፋት ነው።
ሦስተኛው የሕሊና ጉዳት ካሣ የሚጠየቅበት ሁኔታ ያለአግባብ ሰውን መያዝና አግዶ ማቆየት ነው። ከሕጉ ቁጥር 2040 እንደምናነበው አንድ ሰው ሕግ ሳይፈቅድለት ለተወሰነ ጊዜ ቢሆንም እንዲሁም በአካሉ ላይ ጉዳት ባይደርስም እንኳ የሌላውን ሰው ነፃነት ቢነካና የመዘዋወር መብቱን በማገድ ቢከለክለው ጥፋተኛ ነው። የሕሊና ጉዳት ካሣም እንዲከፍል ይገደዳል።
አራተኛው የሕሊና ጉዳት ካሣ የሚጠየቅበት ሁኔታ የሥም ማጥፋት ነው። አንድ ሰው በንግግሮቹ፣ በጽሑፎቹ ወይም በሌላ ዓይነት አድራጎቶቹ በሕይወት ያለን ሰው ሥም በማጥፋት ስሙ የጠፋው ሰው እንዲጠላ፣ እንዲዋረድ፣ ወይም እንዲሳቅበትና ያለው ዕምነትና መልካም ዝናው ወይም የወደፊት ዕድሉ እንዲበላሽ ካደረገ ለጥፋቱ አላፊ ነው።
በመሆኑም የተሰደበው ወይም ሥሙ የጠፋው ሰው የሕሊና ጉዳት ካሣ መጠየቅ ይችላል። ይሁንና ሁሉም ዓይነት ስድብና የሥም ማጥፋት የሕሊና ጉዳት ካሣ ለመጠየቅ ምክንያት አይሆኑም።
ሥም አጥፊው ሰው ተበዳዩን ወንጀል ሰርቷል በማለት ሥሙን ያጠፋበት ከሆነ፤ በሙያው ችሎታ እንደሌለው ወይም እውነተኛ እንዳልሆነ አስቆጥሮት ከሆነ፤ ነጋዴ ከሆነ እዳውን ለመክፈል አይችልም በማለት አስመስሎ ለማሳመን የሚጥር ከሆነ፤ ተላላፊ በሽታ አድሮበታል በሚል ያስወራበት ከሆነ ወይም አስነዋሪ የሆነ ጠባይ አለው በማለት ያስወራበት ከሆነ ተበዳዩ የሕሊና ጉዳት ካሣ ለመጠየቅ መብት አለው።
አምስተኛው የሕሊና ጉዳት ካሣ የሚጠየቅበት ሁኔታ የባልና ሚስትን መብት መንካት ነው። አንድ ሰው ሴትዮዋ ባለባል እንደሆነች እያወቀ ያለባሏ ፈቃድ ባሏን ትታው እንድትሄድ ቁርጥ አሳብ እንዲኖራት ካደረገ ጥፋተኛ ነው። በተጨማሪም ባሏ ነገሩን እንደሚቃወም እያወቀው የሰው ሚስት በቤቱ ያስቀመጠ ወይም ያስተናገደ ሰው ጥፋት አድርጓል።
ነገሩ የተደረገው በባለትዳር ወንድ ላይም ከሆነ ውጤቱ ተመሳሳይ ነው። በዚሁ መነሻ ይህንን ያደረገ ሰው የሕሊና ጉዳት ስላደረሰ ካሳ እንዲከፍል ይገደዳል።
ነገር ግን ባልና ሚስቱ ተለያይተው ለመኖር ተስማምተው ከሆነ ከላይ የተጠቀሰውን አድራጎት መፈጸም ጥፋት አይደለም። በተጨማሪም ባልየው ሚስቱን አሰቃይቷት ከሆነ ወይም ግፍ መስራቱን ግለሰቡ በሕሊናው በመገመቱ ምክንያት ሴትዮዋን በሰብዓዊ ርህራሄ ተቀብሎ ያኖራት ከሆነ ላለመጠየቅ በቂ ምክንያት ነው።
ስድስተኛው የሕሊና ጉዳት ካሣ የሚጠየቅበት ሁኔታ ልጅን ከአሳዳሪው ነጥቆ መውሰድ ነው። በወንጀል ሕጉ መሰረት አንድ ሰው ለአካለ መጠን ያላደረሰ ልጅን (18 ዓመት ያልሞላውን) በኃይል አፍኖ ወይም በዛቻ፣ በማስገደድ፣ በተንኮል፣ በማታለል ወይም በማናቸውም ዘዴ የልጁን ፈቃድ ካገኘ በኋላ ጠልፎ የወሰደ ከሆነ እንደነገሩ ክብደት እስከ 20 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል።
ይህ አድራጎት ታዲያ በፍትሐብሔርም ለልጁ ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች የሕሊና ጉዳት ካሳ የመክፈል አላፊነትንም ያስከትላል። የሚከፈለው ካሣም በልጁ ተጠልፎ መጥፋት ምክንያት በወላጆች ወይም በአሳዳሪዎች ላይ ለሚደርሰው ጭንቀት ማካካሻ ስለመሆኑ ንጋቱ ተስፋዬ ከላይ በገለጽኩት መጽሐፉ አስፍሮታል።
ሰባተኛው የሕሊና ጉዳት ካሣ የሚጠየቅበት ሁኔታ የንብረት መብት መደፈር ነው። የንብረት መብት በሕገ መንግሥቱም ሆነ በፍትሐብሔር ሕጉ ጥበቃ ተደርጎለታል። በዚሁ መሰረት ማንም ሰው በሕግ ወይም በባለይዞታው ሳይፈቀድለት ወይም እየተቃወመው በመሬቱ ወይም በቤቱ ውስጥ ከገባ ወይም ንብረቱን ከወሰደበት ጥፋተኛ ነው። የሕሊና ጉዳት ካሣ እንዲከፍልም ይገደዳል።
ስምንተኛው የሕሊና ጉዳት ካሣ የሚጠየቅበት ሁኔታ የአካል ጉዳት ወይም ሞት ነው። ተከሳሽ አላፊ በሆነበት አንድ አደጋ አካሉ ለጎደለበት ሰው ወይም እሱ ከሞተ በቤተዘመዱ ላይ ለደረሰው የሕሊና ጉዳት ማካካሻ እንዲሆን ካሣ እንዲቆረጥ ሕግ ያዛል።
የአካል ጉዳት ከገንዘብ ኪሳራ በተጨማሪ የሕሊና ስብራትንም ያስከትላል። አካሉ የተጎዳ ሰው ይታመማል። በመንፈሱም ይሰቃያል። ሕይወቱም ከአስደሳች ገጾች ይልቅ አሳዛኝና ጎምዛዛ ቀለም ይበዛዋል። በአደጋ ምክንያት ሰው ሲሞትም የሟች ዘመዶች ከሚያጋጥማቸው ቁሳዊ ኪሳራ ባሻገር ሀዘናቸው ይበረታል፤ ሕሊናቸው ይጎዳል። ስለሆነም ለእነዚህ ሁኔታዎች የሕሊና ጉዳት ካሣ ሊከፈል ያስፈልጋል።
ዘጠነኛው የሕሊና ጉዳት ካሣ የሚጠየቅበት ሁኔታ የንጽህና ክብር መደፈር ነው። አንድ ሰው በወንጀል ሕግ በተደነገገው መሰረት አስገድዶ ከደፈረ ወይም ለክብረ ንጽህና ተቃራኒ የሆነ ድርጊት ፈጽሞ ከተቀጣ ከውል ውጭ በሆነ አላፊነትም የሕሊና ጉዳት ካሣ ይከፍላል።
አስረኛው የሕሊና ጉዳት ካሣ የሚጠየቅበት ሁኔታ በሚስት ላይ የደረሰ ጉዳት ነው። በሕጉ መሰረት ያገባች ሴት በደረሰባት የአካል ጉዳት ምክንያት በትዳር ውስጥ ለባሏ የምትሰጠው ጥቅም ወይም ደስታ የቀነሰ እንደሆነ ጉዳት አድራሹ ለባሏ የሕሊና ጉዳት ካሣ ይከፍላል።
እዚህ ላይ ሚስት በባሏ ላይ በደረሰ የአካል ጉዳት ምክንያት ባሏ የሚሰጣት ጥቅም ወይም ደስታ ሲቀንስ የሕሊና ጉዳት ካሣ እንድትጠይቅ የፍትሐብሔር ሕጉ አልፈቀደላትም።
ይሁንና በ1952 ዓ.ም. ወጥቶ በሥራ ላይ ያለው የዚህ ሕግ መሰል ድንጋጌዎች ከሕገ መንግሥቱና ከዚያ በኋላ ከወጡ ሌሎች ሕጎች ጋር የሚጣረሱ በመሆናቸው መተርጎም ያለባቸውም በሕገ መንግሥቱ ከተረጋገጠው የፆታ እኩልነት መብት አንጻር መሆን አለበት።
ዘመኑን ያልዋጀው ከአንድ ሺ ብር የማይበልጠው ካሣ
ከላይ ለተዘረዘሩትና በሕጉ የሕሊና ጉዳት ካሣ ለመጠየቅ ምክንያት ይሆናሉ ለተባሉት ጉዳቶች የሚከፈለው የካሣ ገንዘብ በማናቸውም ሁኔታ ከአንድ ሺ ብር ሊበልጥ እንደማይችል ሕጉ በግልጽ አስቀምጧል።
እርግጥ ነው የፍትሐብሔር ሕጉ በወጣበት የ1950ዎቹ ዓመታት አንድ ሺ ብር ከፍተኛ ገንዘብ ነው። ምናልባትም አንድ ደህና የመኖሪያ ጎጆ ለመቀለስ በቂ ገንዘብ ሊሆን እንደሚችል “የያኔው ትውልድ” አንባብያን ሊያስታውሱት ይችላሉ።
ነገር ግን አሁን ባለንበት ዘመን የአንድ ሺ ብር የመግዛት አቅም በጣም ደካማ ነው። እናም ከላይ በዝርዝር ለተመለከትናቸው በገንዘብ ሊተመን የማይቻል ከባድ የሕሊና ስብራት ለሚያደርሱ ጉዳቶች የሚከፈለው የሕሊና ጉዳት ካሣ ከአንድ ሺ ብር የማይበልጥ መሆኑ ዘመኑን ያልዋጀ ነው።
በዚህ ረገድ ከቁሳዊ የጉዳት ኪሳራ በተጨማሪ ለሕሊና ጉዳት ካሣ ለማስከፈል ፍርድ ቤቶች በእጅጉ ሲፈተኑ እናስተውላለን። ሕጉ የሕሊና ጉዳት ካሣ በማናቸውም ምክንያት ቢሆን ከአንድ ሺ ብር መብለጥ እንደሌለበት አስሮ በመደንገጉ ምክንያት ፍርድ ቤቶች በሚሊዮን ብሮች እንኳ ለማይገመቱት የሕሊና ቁስሎች ማካካሻ የሚወስኑት የጉዳት ካሣ ከአንድ ሺ ብር ሊበልጥ አይችልም።
ለዚህ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተወሰነ አንድ የክርክር ዶሴ ማሳያ አድርገን በማቅረብ ጽሑፋችንን እንቋጭ።
በኦሮሚያ ክልል ጂማ ዞን አካባቢ ነው። እናትና አባት ልጃቸውን በመኪና አደጋ በሞት ያጣሉ። በዚሁ መነሻ ከቁሳዊው ካሣ ባሻገር የሕሊና ጉዳት ኪሳራ ክስ መስርተው ለሞራል ካሣ እንዲሆን ለእያንዳንዳቸው አንድ ሺ ብር ኪሳራ ከኢንሹራንስ ድርጅቱ እንዲከፈላቸው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይወስናል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ውሳኔውን አጸናው።
ይሁንና ጉዳዩ ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ሲቀርብ ሕጉ “የጉዳት ካሣው በማናቸውም ምክንያት ከአንድ ሺ ብር የበለጠ ሊሆን አይችልም” ስለሚል በአደጋው ምክንያት የሕሊና ስብራት የደረሰባቸው ሰዎች ብዙ ቢሆኑም የሚከፈላቸውም ካሣ ተደምሮ ከአንድ ሺ ብር መብለጥ እንደሌለበት በማተት ወላጆች እያንዳንዳቸው 500 ብር የሕሊና ጉዳት ካሣ እንዲያገኙ ነው የወሰነው።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 18/2012
ገብረክርስቶስ