የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በኢትዮጵያ ያገር ሽማግሌዎች ሚና ምን እንደነበረና አሁን ያለው ሚና ምን እንደሚመስል ለማሳየት ያህል ነው፡፡ ባገር ሽማግሌዎች ሚና ላይ ብዙ ጥናታዊ ጽሑፎች እንዳሉ እርግጠኛ ነኝ፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚካሄደው ፖሊቲካዊ ለውጥ አንፃር ያገር ሽማግሌዎች ልክ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ የሚገጥማቸው ነገር አዲስ ሊሆንባቸው ይችላል፡፡ ለአዲስ ክስተት ደግሞ አዲስ አስተሳሰብ እንደሚያስፈልግ ሁሉ የሽማግሌዎች ሚናም ባዲስ ሊቀየር ይችላል፡፡
በመጀመሪያ ያገር ሽማግሌዎች ማኅበራዊ ሚና ምን እንደነበርና እንዴት ከጊዜ ጋር እንደተቀያየረ ባጭሩ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡ በቀድሞው ጊዜ ከልደት እስከሞት ባሉት ሁነቶች የሽማግሌዎች ተግባር ግልጽ ነበር፡፡ በግርዛት ጊዜ የጎረቤት ሽማግሌ ተለምነው ይመጣሉ፤ ለግርዛቱ አዲስ ምላጭ፤ ለደም ማድረቂያ የሚቃጠል ጨርቅ ከነአመዱ ይቀርባል፡፡ ምላጩ ሕፃኑን ሲነካው የሕፃኑ ለቅሶ ይሰቀጥጣል፡፡
ሽማግሌው ቅጠላ ቅጠል በጥሰው፤ ስራስር ምሰው ያዘጋጁትን ያገር ባህል መድኃኒት በግርዛቱ ላይ ይደመድሙታል፡፡ ቀጥሎም ለወላጅ እናትየውና ለሕፃኑ የአናት ቅቤ ይደረግላቸዋል፡፡
ሣር ይጎዘጎዛል፣ ቡና ይቆላል፤ ዕጣን ይጨሳል፤ ከተቻለም ሽቶ የረጫል፡፡ ልጁን ለማየት ለሚመጡ ዘመዶች፤ ጎረቤቶች፤ ጓደኞች ሁሉ ገንፎ በቅቤ ይቀርብላቸዋል፤ በጣታቸው ለማይበሉ የቀንድ ወይም የዘመኑ ማንኪያ ይቀርብላቸዋል፡፡ በመጀመሪያ ገንፎው የሚቀርበው ለሸማግሌው ነው፡፡ በዚህ የወንዱ ልጅ የግርዛቱ ሥርዓት ይጠናቀቃል፡፡
እዚህ ያቀረብኩት ስለወንድ ልጅ ግርዛት ብቻ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሽማግሌው የሴት ልጅ ግርዛትን በተመለከተ አንድ እምነት አላቸው፡፡ ይህም የሴት ልጅ ግርዛት ከፍተኛ የወሲብ ስሜትን ስለሚቀንስ ለትዳር ታማኝነትን ያረጋግጣል ብለው ያምናሉ፡፡ ስለወንድ ልጅ ግርዛት ያሉት ነገር እንዳለ አላውቅም፡፡ እኔም እዚህ ያቀረብኩት በዓይኔ ያየሁትን ስለሆነ በሌላ አካባቢ የሚደረገውን በቅጡ አላወቀውም፡፡ ይህ ባህላዊ የግርዛት ሥርዓት በዘመናዊ የግርዛት ዘዴ በመተካት ላይ ይገኛል፡፡ ጤና ጣቢያዎችና ክሊኒኮች ሕፃናቱን ይገርዛሉ፡፡ ይህ ዘመናዊ ግርዛት የሠፈር ሽማግሌዎችን የግርዛት ሚና እየተካው ይገኛል፡፡
ሽማግሌዎች ለግርዛት ይጠቀሙባቸው የነበሩ ባህላዊ ቁሳቁሶች፤ መድኃኒቶች፤ ቅጠላቅጠሎች ሁሉ ለዘመናዊ ግርዛት ስለማይፈለጉ ጥቅማቸው ሁሉ እየተረሳ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የሽማግሌዎቹም የግርዛት ክህሎት አብሮ ተረስቷል ማለት ይቻላል፡፡
ከግርዛቱ በኋላ ለልደቱ ዝግጅት መደረግ ይጀመራል፡፡ የልደቱ በዓል ለወንዱ ልጅ በተወለደ በአርባኛው ቀን ሲሆን ለሴትዋ ደግሞ በሰማንያኛው ቀን ይደረጋል፡፡ ለቀኑ መለያየት ምክንያቱን አላውቀውም፡፡ በሁለቱም ወቅት የጎረቤት ሽማግሌዎች ሚና አላቸው፡፡ የክርስትና እምነት ተከታዮች ከሆኑ ድሮ ይህ ቤተክርስቲያን ተገኝተው ያስቀድሳሉ፡፡ ሕፃኑ በተቀደሰበት ጸበል ከተጠመቀ በኋላ የክርስትና ስም ይወጣለታል፤ ይቆርባል፡፡ ሽማግሌዎች የክርስትናውን ሂደት በጥሞና ይከታተላሉ፡፡ ወደቤት ተመልሰውም ለልደቱ የተዘጋጀውን ቁርስ ባርከው ፀሎት ያደርሳሉ፤ ቡራኬውን ለታደሙት ቤተዘመዶችና ጎረቤቶች ያበረክታሉ፡፡
ከቁርስ በኋላ የልደቱን ሥርዓት የሚከውን ቄስ ወይም ዲያቆን ካልተገኘ በዕድሜ ገፋያሉት ሽማግሌ ይቆሙና ፀሎት ያደርሳሉ፤ ቀጥለውም ሕፃኑን ይመርቃሉ፡፡ ይህ የሽማግሌ ምረቃ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው ነው፡፡ የልጁ ልደት በየዓመቱ ዳቦ ተጋግሮ ጠላ ተጠምቆ መከበር ይጀምራል፡፡
የዘመኑ የልደት አከባበር ከበፊቱ ፍጹም የተለየ ነው፡፡ ለልደቱ በዓል አከባበር ሽማግሌ አያስፈልግም፡፡ ይልቅ በሠፈሩ ውስጥ የሚገኙ ሕፃናትና ወጣቶች የልደት በዓሉን እንዲያዳምቁ ይጠራሉ፡፡ ወላጆች ተበድረውም ሆነ አጠራቅመው የልደት ድግሱን ይደግሳሉ፤ የልጁ ስምና ዕድሜው የተጻፈበት ኬክ ይገዛል፤ ባለጌጥ ቆብ፤ ባለቀለም ልብስና ለስላሳ ጫማ ለባለልደቱ ይገዛለታል፡፡ ሻማዎች በዕድሜው ቁጥር ልክ ይገዙለታል፡፡ የጎደለ ነገር ካለ ልጁ ማልቀስ ይጀምራል፡፡ ወላጆች ልጁን ጠይቀው የጎደለውን ያሟላሉ፡፡
ለስላሳ መጠጥ በተጋባዥ ልክ ያገዛል፤ ደረቅ ብስኩት፤ ከረሜላ ይገዛል፡፡ ጣራና ግድግዳው ልዩ ልዩ ቀለማት ባሏቸው ስስ ወረቀቶች ያጌጣሉ፤ በለልዩ ልዩ ቀለማት ፊኛዎች በጣራውና በግድግዳው ይንጠለጠላሉ፤ አንዳንዱ ፊኛ በራሱ ፈቃድ ይፈነዳል፡፡ የክፍሉ ወለል ሣር በሚመሳስሉ ወረቀቶች ይሸፈናል፡፡ ከሰዓት በኋላ የልደት በዓሉ ይጀመራል፡፡ ኬኩ ይቆረሳል፤ ለስለሳው ይከፈታል፤ ኬኩ ከረሜላው ደረቅ ብስኩቱ በትናንሽ ሰሃን እየተሰፈረ ይታደላል፡፡
ኬኩን ከበሉ በኋላ ሕፃናቱ ይዘምራሉ፤ ይጨፍራሉ፡፡ መልካም ልደት የተሰኘ የፈረንጅ መዝሙር ይዘመራል፡፡ በበዓሉ መገባደጃ ላይ ከተጋባዦቹ አንዱ የመልካም ልደት ምርቃት ያደርግና የበዓሉ ፍጻሜ ይሆናል፡፡
በዚህ ዘመናዊ በሚመስል ልደት ካህናት ቀሳውስት ወይም ያገር ሽማግሌ አይፈለጉም፡፡ የጥንቱን ያገር ሽማግሌ ማኅበራዊ ሚና ጥሩ አድርጎ የሚያሳየን የጋብቻ ሥርዓት ነው፡፡ ወላጆች ለትዳር የደረሱ ልጆቻቸውን ለመዳር ሲፈለጉ መነጋገር ይጀምራሉ፡፡ ልጅህን ለልጄ ተባብለው ቃል ይገባባሉ፡፡ በዚህ መሠረት ልጆቻቸውን ይድራሉ፡፡ ይህ ቀላሉ የጋብቻ ዘዴ ነው፡፡ ጠልፎ ማግባትም አለ፡፡ ለዚህ ግን ሽማግሌ ያስፈልጋል፡፡ ሽማግሌ ካልተላከ የሴቷ ወገን የተናቀ ስለሚመስለው ጠብና ቂምበቀል ያስከትላል፡፡ ዳፋው ብዙ ነው፡፡ በጠለፋ ጋብቻ ያገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
ሌላው ዘዴ የወንዱ ወላጆች ሦስት ያህል የጎረቤት ሽማግሌዎችን ጋብዘው ስለልጃቸው ትዳር ጉዳይ፤ ማንን እንደሚያገባ፤ ለምን ልጅቷ እንደተመረጠች ያወያዩዋቸዋል፡፡ ሽማግሌዎቹም ቀጥተኛና ስውር ጥያቄዎችን ያቀርባሉ፡፡ የሴትየዋ ቤተሰቦች ሀብታሞች ስለሆኑ ነው የተመረጡት ወይስ የሊቃውንት ቤተሰብ ስለሆኑ፤ ትውልዳቸው ከንጉሣውያን ቤተሰብ ወገን ስለሆነ ነው ወይስ ባላባትና ባለርስት በመሆናቸው ነው ለጋብቻ የተፈለጉት? የሚል ጥያቄ በልዩ ልዩ መልኩ ለወንዱ ወላጆች ይቀርብላቸዋል፡፡
ለእነዚህና ለመሳሰሉት ጥያቄዎች ሽማግሌዎቹ መልሳቸውን ካገኙ በኋላ አንዳንድ ጉዳዮችን ለማጣራትና ለማረጋገጥ ድጋሚ እንደሚመጡ አሳውቀው ጠላቸውን ጠጥተው ወደየመጡበት ይመለሳሉ፡፡
ሽማግሌዎቹ የሚያጣሩትን ሁሉ ካጣሩ በኋላ ወደ ሴቷ ወላጆች ዘንድ ለሽምግልና ለመሄድ ቀጠሮ ይይዛሉ፡፡ በቀጠሯቸው መሠረት ስለወንዱ ልጅ ያላቸውን የተሟላ መረጃ ይዘው ከሴቷ ወላጆች ጋር ስለሚገናኙበት ሁኔታ ተነጋግረው ይጨርሳሉ፡፡
ከዚያ በኋላ ወደ ሴቷ ወላጆች መልዕክተኛ ተልኮ የቀጠሮው ቀን ይወሰናል፡፡ በሴቷ ወላጆች በኩል ደግሞ ከሦስት ያላነሱ ሽማግሌዎች ተመርጠው ይዘጋጃሉ፡፡ የሁለቱ ወገኖች ሽማግሌዎች ከተገናኙ በኋላ ውይይታቸውን የተዘጋጀላቸውን ግብዣ እያጣጣሙ ይቀጥላሉ፡፡ የውይይቱ ዓላማ ስለወንዱ ወላጆችና ስለልጃቸው ጠባይ፤ ሀብት፤ ዝርያ፤ የማኅበራዊ ደረጃ፤ ስለሚወረስ የጤና ችግር ሁሉ ለመረዳት የሚጠቅሙ ጥያቄዎች በማቅረብ ጭምር ነው፡፡
በተለያዩ ጊዜያት ሁለት ወይም ሦስት ስብሰባዎች ካደረጉ በኋላ ልጃችንን ለልጃችሁ ሰጥተናል ብለው ስለጋብቻው ሽማግሌዎቹ ስምምነታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ከዚያም በወንዱም ሆነ በሴቷ ወገኖች የሠርጉ ዝግጅት ይቀጥላል፡፡ በሠርጉ ማግስት የልጅቷ ክብረ- ንጽህና ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሽማግሌዎቹ በታደሙበት በጠዋት ሚዜዎች ብርአምባር ሰበረልዎ እያሉ ለወላጆች በይፋ በጭፈራ ያበስራሉ፡፡
በዘመናዊው ጋብቻ የሽማግሌዎች ሚና ከጥንቱ ፍጹም የተለየ ነው፡፡ ጋብቻውን የሚያጸድቁት ወላጆችና ሽማግሌዎቹ ሳይሆኑ ሁለቱ ተጋቢዎች ብቻ ናቸው፡፡ ሁለቱም ቀደም ሲል ባደረጉት ትውውቅ ሳቢያ ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው ስለየራሳቸው ልዩ ልዩ ጥናት ያካሂዳሉ፡፡ የፍትወተ ሥጋ ግንኙነትና ልጅ የመውለድ ችሎታ ሳይቀር የትምህርት፤ የሥራ፤ የገቢ፤ የውርስና የወደፊት የኑሮ አቅጣጫና ሌሎችም ዝርዝር ጉዳዮችን ስለእያንዳንዳቸው በስውርና በግልጽ አጣርተውና ተነጋግረው ለመጋባት ሊወስኑ ይችላሉ፡፡
አንዴ ከወሰኑ በኋላ ግን ሁለቱም ለየወላጆቻቸው የማይለወጠውን ውሳኔያቸውን ያሳውቃሉ፡፡ የወንዱ ወላጆች ሽማግሌዎችን ወደ ሴቷ ወላጆች ዘንድ ለይስሙላ ይልካሉ፡፡ የሴትዋም ወላጆች የራሳቸውን ሽማግሌዎች ከቁርስ ግብዣ ጋር አዘጋጅተው ከወንዱ የተላኩትን ሽማግሌዎች ለወጉ ያህል ይቀበላሉ፡፡
ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ማለት ይሄ ነው፡፡ መልሱ ይታወቃል፡፡ ባይሆን በዚህ የሽማግሌዎች ስብሰባ የድግሱ ቀን ሊወሰን ይችል ይሆናል፡፡ ይህም ቢሆን የሁለቱን ተጋቢዎች ይሁንታን ይጠይቃል፡፡ የሽማግሌዎች ጋብቻን የመወሰን ሥልጣን በዘመኑ ጋብቻ ውስጥ ፍጹም አያስፈልግም፡፡
ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች የሚፈለጉበት ሌላው ጉዳይ ሰው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ ለሚደረገው ሥርዓት ነው፡፡ ሰው ሲሞት ለመገነዝ የጎረቤት ሽማግሌ ይፈለጋል፡፡ ፀሎት ለማድረግ የኃይማኖት ሰዎች በኀዘኑ ቤት ይገኛሉ፡፡ ይህን ያገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት ሰዎች ሚና የዘመኑ ወጣት ሊተካው አልቻለም፡፡
እርግጥ በሆስፒታልና በጤና ጣቢያ ሕይወታቸው ያለፈና ዘመድ የሌላቸው ምስኪኖች በማዘጋጃ ቤት አማካኝነት ሥርዓተ ቀብራቸው ይፈጸማል፡፡ ይሁን እንጂ ይህም ቢሆን ሰው ሲሞት በሚደረገው ሥርዓት ያገር ሽማግሌዎች የኃይማኖት አባቶችን ማኅበራዊ ሚና የሚቀንስ አይደለም፡፡
እስከአሁን እኔ የማውቀውን ያህል ባጭሩ ለማሳየት የሞከርኩት ከግርዛት እስከ ግንዛት ባሉት ሁነቶች ያገር ሽማግሌዎች ሚና ምን እንደሚመስል ነው፡፡ ሌላው ጥንታዊ ያገር የሽማግሌዎች ሚና የሚገለጸው በእርቅ ጉዳይ ላይ ነው፡፡ በተለይ በገጠሩ አካባቢ ምርት ከተሰበሰበና ለቤተሰብ ፍጆታ የሚቀነሰው ተቀንሶ ለገበያ የሚቀርበው ምርት በሚያስገኘው ገቢ መዝናናት የተለመደ ነው፡፡
አረቄና ቢራ መጎንጨት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ግን እንዳንድ ጊዜ ጠብ ይፈጠራል፡፡ ያካል ጉዳትም ይደርሳል፡፡ የተጎዳው ሰው ብድሩን ለመመለስ ያደፍጣል፡፡ በዚህም የአካል ጉዳት አንዳንዴም ሞት ሊከተል ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ የበዳይ ወገኖች እርቅ ለመፍጠር ይጥራሉ፡፡
እርቁን የሚፈጥሩት ባገር ሽማግሌ አማካኝነት ብቻ ይሆናል፡፡ ሽማግሌዎችም አጥፊውን ካጣሩ በኋላ ጉማ ወይም ካሣ ለተጎዳው ወገን ያስከፍላሉ፡፡ ዳግም በቂም በቀል እንዳይፈላለጉ ያደርጋሉ፡፡ በዚህም በሀገሩ ሰላም ይወርዳል፡፡ በዳይና ተበዳይ ወዳጆች ሆነው ወደየሥራቸው ይሄዳሉ፡፡ ቤተዘመድ ሁሉ እፎይታ ያገኛል፡፡ ይህ ያገር ሽማግሌዎች ፍትሐዊ ተግባር በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ነበረው፡፡
በአሁኑ ዘመን ግን ጠበኞች ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ክሳቸውን ይመሠርታሉ፡፡ በወንጀል ብቻ ሳይሆን በፍትሀብሔር ጉዳይም ቢሆን ጉዳዮችን ወደ ፍርድ ቤት ማቅረብ የተለመደ ነው፡፡ ያንኑ ያህል ጉዳዩን በሽምግልና ለመጨረስ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር እያነሰ ሄዷል፡፡
በተለይም የባልና ሚስት ፍቺን በተመለከተ ጉዳዩ ለፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ በሽማግሌ እንዲታይ ፍርድ ቤቱ ያዝ ነበር፤ አሁን ግን ጉዳዩ በሽማግሌ እንዳይታይ ፍርድ ቤቱ አግዷል፡፡ በዚህም የሽማግሌዎች በባልና ሚስት ጉዳይ የነበራቸው ሚና ተሠርዟል ለማለት ይቻላል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ያገር ሽማግሌዎች አስተዋጽዖ ትርጉም ያጣበት ሌላው ጉዳይ ፖለቲካ ይመስለኛል፡፡ በፊውዳሉ ሥርዓት ጊዜ አንድ ግለሰብ በፖለቲካው፤ በሹመቱ፤ በኢኮኖሚ ጥቅሙ አድልዎ ሲደረግበትና ሲከፋው ይሸፍታል፡፡ የነፍስ ወከፍ መሣሪያ ይዞ ጫካ ይገባል፤ የደን ፍሬ እየለቀመ፤ የዱር አውሬ እያደነ፤ መንገደኞችን እየዘረፈ ይኖራል፡፡ ያካባቢው ሕዝብ ከፈራው ይገብርለታል፡፡ አለዚያም ለወረዳው ገዥ ፀጥታ ደፈረሰ በማለት ያመለክታል፡፡ የወረዳው ገዥ ወይም ባላባት ወይም አገረ ገዥው ሽፍታው ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል፡፡ ይህን ዕርምጃ የመንግሥት ተወካዮች በወቅቱ ካልወሰዱ ውሎ አድሮ ሥልጣናቸው ይደፈራል፤ ያካባቢው ሕዝብም ይንቃቸዋል፡፡ የሽፍታው ተሰሚነት እየጨመረ ሲሄድ ያካባቢው ያገር ሽማግሌዎች መምከር ይጀምራሉ፡፡
ሽማግሌዎቹ በመንግሥት አስተዳዳሪዎችና በአካባቢው ሽፍታ መካከል ዕርቅ እንዲወርድ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ የሁለቱ ወገኖች የኃይል ሚዛን ተመጣጣኝ ከሆነ የሽማግሌዎቹ ጥረት የተሳካ ሊሆን ይችላል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ግን የፖለቲካው ውዝግብ የተወሳሰበና ለሽምግልና የማይመች እየሆነ መጥቷል፡፡ ሽፍትነት ስሙን ቀይሯል፡፡ በታዳጊ አገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ ድህነት እጅግ የተንሰራፋባቸው ከመሆኑ ሌላ ያልሠለጠነ ፖለቲካም ችግራቸውን አባብሶት ይገኛል፡፡ በማኅበራዊም ሆነ በኢኮኖሚው መስክ ጥረው ግረው ሀብት ያፈሩ ዜጎችን ለመወዳደር የተሳናቸው ጥቂት ዋልጌዎች ፖለቲካን የሀብት ማካበቻ ስልት አድርገውታል፡፡
በሕዝብ ስም እየማሉና እየተገዘቱ ታማኝና ተቆርቁዋሪ መስለው ዓላማቸው ግብ እስኪመታ ምንጣፍ ይሆናሉ፡፡ ልክ ሥልጣን ማማ ላይ እንደወጡና የሥልጣን ኮርቻን እንደያዙ ሕዝብን መናቅ፤ ማንኳሰስ፤ መሳደብ፤ ማደህየት፤ ማዋረድ፤ መደፍጠጥ ይጀምራሉ፡፡ ሕገ መንግሥት ጽፈው በሕዝብ ላይ ይጭናሉ፤ የሥልጣናቸው ዋልታ የሆኑ ሕጎች፤ ደንቦችንና መመሪያዎችን ያወጣሉ፡፡
ሕጎቹ በዢው መደብ ላይ ተግባራዊነት አልነበራቸውም ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ሂደት ያገር ሽማግሌዎች፤ የኃይማኖት መሪዎች፤ ሕዝባዊ ማኅበራት ሁሉ የቀድሞ ሚናቸው ተቀይሮ በአንፃሩ የጭቆና ተባባሪ እንዲሆኑ ተደርገው ነበር፡፡
በተለይም የኃይማኖት መሪዎችና አዛውንቶች ተገደውም ሆነ ወደው የመንግሥት መሣሪያ በመሆን በሕዝብ ላይ የሚደርሰው ምድራዊና መንግሥታዊ ሰቆቃ በገነት እንደሚካካስ አድርገው በመስበክ የማይፋቅ በደል አድርሰዋል፡፡ ያገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት መሪዎች የነበራቸው ተሰሚነት ተሸርሽሮ ሊጠፋ ጥቂት ቀርቶታል፡፡ እነዚህ ሽማግሌዎች አሁን በምንገኝበት የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን በማኅበራዊ፤ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች እንደቀድሞው ዘመን ተሳትፎ ማድረግ የማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸው ያሳዝናል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የሥልጣኔ ደረጃ ደርሰን አሁን በማሽቆልቆላችን በምናሳያቸው ድርጊቶች እንስሳዊ ባህሪያችን ከጫፍ አድርሶናል፡፡ ሰው ገድለን ሬሳውን ዘቅዝቀን ሰቅለናል፣ ብልት አኮላሽተናል፣ እግር ቆርጠን አሰናክለናል፣ እስረኛን ጨለማ ቤት ከተን አሳውረናል፣ ሰውን ጫካ ውስጥ ላውሬ ምግብነት ሰቅለናል፣ መሬት ቆፍረን ጉድጓድ ውስጥ ሰውን አስረናል፣ አፈሩ ቢናድ እዚያው ተቀብሮ ከምድር ሲዖል ይገላገላል፤ የፀሐይ ብርሃን በማጣት ቆዳው ይለወጣል፤ የሴት ሽንት የተሸናበትን አፉንና የተገረፈበትን ፊርማ በጀርባው ይዞ ይኖራል፡፡
በቦምብ የተቦደሰውን፤ በታንክ የተጨፈለቀውን፤ በላውንቸር የተበጣጠሰውን አካል ቤቱ እንኳን ሊቆጥረው መቻሉን ያጠራጥራል፡፡ በዚህ ድርጊታችን የዓለም ሕዝብ ሁሉ በታላቅ መደናገር ይመለከተናል፡፡ በግንባራችን ላይ የተጻፈውን ይህንን አውሬነትና ማንነት ልንፍቀው ስለማንችል የውጭ ሰው ሲያገኘን አደጋ የምናደርስበትና የምንዘነጣጥለው አውሬዎች ልንመስለው እንደሚችልና እንደሚፈራን ልንዘናጋ አይገባም፡፡
ምናልባት ይህ ድርጊታችን ጸፅቶን በሚቀጥለው ጊዜ ወደ ሰውነት ባኅሪያችን ለመመለስ፤ ጥንታዊ ሥልጣኔያችንን በመመርመር፤ ባህላዊና መንፈሳዊ እሴቶቻችንን መልሰን ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፡፡ በዚህ በኩል በተለይም ያገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ተገቢው ሥፍራ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ እየቀነሰ የመጣውን መኅበራዊ ሚናቸውን መልሶ ማጠናከርና በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት እንዲዳብር ሁላችንም ጥረት ማድረግ ይገባናል፡፡
ለዚህም የአዲሱ ለውጥ መሪዎቻችን የጀመሩትን ለውጥ በትጋት እንዲቀጥሉና ባህሉና መንፈሳዊ እሴቶቹ ተቦርቡሮበት የተጎዳውን ሕዝብ መልሰው እንዲያበረታቱትና እንዲያነቃቁት ታላቅ ሕዝባዊ አደራ አለባቸው እላለሁ፡፡
አመሰግናለሁ፡፡መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም የተከበረች ቀን ትሁን፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 3/2011
ጌታቸው ሚናስ