ጎንደር፡- በ1628 ዓ.ም በዓፄ ፋሲለደስ የተመሰረተው የአፄ ፋሲል ቤተመንግስት በጎንደር ከተማ የሚገኝ የምሽጎችና የቤተመንግስታት ግምቦች ስብስብ ሲሆን በ1979 ዓ. ም. በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ሳይንስና ባህል ማዕከል /ዩኔስኮ/ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል።
የፋሲለደስ ቤተመንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የቱሪስት መስህብ ቅርሶች ውስጥ አንዱ ሲሆን በርካታ የሀገር ውስጥና የውጪ ጎብኝዎችን በማስተናገድ ይታወቃል፡፡ በሀገራችን ያሉ አብያተ መንግስታት የሚጎበኙት በውጫዊ ውበትና ታሪካዊነታቸው ሲሆን ከዚያ በዘለለ በአብያተ መንግስታቱ ውስጥ ምን ይከወን እንደነበር የሚያሳዩ ትዕይንቶች ለጎብኝዎች ሲቀርቡ አይስተዋልም፡፡
ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ጎንደር ከተማ በሚገኘው የፋሲለደስ ቤተመንግስት ውስጥ ‘‘ህይወት በአብያተ መንግስት’’ የሚል ፕሮጀክት ተጀምሯል፡፡ ፕሮጀክቱ በዚያን ዘመን በአብያተ መንግስታት ይከወኑ የነበሩ ድርጊቶችን ቁልጭ አድርጎ ለማሳየት ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን ለሙከራም ባሳለፍነው የጥምቀት በዓል እለት ለክብር እንግዶች የንጉስ እራት በማዘጋጀትና ትዕይንቶችን በመከወን ተጀምሯል፡፡
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በዚህ የንጉስ እራት ላይ ተጋብዞ ትዕይንቱን የተከታተለ ሲሆን የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ገፅታ በተመለከተም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ስለሺ ግርማ የፕሮጀክቱ ዋና አላማ በኢትዮጵያ ካሉ በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎች አንዱ በሆነው የጎንደር አብያተ መንግስት እስካሁን ጎብኝዎች አይተውት የሚሄዱት የነገስታቱን ቦታ ብቻ ስለሆነና ይህም የቆይታ ጊዜያቸውን ከማራዘምም ሆነ ታሪኩን በአግባቡ ከማወቅ አንፃር ክፍተት ስላለበት በቦታው በሚካሄዱ ክንዋኔዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ቱሪዝም ኢትዮጵያ ከጎንደር ባህል ማእከል ጋር በመነጋገር ‘’ ህይወት በአብያተ መንግስት’’ በሚል ለሙከራ የጀመረው ይህ ፕሮጀክት ነገስታቱ ይኖሩት የነበረውን የህይወት ዘይቤ ማለትም የፀጥታ ጥበቃውን፣ የውበት አጠባበቅ ስርዐቱን፣ የምግብ አቀራረቡን፣ የግብር ማብላት ስርዐቱን፣ አመጋገቡን፣ ዝማሬውን፣ እና አጠቃላይ እንቅስቃሴዎችን ለጎብኝዎች በማሳየት ለበለጠ ሳቢና ማራኪ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
ከባህል ማዕከሉ ጋር በመነጋገር 154 ወጣቶችን ለዚህ ፕሮጀክት ወደ ቤተመንግስቱ በማምጣት የተለያዩ ክዋኔዎች ላይ እንዲሳተፉ እየተደረገ ሲሆን በጊዜው የነበረውን የፈረስ ግልቢያ ለማሳየትም ፈረሶች በግቢው ተዘጋጅተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ለሙከራ ከተጀመረ ወዲህ ጎብኝዎች መደሰታቸውን የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው ንጉስ እና ንግስት፣ የጥበቃ ባልደረባ፣ ምግብ አቅራቢ፣ ፈረስ ጋላቢ ወይም በጊዜው ከነበሩ የቤተመንግስቱ አባላት አንዱን ሆነው መከወን ለሚፈልጉ ጎብኝዎችም እድሉ መመቻቸቱን አስረድተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በተሞከረበት ወቅት ውጤታማ ሆኖ በመገኘቱ እና በጎብኝዎችም ተወዳጅነትን በማትረፉ ይህንን የቤተመንግስት ህይወት የሚያሳይ ስራ ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ መሰል የቱሪስት መዳረሻዎች በተለይም አብያተ መንግስታት ወደሚገኙባቸው በመውሰድ ለመስራትና ተሞክሮውን ለማስፋት እንደታሰበ አቶ ስለሺ ይጠቅሳሉ፡፡
ይህንን መሰል ፕሮጀክቶች የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም ከቱሪዝም ዘርፉ የተሻለ ገቢ ለማግኘት ትልቅ ድርሻ የሚኖራቸው ሲሆን “ህይወት በአብያተ መንግስት’’ በጎንደር የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ በአንድ ቀን እንደሚያራዝም ተረጋግጧል፡፡
የቆይታ ጊዜያቸው መራዘሙ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ፣ ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ ከማሳደግ፣ ትክክለኛውን ባህል ለጎብኝዎች ከማስተዋወቅ፣ ታሪክን ከመዘከር እና መሰል ጥቅሞች አንፃር ሲታይ ጠቀሜታው ከፍ ይላል ብለው እንደሚያምኑ ያስረዳሉ፡፡
አገልግሎቱን ሙሉ ለሙሉ ለማስጀመርና ቅርሱን በማይጎዳ መልኩ እንዲከናወን ለማስቻል ለተቀጠሩት ሰራተኞች ቋሚ ደመወዝ፣ ለአልባሳትና የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች መግዣ፣ ለእንስሳቱ ምግብ እና መሰል ወጪዎች የመግቢያ ቲኬት ክፍያ ማሻሻል ስለሚያስፈልግ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ውይይት በማድረግ ተግባራዊ እንደሚሆን ሰምተናል፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳድር ተቀዳሚ ከንቲባ ኢንጅነር ማስተዋል ስዩም በበኩላቸው በጎንደር ከተማና ዙሪያዋ ያሉ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን የበለጠ ለማስተዋወቅ ሰፊ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀው የከተማ አስተዳድሩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ፕሮጀክቶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
ቱሪዝሙን ለማሳደግ ከተማው ካለበት የበጀት እጥረት አኳያ እንደዚህ አይነት ፕሮግራሞችን በፓኬጅ ያዘጋጀ ሲሆን የንጉስ እራት ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርግ እና በባህላችን እንድንኮራ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሚስተዋሉ ችግሮች ከባህል ጋር ከመጣላትና ባህልን ከመርሳት እንደሚመነጩ የተናገሩት ኢንጅነር ማስተዋል፣ ባህሎቻችን ለችግሮቻችን ሁሉ መልስ እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡ ህብረተሰቡ ስለአንድነት እያሰበ አዕምሮውን ከፍ በማድረግ ሀሳቡ እድገትና ብልፅግና ላይ እንዲሆን ባህል ትልቅ ድርሻ ያለው ሲሆን ህይወት በአብያተ መንግስት ለዚህ ትልቅ ማሳያ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል፡፡
ፕሮጀክቱ አንድ ጎብኚ በቤተመንግስቱ በሚኖረው ቆይታ ህንፃውን ተመልክቶ እና ፎቶ አንስቶ ከመሄድ ባሻገር በወቅቱ በቤተመንግስቱ ውስጥ ህይወት ምን ይመስል እንደነበር አይቶ የሚሄድበት እና በቆይታው የሚደሰትበት ይሆናል።እንዲሁም ሌሎችንም ጓደኞቹን ወደ ቦታው እንዲጋብዝ ያስችላል፡፡
እንደ ኢንጅነር ማስተዋል ገለፃ የሀገር ውስጥም ይሁን የውጪው ጎብኝ በከተማዋ ረዘም ያለ የቆይታ ጊዜ ኖሮት የተሻለ ጊዜ እንዲያሳልፍ፣ በሚቆይበትም ጊዜ ለከተማዋ ኢኮኖሚ መነቃቃት የበኩሉን እንዲያበረክት የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን የማስፋፋት ስራ ይሰራል፡፡
ለአብነትም በከተማዋ ውስጥ ያሉ ነገር ግን እምብዛም የማይታወቁ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት፣ ድልድዮች እና ሌሎችም መዳረሻዎችን የማልማት ስራ ይሰራል፤ ለጎንደር ከተማ እድገት ገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በቅርቡ የሚከናወን ሲሆን ለዚህም በቤተመንግስቱ የእራት ግብዣ እንደሚኖር ተጠቁሟል፡፡
ለጎንደር ከተማ እድገት ገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በቅርቡ የሚከናወን ሲሆን ለዚህም በቤተመንግስቱ የእራት ግብዣ እንደሚኖር ተጠቁሟል፡፡
በፋሲል ቤተመንግስት አሁን የተጀመረው ‘ህይወት በአብያተ መንግስት’ ፕሮጀክት ባህልንና ወግን ለተተኪ ትውልድ በማስተላለፍ በኩል ጉልህ ድርሻ ከማበርከቱም ባሻገር ትክክለኛ ታሪክን ለማሳየት ጠቀሜታው ጎላ ያለ ነው ይላሉ ኢንጅነር ማስተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በሙከራ ደረጃ ታይቶ ውጤታማ መሆኑ ተሞክሮውን ወደሌሎችም አብያተ መንግስታት ለማስፋት የታሰበ ሲሆን በፋሲል ቤተመንግስት ውስጥ የቅርሱን ህልውናና ደህንነት ባስጠበቀ መልኩ ሌሎችንም ተግባራት ለማከናወን ውጥን ተይዟል፡፡
በግቢው ውስጥ አንበሶችን ለማስገባት ቅድመ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የስምምነትና የፋይናንስ ማሰባሰብ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡
የከተማ አስተዳድሩ ከጎንደር ከተማ ልጆች ማህበር ጋር በመተባበር እየሰራ ባለው አንበሶችን የማስገባት ስራ ሁለት ደቦሎችን ወደ ቤተ መንግስቱ ለማስገባት እንዲቻል ከቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ፈቃድ ለማግኘት ጥያቄ ቀርቧል፤ ጎን ለጎንም ከእንስሳት መብት ጋር በተያያዘ ሊደረግላቸው ስለሚገባ እንክብካቤ ጥናት ተሰርቶ ቀርቦ ተቀባይነት ማግሸቱን አስታውቀዋል፡፡
አንበሳ የሚያቀርቡ አካላት አንበሶችን ለመስጠት ፈቃዳቸውን በመግለፃቸው የከተማ አስተዳድሩ አስፈላጊውን በጀት አቅርቦ አፀድቋል፡ በከተማዋ ዘላቂ የእንሳስት ፓርክ በመመስረትም አንበሶቹ ሲዋለዱ የሚገቡበት፣ ሌሎችን እንስሳት በማስገባትም የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ቦታ የመከለል ስራ የተሰራ ቢሆንም በመንግስት በጀት ሊከናወን የሚችል ባለመሆኑ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶቸን ለማሳተፍ እቅድ ተይዛል፡፡
የከተማ አስተዳድሩ በቤተመንግስቱ ግቢ ውስጥ ይህንን መሰል ስራዎች መስራቱ ለስራ እድል ፈጠራ እና የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ ከማራዘም አንጻር ውጤት እንደሚመዘገብበት ኢንጅነር ማስተዋል አብራርተዋል፡፡ ማንኛውም በቤተመንግስቱ ግቢ ውስጥ የሚከናወን ተግባር በቅርሱ ደህንነት ላይ ምንም አይነት ስጋት እንደማይፈጥር አስቀድሞ ጥናት የተደረገበት ሲሆን ሁነቶቹ በጥንቃቄ እንደሚከወኑም አረጋግጠዋል፡፡
በሁነት ዝግጅትና አስጎብኝነት ስራ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ አቻምየለሽ አሸናፊ ትውልድና እድገታቸው ጎንደር ነዋሪነታቸው ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ ሀገርኛ ባህል፣ ወግ እና ስርዐት እየጠፋ እንደመጣ የሚናገሩት ወይዘሮ አቻምየለሽ በዚህም ስሜታቸው እንደተጎዳ ይገልፃሉ፡፡
ይህንን ስሜታቸውን ይዘው በጎንደር ፋሲለደስ ቤተመንግስት ውስጥ በጥምቀት በዓል እለት በመገኘት የቤተ መንግስት የእራት ግብዣውን አዘጋጅተው አቅርበዋል፡፡ ይህንን በማድረጋቸው የተዘነጋውን ባህል እና ወግ ለወጣቱ ትውልድ ማስተዋወቅ እና የሚያውቁትን ደግሞ ዳግም ማስታወስ እንደቻሉ ይናገራሉ፡፡
በዚህ የእራት ግብዣ ፕሮግራም ላይ 300 ገደማ ሰዎች ተሳትፈዋል። በፕሮግራሙ በይበልጥ ወጣቶች መገኘታቸው ደግሞ ታሪክን ከማስቀጠል አኳያ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው የሚሉት ወይዘሮ አቻምየለሽ ቀደመ ሲል የነበሩት መልካም ነገሮች በመረሳታቸው ዛሬ ላይ በወጣቶች ዘንድ ብዙ ጥፋቶች እየተስተዋሉ ስለመሆናቸው ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡
የተሳሳተውን የወጣት ትውልድ አዕምሮ በመመለስ የሀገር ፍቅር ስሜቱን ማሳደግ የሚቻለው ደግሞ መልካም ባህልና ስርዓትን በማሳየትና በማስተማር ሲሆን ይህንን በመጠበቅም ከትውልድ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ አቻምየለሽ አሁን ከተከናወነው የእራት ፕሮግራም በተጨማሪም በስነ ስርዓቱ ላይ በእናቶችና አባቶች ወግ እንዲሁም በቡና ጠጡ ፕሮግራሞች በድርጅታቸው ኮኒ ኢቨንት ኦርጋናይዘር አማካኝነት ስራውን አጠናክረው የመቀጠል ውጥን እንዳላቸው ገልፀውልናል፡፡
ወይዘሮ አቻምየለሽ ባዘጋጁት በዚህ የንጉስ እራት ግብዣ ስነስርዐት ላይ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ በወቅቱ የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ በአሁኑ ሰዓት የኢፌዲሪ የንግድ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል፣ የቀድሞው የክልሉ ሰላምና ደህንነት ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ማስተዋል ስዩም፣ የጋሞ አባቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው የክልሉና የከተማዋ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም እንግዶች ተገኝተው ተጋብዘዋል፡፡እኛም ነባር ባህልን ዳግም ያስታወሰ ድንቅ ዝግጅት ስንል አድናቆታችንን ቸረነዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 15/ 2012
ድልነሳ ምንውየለት