አዲስ አበባ፦ ፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ፖሊስ ምርመራውን ባጠናቀቀባቸው በእነ ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው እና ሌሎች ሰባት ተጠርጣሪዎች ላይ ትናንት በፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ክስ መሰረተ፡፡
በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው ተጠርጣሪዎች እንደቅደም ተከተላቸው፤ ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው፣ ብርጋዴር ጀኔራል ጠና ቁርንዴ፣ ኮሎኔል ደሴ ዘለቀ፣ ኮሎኔል ጌትነት ጉድያ፣ ኮሎኔል ጎይቶም ከበደ፣ አቶ ቸርነት ዳና፣ እሌኒ ብርሃን እና አቶ ሮመዳን ሙሳ ናቸው፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በሜቴክ ስር ለሚገኘው ለአዳማ እርሻ መሳሪያዎች ኢንጂነሪንግ ኢንደስትሪ አገልግሎት የሚውሉ ትራክተርና ተቀጽላዎች መመሪያ በጣሰ የግዢ አፈጻጸም በባከነ በርካታ መጠን ያለው ገንዘብ ተጠርጥረው መከሰሳቸውን ዐቃቤ ህግ የመሰረተው ክስ ያመለክታል፡፡
ግለሰቦቹ ለራሳቸው ጥቅም በማግኘት፣ ለሌሎችም በማስገኘትና በመንግሥት ላይ ጉዳት በማድረሳቸው በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት በስልጣን አላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው መከሰሳቸውም በክሱ ተጠቅሷል፡፡
ዐቃቤ ህግ 24 ምስክሮችን እና 22 የሰነድ ማስረጃዎችን እንዲሁም የፎቶ ግራፍ ማስረጃ 18 ገጽ ሰነዶችን ጠቅሶ አቅርቧል፡፡ የተጠርጣሪ ጠበቆች በእንግሊዝኛ የቀረቡ ሰነዶች በክሱ መኖራቸውን በመጠቆም ተተርጉሞ እንዲቀርብ፣ ለመቃወሚያ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸውና ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡
ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ትርጉሙ እየተሠራ በመሆኑ እንደደረሰ እንደሚያቀርብ ለችሎቱ አስረድቷል፡፡ ዋስትና የጠየቁ ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበት ጉዳይ ከ10 ዓመታት በላይ የሚያስፈርድ በመሆኑ ጥያቄያቸው ውድቅ እንዲሆንለትም አመልክቷል፡፡ ተጠርጣሪዎች በጠበቆቻቸው አማካኝነት የመቃወሚያ ጊዜ እንዲራዘም ያቀረቡትን ጥያቄ ማስረጃዎቹ በርካቶች በመሆናቸው ቢፈቀድላቸው እንደማይቃወምም ጠቁሟል፡፡
ፍርድ ቤቱም በግራ ቀኝ የተነሱትን ጉዳዮች አድምጦ የሰነዶቹ የአማርኛ ትርጉም በ10 ቀናት ውስጥ በጽህፈት ቤት እንዲቀርብ፣ ጠበቃ ያላቀረቡ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተማክረው እንዲያቀርቡ አዝዟል፡፡ የዋስትና መብት አስመልክቶ የቀረበውን ጥያቄ የተጠረጠሩበት ወንጀል ከተረጋገጠባቸው እስከ 25 ዓመታት ሊያስፈርድባቸው የሚችል መሆኑን በመጥቀስ ጥቄውን ውድቅ አድርጎታል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ያልተያዙ እነ ኮሎኔል ጌትነት ጉድያ በዴ፣ ኮሎኔል ጎይቶም ከበደ አለሙ እና እሌኒ ብርሃን አባዲ የተባሉ ተጠርጣሪዎችን በአድራሻቸው ፈልጎ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ ለጥር 17 ቀን 2011 ዓ.ም መቃወሚያቸውን ለማዳመጥ ቀጥሯል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 3/2011
ዘላለም ግዛው