በዚህ ርዕስ ሥር ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ የሞከርኩት ከብዕሬ ጥቁር ቀለም እኩል ከጠቆረ ስሜት የመነጨ የትካዜና የርህራሄ ሀዘን ውስጤን እያመሳቀለ እንደነበር ማስታወሱ ጥሩ መንደርደሪያ ይሆነኛል።
ሀገሬ ለዘመናት ከውጭ ወራሪዎች ብቻ ሳይሆን ከውስጥም በወንድማማቾች መካከል የተለያዩ ጦርነቶችን ስታስተናግድ መኖሯን ያነበብነው ከታሪክ ገፆች ላይ ብቻ አይደለም። በእኛው በራሳችን ጀንበር ጭምር የተፈጸሙብን የባዕዳን ወረራዎችና የእርስ በእርስ እልቂቶች የትናንት መራራ ትዝታዎቻችንና ማስታወሻዎቻችን ናቸው። የ1969 ዓ.ምን የምሥራቁን የሶማሊያ ወረራና በሰሜኑ የሀገራችን ክፍሎች የተፈጸሙትን የተራዘሙ የእርስ በእርስ የፍልሚያ ታሪኮች ብቻ ማስታወሱ ለአብነት ይበቁ ይመስለኛል።
እያንዳንዱ ወር በራሱ የሚዘከርለትና የሚታወስበት ታሪካዊም ሆነ ማሕበራዊ ክስተቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይታመናል። ለምሳሌ፤ የየካቲት ወር ስም ሲጠራ ብዙ ሀገራዊ ታሪኮችና ትዝታዎች ተግተልትለው ይመጡብናል። ወሩ በዓመቱ ስድስተኛ ረድፍ ላይ መገኘቱ ብቻ ሳይሆን የተሸከማቸው ትውስታዎችም ከአቻዎቹ ወራት በላቀ ደረጃ የገዘፈ እንዲሆን አግዘውታል። ትውስታዎቹ ለእያንዳንዱ ሰው የተለያየ ትርጉም ስለሚሰጡ የግል አቋሜን በማንፀባረቅ ለመፈረጅ፣ ጠልቄና ጫን ብዬ ለመኄስም አልሞክርም።
እንዲያው በደምሳሳው በጥቂቶቹ ላይ ብቻ ቅኝት ለማድረግ ያህል በየካቲት 1888 ዓ.ም ጀግኖች አያቶቻችን ዐድዋ ላይ ዘምተው በአንድ ጀንበር ለዘመናት ሲተረክ የሚኖር ገድል አስመዝግበው አቆይተውልናል። ለእነዚያ ጀግኖች አባቶችና እናቶች ክብር ይሁን።
በየካቲት 1929 ዓ.ም ፋሽስቶች በጨፈጨፏቸው ንፁሃን ደም አዲስ አበባና አካባቢው በደም አበላ ተጥለቅልቆ እንደነበር 83 ዓመታትን ወደ ኋላ ተጉዞ ማስታወሱ ቢዘገንንም ነፃነታችንን ያፀናው ያ የጀግኖች ደም መሆኑን ስናስብ ግን ብሔራዊ ኩራታችን ይጨምራል። በዚሁ በየካቲት ወር 1966 ዓ.ም ሕዝባዊ አብዮት በኢትዮጵያ ምድር ዳር እስከ ዳር ተቀጣጥሎ የንጉሣዊውን ሞአ አንበሳ ዘእመነ ነገደ ይሁዳ የአገዛዝ በትረ ሥልጣንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሰብሮ ሕዝቡና ታሪክ ነፃ መውጣቱም ታሪካችን ነው።
በዚሁ በየካቲት ወር 1967 ዓ.ም የዳግማዊ ወያኔ (ህወሃት) ትግል ደደቢት በረሃ ውስጥ “ሀ” ብሎ ተጀምሮና ፋፍቶ እንደምን የደርግን ሥርዓት እንዳስወገደ ብንተርክ በእነዚያም ሆነ በእነዚህኞቹ ወገኖች መካከል ብዙ ጉዳዮች ስለሚቀነቀኑለት ዝርዝሩን የማልፈው በሆድ ይፍጀው ትዝብት ነው።
እንዲያው በጅምላ እይታ እንቃኘው ከተባለ ግን የጦርነት ታሪካችን የተመዘገበው ከባዕዳን ወራሪዎች ጋር የተደረገው ፍልሚያ ብቻ እየተነቀሰ ሳይሆን በእኛ መካከልም በርካታ የጥቁር ደም መቃባቶች ተፈጽመው እንደነበር ደግሞ ደጋግሞ ማስታወሱ ለትምህርት ይበጅ ይመስለኛል።
ከአንድ ሦስት ዐሠርት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የቴአትርና የባህል አዳራሽ አንድ አስደናቂ ቴአትር ለተመልካች ቀርቦ ነበር። የቴአትሩ ርዕስ “ጋሞ” ይሰኛል። የቴያትሩ ደራሲ ደግሞ የምናከብረው የጥበብ ሰው ጋሼ ጸጋዬ ገ/መድኅን ነበር። አዘጋጁ ደግሞ አባተ መኩሪያ ሲሆን ተዋናዮቹ ፈቃዱ ተክለ ማርያም፣ ገለታና ሱራፌልን የመሳሰሉ የቴአትር ቤቱ ድንቅ ተዋናዮች ነበሩ። ቴአትሩን ለሁለት ሰዓት ከአርባ አምስት ደቂቃ ያህል ለሚፈጅ ረጅም ሰዓታት የተወኑት ሁለት ገጸ ባህርያት ብቻ ነበሩ።
ቴአትሩ በመድረክ ላይ የቆየው ካልተሳሳትኩ ሁለቴ ወይንም ሦስቴ ብቻ ይመስለኛል። ምሉዕ ታሪኩን የሚያስታውሱ የዓይን ምስክሮች ተሳስቼ ከሆነ ሊያርሙኝ ይችላሉ። በሦስተኛው ወይንም በአራተኛው ቀን በአንድ ከፍተኛ የደርግ መንግሥት ባለሥልጣን የሚመራ የታጠቀ ኃይል ድንገት ቴያትር ቤቱን በመውረር ትርዒቱ እንዲቆም ቀጭን ትዕዛዝ በማስተላለፉ ያን የመሰለ ቴአትር በከንቱ መክኖ ቀረ። ከዓመታት በፊት የቴያትሩን ማኑስክሪፕት እንዳነበው የሰጠኝ ዛሬ በሕይወት የሌለው አብሮ አደጌ ሻለቃ አባይነህ አበራ ሲሆን፤ ንባቤን የጨረስኩት በእንባና በተመሳቀለ ስሜት ውስጥ ሆኜ ነበር።
የቴአትሩ ታሪክ በአጭሩ በወቅቱ በሰሜናዊ የሀገራችን ክፍል ይካሄድ የነበረውን የሁለት ወንድማማቾች ጦርነት የሚወክሉ ሁለት ወንድማማች ገፀ ባህርያት በግዳጅ ቀጠናቸው ምሽግ ውስጥ እንዳደፈጡ እርስ በእርስ ቃታቸውን አነጣጥረው እየተጠባበቁ የሚያወጉት መራር ወግ ነበር። “ከአንድ ማህጸን የወጣን የአንድ እናት ልጆች ለምንድን ነው እርስ በእርስ ጎራ ለይተን እንድንገዳደል የፈረዱብን?” እያሉ ከእንባ ጋር የሚያደርጉት ውይይት (Dialog) በእጅጉ ልብን የሚሰብር ነበር። ሁለቱ ወንድማማቾች በተቃራኒ ጎራ ተሰልፈው በጦር ሜዳ መገናኘታቸው በራሱ ግጥምጥሞሹን ያወሳስበዋል።
ተውኔቱ ተመልካቹን በሙሉ በእንባ ያራጨ እንደነበር ያዩት ሊመሰክሩ ይችላሉ። “ዕድሜ ለደርግ” ያን የመሰለ ቴአትር በአጭሩ ቀጭቶ አስቀረው። እንደሚመስለኝ ያ ቴያትር ዛሬ ለመድረክ ቢቀርብ ጊዜው ይመስለኛል።
የጎንዮሽ ትረካውን እዚህ ላይ አቁሜ ወደ ተነሳሁበት ዋና ጉዳይ ልዝለቅ። የዘንድሮው የ2012 ዓ.ም የየካቲት ወር ከ“ጋሞ” ቴአትር የገዘፈ እውናዊ ቴአትር እያሳየን ያለ ይመስለኛል። ህወሃት የበረሃ የትጥቅ ትግሉን የጀመረበት 45ኛ ዓመት ክብረ በዓል በትግራይ ክልል ተከብሮ ከሦስት ቀናት በፊት የተጠናቀቀው ሞቅና ደመቅ ባሉ ዝግጅቶችና ትርዒቶች ነበር። ለበዓሉ የተደኮነው ድንኳን ገና ፈርሶ ስላልተጠናቀቀ ዛሬም ድረስ የበዓሉ ስሜት ትኩስ ነው።
ስለ ህወሃትም ሆነ ስለ በዓሉ አከባበር ብዙ ለማለትና ለመኄስ እጅግም አልዳፈርም። ለማንሳት የምሞክረው በበዓሉ ላይ ጎልቶ የተደመጠውን፣ የታየውንና በግሌም ስሜቴን በሀዘን ያነዘረውን አንድ ክስተት ብቻ መዝዤ በማውጣት ይሆናል። ድርጊቱ ያሳሰበኝ “የብሔራዊ ጦርነት ውርስን” ለትውልዱ እንደማውረስ ተደርጎ እንዳይቆጠር ስጋት ስለገባኝ ነው። ይህ የጸሐፊው የግል አቋም ይሁን እንጂ ብዙ ዜጎች በድርጊቱ ተመሳሳይ ስሜታቸውንና ሀዘናቸውን ደጋግመው ሲገልጹ አድምጫለሁ።
ትንንሽ ታዳጊ ሕጻናት ደብተራቸውን አስቀምጠውና የአርቴፊሻል ጠብመንጃ ታጥቀው ሲፎክሩ ያስተዋልነው ሆቸ ጉድ በሚል ግርምት ብቻ አይደለም። ወንድም ከወንድም ጋር የተደረገ የጦርነት ውርስ በሦስተኛው ትውልድ አገርሽቶ እንዲቀነቀን ለምን እንዳስፈለገ ለጸሐፊው ግልጽ አይደለም። የዛሬ አርባ አምስት ዓመት ወደ ኋላ ተመልሶ የእንተላለቅ ያረጀ ዜማ በሕጻናት አንደበት ማዘመር በግሌ እንቆቅልሽ ብቻ ሳይሆን ግራ የሚያጋባ ክስተት ስለመሆኑ መመስከር አይገድም።
ከሕጻናቱ የጦርነት ናፍቆት ጎን ለጎን ለበዓሉ ድምቀት እንዲሆን የተካሄደው ወታደራዊ ሰልፍና ዛቻም አሰቅቆኛል። በየአደባባዮቹ ላይ የቆሙት የሚሳዬልና የሮኬት ግዙፍ ቅርጾችም የሚያስወነጭፉት የስጋት ቀለህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በአጭሩ የህወሃት 45ኛ ዓመት ክብረ በዓል አከባበር በግሌ አስደንግጦኛል፣ አሳስቦኛል፣ አሰቅቆኛልም። የጦርነቱ ፊሽካ እውን ሆኖ ቢነፋ ማን በማን ላይ ሚሳዬል ሊተኩስ ነው። ማን ማንን ገሎ ሊፎክር ወይንም ማርኮ ሊያቅራራ ነው። በምኞት የተገለጸው የይዋጣልን ፉከራ በግሌ የሚያስታውሰኝ “የጋሞ” ቴያትርን ነው። ዝርዝር ስጋቴን ለጊዜው እዚህ ላይ ገትቼ ወደ ሌላ በጎ ትዝብት ልሸጋገር።
እኔ ጸሐፊው የትግራይ ክልልን ደጋግሜ ከዳር ዳር የመጎብኘት እድሉ ገጥሞኝ ስለነበር የትግራይን ሕዝብ ደግነትና ፍቅር በሚገባ ለመረዳት ችያለሁ። ይህንን ሕዝብ ፍቅር ብቻ የሚል ቃል አይገልጸውም። እንስፍስፍ አንጀት ያለው፣ ሰው በልቶ የጠገበ የማይመስለው እንግዳ ወዳድ ስለመሆኑ የምመሰክረው በእውነትና ስለ እውነት ነው። እርግጥ ነው እንደማንኛውም የተቀረው የሀገራችን ሕዝብ የትግራይም ሕዝብ ባለፉት ሥርዓቶች በእጅጉ ጉዳት ደርሶበታል። ይህንን መሰሉን የሕዝባቸውን መከራ ከትከሻው ላይ አሽቀንጥሮ ለመጣልም ልጆቹ በህወሃት ጥላ ሥር ተሰባስበው የከፈሉት መስዋዕትነት የሚዘነጋ አይደለም። በእዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ስለተባለና ስለ ተጻፈ ደግሜ ዝርዝሩን አልተርክም።
ይህ መልካምና ቅን ሕዝብ በህወሃት 45ኛ ዓመት በዓል ላይ በዋናነት የተላለፈለት መልዕክት ከጦርነት ቅስቀሳ ያላነሰ፣ ለዘመቻና ለንቅናቄ የሚያበረታታ መሆኑን ሳስተውል በእጁጉ መንፈሴ ታውኳል። ሕዝቡ በማን ላይ ይዝመት? ከማንስ ጋር ይዋጋ? ለምንስ ውጤት የሚሉ ጥያቄዎችን መሪዎቹ ልብ ተቀልብ ሆነው አስበውበት ይሆንን ብዬ እጠይቃለሁ። ለመሆኑ ሕዝቡስ ዝመት፣ ተዋጋ፣ ግደል ተጋደል ስለተባለስ “ለምን? ማንን? እና በማን አዝማችነትና ፊት አውራሪነት?” ብሎ መጠየቁ መች ይቀራል።
በትግልና በፖለቲካ ፍልሚያ ጥርሳቸውን የነቀሉት ጎምቱ የክልሉ መሪዎችስ ቢሆኑስ ይህንን የመሰለ ቅስቀሳ ሲያደርጉ በእውነቱ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል አስልተው ይሆንን? ብለን እንጠይቃለን። ሰከን ብለው ቢያስቡት ምናልባትም ሊጸጸቱ እንደሚችሉም እንገምታለን። በፖለቲካና በርዕዮት ዓለም ፍልስፍና ጫፍና ጫፍ ቆሞ መከራከርና በሃሳብ መሟገት ያለና የነበረ እውነታ ነው። “አንተ አትረታኝም፣ የምረታህ እኔ ነኝ፣ አታሸንፈኝም፣ አሸንፍሃለሁ ወዘተ…” የሚሉት ፖለቲካዊ አገላለጾች በሰላማዊ መንገድ የሚተገበሩና የሚቀነቀኑ ቢሆን ችግር የለበትም። በዳይነትና ተበዳይነት ቢኖርም ሕዝብን ባከበረ ሁኔታ ተወቃቅሶ መተራረም ይቻላል። ነገሮችን እያከረሩ በማጦዝ ለውጊያና ለዘመቻ ወንድም ከወንድም ጋር ጦር እንዲማዘዝ መገፋፋት ግን በየትኛውም ወገን በኩል ቢሆን ለማንም እና ለምንም ጠቃሚ አይደለም።
ብዕሬ የትኛውንም ቡድን በአድርባይነት አያሞካሽም፤ ማንንም በኢ-ምክንያታዊ ጥላቻ አይነቅፍም። የማንም የፖለቲካ ጫናም አይሸከምም። የብዕሬ ነጻነት የሚመነጨው ከጸሐፊው ነጻ ሃሳብ ብቻ ነው። ዛሬ በቀላሉና በጥቂቶች ፍላጎት ሊጫር የሚሞከረው የጥላቻና የግጭት ክብሪት ውሎ አድሮ የሚያደርሰው ሀገራዊ አደጋ ልንገምተው ከምንችለው በላይ ለትውልድ ክፉ ቅርስ ሆኖ የማይተላለፍበት ምክንያት አይኖርም የሚል የግል አቋም አለኝ።
ህወሃት የ45ኛ ዓመት ልደቱን ማክበሩ መብቱ ነው። ይህንን መብት ማንም ሊከለክላቸው የሚችል አይመስለኝም። ነገር ግን በበዓሉ አከባበር ላይ የሚተላለፉት መልዕክቶች ምን ይዘት ይኑራቸው ብሎ ደግሞ ደጋግሞ ማስተዋልና መመካከር ግን ጠቢብነት ነበር። ህወሃት ስልሳ ሺህ ሰው የገበርኩበትና በርካቶች ለአካል ጉዳተኝነት የተዳረጉበት የትግል ድል ውጤት ነው እያለ ሲናገር ቢያንስ ለሦስት ዐሠርት ዓመታት ያህል ሰምተናል። ልጆቻቸውን ለትግሉ የገበሩ የትግራይ እናቶችና አባቶች፣ የአካል ጉዳተኞችና ቤተሰቦቻቸው የተሰበረ ቅስም እንዴት እንደሚጠዘጥዝ የደረሰበት ብቻ ሳይሆን ደግሞ ማስታወሱ በራሱ እኩል ያማል። በአንጻሩም ተሸናፊ የተባለው የወቅቱ የኢትዮጵያ ሠራዊት እናቶችም በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ልጆቻቸውን፣ ልጆችም አባቶቻቸውንና ወንድሞቻቸውን መገበራቸውና ዛሬም ድረስ ጥቁር የሀዘን ማቃቸውን እንደተከናነቡ እንዳሉ ማስታወሱ ልባምነት ነው። በዚያም ወገን የረገፉት የኢትዮጵያ ልጆች ሲሆኑ በሌላኛውም ወገን የረገፉት የዚያችው የመከረኛ ኢትዮጵያ ልጆችና ወንድማማቾች ናቸው።
“የገደለው ባልሽ፤ የሞተው ወንድምሽ፣
ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ”
ይሉት ዓይነት አባባል ሃሳቤን ይሰበስብልኝ ይመስለኛል። በግሌ በበዓሉ ላይ የተላለፉት አንዳንድ መልዕክቶችና ትርዒቶች በሚገባ ቢፈተሹ ኖሮ መልካም ሊሆን ይችል ነበር ብዬ አስቤያለሁ።
በትግራይ ክልል መሪ ድርጅት እና በማዕከላዊ መንግሥት መካከል ጣልቃ ገብቶ ነገሮችን ማርገብ የሚችል አቅም ያለው መፍትሔ አመንጭ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዛሬ እንደ እህል እርቦናል፤ እንደ ውሃም ጠምቶናል። ፍጥጫውም አሳስቦናል። በሁለቱም ወገኖች መካከል ያለው መካረር ለሕዝቡ፣ ለቀጣዩ ትውልድ፣ ለታሪክም ጭምር ይበጃል የሚል አቋም በግሌ የለኝም፤ ሊኖረኝም አይችልም። የክልሉ መሪዎችና ፖለቲከኞች እልሃቸውን አቀዝቅዘው፣ መንግስትም ሆደ ሰፊ ሆኖ ተቀራርበው ቢነጋገሩ ይበጃል። ዝቅ ማለት የሚገባው ወገን ዝቅ እንዲል፣ የተካረረው ውጥረትም እንዲረግብ የማድረግ አቅም ያለው ገላጋይ ኃይል በሀገር የለም ወይ እያልን ብንጠይቅ አያስወቅሰንም። ለምን ቢሉ ነገሮች ቢጦዙና ቢከሩ የከፋ ውጤት ያስከትላሉ እንጂ መፍትሔ ሊሆኑ ስለማይችሉ።
ሞትና እልቂትን እስከሚበቃን ተለማምደን እንባችን ነጥፏል። “ዝመት፣ ተዋጋ፣ ተጋደል” የሚሉት ዓይነት መፈክርም ትውልድና ሀብታችንን እንክት አድርጎ በልቶ መለመላችንን እንዳስቀረን እናውቃለን። ሕዝቡ የሀዘን ፍራሽ ጎዝጉዞ መቀመጥን፣ ጥቁር ከል ለብሶ ማንባትን ኖሮበታል። ይህን መሰሉ ሁኔታ ዳግም ተፈጥሮ ማየት ቀርቶ ማሰቡ በራሱ መንፈስን ያጠለሻል።
“የወታደር እናት ታጠቂ በገመድ፣
ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ”
የሚለውን እንጉርጉሮ ዛሬም እንደ ትናንቱ የወትሮ ዜማ አድርጎ ከእንባ ጋር መተከዣ ለማድረግ የሕዝቡ አቅም ተንጠፍጥፎ ያለቀ መሆኑን ለመረዳት ለምን ጥበብና አቅም እንደጠፋ ግልጽ አይደለም። “ያዋከቡት ነገር፤ ምዕራፍ አያገኝም” በማለት የዛሬ አርባ ዓመታት ግድም የተቀነቀነው ዜማ ጥሩ ማጠቃለያ ሊሆን ስለሚችል ለመሰነባበቻነት አስታውሼ ነገሬን እጠቀልላለሁ። ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 14/2012
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com