ደራሲና ሃያሲ ዓለማየሁ ገላጋይ በአንድ መድረክ ላይ ስላጋጠመው ገጠመኝ በተናገረው ጉዳይ ልጀምር። መቼም ደራሲ አስተዋይ ነውና ከአንድ ጎበዝ መምህር ያስታወሰውን ለታዳሚው አካፍሏል። በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት በቀላሉ ማስረዳት የሚችሉ መምህራን ቢኖሩን ሁላችንም አስተዋይና በጎ አሳቢ እንሆን ነበር።
መምህሩ ክፍል ውስጥ አንድ ቀን እያስተማረ ነው። የዕለቱ ርዕሰ ጉዳይ ደግሞ ስለማድነቅ ነበር። መምህሩ እንደሚያስተውለውም ብዙ ጊዜ ሰዎች ለመሰዳደብ እንጂ ለመደናነቅ ቃላት ማውጣት አይችሉም። መምህሩ ይህን የመተቻቸት እንጂ የመደናነቅ ልማድ እንደሌለ ለማሳየት ቀላል ምሳሌ ነው የተጠቀመ።
ከክፍሉ ውስጥ አንዲት ቀጫጫ ተማሪ ወደ ፊት ለፊት እንድትወጣ አደረገ። ተማሪዎችንም ‹‹እስኪ ይቺን ልጅ ስደቧት›› አላቸው። ተማሪዎች የስድብ መዓት አዥጎደጎዱት። ‹‹ደረቅ፣ አጥንት፣ አንድ ሐሙስ የቀራት፣ መጣጣ፣ እንጨት…›› እያሉ ሲረባረቡ ‹‹በሉ በቃችሁ›› አለ መምህሩ። ቀጥሎ ደግሞ ‹‹እስኪ አድንቋት›› አላቸው። ተማሪዎች ቃላት አጡ፤ ‹‹ለግላጋ መለሎ›› አሉና ከሁለት ቃላት በላይ መሄድ አልቻሉም።
መምህሩ ተማሪዋን ወደ ቦታዋ መለሰና ሌላ አንዲት ወፍራም ተማሪ ወደ ፊት ለፊት አወጣ። ይችኛዋንም ልክ እንደ ቀጫጫዋ ‹‹እስኪ ስደቧት›› አላቸው። አሁንም ተማሪዎች ተረባረቡ። ‹‹ዘረጦ፣ ኩንታል፣ ዝፍዝፍ፣ ሸክም፣ ጎተራ….›› እያሉ ቀጠሉ። መምህሩ ‹‹እስኪ አሁን ደግሞ አድንቋት›› አላቸው። ‹‹ድንቡሽቡሽ፣ ለስላሳ›› እያሉ ከሁለት ቃላት በላይ መሄድ አልቻሉም።
በመጨረሻም መምህሩ እንዲህ አላቸው። ‹‹አያችሁ! ቀጫጫዋንም ወፍራሟንም ማድነቅ አልቻላችሁም፤ ለስድብ ሲሆን ግን ለሁለቱም ቃላት አላለቀባችሁም ነበር፤ ለሁለቱም ግን የአድናቆት ቃላት አጠራችሁ›› እያለ ስለቅንነት አስረዳቸው።
የመምህሩ ምሳሌ ጥሩ ማሳያ ነው። የብዙዎቻንንን ነባራዊ ሁኔታ የሚገልጽ ነው። ቀጭንም ወፍራምም አናደንቅም፤ ረጅምም አጭርም አናደንቅም። ቀጫጫ የተሳደበ ሰው ወፍራም ማድነቅ ነበረበት አይደል? ወፍራም የሚጠላም ቀጫጫ መውደድ ነበረበት አይደል? ግን ሁለቱንም መሳደብ ነው የሚቀድመን። በሁለቱም መሳለቅ ነው የሚታየው። የማድነቅ ልምድ የለንም። ይህን የሚገልጽ አንድ ግድግዳ ላይ (መኖሪያ ቤት ይሁን ንግድ ቤት አላስታውስም) ያየሁትን ግጥም እንደ ማዳበሪያ ልጠቀምና ወደ ዋናው ጉዳይ ልግባ።
ቢወፍሩ ዱባ ቢቀጥኑ ትንኝ
ቢናገሩ አፈኛ ዝም ቢሉ ሞኝ
ፈጣሪ ከሰው አፍ አንተው ሰውረኝ
ቅዳሜ የካቲት 7 ቀን 2012 ዓ.ም ዕለት ደግሞ በአዲስ አበባው ስካይላይት ሆቴል አንድ መድረክ ተሰናድቶ ነበር። በመድረኩ ላይ አንጋፋ ደራሲያን፣ ተዋንያን፣ ድምጻውያንና ሌሎች ታዋቂ ሰዎች ነበሩ። ዋና ዓላማውም በኪነ ጥበብ ሥራዎቻቸው በህብረተሰቡ ውስጥ ቅንነትን ማስረጽ ነው። በመድረኩም ስለቅንነት ተወያዩ ገጠመኞቻቸውንም ተናገሩ። አዘጋጁም ‹‹ቅን ኢትዮጵያ›› ይባላል። ወደ መድረኩ ከመግባታችን በፊት ‹‹ቅን ኢትዮጵያ›› ምን እንደሆነ እንወቀው።
ቅን ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው። በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጄንሲ ሥር በ2002 ዓ.ም ተመዝግቦ የተቋቋመ ነው። መነሻ ያደረገውም በኢትዮጵያውያን የመደናነቅን ቀን ማክበር በሚለው የዶክተር ቶሎሳ ጉዲና ሀሳብ ነው። በመርሃ ግብሮቹም የመገናኛ ብዙኃንንና ታዋቂ ሰዎችን በመጠቀም ስለቅንነትና መደናነቅ መድረክ እያዘጋጀ ያወያያል። በትምህርት ቤቶች ውስጥ መድረኮች በማዘጋጀት ተማሪዎች እርስበርስ እንዲሞጋገሱና እንዲመሰጋገኑ ያደርጋል።
ያለፈው ቅዳሜ በነበረው የቅን ኢትዮጵያ መድረክ ላይ የተገኙት ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው የተናገሩት ገጠመኝ የቅንነትን ዋጋ ያሳያል። እግረ መንገዱንም ቅንነት በማጣት ምን ያህል ችግሮች እንደሚደርሱ ያሳያል። ገጠመኛቸው ይሄ ነበር።
በሚሳሩበት ድርጅት ውስጥ አንዲት ሴት መጣች። የወይዘሮ ፍሬያለም ፀሐፊ አንዲት ሴት እንደምትፈልጋቸው ነገረቻቸው። ወይዘሮ ፍሬያለምም ትግባ አሉና እንግዳዋ ገባች።
ሴትዮዋ ‹‹ምንድነው?›› ተብላ ስትጠየቅ ችግሯን ከመናገር ይልቅ እምባ ቀደማት። ወይዘሮ ፍሬያለምም እንደምንም ካረጋጉ በኋላ መናገር ጀመረች። ‹‹አንድ ነገር ብቻ ነው የማስቸግርሽ፤ ሌላ ሥራም አልፈልግም፤ ጽዳት ቅጠሪኝ›› አለች። ይቺ ጽዳት ቅጠሩኝ የምትለዋ ሴት ለ10 ዓመት ያህል በመምህርነት ሙያ አገልግላለች። አሁንም በሚገባ የማስተማር ብቃት አላት።
ዳሩ ግን በሙያዋ ላይ እያለች በወሊድ ምክንያት በደረሰባት ችግር ለረጅም ጊዜ ከሥራ አቋረጠች። ሦስት ልጆችን ወልዳ አራተኛ ስትወልድ በወሊድ ምክንያት በደረሰባት ችግር ከትዳር ጓደኛዋ ጋርም ተለያዩ። ቀጥሎ ያለው ሕይወት የጉስቁልና ሆነ። ለመምህርነት የሚሆን የአለባበስ አቅምም የላትም። እንዲህ ሆኜ ተማሪዎች ፊት አልቀርብም የሚል ስሜት ተፈጠረባት።
ወይዘሮ ፍሬያለም ትምህርት ቤት ያስተዳድሩ ስለነበር ሴትዮዋን በጽዳት ሰራተኝነት ሳይሆን በመምህርነት ነው የምቀጥርሽ አሏት። ማመን አልቻለችም፤‹‹እንዴትስ እንዲህ ተጎሳቁዬ፣ ይሄን ለብሼ ከተማሪ ፊት እቀርባለሁ›› አለች። ወይዘሬ ፍሬያለምም ‹‹አይ ይሄን ለብሰሽ አይደለም›› በማለት ደመወዝ እየከፈሉ የማረፊያ ጊዜ ወስዳ ለሥራ እንድትመጣ አደረጓት። በተሰጣት እረፍት ውስጥ ራሷን አረጋግታ መምህር ሆና መጣች። ከዚያ በኋላ በድጋሚ መምህር ሆነች። በሳይንስ ትምህርቶች ላይ ባላት ብቃት ተማሪዎች ይወዷታል። ተሸላሚ መምህር ናት።
ጉዳያቸው ወደ ሚዲያ መድረስ ያልቻለ የዚህ አይነት ብዙ ችግሮች ይኖራሉ። ከዚህ ገጠመኝ ሁለት ነገር እንረዳለን። አንዱ የወይዘሮ ፍሬያለም ቅንነት ነው። የትኛውም ድርጅት ያለማስታወቂያ ሰው አይቀጥርም፤ ቢቀጥርም በዘመድ አዝማድ ወይም በሌላ ጥቅማጥቅም እንጂ ለእንዲህ አይነት ችግረኛና ለማያውቁት ሰው አይደለም። በሌላ በኩል ደግሞ ሴትዮዋ የፈለገችው የጽዳት ሥራ ነው፤ ዳሩ ግን ታሪኳን በማወቅና ብቃቷን በማየት የሚገባትን ቦታ አገኘች።
ሁለተኛው የምንረዳው ነገር ደግሞ የዚህን ተቃራኒ ነው። ሴትዮዋ ያ ሁሉ ችግርና መጉላላት የደረሰባት ቅንነት ባለመኖሩ ነው። እንዲህ ሁሉ ነገር አልፎ ወደ መደበኛ ሥራዋ ልትመለስ የትዳር አጋሯ ፈታት። በአለባበሷና በሰውነቷ መጎሳቆል ጽዳት እንኳን የሚቀጥራት ጠፋ። ይሄ ችግር ደግሞ በብዙ ቦታዎች የምናየው ነው። ቅንነት ካለ ግን እንዲህም ማድረግ ይቻል ነበር ማለት ነው።
እንዲህ አይነት የስነ ምግባር ቀረፃዎችና የበጎነት ትምህርቶችን ማስረጽ የሚቻለው በታዋቂ ሰዎችና በአርቲስቶች አማካኝነት ነው። ለዚህም ነው ብዙ ጊዜ ለተማሪዎችና ለወጣቶች መድረክ ሲዘጋጅ ታዋቂ ሰዎች ይጋበዛሉ። አርቲስቶች ይኖራሉ። ምክንያቱም ከእነዚያ ሰዎች የሚወጣ ምክር ሁሉ ወደ ወጣቶች አዕምሮ ይገባል።
ለምሳሌ ተማሪ እያለን የመምህሮቻችንን ፈለግ እንከተላለን። ተመስጋኝ የሒሳብ መምህር ካለ የሒሳብ መምህር ነው መሆን የምንፈልገው። ተመስጋኝ የኬሚስትሪ መምህር ካለ እሱን መሆን ነው የምንፈልገው። ከመምህሮቻችን አረማመዳቸውንና አነጋገራቸውን ሁሉ ሳይቀር ለመምሰል እንሞክራለን። በዚህ ሂደት ውስጥ ነው መጥፎ አርዓያነትም ካለ ሰዎችን ይዞ የሚጠፋው። ለዚህ ነው ታዋቂ ሰዎችና አርቲስቶች በጎነትና ቅንነትን ያሳዩ የሚባለው።
አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ በዚሁ ቅን ኢትዮጵያ ባዘጋጀው መድረክ ላይ እንደተናገረው፤ ቅንነትን ወደ ህብረተሰቡ ማስረጽ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ እንዲህ አይነት መድረኮች ያስፈልጋሉ። አርቲስቶች በሥራዎቻቸው ሁሉ ሊያንጸባርቁት ይገባል። መገናኛ ብዙኃን እንዲህ አይነት ይዘት ያላቸው ወደ ህብረተሰቡ ቢያደርሱ አንዱ ከአንዱ እያየ እርስበርስ መማማርን ያጠነክራል። በህዝብ ዘንድ ታዋቂነት ያላቸው ሰዎች በየሥራ ድርሻቸው ቅንነትን የሚያሳዩ ከሆነ ቅን ትውልድ ይፈጥራሉ።
በነገራችን ላይ ኪነ ጥበብ ትውልድ የማነጽም፣ የመናድም አቅም አለው። ወጣቶችን ልብ ብሎ ማየት በቂ ምስክር ነው። በተለይም በፊልምና በእግር ኳስ ዘርፍ ታዋቂ የሆኑ ሰዎችን ፈለግ ይከተላሉ። የሚያደርጉትን ለማድረግ ይጥራሉ፤ በተለይም በታዳጊዎች ላይ ይጠነክራል።
ማንም ሰው በጎ ነገር ሊያደርግ ይችላል፤ የታዋቂዎችን ያህል ግን ተፅዕኖ ሊፈጥር አይችልም። በአንድ በኩል የመሰማት ዕድል የለውም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ቢሰማ ራሱ ታዋቂዎች ያደረጉትን ያህል መነጋገሪያ አይሆንም። አንድ አርቲስት በጎ ነገር ሲያደርግ የእሱን ፈለግ በመከተል ሌሎችም ያደርጋሉ።
ቅን ኢትዮጵያ ባዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ የተገኙት ታዳሚዎች በወጣቶችና አዋቂዎች ዘንድ ተፅዕኖ የፈጠሩ ናቸው። የየኛ የሙዚቃ ቡድን አባላት እና የጃኖ ባንድ የሙዚቃ ቡድን አባላትን ጨምሮ በተለያዩ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ድራማዎች የሚታወቁ ተዋንያን፣ የማስታወቂያ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
ቅን ኢትዮጵያ በቀጣይ እሰራቸዋለሁ ያላቸው ነገሮች አሉ፤ የሚተገብረው ከሆነ ትልቅ ነገር ነው። በውጭው ዓለም ሲደረግ እያየን የምንቀናበት ነገር ነው። ይሄውም በጎ ሥራ በሰሩ ድርጅቶችም ሆነ ግለሰቦች ላይ ዘጋቢ ፊልም መሥራት። በአገራችን የአንድ ታዋቂና አንጋፋ ድርጅት ታሪክ ለማወቅ ወደ ኢንተርኔት ጎራ ብንል አንድ አንቀጽ እንኳን አናገኝም። ከስሙ ጋር የሚቀራረብ ሌላ ጉዳይ የያዘ ሀሳብ አምጥቶ የውጭ አገር ታሪክ ነው የሚነግረን። በመጽሐፍና በዘጋቢ ፊልም መልክማ ጭራሽ አይታሰብም። ቅን ኢትዮጵያ ይህን የሚተገብረው ከሆነ ይበል የሚያሰኝ ነው።
ኢትዮጵያዊ ቅንነት ተፈጥራዊ ባህሪ ነው። ዳሩ ግን ይህን ውስጣዊ ባህሪ ተግባራዊ ለማስደረግ የሚያነሳሳ አካል መኖር አለበትና እንዲህ አይነት ቅን አድራጊዎችን ያብዛልን።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 14/2012
ዋለልኝ አየለ