ጎሽ ለልጇ …

የዓመታት ትዳሯን ሞት ከፈታው ወዲህ ወይዘሮዋ የብቸኝነት ሕይወት ወርሷታል፡፡ አራት ልጆቿን ያለአባት ማሳደግ፣ ቤቷን ያለአባወራ መምራት ለእሷ ቀላል አልሆነም። እሷ ባትማርም በተቻላት አቅም ልጆቿን ታስተምራለች፡፡ ሁሉም ሴቶች ናቸውና በምክንያት ቤት እንዲውሉ አትሻም።

ልጆቹ አስቀድሞ ሕይወት የገባቸው ይመስላል። ለትምህርት የሰጡት ትኩረት ለየት ያለ ነው። ሁሉም ትምህርት ቤት ውለው ሲመለሱ የነገውን ዓለም ያስባሉ፡፡ ትናንት እንደእነሱ የተማሩ ወድቀው እንዳልቀሩ ሰምተዋል፡፡ አብዛኞቹ ጥሩ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በመማራቸው፣ ቀለም በመለየታቸው ነው፡፡ ይህ እውነት በተለይ ለሴት ልጆች ትርጉሙ ይለያል፡፡

ወይዘሮ ካንቺ ወዲያ ዘውዱ ኑሮና ሕይወቷ ምስራቅ ጎጃም ሉማሜ ከተማ ነው፡፡ ቀደም ሲል በተወለደችበት የገጠር ቀበሌ ልጅነቷን አሳልፋለች፡፡ ከዓመታት ወዲህ ወደከተማው ዘልቃ ትዳር ይዛ ልጆች ከወለደች ወዲህ ሕይወቷ በዚሁ አካባቢ ሆኗል፡፡

ካንቺ ወዲያ ባለቤቷ በሞት ከተለያት በኋላ ጥቂት ጊዜያትን በብቸኝነት ቆየች፡፡ ውሎ አድሮ ግን የትዳር አጋር የሚሆናት ሰው ለጋብቻ አሰባት፡፡ እንዲህ መሆኑን አልጠላችውም። በብቸኝነት መኖር ለሴት ልጅ በእጅጉ ከባድ ነው፡፡ በብዙ ይፈትናል። በትዳር መሰብሰቧ ያኮራታል፣ ያስከብራታል፡፡ አራት ልጆች ቢኖሯትም ብቸኝነትን ለማምለጥ፣ ተከብራ ለመኖር ስትል ሁለተኛውን ጋብቻ መሠረተች፡፡

የስለት ልጅ…

የመጀመሪያዎቹ የጥምረት ጊዜያት መልካም ሆነው ተጓዙ። አባወራው ከትዳሩ ልጅ ማግኘትን ይፈልጋል፡፡ ይህ ፍላጎት ደግሞ የእሱ ብቻ አልሆነም፡፡ እሷም ብትሆን ወንድ ልጅ ለመውለድ ስትመኝ፣ በየታቦቱም ስትሳል ቆይታለች፡፡ ከአሁኑ ባሏ ወንድ ልጅ ብታገኝ ደስታዋ ነው፡፡ በስለቷ የልቧ ሞልቶ ፈጣሪዋን የምታመሰግንበት ቀን ይናፍቃታል ፡፡

ካንቺ ወዲያና ባለቤቷ በትዳር ያቆሙት ጎጆ ከጥቂት ቆይታ በኋላ የምሥራችን አበሰረ፡፡ እንደታሰበው ሆኖ ወይዘሮዋ ነፍስጡር ሆናለች፡፡ ይህ ከታወቀ ጀምሮ በጥንዶቹ መሐል መተሳሳቡ ጨምሯል፡፡ እሷ ለዓመታት የወንድ ልጅ ናፍቆት ሲያሳሳት ኖሯል፡፡ አሁን ግን ስለቷ ሰምሮ የልቧ ሞልቷል፡፡

ወይዘሮዋ እንደማንኛዋም ነፍሰጡር ከሕክምና ትሄዳለች። የክትትል ቀጠሮ በኖራት ጊዜ በተሻለ ሆስፒታል መገኘት ልማዷ ነው፡፡ እንዲህ መሆኑ ጤናዋን አስጠብቆ ልጇን በሠላም ያሳቅፋታል፡፡

ከዘጠኝ ወር በኋላ …

አሁን ወይዘሮዋ የመውለጃ ጊዜዋ ደርሷል፡፡ ይህ እንደታወቀ ለአራሷ የሚበጅ ቤት ያፈራው ሁሉ ሲዘጋጅ ቆይቷል፡፡ ለመውለድ የመጀመሪያዋ አይደለምና የምጡን ስቃይ አልፈራችም፡፡ አባወራው በበኩሉ የሚወለድለትን አቅፎ ሊስም ፣ እንደአባትም ልጁ ሊያደርገው ጓጉቷል። ጊዜው ደርሶ ከቀናት በአንዱ ወይዘሮዋ ከሆስፒታል ተገኘች፡፡ ማለዳውን የጀመራት ምጥ በዋዛ አልተዋትም። እያንቆራጠጠ፣ እያስጨነቀ ሰዓታትን አስቆጥሯል፡፡

የቆይታው ብዛት አዋላጆቹን ከአንድ ውሳኔ ያደረሳቸው ይመስላል፡፡ ለመወለድ ከጫፍ ደርሶ ‹‹መጣሁ›› የሚለውን ጨቅላ በመሣሪያ ታግዘው ለማውጣት ተዘጋጅተዋል፡፡ እንዳሰቡት ሆኖ ሕጻኑን ከእናትዬው ማሕፀን ጎትተው አወጡ። የጨቅላው ለቅሶና የእናቲቱ እፎይታ በአንድ ተጋመደ፡፡ እናት ፈጥና ምጧን ረሳች፡፡ በፈገግታ ልጇን አንስታ ታቀፈች ፡፡

እንዲህ በሆነ ጥቂት ግዜ በኋላ እሷን ጨምሮ ባለቤቷ ያዩት እውነታ ከድንጋጤ ጣላቸው፡፡ የእነሱ ልጅ ጭንቅላት እንደሌሎች ሕጻናት አይደለም፡፡ መሐሉ ተሰርጉዶ፤ ግንባሩ ጥግ ተሰብሯል፡፡ እጆቹ እንደልብ አይታዘዙም፣ ወገብና እግሩ እንዳሻው አይሆንም፡፡ እንዴትና ለምን ማለታቸው አልቀረም።

ውሎ አድሮ ጉዳዩ በውል ተረጋገጠ፡፡ በወሊድ ጊዜ ልጁን ከማሕፀን ለማውጣት በነበረው ትግል በአዋላጆቹ ስህተት ሕፃኑ ከፍ ያለ ጉዳት አጋጥሞታል፡፡ ወላጆቹ ችግሩን በቅርብ ላሉ ባለሙዎች አሳይተው ይህንኑ አረጋግጠዋል። መፍትሔውን ሲጠይቁ ደግሞ ከጥቂቶቹ ያገኙት ምላሽ አስደንጋጭና ተስፋ አስቆራጭ ነበር፡፡

አንዳንዶቹ የልጁ ጉዳት ከጭንቅላቱ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ፈጽሞ እንደማይድን ነገሯቸው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ተስፋ ሳይቆርጡ ከፍወዳለ ሕክምና ቢወስዱት እንደሚድን ነገሯቸው። መልካም ነገር ያሏቸውን ሀሳብ ይዘው ሐኪም ፊት ቀረቡ፡፡ ሐኪሞች የሀሳባቸውን አልነሷቸውም፡፡ ተገቢውን የሕክምና ማስረጃ ጽፈው ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አመላከቷቸው፡፡

‹‹ለሚሞት ልጅ አትድከሚ››

ወይዘሮዋ ውላ አላደረችም፡፡ በስንት ስለት ያገኘችው ወንድ ልጇ ተሰናክሎ መቅረቱ ከኅዘን ያለፈ ቁጭት አሳድሮባታል፡፡ እሷ ከትንፋሽ በቀር አንዳች ምልክት ባልነበረው ጨቅላ ፈጽሞ ተስፋ መቁረጥ አትፈልግም፡፡ እንደልጅ እየሳቀ፣ ባያጫውታትም፣ ዓይኗን እያየ ባይለያትም ለእሷ የአካሏ ክፋይ ተወዳጅ ልጇ ነው፡፡ የገባችበት ገብታ ጤናውን ትሻለች፡፡

ጨቅላ ልጇን አዝላ ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ስትነሳ አንድም ሰው ‹‹በቸር ግቢ›› ያላት የለም፡፡ ስለሕክምናው ለመሄድ መቁረጧን ያስተዋሉ ብዘዎች ከዳር ቆመው አሽሟጠጧት፣ አነወሯት፡፡ ለማይድን ልጅ አገር ቆርጣ የመሄዷ ጉዳይ አናዷቸው፣ ሊመልሷት፣ ሞከሩ፡፡ ሁሉም እየተነሳ ይፈረድባት፣ ይቆጣት ያዘ፡፡ እሷ ግን በፈጣሪዋ ተስፋ አልቆረጠችም፡፡ በስለት ለምና ያገኘችው ብቸኛ ወንድ ልጇ መሆኑን አስባ መንገዷን ቀጠለች፡፡

ካንቺ ወዲያ አዲስ አበባን በስም ካልሆነ አይታት አታውቅም፡፡ እሷ ትውልድ ዕድገቷ ገጠር ላይ ነው፡ ፡ ዛሬ ግን ከማታውቀው ሰፊ የከተማ ባሕር ልትሰምጥ ግድ ሆኗል። እሷ ማንበብ መጻፍ ይሉትን አታውቅም፡፡ ስልክ መደወል አትችልም፡፡ ጉዞ በጀመረች ጊዜ አብሯት የመጣ፣ የተከተላት ወዳጅ ዘመድ ጎኗ የለም፡፡ ይህ ሁሉ ጎዶሎ ከእሷ ጋር መሆኑን ታውቃለች፡፡ እንዲያም ሆኖ ችግሩ ሰበብ አልሆናትም፡፡ ልጇን ከጀርባዋ እንዳዘለች መሐል አዲስ አበባ ገብታለች፡፡

አዲስ አበባ ላይ …

ስፍራው ስትደርስ ካገሯ መነሳቷን ያወቀ አንድ ሰው ከመናኸሪያው ቆሞ ጠበቃት፡፡ ይህ ሰው የድሮው ሟች ባለቤቷ ታናሽ ወንድም ነው፡፡ ባገኘችው ጊዜ ደስታዋ ወሰን አጣ፡፡ በምስጋና ፈጣሪዋንና እሱን ደጋግማ አመሰገነች፡፡ መልካሙ ሰው የደረሰባትን ችግር ሰምቷል። ቤቱ መውሰድ ባይችልም ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሊያደርሳት፣ ጉዳይዋን ሊፈጽምላት ተዘጋጅቷል፡፡

አሁን ሁኔታዎች ተመቻችተው መስመር ይዘዋል። ከሆስፒታሉ የደረሰችው ወይዘሮ ለልጇ ሕክምና ልታገኝ፣ የልቧም ሀሳብ ሊሞላ ነው፡፡ ከሆስፒታሉ ግቢ እንደደረሱ ማረፊያ የሚሆን ቦታ አላጣችም፡፡ በቀጣይ ቀናት ሕጻኑ በቂ ምርመራ አግኝቶ ጉሉኮስ ተሰጠው።ለተከታታይ ቀናት ጤናውን እያዩ በእጃቸው ያቆዩት ሐኪሞች እንደሌሎቹ ተስፋዋን አልነጠቋትም።ውሎ አድሮ በልጇ ላይ ያየችው ለውጥ ተስፋዋን አለመለመው፡፡ ወደውስጥ የታጠፈው ምላሱ ተዘርግቶ በወጉ ምግብ መቅመስ፣ ጡት መጥባት ጀመረ፡፡ የተቆለመመ አንገቱ ተመለሰ፡፡ የታሰሩ እጆቹ ተፍታቱ፣ የላመው አጥንቱ በአካል እንቅስቃሴ ጠንክሮ ቀና ለማለት ሞከረ፡፡ እንዲህ አይነቱ ለውጥ ለእናት ካንቺ ወዲያ ከተስፋ በላይ ሆኖ አከረማት፡፡

ከአንድ ወር ላላነሰ ግዜ በአዲስ አበባ የቆየችው ወይዘሮ ለዳግም ቀጠሮ እንድትመለስ ተነገራት። ይህን ጊዜ ሀገሯ መግባት ነበረባትና ልጇን አዝላ ወደቤቷ አቀናች፡፡ መንደሯ ስትደርስ ግን ማናቸውም የልጁን ለውጥ አይተው ማረጋገጥ አልፈለጉም፡፡ ሁሉም የትናንትና ችግሩን እያስታወሱ ዳግመኛ ይዛው እንዳትመለስ በቁጣና ማስጠንቀቂያ አሳሰቧት፡፡

ካንቺ ወዲያ የሰማችው እያቆሰላት፣ በተናገሯት ክፉ ሀሳብ ተክዛ ሰነበተች፡፡ ወይዘሮዋ የሌሎቹ ሲገርማት የባለቤቷ ባሕርይ መለወጥ ደግሞ ይበልጥ አስከፍቶ አንገቷን አሰደፋት፡፡ ገና ስትመጣ አንስቶ ፊት ነስቷታል። እሱም ለማይድንና ተስፋ ለማይጣልበት ልጅ ሀገር አቋርጣ መሄዷን አላመነበትም፡፡

ሚስት ሀሳቡን ስትረዳ ለምን ብላ ጠየቀችው። የልጅ አባት፣ ባለቤቷ ለምላሹ አልዘገየም፡፡ ልጁን ለለማኝ፣ አልያም ለመንግሥት ሰጥታ ሠላማዊ ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ ቁርጥ ባለ ቃል አረጋገጠላት፡፡ የሰማችውን ማመን ባትፈልግም የሆነው ሁሉ እውነት ነበር፡፡ አባወራው ከዚህ በኋላ ለእንዲህ አይነቱ ልጅ ወላጅ አባቱ መባልን አይፈልግም፡፡

ፈተና …

አሁን የጥንዶቹ አዲስ ትዳር መፈረካከስ ይዟል። የሁለቱ ሀሳብ መለያየት ጎጇቸውን እያቆመው አይደለም፡ ፡ ካንቺ ወዲያ ስለልጇ ጉዳት የሚያጽናናት አንድ ሰው እንኳን ጎኗ የለም፡፡ ‹‹አይዞሽ›› የሚሏት አባቷን በሞት ካጣች ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ ዳግመኛ ለቀጠሮ ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ስትዘጋጅ አንዳች ሳንቲም ከእጇ አልነበረም፡፡ ባሏን ስትጠይቅ ፊቱን ያዞርባታል። ሌሎችን ስታማክር ጉዞዋ ለሌላ ጥቅምና በልጁ ለመለመን መሆኑን እያወሱ ያነውሯታል፡፡ ይህን ሁሉ ፈተና የያዘችው ወይዘሮ ከመንገዷ አልታቀበችም፡፡ በቤቷ የምታረባቸውን ዶሮዎች በሙሉ ሸጣ ልጇን አዝላ ዓባይን ተሻገረች፡፡

ተመልሳ ከሆስፒታሉ ሕክምናውን ስትቀጥል በውስጧ ካለው ተስፋ በቀር ማንም ጎኗ አልነበረም፡፡ የቀድሞ ባሏ ወንድምም የአቅሙን ያህል አድርጎ ወደራሱ ሥራ ሄዷል፡፡ ወይዘሮዋ ስለእሱ ያላት ምሥጋናና ክብር ለየት ይላል፡፡ እሱ ሰው ሁሉ ባነወራት ጊዜ በክፉ ቀን የደረሰላት ባለውለታዋ ነው፡፡

ካንቺ ወዲያ አሁን የአዲስ አበባን ሕይወት ለብቻዋ መጋፈጥ ይዛለች፡፡ ማንበብ መጻፍ የማትችለው ወይዘሮ በሌሎች እገዛ የተጻፈውን እያስነበበች ስትሮጥ ትውላለች። ተስፋ አለው በተባለው የሦስት ዓመት ልጇ ላይ ዕምነቷ እንደጸና ነው፡፡ ለጊዜው በሆስፒታሉ ማረፊያና ምግብ ተሰጥቷታል፡፡ በየጊዜው በሐኪሞች የታዘዘለትን ሕክምና በትኩረት ትፈጽማለች፡፡

‹እህል ውሃችን አለቀ በቃ ! ››

ከወር በኋላ ሀገሯ ስትመለስ አባወራውን ለትራንስፖርት ጥቂት እንዲያግዛት ተማጸነችው፡፡ ያለውን ይሰጠኛል በሚል ተስፋ አድርጋ ነበር፡፡ እሱ ግን በተቃራኒው ቁርጥ ሀሳቡን አሳወቃት፡፡ ከዚህ በኋላ ከእሷ ጋር ትዳር እንደማይቀጥል፣ ልጁም የሚበጅ ባለመሆኑ እንደማይፈልገው ነገራት፡፡ በዚህ መነሻ እህል ውሃቸው አልቆ ትዳራቸው ተፈታ፡፡ ወይዘሮዋ የፈረሰ ጎጇዋን በልቧ፣ የታመመ ልጇን በጀርባዋ አዝላ ዳግም ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተመለሰች፡፡

ቁጭ ብላ በተከዘች ቁጥር ባሏ በገዛ ልጁ ላይ የተናገረውን ታብሰለስላለች፡፡ በጊዜው ልጁ የገንዘባችን መጨረሻ፣ የጉልበታችን ማድከሚያ ነው ይላት ነበር፡፡ ለእነሱ ስለማይበጅም እንደ ዕቃ አውጥታ እንድትጥለው ሲያሳስባትም ቆይቷል፡፡ እሷ ግን ‹‹ልጄን አልጥልም፣ በሕይወት እስካለ አስታምመዋለሁ ከሞተ ደግሞ እቀበረዋለሁ›› በሚል አቋም ቤት ትዳሯን ፈታለች፡፡ አራት ሴት ልጆቿን በትናለች፡፡ እንዲህ በማድረጓ ደግሞ ተቆጭታ፣ ተጸጽታ አታውቅም፡፡

‹‹አዲስ መዝገብ›› ስትል የሰየመችውን የስለት ልጇን ጠጋ ብዬ አስተዋልኩት፡፡ መልኩ በእጅጉ ያምራል። ለመንካት የሚያሳሱ እጆቹን በጥንቃቄ ዳሰስኳቸው። ይለሰልሳሉ፡፡ በወጉ ግን እየሠሩ አይደለም፡፡ ወገቡና አንገቱ አይንቀሳቀስም። እናት ባሻት አቅጣጫ ስታዞረው እንዳለችው ይሆናል፡፡ ሁኔታው በእጅጉ ውስጥን የሚፈትን፣ አንጀትን የሚበላ ነው። ሕጻን አዲስ እንደ ዕድሜ እኩዮቹ አያለቅስም፣ አይረብሽም፣ አይስቅም፡፡

እናቱ ለማስተኛት፣ ለማዘልና ለማቀፍ ተመችቷት አያውቅም። ገና በእጇ ሲገባ እንደወረቀት እጥፍጥፍ ይልባታል፡፡ እሷም ሆነች እሱ ተቀምጠው አያውቁም፡ ፡ ምግብ በፈለገ ጊዜ አንጀቱ ሲታጠፍ አይታ ያላትን ታጎርሰዋለች። በደመነፍስ እንደማላመጥ ብሎ ከአፉ ደጃፍ ይተወዋል፡፡ በእሷ እገዛ እንደምንም ለሆዱ እንዲደርስ ታደርጋለች፡፡

የሕጻኑ ሁኔታ አስገርሞኝ በሀሳብ ተውጬ ፈዘዝኩ። ፊቴን ያየችው እናት የሚንከባለሉ ዓይኖቹን እየጠቆመች አንዳች ምልክት እንድሰጠው ጠየቀችኝ። እንዳለችኝ ለማድረግ እጆቼን በዓይኖቹ ዙሪያ ደጋግሜ አመላለስኳቸው፡፡ ዓይኖቹ እጆቼን አይተው አልተከተሉም፡፡ እንደነበሩ ናቸው፡፡ ደነገጥኩ፡፡ ሁኔታውን በዝርዝር ከመጠየቄ በፊት እናት ግልጹን ነገረችኝ፡፡ ሕጻኑ ሲወለድ አንስቶ እስካዛሬ ድረስ ሁለቱም ዓይኖቹ አይተውለት አያውቁም፡፡ እውነቱን ከእሷ ሳውቀው ደግሞ ይበልጥ ውስጤ ተረበሸ፡፡ እሷ ግን ተስፋ አልቆረጠችም። የዓይኑ ሕክምና በምኒሊክ ሆስፒታል ሐኪሞች እየታየለት መሆኑን ነገረችኝ፡፡ ተስፋዋ ልቤን ሞላው፣ ጥንካሬዋ አበረታኝ።

ልጅን ያለ …

አራት ልጆቿ በሕጻኑ ሕመም ምክንያት ከአንድ ቤት አልኖሩም፡፡ እናት ጎጆዋን ዘግታ ከወጣች ወዲህ ኑሯቸው በተለያየ ዓለም ሆኗል፡፡ አስቀድማ እነሱን ማስተማሯ በጅቷታል፡፡ ትልቋ ልጇ የጤና ባለሙያ ሆናለች፡፡ ሁለተኛዋ አስራ ሁለተኛን ጨርሳ አዲስ አበባ ሰው ቤት ተቀጥራለች። ‹ሌላዋ ደግሞ እዛው ሉማሜ ተቀምጣ የእናቷን መምጣት እየጠበቀች ነው፡፡ በደረጃ ታልፍ የነበረችው የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ደግሞ ትምህርቷን አቋርጣ ከእናቷ ጋር መንከራተት ይዛለች፡፡

እኔና ወይዘሮዋ የተገናኘነው ሆፕ.ኤስ.ኤች በተባለው ግብረሠናይ ድርጅት ውስጥ አዲስ ዓመትን ለመቀበል በተደረገው የወላጆችን የሕጻናት ዝግጅት ላይ ነበር፡፡ ሆፕ እንደ ሕጻን አዲስ መዝገቡ ላሉ ሕጻናትና ወላጆቻቸው ድጋፍ፣ ምክርና ሕክምና የሚሰጥ ተቋም ነው፡፡

ወይዘሮ ካንቺ ወዲያ ልጁን ለሕክምና ካገሯ ይዛ በወጣችበት አጋጣሚ በአካባቢው የሠላም እጦት ምክንያት መንገድ በመዘጋቱ የዚህ ድርጅት እንግዳ ሆናለች፡፡ ዛሬም በሀሳቧ የተዘጋ ጎጆዋ የተበተኑ ልጆቿ ይታዩዋታል፡፡ ዘወትር አንገቷን ደፍታ መንገዷን ታስባለች፡፡

ብዙ የተባለችበት ልጇ አልዳነላትም፡፡ ዛሬም ከሕመሙ ጋር ቀጥሏል፡፡‹‹ ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች›› እንዲሉ ሆኖባት ወይዘሮዋ ስለትንሹ ፍሬዋ ብዙ ዋጋ ከፍላለች፡፡ እንዲያም ሆኖ ነገን በተስፋ እየጠበቀች ነው፡ ፡ መልካም ልቦች ያላቸውን ካገኘች፣ ለትራንስፖርት አታጣም፡፡ ሀገሯ ሠላም ሆኖ መንገዱ ከተከፈተ ለቤቷ ትበቃለች፤ ለልጆቿ ትደርሳለች መንፈሰ ብርቱዋ ወይዘሮ ካንቺ ወዲያ ዘውዱ፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You