ከኢትዮጵያ አጠቃላይ በጀቷ ውስጥ ዓመታዊ የግብር ገቢዋ የሚሸፍነው 60 በመቶውን ብቻ ነው። የተቀረው በጀት በዋናነት ከብድርና እርዳታ ይሰበሰባል። ይህን ታሪክ በመቀየር እንደ አደጉ ሀገራት ሁሉ አብዛኛው የልማት ገንዘብ ከግብር እንዲገኝ ደግሞ የገቢዎች ሚኒስቴር የሪፎርም ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል። በታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም ግዴታዬን እወጣለሁ መብቴን እጠይቃለሁ በሚል መሪ ሃሳብ የተጀመረው የግብር ንቅናቄ ደግሞ ከፍተኛ መጠን ያለው የግብር ክፍያ እንዲገኝ አግዟል።
በወይዘሮ አዳነች አቤቤ የሚመራው የገቢዎች ሚኒስቴር ሰፊ የግብር አሰባሰብ ዘመቻ በማካሄድ በ2012 የበጀት ዓመት ስድስት ወራት ብቻ 127 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ሰብስቧል። ይህም ከእቅዱ ጋር ሲነጻጸር ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የተገኘበት ነው። የወቅቱ የተቋሙ ስኬት ደግሞ ያለባለሃብቱ እና ያለሃቀኛ ግብር ከፋዮች ተሳትፎ እንዳልመጣ በመታመኑ ለተመረጡ ግብር ከፋዮች የ«እናመሰግናለን» ግብዣ ከትናንት በስቲያ ተደርጓል።
የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ ሙዚየም የመናፈሻ ስፍራ ላይ በተዘጋጀው የእናመሰግናለን ግብዣ መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው፤ «ለእናንተ ግብረ ክፍያ እቅዳችንን ልናሳካ፣ ለሃገራችንም ልማት የሚውል ገንዘብ ልናገኝ አንችልም» በማለት ታዳሚውን አመሰገኑ። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከዚህ የተሻለ ውጤት እንዲገኝ የ10 ዓመት መሪ እቅድ ማዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ በእቅዱም መሰረት በ2022 ዓ.ም ኢትዮጵያ 3ነጥብ 8 ትሪሊዮን ብር ግብር እንደምትሰበስብ ግብ መጣሉንም ያመለክታሉ።
ለዚህ ሀገራዊ ፋይዳው ለጎላ እቅድ የግብር ከፋዩ ሀቀኛ ሥራ ከፍተኛ ድርሻ ስላለው በቀጣይም የውይይት መድረክ መዘጋጀቱን ይጠቁማሉ። ለግብር መጠኑ ማደግ የሚከናወኑ የአሰራር ማሻሻያዎች፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማሳደግ እና የህግ ማዕቀፎች እንደሚቀጥሉ የሚናገሩት ወይዘሮ አዳነች፤ ከዚህ በዘለለ ግን ህጋዊዎችን የማመስገኑና የማበረታታቱ ተግባር እንዲሁም ደግሞ ህገወጦችን የማስተካከሉ ተግባር እንደሚቀጥል ያስረዳሉ። በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 518 ድርጅቶች ወደ ግብር ክፍያ ስርዓቱ እንደገቡ መደረጉ እና በስድስት ወራት ውስጥ 1ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ ምርቶችን መያዛቸውን በመግለጽ፤ ህጋዊን ማክበር ህገወጥን የማረቅ ሥራ የማይቋረጥ ሥራ መሆኑን ይገልጻሉ።
በመርሐ ግብሩ ላይ ሱር ኮንስትራክሽንን በመወከል የተገኙት ኢንጂነር ታደሰ የማነ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ግብር የሚከፈለው ለሃገር ልማት በመሆኑ ለከፋዩ ኩራት ነው። በዚህ መርህ መሰረት በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ግብር የሚከፍለው ሱር ኮንስትራክሽን በስድስት ወራት ብቻ ከ909 ሚሊዮን ብር በላይ ግብር ከፍሏል። በቀጣይም ለሀገር ልማት የሚውለውን ግብር በሃቀኝነት የመክፈሉ ሂደት ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።
ሁሉንም ግብር ከፋይ በሃቀኝነት እንዲከፍል ለማድረግ ሰፊ ሀገራዊ ሥራ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። ይሁንና በትክክለኛው መንገድ የሚከፍሉትንም ጨምሮ ተጨማሪ አምጡ እየተባለ ከህግ ውጪ የሚጠየቁበት አሰራር መስተካከል እንደሚገባው ያስገነዝባሉ። ከፋዩን በሃቀኝነት ግብር ሰብሳቢው ተቋምም በህጋዊ መንገድ በጋራ መስራታቸውን ከቀጠሉ ግን ለሃገርም የሚበጅ ውጤት መመዝገቡ አይቀሬ መሆኑንም ያመለክታሉ።
የቶታል ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ቲቦ ሌሱዩኧር ደግሞ 160 የቶታል ጋዝ ማደያ ጣቢያዎች በኢትዮጵያ መኖራቸውን ይናገራሉ። እያንዳንዱ የማደያ ባለቤት በስራው ላይ ህጋዊ መንገድ እንዲከተል እና ግብር በተገቢው መንገድ እንዲከፍል እገዛ እንደሚደረግ ያስረዳሉ። የትኛውም የበለጸገ ሃገር የሚሰበስበውን የግብር መጠን በማሳደግ ለሰፋፊ የህብረተሰብ ጥቅም የሚውሉ ፕሮጀክቶች ላይ ያውለዋል። በኢትዮጵያም የሚሰበሰበው ግብር ባለሃብቱን ጨምሮ ለዜጎች የሚውሉ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት የሚውል በመሆኑ ዞሮዞሮ ኢንቨስተሩም የሚጠቀምበት እድል እንዳለው ያብራራሉ።
ወይዘሮ ሀሊና በለጠ በበኩላቸው እንዳስረዱት፤ የህሊና ገንቢ ምግቦች በዓመት 23 ሚሊዮን ብር ግብር ይከፍላል። የድርጅታቸውን ምርቶች በሚሸጡበት ወቅት ሸማቾችም ለማህበራዊ ኃላፊነት የበኩላቸውን ይወጣሉ። ይህም አንድ ምርት በገዙ ቁጥር ለኢትዮጵያ የሚከፈለው ግብር ስለሚጨምር የምርት መገበያየቱ ብቻ ሳይሆን ከዚያም ያለፈ ማህበራዊ ኃላፊነት መወጣታቸውን እንዲያውቁት ይደረጋል። ዛሬም ነገም በሀቀኝነት ግብር መክፈል ደግሞ ክብርም፤ ኩራትም ነውና ማንኛውም ሀገር ወዳድ ሰው ይህን ተግባር ሊያስተጓጉል አይገባም።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 14/2012
ጌትነት ተስፋማርያም