አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች ለሚኖሩ እና የላብራቶሪ አገልግሎት የመጠቀም እድል ላላገኙ ህጻናት የሚሆን ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪ ወደ ሥራ ሊገባ ነው።
«ስቲም» የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ ኢንጂነሪንግ እና ሒሳብ ትምህርቶች ተቋም ዋና ኃላፊ ወይዘሮ ቅድስት ገብረአምላክ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በቀጣይ ሳምንት ከኦሮሚያ ክልል የሚነሳው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የተማሪዎች ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪ በዓመት ለ13 ሺ ተማሪዎች አገልግሎት ይሰጣል። ላብራቶሪው በተለይ የሳይንስ ትምህርቶች ላይ ህጻናት የተግባር ዕውቀት እንዲያገኙ ስለሚረዳ ለትምህርት ጥራት መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።
እንደ ወይዘሮ ቅድስት ገለጻ፤ በገጠራማ አካባቢ የሚገኙ ህጻናት ተማሪዎች ላብራቶሪው በአካባቢያቸው በሚሄድበት ወቅት በተደራጀ መልኩ አገልግሎቱን አግኝተው በንድፈ ሃሳብ ብቻ የተማሩትን ዕውቀት በተግባር እንዲፈትሹ ይደረጋል። ለዚህም እንዲረዳ ከአስፈላጊ ቁሳቁስ በተጨማሪ ላብራቶሪው በሚንቀሳቀስበት ቦታ ሁሉ አብረው የሚጓዙና ለተማሪዎች ሙያዊ እገዛ የሚሰጡ ሁለት ከፍተኛ ኤክስፐርቶች ተመድበዋል።
የስቲም ተቋም ቺፍ ቴክኖሎጂ ኦፊሰር አቶ ኢዩኤል ኃይሉ እንደገለጹት፤ የመጀመሪያው ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪ ዘመናዊ የጭነት ተሽከርካሪ ላይ በተዘጋጀ ተጎታች ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሳል። ላብራቶሪው በውስጡ የስሪ ዲ ፕሪንተር፣ የፊዚክስ እና የኤሌክትሮኒክስ ዘመናዊ መሳሪያዎችን እና ሙሉ የላብራቶሪ እቃዎች እንዲሟሉለት ተደርጓል። የላብራቶሪውን ሙሉ ግብዓቱን ለማሟላት ሁለት ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል።
ላብራቶሪው በሚጓዝባቸው አካባቢዎች ሁሉ ለጥገና የሚሆን እና ሌሎች አስፈላጊ ወጪዎች እንደሚሟሉለት የገለጹት አቶ ኢዩኤል፤ የላብራቶሪው ኤክስፐርቶች ደመወዝ እና የነዳጅ ወጪን ጨምሮ ለተለያዩ ጉዳዮች በዓመት አንድ ነጥብ 5ሚሊዮን ብር እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች ለሚገኙ ተማሪዎች የሚሆን የላብራቶሪ እጥረት በመኖሩ በቀጣይ ተማሪዎቹን በተግባር ለማስተማር ከ100 በላይ ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ፍላጎት መኖሩን ጠቅሰዋል። ለዚህ ደግሞ መንግሥት እና የገንዘብ ድጋፍ የሚሰጡ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
እንደ ስቲም የሳይንስ፣ቴክኖሎጂ ኢንጂነሪንግ እና ሒሳብ ትምህርቶች ተቋም መረጃ፤ ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪው ከቢሾፍቱ ከተነሳ በኋላ በሚያርፍባቸው አካባቢዎቸ ሁሉ በአንድ ጊዜ እስከ ስልሳ ህጻናት የቤተሙከራ አገልግሎት እንደሚሰጥ ታቅዷል። የተማሪዎች ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪው በየካቲት ወር አጋማሽ በኋላ በቢሾፍቱ ከተማ ፈቃ ሳይንስ ማዕከል በይፋ ተመርቆ ሥራ ይጀምራል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 14/2012
ጌትነት ተስፋማርያም