የሰባቱ ሐይቆች ከተማ ቢሾፍቱ ገና ከንጋት የፀሐይ መውጫ ወቅት ጀምሮ ደምቃለች። ፈረሰኞች የኢትዮጵያን ባንዲራ ይዘዋል፤ በርካታ ወጣቶች ደግሞ ዶክተር አብይ ከጎንህ ነን የሚል ጽሁፍ የታተመበት ነጭ ካናቴራ ለብሰዋል። በቡድን በቡድን ሆነው የፍቅር እና የሰላም መልዕክት እያስተላለፉ ወደ ከተማዋ ስታዲየም የሚተሙትም በርካታ ናቸው። ይህ ሁነት ትናንትና «ዶክተር አብይ እና ብልጽግና ምርጫዎቼ ናቸው» በሚል መሪ ሃሳብ በኦሮሚያ ክልል በቢሾፍቱ ከተማና በዙሪያዋ የሚገኙ ነዋሪዎች ያካሄዱት የድጋፍ ሰልፍ አካል ነው።
በድጋፍ ሰልፉ ወቅት ከ15ሺ በላይ የሚሆኑ የቢሾፍቱና አካባቢዋ ነዋሪዎች እና ፈረሰኞች ከዶክተር አብይ ጎን መቆማቸውን የሚያመላክቱ መፈክሮችና ካናቴራ ለብሰው በከተማዋ ስታዲየም ተገኝተዋል። የተለያዩ ክልሎች ፐሬዚዳንቶች እና የኦሮሚያ አባገዳ ባንዲራዎች ደግሞ እዚያም እዚህም ከኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ጋር ይታያሉ።
በሰልፉ ላይ የተካፈሉት የሃገር ሽማግሌ አቶ ከበደ ቱሉ ዘንባባ ይዘው በስታዲየሙ ተገኝተዋል። ዶክተር አብይ አህመድ የሰላም መሪ በመሆናቸው የልምላሜ እና የደስታ ምልክት የሆነውን ዘንባባ ይዘው ከቤታቸው መውጣታቸውን ይናገራሉ። ሰልፉም ከአፈና እና እስር በተላቀቀ ሁኔታ በሰላምና በፍቅር ለመምራት የሚያደርጉት ጥረት የሚደገፍ በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ይገልፃሉ። «ህዝቡም የፍቅርና የአንድነት አራማጅ የሆኑትን መሪውን ደግፎ ስታዲየም መውጣቱ በቀጣይም ለእርሳቸው የሚሰጠውን ድጋፍ ያሳያል»ይላሉ። ፍቅር ለሰጠ የፍቅር ምላሽ መስጠት ባህላችን አንዱ አካል መሆኑን ያስረዳሉ።
የድጋፍ ሰልፉ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ በጨዋ ደንብ የተከናወነ እና በሰላማዊ መንገድ የተሰናዳ መሆኑን ያደነቁት አቶ ከበደ፤ ይህ የሚበረታታ ልምድ በማስቀጠል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሚያከናውኑት የጽዳት እና በመልካም ስነምግባር ትውልድን የመቅረጽ ሂደት ውስጥ የእራስን አሻራ ማሳረፍ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።
ሌላዋ በሰልፉ የተሳተፉት የቢሾፍቱ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሐቢባ አሊ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ለዶክተር አብይ ለህዝብ ያሳየው ፍቅር ምላሽ በማግኘቱ አሁን ደግሞ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ፍቅሩን እየመለሰለት ይገኛል። ነገን በደስታ እና በፍቅር ለመኖር አሁን ላይ ፍቅር ያሳዩንን መሪ መደገፍ ብልህነት ነው። ይህ ድጋፍ በቀጣይ ጊዜያት ደግሞ በሰልፍ ብቻ ሳይሆን ሁሉም በየሙያው ጠንካራ ሥራ በመስራት የበለጠ አጋር መሆኑን የሚያሳይበት መሆን ይኖርበታል።
ማንኛውም የከተማዋ ነዋሪ ግጭት እና ረብሻ ለማስነሳት የሚሞክሩትን ሳይሆን እንደ ዶክተር አብይ እባካቸሁ ተረጋጉ እያሉ የሚሰብኩትን የሚፈልግ መሆኑን ይገልፃሉ። በመሆኑም የወቅቱን የኢትዮጵያ መሪ ደግፎ ከጎን መቆም ጥቅሙ ለእራስም ለሀገርም ነውና፤ የቢሾፍቱ አካባቢ ህዝብ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች የሚታየው ድጋፍ ይበል የሚያሰኝ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
በድጋፍ ሰልፉ ወቅት የተገኙት የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ሽፈራው እንደተናገሩት፤ እውነተኛ ፌዴራሊስት የሆነውን ብልጽግናን እና የአባገዳ ልጅ የሆኑትን ዶክተር አብይን መደገፍ ለእራስ ክብር እና ዋጋ መስጠት ነው። ህበረተሰቡም የድጋፍ ሰልፉን ማካሄዱ በመንግሥት በኩል እየተከናወኑ ለሚገኙ የልማት ስራዎች መጠናከር የሞራል ስንቅ ይሆናል።
በኢትዮጵያ የታየው የፖለቲካ ምህዳር መስፋት እና ዘርፈ ብዙ የልማት ጎዳናዎችን የመክፈት ጅማሮ የዶክተር አብይ እና የብልጽግና ውጤት መሆኑን ከንቲባዋ ይገልፃሉ። ዶከተር አቢይ የዜሮ ድምር ፖለቲካን በማስቀረት በመተባበር እና ህብረት ላይ የተመሰረተውን የመደመር እሳቤ ነው
የሚከተሉት የሚሉት ወይዘሮ አለምፃሃይ ህብረተሰቡም ይህን ሃሳብ ተረድቶ ለመሪው ያለውን ድጋፍ በማሳየት በቀጣይ ደግሞ የተሻለ ውጤትን ለማስመዝገብ ዋነኛው ተዋናይ መሆኑን ማስመስከሩን ያስረዳሉ። «በእራሱ ተነሳሽነት የድጋፍ ሰልፉን በማስተባበር እና በሰላም በመከወን ጨዋነቱን ላሳየው ህዝብም ምስጋና ይገባዋል» በማለትም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 14/2012
ጌትነት ተስፋማርያም