ፍቼ ከተማ ከማለዳው ጀምሮ እንግዶቿን በማስተናገድ ላይ ነች። በፈረስና በእግር ወደ ከተማዋ የሚተሙት የአካባቢው ነዋሪዎች በዘፈንና በጭፈራ ታጅበው ጎዳናዎች ላይ ይርመሰመሳሉ። ባጃጆች፣ ሞተር ብስክሌቶችና ተሽከርካሪዎች መብራት እያበሩና የጡሩንባ ድምጽ እያሰሙ ሰልፈኛውን አጅበውታል። ከተለያየ የዞኑ ወረዳዎች በትልልቅ መኪኖች ተሳፍረው ወደ ከተማዋ የሚገቡት የሰልፉ ታዳሚዎችም መፈክሮችን እያሰሙ የክልሉንና የፌዴራል ሰንደቅ ዓላማዎችን በማውለብለብ የድጋፍ ሰልፉን ተቀላቅለዋል። ፍቼ ከተማ ከአፍ እስከ ገደፏ ጢም ብላለች። በተለይም ሰልፈኞቹ የታደሙበት ስታዲየም ጠጠር መጣያ የለውም። የወጣቶች ጭፈራ፣ የእናቶች እልልታ፣ የአባቶች ምስጋናና ምርቃት ሲዘንብ አርፍዷል።
ለዚህ ሁሉ ትዕይንት ምክንያቱ ለዶክተር አብይ አህመድ ድጋፍ ለመስጠት በማሰብ ነው። የድጋፍ ሰልፈኞቹ ካስተላለፏቸው መልዕክቶች ‹‹አቢቹን ለኢትዮጵያ የሰጠ ፈጣሪ ይመስገን፣ በመደመር ፍልስፍና ህብረ ብሄራዊነትን እንገነባለን ፣ብልጽግና ለሁሉም- ሁሉም ለብልጽግና›› የሚሉ ይገኙበታል።
አቶ አምዴ ቶሎሳ የድጋፍ ሰልፉ ላይ ከታደሙ የደገም ወረዳ ነዋሪዎች አንዱ ናቸው። ከሚኖሩበት ወረዳ ብዙ ኪሎ ሜትር አቋርጠው የመጡት ይህንን ዓለም የመሰከረለትን የሰላም ጀግና ለመደገፍ መሆኑን ይገልፃሉ ። «ዶክተር አብይ ኢትዮጵያን ከጨለማ ወጥታ የብርሃንን መንገድ እንድትከተል የሚጥር መሪ ነው» ይላሉ። ዶክተር አብይ በሀሳብ ልዕልና የሚያምን እንጂ አለመግባባቶችን በጠመንጃ አፈሙዝ ለመፍታት የሚሞክሩ መሪ አለመሆናቸውን ያስረዳል። «ወደ ስልጣን የመጣውም ግንባር ለግንባር ተፋጦ በመሞገትና ሃሳብን በሃሳብ በማሸነፍ ነው። ለዚህም ነው የምደግፈው» በማለትም ያብራራል።
«እኔ የጀነራል ታደሰ ብሩ ልጅ ነኝ ። ጀነራል ታደሰ የኦሮሞን ህዝብ አንድነት ለማጠናከር ሲጥር የነበረ ሰው ነው። ዶክተር አብይም እንዲሁ አይነት አስተሳሰብ ያለው ነው» በማለትም ያክላል። ዕድገት፣ ሰላምና ብልጽግናን የሚናፍቅ መሪ በመሆናቸውም እንደሚደግፋቸው ያስረዳሉ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካም ጭምር ነው። እሳቸውን መርዳት ኢትዮጵያን ከገባችበት ቀውስ የሚያወጣ ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ እረዳለሁ ይላሉ፡
ወይዘሮ ሸጊቱ መኮንን ሌላዋ አዲስ ዘመን ያነጋገራት የፍቼ ከተማ 04 ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ዶክተር አብይ በሀገሪቱ ላይ እያሳዩት ባለው ለውጥ በጣም ደስተኛ ናቸው። የዴሞክራሲን ስርዓትን፣ እኩልነትን፣ አንድነትን በሀገሪቱ ለማስፈን እያደረገ ያለው ጥረት የሚያኮራ መሆኑንም ይገልፃሉ። ሁሉም ህዝብ ቢደግፈው ከዚህ በላይ ሊሰራ እንደሚችል አመኔታ አሳድረዋል።
«የህግ በላይነትን በማስከበር በኩል የሚታዩ ችግሮችን በማስወገድ በየትኛውም አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች ዋስትና እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል»ይላሉ። በፍቼ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦች ያለምንም ችግር በፍቅር እንደሚኖሩ የጠቀሰችው ወይዘሮዋ ሌሎች አካባቢዎችም ከፍቼ መማር እንደሚገባቸውም ነው ያስገነዘቡት።
የድጋፍ ሰልፉን ምክንያት በማድረግ ንግግር ያደረጉት የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ብርሃኑ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የብልጽግና ፓርቲ አመራር ሰጪው ዶክተር አብይ አህመድ ፍላጎታቸው ሀገሪቱን በሁሉም ዘርፍ ማበልጸግ ነው። ይህ ማለት ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ ነው። የኢኮኖሚ ብልጽግና ሲባል ህብረተሰቡን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ማላቀቅና ኢትዮጵያ ከዓለም ተወዳዳሪ እንድትሆን ማስቻል ላይ ያለመ ነው።
የፖለቲካ ብልጽግና ሲባልም የዴሞክራሲ ተቋማትን መገንባት፣ የህዝቦችን አንድነትና እኩልነት ማረጋገጥ፣ የሰዎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበር ማስቻል፣ እውነተኛ የዴሞክራሲዊ ሥርዓትን ማስፈንን የሚመለከት መሆኑንም ያብራራሉ። በዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው ብልጽግና ፓርቲም የህዝቦችን ትስስርና አንድነት የሚያጠናክር በጋራ መስራትና መበልጸግን የሚከተል ስለሆኑም ይገልፃሉ። «ህብረ ብሄራዊ አንድነቷ የተጠበቀ ሀገር ለመመስረት የትናንት ስህተቶችን መድገም ሳይሆን ማረም እና በህዝቦች መካከል ጠንካራ ግንኙነት መመስረት ነው። አሁንም ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ከብልጽግና ፓርቲ ጎን በመቆም የተሻለች ሀገር ለመፍጠር ድጋፋችሁን አጠናክራችሁ ልጥቀጥሉ ይገባል» ብለዋል ።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ ከአሥራ ሦስት ወረዳዎችና አንድ ከተማ መስተዳድር የተውጣጡ እድምተኞች የተገኙ ሲሆን በተሰማቸው ደስታ ለብልጽግና ፓርቲ ከ20 የሚበልጡ ሰንጋዎችን፣ በጎችንና ፍየሎችን በስጦታ አበርክተዋል። የዞኑ የሙዚቃ ባንድ፣ የማርሻል አርት ትዕይንትና የፈረሰኞች ትርዒትም ለበዓሉ ልዩ ድምቀት የሰጡ ነበሩ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 14/2012
ኢያሱ መሰለ
ፎቶ፡- እዮብ ተፈሪ
Reinforced Concrete Pipes in Iraq Elite Pipe Factory offers reinforced concrete pipes that are perfect for handling high loads and severe conditions in infrastructure projects. These pipes are built with advanced reinforcement techniques to ensure durability and reliability. As one of the top manufacturers in Iraq, Elite Pipe Factory guarantees that our reinforced concrete pipes meet all necessary standards and provide exceptional performance. For more information, visit elitepipeiraq.com.