የተወለዱት ወልቃይት ውስጥ በምትገኝ አንዲት የገጠር መንደር ነው።እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ግን በአካባቢው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ምክንያት የትውልድ ቀያቸውን ለቀው እናታቸው ወደ ተወለዱበት ሽሬ እንደስላሴ ይመጣሉ። በአጎታቸው ቤት ተቀምጠው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሩ። በመቀጠልም መቐለ አፄ ዮሃንስ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታተሉ። በቀድሞ ስሙ በኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛም ገብተው በመምህርነት ስላጠኑ ጋሞ ጎፋ ተመደቡ። ይሁንና በትግራይ የተመደቡ ሌሎች መምህራን አካባቢው የጦርነት ቀጣና ነው በሚል ስጋት ለመሄድ ማንገራገራቸውን ይሰሙና ጓደኛቸውን ለውጠው በበጎ ፍቃደኝነት በተወለዱበት አካባቢ ለመስራት ተስማሙ። ጥቂት እንዳገለገሉም የደርግ መንግስት ያደርገው የነበረውን ጫና በመቃወም ህወሓትን ተቀላቀሉ።
እስከ 1979 ዓ.ም ድረስም የደርግን መንግስት ለመጣል ይደረግ በነበረው የህወሓት ትግል መሪ ተዋናይ ከነበሩት አመራሮች አንዱ ሆነው ዋጋ ከፈሉ። ይሁንና የድርጅቱ አካሄድ ሲነሳ ከነበረው መርህ አንፃር እያፈነገጠ መምጣቱን ሲገነዘቡ በህመም ሰበብ ትግሉንም፤ አገርም ለቀው ወጡ። ለህክምና ከሄዱባት ጎረቤት አገር ሱዳን ለጥቂት ወራት ከቆዩ በኋላ በታላቅ ወንድማቸው ድጋፍ አሜሪካ ገቡ። በአገረ አሜሪካም እንደ እሳቸው ሁሉ ባለመግባባት ትግሉን ጥለው ከወጡ የትግል አጋሮቻቸው ጋር በመሆን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ትዴፓ/ መሰረቱ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በውጭ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወደአገራቸው እንዲገቡ በአቀረበላቸው ጥሪ መሰረትም እሳቸውና ጓደኞቻቸው ከ32 ዓመታት በኋላ የተወለዱበትን ምድር መርገጥ ቻሉ። አሁን ከህዝባቸው መሃል ሆነው የመሰረቱት ፓርቲ በምርጫው ብርቱ ተወዳደሪ ይሆን ዘንድ ከኋላ ደጀን ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ከዛሬው የዘመን እንግዳችን ከአቶ መኮንን ዘለለው ጋር በተለያዩ ፖለቲካዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገናል።እንደሚከተለው እናቀርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- በህወሓት የትጥቅ ትግል ውስጥ የነበረዎትን ቆይታ ምን ይመስል እንደነበር ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ መኮንን፡- ሁሉም እንደሚያውቀው የነበረውን ስርዓት ለመገርሰስ እኔም ሆንኩ መላው የትግራይ ህዝብ በስሜትና በወኔ ነበር ሲታገል የነበረው። በተለይም ደግሞ ትግሉ በተጀመረባቸው ዓመታት ጭቁኑን የትግራይ ህዝብ ነፃ ከማውጣት ባለፈ ከመላው የአገራችንን ህዝብ ጋር በመተባበር አንዲት ኢትዮጵያ የመመስረት አላማ ሰንቀን በትጋት ነበር ስንታገል የነበረው። በተለይ እኔ በወቅቱ በኤርትራ ይደረግ የነበረው እንቅስቃሴ ጉዳይ ጊዝያዊ ግጭት እንጂ ወደ መገንጠል ያደረስናል ብዬ አላምንም ነበር። አብረን ታግለን ተመልሰን አብረን እንደ ቀድሟችን አንድ እንሆናለን የሚል ግምት ነበረኝ። ህወሓትም በስትራቴጂው በእኩልነትና በአንድነት የበለፀገች አንዲት አገር የመፍጠር አጀንዳ ነበረው። ልክ እንደዛሬው ሳይሆን የብሄር ትግልን ሰራዊት ለማሰበሳብ እንደ ታክቲክ ከተጠቀምንበት በኋላ ተመልሰን አንዲት አገር እንፈጥራለን የሚል ህልም ነበር የነበረን። እንዳሰብነው በወቅቱ ታክቲኩ ሰርቷል፤ ትልቅ ሰራዊትም መፍጠር ችለናል። በተቃራኒው እንደኛ ሲታገል የነበረው ኢህአፓ ያንን ያክል ሰራዊት መፍጠር አልቻለም ነበር።
ሲውል ሲያድር ግን የተነሳንበት የስትራቴጂውን አላማ ካስፈፀምን በኋላ መንሸራተት መጣ። በተለይም የኤርትራ የመገንጠሉ ሃሳብ እየጎለበተ ሄደ። ይሁንና ድርጅቱ ሲመሰረት እስከመጨረሻው የአገሪቱን አንድነት አስጠብቀን እንቀጥላለን የሚል ነበር። ይህንን አጀንዳ ሲያርምድ የነበረው የተማረው ሃይልም በጦርነቱ እያለቀ ሄደና የብሄርተኝነቱ ስሜት እየጎለበተ መጣ። በኋላም አጠቃላይ አቅጣጫው ቆፍጣና ወታደር የሚያደርግ እንጂ በእውቀት የተመራ ወደአለመሆን ተቀየረ። መሪዎቻችንም ስልጣን እያካባቱ መጡ። የፖለቲካ ጥያቄ የሚቀርቡ ሃይሎችም ቀስ በቀስ ይገለሉ ጀመር። አንዳንዶቹም ድርጅቱን ጥለው ወጡ። ከዚያም ህወሓትን ለማረምና ለማስተካከል አዳጋች የሆነበት ደረጃ ደረሰ። ከዚያ በኋላ የስትራቴጂው አላማ ተቀየረ። እኔና አንዳንዶቹ ታጋዮች ስለኢትዮጵያ አንድነት የምናራምድ በመሆኑ ከጊዜው ጋር የማይሄዱ የሚሉ ብዙ ቅፅል ስሞች ይወጣልን ነበር።
አዲስ ዘመን፡- የእርስዎና የሌሎች አባላት ዋነኛ ልዩነት ምን ነበር?
አቶ መኮንን፡- እኛ በብሄር ህዝቡን ካንቀሳቀስን በኋላ መታገያ እንጂ የፖለቲካ መስመር መሆን የለበትም የሚል አቋም ነበረን። እርግጥ ነው፤ በወቅቱ የብሄር ጭቆና ነበር። ይሁንና ነፃነትና እኩልነት ከተረጋገጠ በኋላ ኢትዮጵያዊ አንድነቱን ማረጋገጥ ይገባል የሚል ነበር የእኛ መከራከሪያ። የትግራይ ህዝብ ፀረ ኢትዮጵያ ስብከት ይሰበክ ነበር። ይህ አስፈላጊ አልነበረም። ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ ወደደም፤ ጠላም ኢትዮጵያዊ ነው። የሚኖረውም የአገሪቱ ህልውና ሲረጋገጥ ነው። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ እንደ ኤርትራውያኖቹ እኛ ኢትዮጵያውያን አይደለንም ብለን መንቀሳቀስ አልቻልንም። እንዳልኩሽ ግን እውነት ነው የትግራይ ህዝብን በብሄሩ ማደራጀታችንን ጠቅሞናል። ይሁንና ፀረ ኢትዮጵያ አድርጎ ማስቀጠሉ ትግሉ አቅጣ ጫውን እንደሳተ ስለገባኝ በ1979 ዓ.ም አካባቢ ድርጅቱን ለቅቄ ወጣሁ።
አዲስ ዘመን፡- ያለማንም አስገዳጅነት በገዛ ፈቃድዎ ማለት ነው?
አቶ መኮንን፡- እንደዛ ለማለት በጣም አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም በወቅቱ ዝም ብሎ ከትግል ማፈግፈግ ከባድ ነበር። የምሄድበትም ሌላ አማራጭ አልነበረኝም። ወደ ደርግ ልመጣ አልችልም፤ ወደ ኤርትራም መቀላቀልም ከባድ ነው። ስለዚህ አይኔን ህክምና ስለሚያስፈልገኝ ወደ ሱዳን ሄጄ ልታከም የሚል ጥያቄ አቀረብኩ።በግልፅ መልቀቁ በወቅቱ ከባድ ነበር። በስብሰባ አንድ ጥያቄ ብታቀርቢ ‹‹መነሻው ምንድነው? ከየት አመጣሽው?›› ብለው ነው የሚያፋጥጡሽ። ከዚያ በኋላ በሰላዮች መከታተል መጣ። ሰለህክምና ሁኔታዬ ስጠይቅ መነፅር ከውጭ ይመጣልሃል አርፈህ ተቀመጥ ተባልኩ። ይሁንና የህክምና ክፍሉ ውጭ ሄጄ መታከም እንዳለብኝ አመልክተው ነበር። ግን ተቀባይነት ሳያገኝ ሶስት ዓመት ጠበቀኩኝ። በእነዚያ ሶስት
አመታት ትግሉን በይፋ ባልለቅም፤ ከብዙ
ነገር ታግጄ ነበር።
ከሶስት ዓመት በኋላ «የቁም እስር ላይ ከሆንኩኝ በግልፅ ይነገረኝ» ብዬ አመለከትኩኝ። ሌሎች እየታከሙ እየመጡ ለምን እኔ እከለከላለሁኝ አልኩ። ይህንን ስል «ማሰር እኮ እንችላለን» ብለው ተቆጡኝ። ከብዙ ክርክር በኋላ ሱዳን ሄጄ እንድታከም ተፈቀደልኝ። በሱዳንም ህክምና ተደረገልኝና መነፅር ታዘዘልኝ። ይሁንና ተጨማሪ ህክምና ወደ ሌላ አገር ሄጄ ማድረግ እንደሚገባኝ ተነገረኝ። በወቅቱ ደግሞ ኢህአፓ ውስጥ የነበረው ወንድሜም ትግሉን ትቶ አሜሪካ ገብቶ ነበርና ከድርጅቱ ወጥቼ ሱዳን መግባቴን ነገርኩት። እሱም ወዲያውኑ ገንዘብ ላከልኝ። በነገራችን ላይ ሱዳን ሆስፒታል ውስጥ ተኝቼ የተቃውሞ ሃሳቤን በግልፅ መናገር ጀምሬ ነበር። ይህንን ተከትሎም ከሆስፒታሉ ምግብ ተከለከልኩኝ። በወቅቱ ገብሩ አስራት ጋር ተጨቃጨቅን። «አንተ ከሃዲ ነህ፤ ውስጥ እያለህም ታስቸግር ነበር» አለኝ። እኔ ግን ይሄ ድርጅት መንገዱን ስቷል በሚል አቋሜ ፀናሁ። ይሄ ድርጅት እንኳ ለትግራይ ህዝብ ሊሆን ለኢትዮጵያም ጠንቅ ነው የሚሆነው አልኩት። «አንተ አድሃሪ ነህ» አለኝ። በኋላም ስዬና መለስ ከአሜሪካ ወደ ሱዳን በመጡበት ጊዜ አስጠርተውኝ አነጋገሩኝ። «ድል አናደርግም ብለህ ተስፋ ቆርጠህ ነው ወይ?» ብለው ጠየቁኝ። እኔ ግን ድርጅቱ እንደሚያሸንፍ ጥርጥር እንደሌለኝ ነገር ግን ትግሉን ስቀላቀል የነበረው አላማ ባለመቀጠሉ ድርጅቱን ለመልቀቅ መገደዴን ነገርኳቸው። በሰራዊት አሸንፈን አዲስ አበባ ልንገባ እንችላለን ነገር ግን ይዘናት የወጣናትን አላማ ይዘን አዲስ አበባ አንገባም አልኳቸው። «ህወሓት ፀረ ዲሞክራሲ ሆኗል እያልክ ነው?» አሉኝና እየሳቁ ጥለውኝ ሄዱ። ከዚያም በኋላ አላየኋቸውም። እኔም በወንድሜ እርዳታ አሜሪካ ገባሁ።
አዲስ ዘመን፡- አሜሪካ ከገቡ በኋላ ትግሉን እርግፍ አድርገው ተዉት?
አቶ መኮንን፡- ከአገሬ ከወጣሁ በጠቅላላው ወደ 33 ዓመት አካባቢ ይሆነኛል። ከአገሬ ከወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ ትግሌን አላቋረጥኩም። በ1987 ዓ.ም አካባቢ ከነአረጋዊ በርሄ ጋር የራሳችንን ፓርቲ አቋቋምን። በነገራችን ላይ አሁንም ድረስ ቢሆን የትግራይ ህዝብ ደርግን ያህል ጠንካራ መንግስት ለማሸነፍ ያደረገውን ትግል እኮራባታለሁ። በወቅቱ ለውጥም መጥቷል። ይሄ ለውጥ ግን የትግራይ ህዝብ ካፈሰሰው ደም አኳያ ስንመዝነው ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በተለይ ወደ ትግል የወጣንባት የፍትህ ጥያቄ ዛሬም በትግራይ አልተመለሰም። ለነገሩ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ሁልጊዜ በመንግስት እንደተነጠቀ ነው። ደርግ የተማሪዎችን እንቅስቃሴ ተጠቅሞ አምባገነን ሆነ፤ ህወሓትም በተመሰሳይ የትግራይ ህዝብን የትግል እንቅስቃሴ ተጠቅሞ የደረሰበት ሁኔታ ይታወቃል። አሁንም እንደዛ እንዳንሆን ስጋት አለኝ። በተለይም ደግሞ ስልጣን በተጨባጭ የህዝብ ሊሆን ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- የእርሶ አካሄድ ትክክል እንዳልሆነ ሲነቅፎት ከነበሩ የትግል አጋሮዎቾ መካከል አቶ ገብሩ አስራት አንዱ እንደነበሩ ጠቅሰውልኛል። በጊዜ ሂደት እሳቸውም በተመሳሳይ ሁኔታ ከድርጅቱ መውጣታቸውን ሲመለከቱ ምን ተሰማዎት?
አቶ መኮንን፡- እኔ በተለይም ገብሩ አስራት ያን ጊዜ ስነገርው ሰምቶኝ የእኔን መንገድ ቢከተል እመኝ ነበር። ምክንያቱም ከዚያ በኋላ ብዙ ዋጋ ከፍሎበታልና ነው። በነገራችን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የህወሓትን ስህተት በድፍረት የገለፀው አቶ አስገደ ገብረስላሴ የሚባል ብርቱ ታጋይ ነው። በመቀጠልም ገብሩ አስራት ነው። ለዚህም ብዙ ዋጋ ከፍሎበታል። እንዴት የታገልክበትን ድርጅት ትከዳለህ? እንዴትስ ይህንን ሚስጥር ታወጣለህ? ተብሎ ብዙ ተሰቃይቷል። በእኔ እምነት የህወሓት አመራሮች ትልቅ ስህተት ብዬ የማምነው የታገሉበትን እውነተኛ አላማ እውን እንዲሆን መስራት ያለመቻላቸው ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከ30 ዓመት በፊት ጥለዋት የሄዷት ኢትዮጵያ እንዴት ተቀበለችዎት?
አቶ መኮንን፡- በነገራችን ላይ መለስ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበረበት ጊዜ በሰላማዊ መንገድ አገራችን ገብተን ለመታገል ጥያቄ አቅርበን ነበር። እንደፖለቲካ ድርጅት እንዲቀበሉን ጠይቀናል፤ ግን ተቀባይነት አላገኘም። ህወሓት አምባገነን ሆኖ መቀጠል አልቻለም። አሁን የሚወድቅበት ገደል አፋፍ ላይ ደርሷል። ከኢህአዴግ የወጡት የለውጥ ሃይሎች ባመጡት ለውጥ ጥሪ ወደአገራችን መግባት ችለናል። እኛ እዚህ በመምጣታችን በጣም ደስተኞች ነን፤ እናመሰግናለን። የእኛም ዋነኛ ህልም የነበረው ውጭ ሆነን ስንታገል የነበረው እንደ ፖለቲካ ፓርቲ በአገራችን መስራት ነው። እዚህ የህዝብ አካል የሆነ ፓርቲ ሆኖ ለመቀጠል የህዝብ ፊርማ ማሰባሰቡ ብዙ ጊዜ ወስዶብናል። ይሁንና አሁን ላይ ፊርማውን አሰባስበን ጉባኤም አካሂደን ተቀባይነት አግኝተናል። እስካሁን የነበረው ትግል ይህንን ለማድረግ ነበር። ደጋፊዎችን አፍርተን ኢትዮጵያዊ የሆነ ድርጅት መስርተን መንቀሳቀስ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ማለት በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት አግኝታችኋል ማለት ነው?
አቶ መኮንን፡- በኢትዮጵያ ታሪክ ህወሓት በጣም አስቸጋሪ ድርጅት ነው፤ ስታለቅሺ ያለቅሳል፤ ስትስቂ ይስቃል።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
አቶ መኮንን፡- ይህንን የሚያደርገው ለማጭበርበር ነው። እኛን በሚመለከት ህወሓት 30 ዓመት ሙሉ በህዝቡ ላይ የፈጠረው ምስል መሰረቱ ትልቅ ነው። እሱ የፈጠራቸው፤ ህይወት የሰጣቸው፤ በእሱ የሚንቀሳቀሱ የተጣመሙ ሃይሎች አሉ። ህወሓት የፈጠረውን መሰረት ለመስበር ቀላል አይደለም። እስካሁንም በዚያ ላይ ነው ስንቀሳቀስ የቆየነው። ህዝቡ በጣም ተጨቁኗል። ነፃ የመውጣት፣ ስልጣን ለመያዝ ፥ ፍትህ ለማግኘት ብዙ ደክሟል። ይሁንና ተጠቃሚ የሆኑት ለእሱ እንዲቆሙ አደረገ። አሁን ለምሳሌ ገበሬዎችን ያየሽ እንደሆነ በአሁኑ ሰዓት በጣም ደህይተዋል። እህል እየተሰፈረላቸው ነው የሚኖሩት።እነዚህ እህል የሚሰፈርላቸው ህብረተሰቦች ህወሓትን ተቃውመው ለመውጣት ይቸገራሉ። ምክንያቱም ያቺን እህል አያገኙም። በተጨማሪ ደግሞ እህል ከሚሰፈርላቸው ጀምሮ እስከ ደብረፂዮን ድረስ ያሉ ደመወዝ የሚከፈላቸው አካላት ገንዘቡ ከህዝብ የሚመጣ ነው ብለው አያምኑም። ያ ጅማት ብቻ የቀረው ደሃ ህዝብ ባወጣው ገንዘብ ደመወዝ እንደሚከፈለው አይረዳም። አንድ ባለስልጣን ከህወሓት ከተጣላ ከቤቱ አውጥተው ይወረውሩታል፤ እንደ ከሃዲ ነው የሚቆጠረው። ከነቤተሰቡና ከነ ልጆቹ ልመና ውስጥ እንዲገባ ነው የሚያደርጉት።
ህዝቡ እውነታውን ይገነዘባል፤ ነገር ግን እንታሰራለን፤ ምን እንበላለን? የሚል ስጋት አለበት። ትግራይ ውስጥ ሁሉም በሚባል ደረጃ መምህራን ሳይቀሩ የህወሓት አባላት ናቸው። ሌላው ይቅርና አንድ ተማሪ አንድ መምህር ቢደፍራት ለማንም መክሰስ መጠየቅ አትችልም።በተለይ ደግሞ ያ መምህር የህወሓት አካል ከሆነ ማንም የሚጠይቀው የለም። ሁሉም በሚባል ደረጃ በፍራቻ የተጠመደ ህዝብ ነው። በሌላ በኩል ከህወሓት ከተላቀቅን አማራጭ የለንም የሚል ጥያቄ አለበት። በተጨማሪም በአንዳንድ አካላት በትግራይ ህዝብ ላይ የሚሰጠው ፅንፍ የወጣ አስተያየት ሌላው ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው አድርጓል። ይህም በሚፈጥረው ስዕል ምክንያት ህወሓት ህዝቡን መልሶ የሚይዝበት ጠበንጃ እንዲያገኝ አድርጎታል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ህዝቡን ዛሬም ድረስ ጠፍሮ ይዞታል። በዚህ ምክንያት ህዝቡ ለእኛ በሙሉ እምነት እኛን እንዳይቀበል ምክንያት ሆኖታል ባይ ነኝ። ይሁንና ህዝቡ አማራጭ እንዳለው አይኑን የሚከፍትለት ካገኘ ያለምንም ጥርጥር ድጋፉን እንደሚሰጠን እርግጠኞች ነን። ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ መታገል ያውቃል። ተደራጅቶ መስራትንም ከህፃን እስከ ሽማግሌው የተካነው ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ ግን እንደ ፓርቲ በርከት ያለ ጭቆና ይደርስብናል። አባሎቻችንም የሚደበደቡበትም ሁኔታ አለ። በነገራችን ላይ ልክ እንደክርስቶስ የተገረፉም አባሎች አሉ። እኔ ራሴ በደህንነት ሁለት ጊዜ በሬስቶራንት ውስጥ ተከብቢያለሁ። ይህ ደግሞ ለመንቀሳቀስ ቀርቶ ለመነጋገር ስጋት ይፈጥራል። የሚደረግብን ማስፈራሪያም ቢኖር ህወሓትን አሸንፈን ቆመን መሄድ ከቻልን ሁሉም ህዝብ ከእኛ ጋር ይሰለፋል የሚል እምነት አለኝ። ለዚህ ደግሞ የፌደራል መንግስቱ ድጋፍ ያስፈልገናል። በተለይ ህዝቡን የምናገኝበት መገናኛ ብዙሃንን የምንጠቀምበት እድል ሊሰጠን ይገባል። በሌላ በኩልም የመንግስት ሃላፊዎች የትግራይ ህዝብን የሚነካ ቃላቶችን ከመናገር መቆጠብ እንደሚገባቸው ለማስገንዘብ እወዳለሁ። በመሰረታዊነት ደግሞ የትግራይን ህዝብንና ህወሓትን ነጥሎ ማየት አለበት። ይህንን ሁሉ ማድረግ ከቻልንና አማራጭ ሆነን ከቀረብን ህዝቡ ፊቱን ወደ እኛ የሚያዞርበት እድል ይኖራል። አሁን ላይ ግን በትግራይ ውስጥ አምስት ስድስት ሆኖ ማውራት አይቻልም፤ ሁኔታው ያስጨንቃል። በእርግጥ ከውጭ ለሚያያቸው ዴሞክራሲያዊ ይመስላሉ። ለምሳሌ እኛ በክልሉ የተመሰረትን ፓርቲ ሆነን ነፃነት ሳይሰጡን ኢዜማ መቀሌ ስብሰባ ማካሄድ ችሏል። ይህም የሚያሳየው በአለም ህዝብ ዘንድ ዴሞክራሲያዊ ሆነው ለመታየት ሲሉ ህወሓቶች አንዳንድ ጊዜ የሚጠሉትን እስከመጋት ድረስ የሚደርሱበት ሁኔታ መኖሩን ነው። በዚህ አጋጣሚም እኛ የምናቀርበውን አቤቱታ ስም ለማጥፋት ብቻ የምንጠቀምበት አድርገው ለመግለፅ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል የተወሰኑ ፓርቲዎች ተመስርተዋል፤ ከሌሎች ጋር በቅንጅት ለመስራት ፓርቲው የጀመረው ነገር ካለ ይግለፁልን?
አቶ መኮንን፡- አንዳንድ ጊዜ ታማኝ ተቃዋሚ የሚባል ነገር አለ። ህወሓት ራሱ የሚፈለፍላቸው ራሱም ፊርማ እያዘጋጀ ያቋቋማቸው ፓርቲዎች አሉ። እነዚህ ታማኝ ፓርቲዎች ምንም አይነት ችግር እንዳላጋጠማቸውንና እንደ ልብ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ይገልፃሉ። ህወሓትን መንቀፍ አይፈልጉም። የህወሓትን ፍላጎት የሚያሟሉ ናቸው። የህወሓት አንደበት ናቸው። እኛ ግን ህዝቡ እንዲፈርድ ነው የምንፈልገው። ትክክለኛ ምርጫ የሚካሄድ ከሆነ አስርም ሆነው ቢመጡ ችግር የለብንም። ምክንያቱም እኛ የሃሳብ ልዩነት እንቀበላለን። ህወሓት ግን ዋናው ችግሩ የሃሳብ ልዩነትን ያለመቀበሉ ነው። ሃይል እስካልተጨመረበት ድረስና በትግራይ ውስጥ ልዩነት ተቀባይነት አግኝቶ ሃሳባችን መግለፅ ከቻልን ህዝቡ የሚፈልገውን ሊመርጥ
ይችላል። ስለዚህ የምርጫው ሜዳ ፍትሃዊ ከሆነ እኛ ዝግጁ ነን። አሁን ግን እየሰራን ያለነው ህዝቡን የማንቃት ስራ ነው። ያለውን ጭቆና፥ ለትግራይ ህዝብ ተቋቋምኩ ቢልም ህወሓት ለትግራይ ህዝብ የማያስብ መሆኑን፥ ለ30 ዓመታት ህዝቡን ያታለለው መሆኑን፤ ለማሳየት ነው እየሞከርን ያለነው። ይህንን ደግሞ ማስወገድ የሚቻለው ህዝቡ እውነተኛ የስልጣን ተጠቃሚ ሲሆን እንደሆነ ለማስገንዘብ እንሞክራለን። በእኛ እምነት ምህዳሩ ከሰፋና ምቹ መደላደሎች ከተፈጠሩ ህዝቡ ነፃነቱ ከተሰጠው በእርግጠኝነት ህወሓትን ማሸነፍ እንደሚቻል እንረዳለን።
አዲስ ዘመን፡- እንደነገሩኝ
ግን በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ናችሁ፤ ካለው ጊዜ አኳያ በዚህ ሁኔታ ምርጫውን ለማካሄድ እንችላለን ብለው ያምናሉ?
አቶ መኮንን፡- እስካሁን ባለን ጊዜ በምርጫ ለመግባት ተስፋ የሚሰጥ ነገር የለም። ህወሓት ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ አልተዘጋጀም። አሁን ባለው ሁኔታ አባሎቻችን እየታሰሩ፤ ፅህፈት ቤት ለመከራየት እንኳ ባልቻልንበትና ብዙ ማስፈራሪያ እየደረሰብን ምርጫውን ለማካሄድ እንቸገራለን። በብዙ መከራ ነው አንድ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት መቀሌ ላይ መክፈት የቻልነው። ህዝቡ ፍራቻ ውስጥ በመሆኑ በይፋ እኛን መደገፍና ከእኛ ጋር ለመሰለፍ አይደፍርም። የመምረጥ ህሊና እንዲኖረው አይደረግም። ደግሞም ለአመታት እንደኛ ያሉ ፓርቲዎች የትግራይ ህዝብ ልጆቹን ያጣበትን ድርጅት የመበተን አጀንዳ እንዳለን ተደርጎ ህዝቡ አዕምሮ ላይ በመሳሉ ከዚህ አስተሰሰብ ለመውጣት ብዙ ጊዜ ይወስድበታል። ታግለው የተጣሉትም ቢሆኑ ከሚደርስባቸው ጫና ስጋት የተነሳ እኛን ከመደገፍ ይልቅ ዝምታን ነው የመረጡት። በነገራችን ላይ በመንግስትም በኩል ፀጥታን ለማስፈን እየተሰራ ያለው ስራ አርኪ የሚባል አይደለም። ይህም ቢሆን ግን ምርጫውን አናቋርጥም። ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ከተካሄደ ህዝቡ በይፋ ደግፎን ባይወጣም በምርጫው ግን ድምፁን እንደሚሰጠን አንጠራጠርም።
አዲስ ዘመን፡- መንግስት ፀጥታን ከማስከበር አኳያ በክልሉ ጣልቃ ገብቶ መስራት አለበት እያሉ ነው?
አቶ መኮንን፡- ይህንን ስልሽ መንግስትም ቢሆን የትግራይን ህዝብ ከህወሓት መነጠል አለበት እያልኩ ነው። ፖለቲካዊ የፕሮፖጋንዳ ስራ መሰራት አለበት። ህወሓት የትግራይ ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለው ጭቆና እና ጫና መገለፅ አለበት። ሌላው ይቅርና እንደርታ ላይ ተፈጥሮ በነበረው የህዝብ አመፅ አመራሩ ወደ ህዝቡ እንዲተኮስ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር። ወታደሩ ግን በህዝባችን ላይ አንተኩስም በማለቱ ነው የባሰ ችግር ያልተፈጠረው። በእኔ እምነት ህወሓት በአሁኑ ወቅት የሚተኩስበት ጠላት እየፈለገ ነው። ይህንን ለህዝቡ ማሳየት ያስፈልጋል። ይህንን ማድረግ የሚችለው ደግሞ የፌደራል መንግስቱ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ የሚሉት ችግር በፕሮፖጋንዳ ብቻ መፈታት ይቻላል ተብሎ ይታመናል?
አቶ መኮንን፡- አሁን ላይ ለውጥ እያየን ነው። ህዝቡ የተጠናከረና ከህወሓት ጋር እየተስማማ አይደለም። ለምሳሌ ከአማራ ክልል ጋር የነበረው አለመግባባት ጽንፈኞች የፈጠሩት መሆኑን ህዝቡ በአሁኑ ወቅት እየተገነዘበ መጥቷል። በተለይ አሁን የተሾመው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የሚናገረው ስለ ሰላም መሆኑን በማየታቸው ህዝቡ የነበረውን ስጋት ከውስጡ እያወጣ መጥቷል። ህዝቡ አሁን በአማራም ሆነ በሌላው ህዝብ ላይ ጥላቻ የለውም። እንዳውም እናንተ ልጆቻችሁን በአውሮፓ ያስቀመጣችሁ ዝመቱ እያላቸው ነው። አሁን ላይ እንደምታዩት መንገድ መዘጋት የሚባል ነገር ቆሟል። በመሆኑም ህዝቡ እውነታውን እንዲገነዘብ በማድረግ ቢያንስ ለህወሓት የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲቀንስ ማድረግ ይቻላል። በዋናነት ግን መንግስት እኛም ሆነ ሌሎች ፓርቲዎች በምናደርገው እንቅስቃሴ ያለ ገደብና ጫና እንድናከናውን ከፍተኛ ስራ መስራት አለበት ብዬ አምናለሁ። አለበለዚያ ተመልሶ አምባገነን ስርዓት እንዲመጣ እናመቻቻለን ማለት ነው። ይህ ደግሞ የሁላችንም ሃላፊነት ነው ሊሆን የሚገባው።
አዲስ ዘመን፡- የትግራይና የአማራ ህዝብ መካከል ያለው ጉርብትና እንዲጠናከር ምን መሰራት አለበት ብለው ያምናሉ?
አቶ መኮንን፡- የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ እምብርት ነው። ኢትዮጵያን የፈጠርናትም እኛ ነን ብለን ነው የምናምነው። ኢትዮጵያ ብትበተንም እንኳ የምንሰበስባት እኛ ነን ብለን ነው የምናምነው። እኔ ከትግርኛ በተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎችንም ባውቅ ደስ ይለኛል። አማርኛ ግን ታሪክ የሰራንበት ቋንቋ ነው ብዬ ነው የማምነው። የአድዋ ጦርነትን ያሸነፍነው በአማርኛ ነው። በቋንቋ ባንግባባ ኖሩ በጋራ ጠላትን ማሸነፍ አንችልም ነበር።ሁለቱ ህዝቦችም ከጉርብትና ያለፈ የጠነከረ ግንኙነት ነው ያላቸው። ብዙ ጊዜ እንደሚባለውም ችግሩ ያለው በሁለቱ ህዝቦች መካከል አይደለም፤ በፖለቲከኞቻቸው እንጂ። ስለሆነም እነዚህ ህዝቦች እንደቀድሞው ሁሉ በፍቅርና በሰላም መኖራቸውን ይቀጥላሉ የሚል እምነት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ሰዎች ህወሓት የቀድሞ አመራሮች አሁንም ስልጣንን ይዘው የመቆየትና ለተተኪ ትውልድ አለማውረሱ ነው ለውጥ ፈላጊ ያል ሆነው ይላሉ። እርስዎ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ? የእና ንተስ ድርጅት የዚህ ችግር ሰለባ አይደለም ይላሉ?
አቶ መኮንን፡- ዋናው ችግር ያ ነው። በተለይ የተማረው ሃይል አይፈለግም።አሁን ላይ እኮ እያሰባሰበ ያለው ሽንኩርት ነጋዴዎችን ነው። ለምሳሌ «አንዷን ሴት ብልፅግና ማለት ምን ማለት ነው?» ብለሽ ብትጠይቂያት ‹‹እሾክ ››ማለት ነው የምትልሽ። የዚያን ያህል ምንም የማያውቁ የህብረተሰብ ክፍሎችን ነው አደራጅቶ ያለው። ብዙ የተማረ ባለበት ክልል ውስጥ ግን ህወሓት አልተቀበላቸውም። ይህንን የሚያደርጉት ከፍራቻ የመጣ ይመስለኛል። አብዛኛውን አባላቶቹን በገንዘብ ነው የያዟቸው። ምሁሩ በአሁኑ ወቅት ተነጥሎ ነው ያለው። ይገርምሻል! ዛሬ ህወሓት ዛሬ የሚሰበስበው በገንዘብ ነው። አንድ ስብሰባ ከተጠራ ውሎ አበል አለ። ሲመጣ የሳምንት ምግብ ሳይቀር ይዞ እንዲሄድ ይደረጋል። በአንፃሩ ደግሞ ወደ እኛ ፓርቲ ስትመጪ ግን ከእኛ ጋር ለመስራት የሚፈልገው በርከት ያለ ወጣት አለ። ለምሳሌ ስራ የሌለው ወጣት በሙሉ አባል እየሆነ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፡- እንዳው ለአንባቢዎቻችን ተዓማኒነት እንዲኖረው የአባላት ብዛት በቁጥር ቢገልፁልን?
አቶ መኮንን፡- አሁን ቁጥሩን በተጨባጭ ለመንገር እቸገራለሁ። ምክንያቱም ከተመዘገበ በኋላ የሚሄድ አለ፤ በዚያው ልክ የሚጨመርም አለ። ስለዚህ ይሄ ነው ለማለት ያስቸግረኛል። ይህም ሆኖ ግን እኔ ባለኝ መረጃ እስከ ሁለት ሺ የሚሆኑ ወጣቶች በቋሚነት ተመዝግበው እንደሚገኙ አውቃለው። የእኛ ችግር የፋይናንስ እጥረት ነው። በየቦታው ለምናደርገው እንቅስቃሴ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ያስፈልጋል። የሚገርምሽ ህወሓት የፈጠራቸው አንዳንድ ድርጅቶች በኢኮኖሚ ከእኛ የተሻሉ ሆነው ነው የምናገኛቸው። ያለውም መንግስት ቢሆን ተስፋ ከመስጠት ባለፈ በተጨባጭ እያደረገን ያለ ድጋፍ የለም።
አዲስ ዘመን፡- ህወሓት ከብልፅግና ፓርቲ መነጠሉ በቀጣይ በፌደራል ደረጃ ለሚኖረው ውክልና ስጋት ይሆናል ብለው ያምናሉ?
አቶ መኮንን፡- ህወሓት ከብልፅግና መነጠሉ ለእኛ ጠቃሚ ነው ብለን ነው የምናምነው። ከብልፅግና ጋር ቢሆን ለማጭበርበርም ብዙ መንገድ ይከፍትለት ነበር ብዬ አስባለው። እኛንም ለማፈን ምቹ ሁኔታ ይፈጥርለት ነበር። በእኔ እምነት በገዛ እጁ ነው ራሱን ገደል ውስጥ ያስገባው። ምንአልባት የያዘው ገንዘብ ብዙ መስሎት ሊሆን ይችላል። አሁን ላይ ህዝቡን ገንዘብ አምጡ ማለት ጀምሯል። መጨረሻው ግን ውድቀት እንደሚሆን አንጠራጠርም። የእኛ አቋም ግን አሁንም የኢትዮጵያ አንድነት ነው። አሁን ላይ እኮ ትግራይ ውስጥ አንድነት ልክ ሰው እንደሚበላ አድርገው ነው እየገለፁ ያሉት። አንድነት በአግባቡ ከተመራ በፌደራሊዝም ስርዓቱ ላይ አደጋ ያመጣል ብለን አናምንም። ከሌሎች ኢትዮጵውያን ጋር ያለንን ግንኙነት የጠበቀ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የእናንተ ፓርቲ በፌደራል ደረጃ ከሚታወቁ ፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ህብረት ለመፍጠር የጀመረው እንቅስቃሴ ካለ ቢጠቅሱልን?
አቶ መኮንን፡- እኛ የምስክር ወረቀታችንን በመጀመሪያ ማግኘት እና እንደፓርቲ መቆም መቻል አለብን። ከዚያ በኋላ ከፕሮግራማችን ጋር የሚስማሙ እንደ ፓርቲ ሆነን ለመቅረብ ፍላጎት አለን። አሁንም ከአንዳንድ እንደ ዓረና ካሉ ፓርቲዎች ጋር ህብረት ለመፍጠር ዝግጅት ላይ ነን። እስካሁን ድረስ የቆየነው ይህንን ስራ ስናከናውን ነው። የብልፅግናንም ሆነ የሌሎች ፓርቲዎችን ፕሮግራም በማጥናት ላይ ነን። ኬሎች ድርጅቶች ጋር በጥምረት መስራቱ ጠቀሜታ ቢኖረው በፕሮግራማችን ጋር መስማማት አለብን።
አዲስ ዘመን፡- አሁን እርሶ በፓርቲው ያሎት ሚና ምንድን ነው? በምርጫስ ይሳተፋሉ?
አቶ መኮንን፡- እኔ ፓርቲውን ከመሰረቱት ሰዎች አንዱና የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ሆኜ ሳገለግል ቆይቻለው። ጉባኤ ከተደረገ በኋላ ግን ከኋላ ደጀን ሆኜ ወጣቱን ሃይል ወደ ፊት በማምጣት እየደገፍኩ ነው ያለሁት።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ያደረጉት ዜግነትዎን መለወጥ ስላልቻሉ ነው?
አቶ መኮንን፡- አይደለም፤ ካስፈለገ ዜግነትን መለወጥ ይቻላል፤ ነገር ግን እንዳልኩሽ ለወጣቱ ቦታ መልቀቅ ስለሚገባንና ከኋላ ሆነን ማገዝ ስለሚገባ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ መኮንን፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 14/2012
ማኅሌት አብዱል