ጤና ይስጥልኝ!
ለጥቂት ደቂቃዎች ወደ አረብ ኢሚሬቷ አቡዳቢ ከተማ ልውሰድዎና ትዝብቴን ላጋራዎማ!
ከዚያ በፊት ይህችን እውነታ ይጨብጡ።
የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች፤ አጠር አድርገን ስንጠራቸው “ኢሚሬቶች”ን እአአ በ1971 አቡዳቢ፣ ዱባይ፣ ሳርጃ፣ አጅማን፣ ኡም አልቁዋኢን፣ ፉጃኢራህ እንዲሁም ራስ አል ካይማህ በጋራ የመሰረቱት ፌዴሬሽን ነው። እአአ በ2020 የዓለም ባንክ መረጃ መሰረትም የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ የህዝብ ቁጥር 9 ነጥብ 89 ሚሊዮን ደርሷል።
የኢሚሬቶች ብሄራዊ የስራ ቋንቋ አረብኛ ሲሆን፤ ዋና ከተማዋም አቡዳቢ ናት። ከሰባቱ ውስጥ ትልቋ ከተማቸው ዱባይ ስትሆን፤ ብሄራዊ የመገበያያ ገንዘባቸው ደግሞ ድርሀም ይባላል። አንድ ድርሀም አሁን ባለው ምንዛሬ መሰረትም 7 ብር ከ9363 ሳንቲም ይመነዘራል።
972 ስኩዌር ኪሎሜትር ስፋት ያላትና በ2016 እ.ኤ.አ 2 ሚሊዮን 908 ሺህ የሚደርስ ህዝብ የሚኖርባት የኢሚሬቶች ዋና ከተማ አቡዳቢ፤ ከጠቅላላ ሕዝቧ ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የሌላ ሀገር ዜጋ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
ከላይ እንዳልኩዎ የአቡዳቢ ከተማ ለዛሬ የትዝብት አምዳችን አብይ ጉዳይ ስትሆን፤ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በከተማዋ ለስራ በተገኘበት ወቅት ተዘዋውሮ ያስተዋለውን ምልከታ እንደሚከተለው በጨረፍታ ያቀርባል።
መልካም ንባብ!
ብዙነት በአቡዳቢ
ከአቡዳቢ ከተማ ጠቅላላ ህዝብ ቁጥር ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የሌላ ሀገር ዜጋ እንደሆነ ይታመናል። በአቡዳቢ የተለያዩ አገራት ዜጎችን መመልከት ብርቅም ድንቅም አይደለም። ከሰባቱም አህጉራት እና ከመላው ዓለም ሰዎች በከተማዋ ይኖራሉ፤ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተውም ሲሰሩ ይስተዋላሉ።
በትላልቅ ሆቴሎች፣ የገበያ ማዕከላት፣ ሱፐርማርኬቶች፣ የታክሲ አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች፣ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች፣ ሱቆች፣ የአየር መንገዶች እና ሌሎችም ተቋማት ውስጥ የተለያየ ቀለም እና ገፅታ ያላቸው ሰራተኞች የእለት ከእለት ስራዎቻቸውን ሲከውኑ ይስተዋላል። በአቡዳቢ ስራ ለመቀጠር ህጋዊነትና ብቃት እንጂ ከየት መጤነት መስፈርት አይደለም።
በእኛ ሀገር እንደሚሆነው በዘር መከፋፈል እና ግጭት ጭራሹንም የማይታወቅባት አቡዳቢ ጥቁሩን ከነጭ አስማምታ እድገቷ ላይ ብቻ ያተኮረች ከተማ ናት። ልዩነት ለእነርሱ የስልጣኔያቸውና የእድገታቸው ምሰሶ እንጂ የቁርሾና የውድቀት ምክንያት አይደለም። ይህ ባይሆን ኖሮ እጅግ ትንሽ በሆነው የሀገሬው ሰው ብቻ ዛሬ ላይ የምትታየውን ሀገር እውን ማድረግ አይችሉም ነበር።
የከተማ ፅዳት እና አረንጓዴ ልማት
የአቡዳቢ ከተማ እጅግ ውብ፣ ፅዱ እና ለዓይን የሚስብ ገፅታን የተጎናፀፈች ናት። በመንገዶቿ የእግር ጉዞ ባደረግንበት ወቅት ምንም አይነት መጥፎ ሽታ የሚባል ነገር ከአፍንጫችን አልደረሰም። በገበያ ማዕከላትና ሱፐር ማርኬቶች እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቆሻሻ የሚባል ነገር ተዝረክርኮም ይሁን መንገድ ላይ ወድቆ መመልከት ዘበት ነው።
አልፎ አልፎ የእግር ጉዞ የሚያደርጉ ነዋሪዎች ቆሻሻቸውን ከመንገዱ ዳር በተቀመጡ ቅርጫቶች በአግባቡ ያስወግዳሉ። ቅርጫት በአጠገባቸው ቢያጡ እንኳን እስኪያገኙ ድረስ ይዘው ይጓዛሉ እንጂ በግዴለሽነት በየቦታው መጣልን አልለመዱም።
አቡዳቢ ሙሉ ገፅታዋ ማለት በሚያስደፍር መልኩ አሸዋማ ቦታ ስትሆን አረንጓዴነትን ተፈጥሮ አላደላትም። በከተማዋ የሚኖሩ ህዝቦች ግን ይህንን የተፈጥሮ ውሳኔ አምነው ቢቀበሉም እጃቸውን አጣጥፈው መቀመጥ አልወደዱም። በከተማዋ ችግኞችን እና አበባ በመትከልና በመንከባከብ አረንጓዴ ለማድረግ የሄዱበት ርቀት የሚገርም ነው።
በመንገድ አካፋዮች እንዲሁም ዳር እና ዳር ላይ ከትላልቅ ዛፎች ጀምሮ እስከ ትናንሽ የግቢ አበቦች ጭምር ለምተው ከተማዋን አስጊጠዋታል። በእርግጥ በከተማዋ የተገኘንበት ወቅት ሞቃት የሚባል ወር ባይሆንም እነዚህ ዛፎች በሞቃታማው ወቅት የከተማዋን ሙቀት በማስተካከል እና መጠለያም በመሆን እንደሚያገለግሉ ከነዋሪዎቹ ሰምተናል።
ሰው ሰራሽ በሆነ መንገድ ከተማዋን እንዲጠጋ ተደርጎ የመጣው የህንድ ውቅያኖስ ሌላኛው የአረንጓዴነት ገፅታን ለአቡዳቢ ያላበሳት ውበቷ ነው። የውቅያኖሱ ውሀ ጥርትና ኩልል ከማለቱ የተነሳ ትኩር ብሎ ላስተዋለው ለዓይን የሚያጠግብ፣ የሚያመጣው ነፋስ ደግሞ ሰውነትን ቀዝቀዝ አድርጎ ሀሴትን የሚያላብስ ነው። በአጠቃላይ ከተማዋ በስራ የደከመ አዕምሮን ዘና ለማድረግ እና መንፈስን ለማደስ የሚያስችል ሁነኛ ገፅታን ተላብሳለች።
መንገድ እና ተሽከርካሪ በአቡዳቢ
የአቡዳቢ መንገዶች እና ተሽከርካሪዎች አንዱ ለሌላኛው የተመቻቹ ከመሆናቸው የተነሳ ልብ ብሎ ላጤናቸው የእለት ተእለት ፍሰታቸው በራሱ ውበት ነው። መንገዶቹ በጥራት እና በውበት የተገነቡ እና ለተሽከርካሪዎች የማይጎረብጡ ናቸው። የመንገድ ላይ ምልክቶች እና መብራቶች በአግባቡ የተቀመጡ ሲሆን የተሽከርካሪ ፍሰቱን ያለምንም መስተጓጎል ቀን ከሌሊት ያሳልጣሉ።
እንዲህ እንደ እኛው አይነት ወዲህ የተገመጠ ወዲያ ደግሞ የተንሸራተተ መንገድ በአቡዳቢ ፈልጎ ማግኘት ህልም ነው። የአቡዳቢ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ከአንገት ሳይሆን ከአንጀት ሲሰሩ ለትውልድ እንደሚተላለፉ ጥሩ ማሳያ ተደርገው ሊቆጠሩ ይችላሉ። የአካፋዮች ስፋት፣ የእግረኛ መንገዶች ምቹነት፣ የብስክሌት መንገዶች አወጣጥ፣ የቀለም አቀባብ ሌላም ሌላም ብቻ ሁሉም የመንገድ መሰረተ ልማት የተገነባው በመናበብና በአርቆ አሳቢነት መሆኑን ልብ ብሎ ለተመለከተው ልብ ያማልላል።
ከየት ተነስቼ የት ልድረስ? ብሎ ግራ ለሚገባው እንግዳ የአቡዳቢ መንገዶች መልስ አላቸው። የመንገድ ስያሜዎች እና መለያ ቁጥሮች በግልፅ እጅግ ዘመናዊ በሆነ ቴክኖሎጂ ተደግፈው ተቀምጠዋል። በራዳር ቴክኖሎጂ ጂፒኤስ በመጠቀምም የፈለጉበት ቦታ መድረስ በዚያች ከተማ ቀላል ነው።
ተሽከርካሪዎች ዘመናዊና ብዙ ጭስ ሲያወጡ የማይታዩ ናቸው። ሁሉም በሚባል ደረጃ አዳዲስ እና የቅርብ ጊዜ ሞዴል ያላቸው መኪኖች ሲሆኑ፤ በመንገዶች ላይ ያለምንም መጨናነቅ ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላሉ። በአቡዳቢ ከተማ ውስጥ በሰዓት ከ80 ኪሎ ሜትር በላይ ማሽከርከር ክልክል ነው። አንድ አሽከርካሪ የፍጥነት ገደቡን አልፎ ሲያሽከረክር ለሶስት ጊዜ በጂፒኤስ የታገዘ የድምፅ ማስጠንቀቂያ ከመኪናው ውስጥ ይደርሰዋል። ይህንን ማስጠንቀቂያ ተግባራዊ ያላደረገ እንደሆነ ከባንክ አካውንቱ ውስጥ የቅጣት ገንዘብ ተቀናሽ ተደርጎ ደረሰኝ እንደሚደርሰው ከአንድ አፍሪካዊ አሽከርካሪ ሰምተን ተደምመናል።
በአቡዳቢ ከተማ የታክሲ አገልግሎት ለማግኘት ረጃጅም ሰልፎችን መሰለፍ፣ በብርድና ፀሀይ ለረጅም ሰዓት መቆም፣ በግፊያና በጥድፊያ ንብረትን እስከመዘረፍ መድረስ፣ ከታሪፍ ውጪ ክፍያ እንዲከፍሉ መጠየቅ እና መሰል እንግልቶች ጨርሶ አይታሰቡም።
ታክሲ ፈልጎ መንገድ የወጣ ሰው በሰከንዶች ከፊት ለፊቱ በስነምግባራቸው አንቱ የተባሉ አሽከርካሪዎችን እጅግ ዘመናዊ ከሆኑ መኪኖች ጋር ያገኛል። መሄድ የሚፈልግበትን ቦታ ተናግሮ መንገዱን ይቀጥላል። ከፊት ለፊቱ ባለው የተሽከርካሪ ስክሪን ላይ የአሽከርካሪውን ሙሉ መረጃ ከፎቶግራፍ ጋር እና ጉዞው እየፈጀ ያለውን የገንዘብ መጠን ይመለከታል። ቦታው ሲደርስ ታዲያ ሲስተሙ የቆጠረውን ገንዘብ ከፍሎ ይወርዳል፤ ከአሽከርካሪውም ሞቅ ያለ ምስጋና ይቀርብለታል።
የአቡዳቢ አሽከርካሪዎች ለደንበኞቻቸው አብዝተው የሚጨነቁ ከመሆናቸው የተነሳ የአየር ማሞቂያ ወይም ማቀዝቀዣ መክፈት ያስፈልግ እንደሆን የሚጠይቁ እነሱ እንጂ ተሳፋሪ አይደለም። በምቾት፣ በተፈለገው ጊዜ እና በትህትና ከቦታ ማድረስን ያውቁበታል ብቻም ሳይሆን ተክነውበታልም ጭምር።
የደህንነት ክትትልና ቁጥጥር
በአቡዳቢ ከተማ የትም ቦታ በየትኛውም ሰዓት ያለምንም ስጋት መንቀሳቀስ ይቻላል። ምክንያቱም እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በደህንነት ካሜራ እይታ ውስጥ ነውና። ከስጋት ነፃ ሆኖ ስራን መከወን ወይም የደከመ መንፈስን ከቤት ወጣ ብሎ ራስን ማሳረፍ የእለት ከእለት ተግባር መሆኑንም ታዝበናል።
በአንድ የገበያ ስፍራ በተገኘንበት አጋጣሚ ያስተዋልነው የመኪና ግጭትን እንጥቀስ። ተደርድረው በቆሙ መኪኖች መካከል ገብቶ ለመቆም የፈለገ አንድ አሽከርካሪ መኪናውን በሚያስተካክልበት ወቅት ሌላ የቆመ መኪና ፈረፋንጎን ገጭቶ ይሰብረዋል። አሽከርካሪውም ወርዶ ግጭቱን ካየ በኋላ መኪናውን አስነስቶ አካባቢውን ለቆ ሄደ። መኪና ገጭቶ መሄዱ ብቻ ሳይሆን የትራፊክ ፖሊሶች በአካባቢው አለመኖራቸውና እንደ እኛ ሀገር ተለክቶ፣ ቀለም ተቀብቶ፣ መንጃ ፈቃድ ተይዞ፣ ካርታ ተነስቶ ወዘተ. አለመመዝገቡ ገረመን ግራ ተጋባንም።
ከገበያ ማዕከሉ በር ላይ ድርጊቱን ሲከታተል የቆየውን የጥበቃ አባል ጠጋ ብለን ሁኔታውን ጠየቅነው። “በአቡዳቢ መኪና ስትገጭ ታርጋህና መኪናህ በራዳር ይያዛል። የተገጨበት ሰው ሲያመለክትም በአድራሻህ ትጠራለህ እንጂ ትራፊክ ፖሊስ፣ ቀለም ምናምን የሚባል ነገር የለም” ሲል አስረዳን። አይ መዘመን ደጉ ብለን ለጥበቃውም ምስጋናችንን አቅርበን ተሰናበትነው።
የድምፅ ብክለት
የኢትዮጵያ በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ አንዴ በመኪና፣ ሌላ ጊዜ በድምፅ ማጉያ ስፒከሮች፣ አለፍ ሲል በማሽነሪዎች ድምፅ ኧረ ይባስ ብሎ በመንገድ ላይ ህገወጥ ነጋዴዎች የሽያጭ ማስታወቂያ እና የግዙኝ ልመና ጆሮው ብጥስ እስኪል የድምፅ ናዳ ይወርድበታል። የመኪና ጥሩምባዎችንማ ለምን እና የት ለመጠቀም እንደተገጠሙ ራሱ አሽከርካሪው አያውቀውም ቢባል ተጋኗል ይባል ይሆን?
በአቡዳቢ ከተማ የመኪና ጥሩምባ ብዙም አገልግሎት ላይ አይውልም። አሽከርካሪዎች የሚግባቡት በመብራት እና በሌሎች የግንኙነት መንገዶች ነው። የግድ ጥሩምባ መጠቀም ያለበት አሽከርካሪ እጅግ የተመጠነ ድምፅን ብቻ ይጠቀማል። ይህም ከፊት ለፊቱ ያለን አሽከርካሪ ሳይረብሽ መልዕክቱን ያስተላልፋል። መሪዎች በሚጓዙበት ወቅት እንኳን ከመኪናም ይሁን ከአጃቢ ሞተር የጥሩንባ ድምፅ ሲወጣ አላዳመጥንም። የድምፅ ማጉያ ሙዚቃም ሆነ ሌሎች የድምፅ ብክለትነም የሚያስከትሉ ነገሮችማ አይታሰቡም።
በነገራችን ላይ ስለመሪ እንቅስቃሴ ካነሳን አይቀር መሪዎች በከተማ ውስጥ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በእኛ ሀገር ከዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሀላፊነት መምጣት በፊት እንደነበረው አይነት መንገድ መዝጋት ብሎ ነገር የለም። ባለው ተሽከርካሪ ፍሰት መሰረት የመሪዎች መኪኖች ይስተናገዳሉ። በጩኸት ድብልቅልቅ ያለ አጀብም የለም።
የአቡዳቢ ከተማ በወፍ በረር ትዝብታችን ይሄን ትመስላለች። የጠቃቀስናቸው ነጥቦች ወደፊት ለምንገነባት ኢትዮጵያ መነሻ ሊሆኑ የሚችሉና ትምህርት የሚወሰድባቸው ናቸው ብለን እናምናለን።
ሰላም !
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 13/2012
ድልነሳ ምንውየለት