ከ1969 እስከ 1971 ዓ.ምን ነጥለን ያወጣነው የዘመን ክፋይ ኢትዮጵያ በተለያዩ እጅግ አደገኛ፣ ወሳኝና ከምንም የከፋ በወቅቱ የተሰነዱ የታሪክ መዛግባት እንደሚያስረዱት የአለም አቀፉን በበላይነት የምታስተባብረው አሜሪካ ስትሆን፤ ሰበቧም “ኢትዮጵያ ከሶሻሊስትና ተራማጅ አገራት ጎራ በግልፅ በመሰለፏ፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ፕሮግራምን መርኋ በማድረጓ፣ የሶሻሊዝምን ፍልስፍና በመቀበሏና ሳይንሳዊ ሶሻሊዝምን በማቀንቀኗ” መሆኑ በሰፊው ተፅፏል። ይህም አገር ውስጥና ከውጭ “ኢትዮጵያ ወደ ፀረ-ኢምፔሪያሊስት ካምፕ እንዳትገባ መከላከል” በሚል ሰበብ በዚያድ ባሬ የሚመራውን የሶማሊያ መንግስትና በእብሪት ተነሳስቶ የከፈተውን ወረራ እስካፍንጫው በማስታጠቅ ግንባር ፈጠሩ። ሶማሊያ ከፊት፤ ሀያላኑ ከኋላ ተሰለፉ። ምናልባት “የኢትዮ-ሶማሊያ/ ኦጋዴን ጦርነት “ ሲባል የሰሙና ጦርነቱ ከሶማሊያ ጋር ብቻ የሚመስላቸው ካሉ ይህ ፅሁፍ ጠቃሚ ይሆናልና እንቀጥል።
ዶክተር ለገሰ ለማን ጠቅሰን ከውስጥ እንጀምር፤ በአገር ወስጥ በእርስ በእርስ ጦርነቱ የሚሳተፉ ሀይሎች ን፤ ሱዳን በግልፅ “ከአገር ውስጥ ሀይሎችና አለም አቀፉ ኢምፔሪያሊዝም” ጎን ከመቆሟ፣ መደበኛ ሰራዊቷን ሳይቀር ወደ ምእራብ ኢትዮጵያ አዝልቃ ከማስገባት፣ ብሄራዊ ጣቢያዎቿን እና ቤተ መንግስቷን ሁሉ ከመፍቀድ አልፋ እዛ “የሚኖሩ ከ10ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያንን አሰልጥና ወደ ኢትዮጵያ በመላክ በቀላሉ ሽብር መፍጠርና ኢትዮጵያን ማፈራረስ በሚል የእብሪትና ማን አለብኝነት አቋም ታህሳስ 1969ዓ.ም በይፋ አሳወቀች። […] 1ኛ ምክትል ፕሬዚዳንት አብዱልቃሲም መሀመድ ኢብራሂም ከፕሬዚዳንት ጃፋር ኤል ኒሜሪ በተሰጠ መመሪያ መሰረት ጀብሀ እና ሻእቢያ የጋራ ግንባር መፍጠራቸውን በፊርማቸው አረጋገጡ፤ ይህም ጥቅምት 1970ዓ.ም በተሰጠ ይፋዊ መግለጫ ተነገረ። የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ህብረት (ኢዲህ) በሰሜን ምእራብ ኢትዮጵያ፤ ኢህአፓ በተለይ በከተሞች ውስጥ ጥቃት በመፈፀም፤ በሰሜንና ሰሜን ምእራብ የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች የእርስ በእርስ ጦርነቱን አጧጧፉት።
አለም አቀፉን ኢምፔሪያሊዝምንም በተመለከተ፤ አሜሪካ የሶማሊያ መንግስት ከኢትዮጵያ መሬት ቆርሶ እንዲወስድ የሚያስችለውን አቅም ለመፍጠር አገራትን የማስተባበሩን ስራ በተያያዘችው መሰረት እብሪተኛው በ1969ዓ.ም ዚያድ ባሬ በሳኡዲ አረቢያ፣ ግብፅ፣ ሶሪያ፣ ኩዌት፣ ኢራቅ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ባህሬን እና ኳታርን በመጎብኘት የተባበሩኝ ድጋፍ የማሰባሰብ ስራ ሰርቶ ወደ አገሩ ተመለሰ። በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የበላይ አስተባባሪነት የፋርስ ባህረ ሰላጤ አገሮችንና ሌሎች የአረብ አገራትን ይጎበኙ ከነበሩ በኤርትራ ከሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ጋር ኢትዮጵያ እንዴት ማጥቃት እንዳለባቸው ተወያዩ።
ጂሚ ካርተር ወደ ተለያዩ አገራት በተለይም ኢራንና ሳኡዲ አረቢያ በመመላለስ ለሶማሊያ የሚሰጠው ድጋፍ በሁሉም መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማስተባበር ላይ መጠመዳቸው፤ መንግስታቸው ለሱዳንና በአካባቢው ለሚንቀሳቀሱ ሀይላት በከፍተኛ ደረጃ በማስታጠቅ ምእራብ ኢትዮጵያን ማመሳቀላቸው፤ ዩጎዝላቪያን “ለኢትዮጵያ መሳሪያ አስተላልፈሻል” በሚል በአሜሪካ መወንጀሏ፤ ጥር 1970ዓ.ም የዩናይትድ ስቴትስ፣ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ የኢጣሊያና የምእራብ ጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ ባለስልጣናት በዋሽንግተን ዝግ ስብሰባ በማድረግ ገለልተኛ ያልሆነ ውሳኔ ሲወስኑ የነበረ መሆኑ፤ “ቦን ለጦር መሳሪያ ግዥ ሊውል የሚችል 11ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ለሶማሊያ በብድር መስጠቷና ይህንኑ ተከትሎ አምባሳደሩ ከአዲስ አበባ መባረራቸው”ን በወቅቱ ኒውዮርክ ታይምስ መዘገቡ፤ የአለም ባንክን የመሳሰሉ ተቋማት ሳይቀሩ ለኢትዮጵያ ምንም አይነት ብድርም ሆነ ድጋፍ ለማድረግ፤ በኢትዮጵያ ግዛት እንዲያስፋፋ መሆኑ ለታሪክ እማኝነት ይሆን ዘንድ ተሰንዶ ይገኛል።
በየካቲት 1970 ዓ.ም በዩናይትድ ስቴትስ አስተባባሪነት እንደ ኢራን፣ ሳኡዲ አረቢያና ስፔን ባሉ ሶስተኛ አገራት አማካኝነት ለሶማሊያ የጦር መሳሪያ የማቀበል ስራ ሰርቷል። በኦጋዴን ጦርነት የተማረኩ በሳጥኖችና የታሸጉ ልዩ ልዩ የኔቶ ጥይቶችንና በዩናይትድ ስቴትስ የተሰሩ ጠብመንጃዎች መገኘታቸውም፤ የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያን በደገፉ አገራት ላይ ተፅእኖ ለመፍጠር ሲያደርግ የነበረው እንቅስቃሴና ሶቪየት ህብረት ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ እንድታቆም ተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረቡና ለማስፈራራት መሞከሩ ፤ የግብፅ ተደጋጋሚ ዛቻና “ሱዳንን የነካ ግብፅን ነካ” በማለት ኢትዮጵያ ላይ ጣት የመቀሰሯ ደባ በወቅቱ ባገር ውስጥና በውጭ መገናኛ ብዙሃን በዝርዝር ተዘግቦ ለዛሬ እማኝነትና የጋራ እውነትነት በቅቷል።
ኢራንና ሳኡዲ አረቢያም የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለሞቃዲሾ ለማቅረብ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ሁሉ ሲታወስ ለብዙዎች ዘመኑ በኢትዮጵያ ላይ የጨከነ መስሎ ነበር። በዚህ አልቆመም፤ በፀረ-ኮሚኒዝም ስም የሳኡዲ ገዥ መደብ አባላት ከአሜሪካ ጎን ተሰለፉ፤ ሳኡዲም ለሶማሊያ ለጦር መሳሪያ ግዥ የሚውል 500 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ሰጠች። ሌሎችም ተደራጁ፤ የስራ ክፍፍል በማውጣትም እንደየሙያና ፍላጎታቸው አስፈላጊውን አደረጉ። በዚሁ ክፍፍል መሰረትም አሜሪካና ፈረንሳይ የተራቀቁ የጦር መሳሪያዎችን ማቀብል፤ እንግሊዝ ሄሊኮፕተሮችና የአየር መቃወሚያዎችን ለመስጠት፤ ምእራብ ጀርመንና ጣሊያን ብረት ለበስ መሳሪያዎችን ለመላክና የጦር መሳሪያዎችንና መለዋወጫዎችን ለማጓጓዝ ስምምነት ላይ ደረሱ። ጊዜው ለኢትዮጵያ እየከፋ መጣ።
ቀይ ባህርን “የአረብ ሀይቅ” የማድረግ ከፍተኛ ህልምና ዝግጅት ያላቸው በአካባቢው የሚገኙ ጎረቤት አገራት ከኢራን ጋር በማበር ከጦር መሳሪያ ክምችቶቻቸው ለሶማሊያ ለመላክ ተስማሙ፤ ሳኡዲ አረቢያ የጦር መሳሪያዎች በአየር ክልሏ እንዲያልፉ ፈቀደች። ከአምስት የአረብ መንግስታት የተውጣጡ የጦር መኮንኖች በአባልነት የሚገኙበት ግብረ ሀይል በሞቃዲሾ ከትሞ የአረብ አገራት የሚሰጡትን ወታደራዊ ድጋፍ እንዲያስተዳድሩ ተደረገ። ኢራንና በስሯ የተሰባሰቡ የአረብ አገራት በብዙ ቶን የሚገመት የጦር መሳሪያና የህክምና እቃዎች ወደ ሶማሊያ ላኩ። የመካከለኛው ምስራቅ አገራት (የኢራን፣ ኢራቅ፣ ሳኡዲ አረቢያና የግብፅ) ንብረት የሆኑ 15 የጭነት አውሮፕላኖች በተከታታይ ምልልስ የጦርና የህክምና መሳሪያዎችን ወደ ሞቃዲሾ አጓጓዙ። የኢትዮጵያ ምድር ራደች፤ የመንግስቱ ኃይለማሪያም ጩኸት ቀለጠ።
የዶክተር ለገሰ “የኢትዮጵያ አብዮት እርምጃና የኢምፔሪያሊዝም ደባ” ጽሁፍ እንደሚነግረን ኢትዮጵያን ለማዳከም ይህ ቀረሽ የማይባል ርብርብ ይደረግ በነበረበት በዚያን ወቅት የኢፔሪያሊዝምና በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ተፅእኖ ሳይበግራቸው በግልፅ ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ አጎራባች አገሮች ኬኒያና ደቡብ የመን ብቻ ነበሩ። በየካቲት 1970 ዓ.ም የግብፅ አየር መንገድ ንብረት በሆነ ቦይንግ 707 አውሮፕላን ቦንቦችን፣ ፈንጂዎችን፣ የመድፍ ጥይቶችንና ሌሎችንም የጦር መሳሪያዎች ጭኖ በድብቅ ወደ ኬንያ የአየር ክልል በመግባት ወደ ሞቃዲሾ ሲበሩ የነበሩ የኬንያ አየር ሀይል ተዋጊ አውሮፕላኖች አስገድደው ማሳረፋቸውንና ድርጊቱም በይፋ በመገናኛ ብዙሀን ለአለም” መግለፃቸው ተጠቃሽ ነው። በከፍተኛ ደረጃ የተቀነባበረና ኢትዮጵያን የማዳከምና የመከፋፈል ዘመቻ ያስቆጣቸው ሶሻሊስት አገራት ያለማወላወል ከኢትጵያ ጎን የቆሙ ሲሆን፤ “በዚህ ረገድ” እንደ ዶክተር ለገሰ ለማ ጥናት ከ16ሺህ በላይ ወታደሮቿን የላከችውና “በግንባር ቀደምትነት ልትጠቀስ የሚገባት አገር ብትኖር ኩባ ናት።”
በመጨረሻም፤ ምንአልባት አገላለፁ ትራጃይ-ኮመዲ ይመስልብን ካልሆነ በስተቀር አጠቃላይ ሂደቱ “ተልባ ቢንጫጫ ባንድ ሙቀጫ” የሚለውን ምሳሌያዊ አነጋገር ያስታውሰናል፤ በሶስት ወር!!!!
ግንባር ቀደም የኢትዮጵያ አጋር የሆነችው ኩባ ፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮ “ምንም እንኳን በዚህ ወሳኝ የእድገት ደረጃው የኢትዮጵያ አብዮት ብዙ ጠላቶች ቢገጥሙትም ድል ማድረጉ ግን የማይቀር ነው።” እንዳሉት፤ ጓድ መንግስቱ ኃይለማሪያም “በአለም አቀፍ ኢምፔሪያሊዝም የበላይ አስተባባሪነት ከ13 የሚበልጡ አገሮች በአገሪቱ ላይ ቢነሱም በኢትዮጰያ ሰርቶ አደር ህዝብ ፅኑ ተጋድሎ፣ እንዲሁም ከሶቪየት ህብረት፣ ከኩባና ከሌሎች አገሮች በተገኘው ከፍተኛ የሞራልና የማቴሪያል ድጋፍ የእብሪተኛው ሶማሊያ ወራሪ ወታደሮች በየካቲት 1970 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ድል ተመትተው ከኢትዮጵያ ተባረዋል።” (“መስከረም”፣ ቅ.7) ሲሉ የተገኘውን ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ አብስረዋል። በ1969 ዓ.ም የተጀመረው ጦርነት በሶስት፤ እንድገመው በሶስት ወራት ውስጥ የካቲት 26 1970 ዓ.ም ተጠናቀቀ። ‹‹የእናት ሀገር ጥሪ››ው ሰመረ፤ “ይህ ነው ምኞቴ እኔ በህይወቴ / ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ”ም በረጅሙ ተዜመ። ተጨማሪውን ካራማራ ትናገር።
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 13/2012
ግርማ መንግሥቴ