የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም.፤ የጣሊያን ወራሪ ሃይል ጠቅላይ አዛዥ ግራዚያኒ ሕዝቡን ሰብስቦ በሱ የሚመራውን የወራሪውን አስተዳደር እንዲቀበል፣ ባወጣው ሕግ እንዲተዳደር ለማድረግ፣ የጣሊያን መንግስት ለኢትዮጵያ እድገትና መሻሻልን እንጂ አገሪቱን ለመጉዳት የመጣ አለመሆኑን ለማሳመንና ለድሆች እርዳታ እሰጣለሁ በሚል የማታለያ ሰበብ ህዝቡን ስብሰባ መጥራቱን የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ።
ታሪክ እንደሚዘክረው ሕዝቡን ለመሰብሰብ ያስገደደው ዋናው ምክንያት ግን በየአቅጣጫው በዱር በገደል ተሰማርቶ ለአገሩ ነጻነት የሚታገለው አርበኛ ቁጥርና በጠላት ላይ የሚያደርሰው አደጋ እየጨመረ በመምጣቱ ነው፡፡ በከተማም ውስጥ ያለው ጫካ ባይገባም ልቡ ሸፍቶ ለጠላት አልገዛም ባይነት ስሜቱ እያደገ በውስጥ አርበኝነት ተግባር ላይ ተሰማርቶ ለአርበኞቹ የስንቅና የመረጃ ምንጭ በመሆኑ ይህን ሕዝብ በማታለልና በማስፈራራት በቁጥጥር ስር ማድረግ እንዳለባቸው በመገንዘብ የተጠራ ስብሰባ ነበር። በወቅቱ ጣሊያን ይህን ኢትዮጵያዊ አንድነት መስበር ግን አልተቻለውም፡፡
በዕለቱ በግራዚያኒ ላይ አደጋ ለመጣል ምክርና ዝግጅት አድርገው በተግባር የገለጹት በወቅቱ በኤርትራ ክፍለ ሃገር የተወለዱት አገር ወዳድ ወጣቶች፤ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ነበሩ። ወጣቶቹ ግራዚያኒ በሰገነቱ ላይ ቆሞ ንግግር ለማድረግ ሲዘጋጅ ከመሃል ሳይታሰብ ፎክረው በመውጣት ያዘጋጁትን ሰባት ቦምብ አከታትለው ወረወሩ። በዚህም ግራዚያኒና ከ52 በላይ አጃቢ ሹማምንቶቹ ቆሰሉ፤ የሞሶሎኒ አማችም አንድ ዓይኑ ጠፋ፤ አንድ እግሩም ተቆርጦ ተዘረረ።
በሁኔታው የተደናገጡትና የተበሳጩት ጣሊያኖችና ባንዳዎቻቸው በእጃቸው ባለ ጠመንጃና ሌላም መሳሪያ ሕጻን፣ ወጣት፣ ሽማግሌና አሮጊት ሳይለዩ በአደባባይ የተሰበሰበውን ኢትዮጵያዊ ረፈረፉት። ቤት ለቤት እየዞሩም ህዝቡን ረሸኑት። የንጹሃኑ ደም በገዛ አገራቸው መሬት ላይ በውጭ ወራሪዎች እጅ ፈሰሰ። ይህች ዕለት.የጣልያኖችን ግፍና ጭካኔ የኢትዮጵያኑን አንድነት፣ ድፍረትና ቆራጥነት ያረጋገጠ ሆኖ በታሪክ ተከትቧል፡፡ በዚያን ወቅት አሸናፊው ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ነበር፡፡
ዛሬ ከዚህ የሰማዕታት ቆራጥና ደማቅ ታሪክ የምንወስደው ጉዳይ መኖሩ ግድ ነው፡፡ ያኔ ጣሊያን የአገራችንን መሬት ከረገጠበት ወቅት ጀምሮ በጀግኖች አባቶቻችን ተደጋጋሚ ድል ተደርጎ እስኪመለስ ድረስ ባንዳ ሆነው ጣሊያንን ሲያገለግሉ የነበሩ የራሳችን ወገኖች ነበሩ፡፡ በዚህ ታሪካችን አገር በመክዳት የሚዘነጉ አይደሉም፡፡ ያም ሆኖ ግን ታሪክ እንደመዘገበው ከሆነ እነዚህ ኢትዮጵያውያን በተለይ የቁርጥ ቀን በመጣ ጊዜ ጣሊያንን በመተው ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያን አንድነት ተቀላቅለው ጣሊያን ወግተዋል፡፡
ጣሊያን በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን ለመውረር በመጣበት ወቅት ይዞት የገባው የመሳሪያ አይነት ዘመናዊ ከመሆኑ ባሻገር ጅምላ በመጨረስ ጭምር በወቅቱ ወደር የማይገኝላቸው ነበሩ፡፡ እናም ይህን ያህል ዘመናዊ መሳሪያ እና የተደራጀ የውትድርና ሳይንሥ የተካነ ሰራዊት ይዞ ነው የአገራችንን መሬት የረገጠው፡፡
ታዲያ አሸናፊው ማን መሆን ነበረበት? ቢባል ‹‹ጣሊያን ነበር ማሸነፍ የነበረበት›› ብሎ ምላሽ ለመስጠት አይከብድም፡፡ በወቅቱ ግን አሸናፊው ጀግኖች አባቶች፣ እናቶች ወጣት አዛውንት ህፃናት ሳይቀሩ በውስጣቸው የነበረው የኢትዮጵያ አንድነት ስሜት ትጥቅ ሆኖ ጣሊያንን አሳፍሮታል፤ ሽንፈቱንም አከናንቦታል፤ አዎ አሸናፊው የኢትዮጵያ አንድነት ነው፡፡
ዛሬ ዛሬ በድህነታችን እየተሸረሸረ ያለው ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ጠባብ ብሄርተኝነት ታክሎበት ሁኔታውን እንደ ያኔው የጣሊያኖች ግፍና ጭካኔ የተሞላበት ተግባር የጨለማ ያህል አግዝፎ ቢያሳየንም ማርከሻው ግን ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ምን ያህል አቅም እና ጉልበት እንደሆነን ትናንት በተግባር ጣሊያን ላይ እንዳየነው ሁሉ አሁን የገጠመንን ጊዚያዊ ችግር ማሸነፊያው መንገድ ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ብቻ ነው፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2012