በበግብጽ ታሪክ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ምርጥ አፍሪካዊ ተጫዋች በሚል የተመረጠ ብቸኛው ተጫዋች ነው። በቅርቡም ለሁለተኛ ጊዜ የቢቢሲ ምርጥ አፍሪካዊ ተጫዋች ዘርፍ አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል። ባለፈው የውድድር ዓመት በፕሪምየር ሊጉ ባስቆጠራቸው 32 ግቦች የወርቃማ ጫማ ተሸላሚ መሆን ችሎ ነበር። በእግር ኳስ ስፖርት ታላቁ ሽልማት ባሎን ድ ኦርም ስድስተኛ ደረጃ በመያዝ ያጠናቀቀ ተጫዋች ነው። ይህ ተጫዋች በርካታ ክብረወሰኖችን በመሰብሰብ ታሪካዊ ተጫዋችነቱን ለሀገሩና ለክለቡ ያስመሰከረው መሃመድ ሳላህ ነው። |
በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ከሚዘጋጁ ሽልማቶች መካከል አንዱና ትልቁ የሆነው የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማት ከትናንት በስቲያ ምሽት በሴኔጋሏ ዳካር ተካሂዷል። በመድረኩም «ፈርኦኑ» ስኬቱን ለሁለተኛ ጊዜ በማጣጣም አራተኛው ተጫዋች ሆኗል። ከዚህ ቀደም፤ ሴኔጋላዊው አል ሃጂ ዲዩፍ (እአአ በ2001 እና 2002)፣ ካሜሩናዊው ሳሙኤል ኤቶ (እአአ በ2003 እና 2004) እንዲሁም ኮትዲቯራዊው ያያ ቱሬ (እአአ በ2011እና 2012) በተከታታይ ለሁለት ጊዜያት አሸናፊ የሆኑ ተጫዋቾች ነበሩ።
ካፍ የአፍሪካ የአመቱ ምርጥ ተጫዋች ምርጫን ማካሄድ የጀመረው እአአ በ1992 ሲሆን፤ በወቅቱ አሸናፊ የነበረውም ጋናዊው አቤዲ ፔሌ ነበር። ሽልማቱም ተጫዋቾች በውድድር ዓመቱ ባሳዩት ድንቅ ብቃት፣ ለሃገራቸው ባደረጉት እገዛ እንዲሁም የተሻለ የእግር ኳስ እንቅስቃሴ በአህጉሪቷ መኖሩን ማመላከታቸውን መሰረት አድርጎ የሚደረግ ነው። በእጩነት የሚቀርቡት ተጫዋቾችም በካፍ የቴክኒክ ኮሚቴ፣ በመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ በካፍ አባል ሃገራት ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞችና አምበሎች እንዲሁም በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ካፕ እስከ ግማሽ ፍጻሜ በደረሱ የክለብ አሰልጣኞች የሚታጩ መሆኑንም ካፍ በድረገጹ ያስነብባል።
የ26 ዓመቱ የሊቨርፑሎች አጥቂ አሸናፊ የሆነው እስከ መጨረሻው ዙር አብረውት የተጓዙትን የክለብ አጋሩን ሳዲዮ ማኔን እና የመድፈኞቹን ኤምሪክ ኦባሚያንግን በመርታትም ነው። ተጫዋቹ በውድድር ዓመቱ ካሳየው ድንቅ ብቃት ባሻገር ለሃገሩ እና ለክለቡ ያስቆጠራቸው 44 ግቦችም ለአሸናፊነቱ ምክንያት ናቸው። ቀያዮቹ በሻምፒዮንስ ሊጉ እስከ ፍጻሜው እንዲደርሱ ተጫዋቹ የነበረው ሚናም የሚዘነጋ አይደለም። በተያዘው የውድድር ዓመትም በተካፈለባቸው 29 ጨዋታዎች 16 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ በደረጃ ሰንጠረዡ ከተቀመጡት ቀዳሚ አትሌቶች መካከል ይገኝበታል።
ሳላህ የካፍ ፕሬዚዳንት አህመድ እንዲሁም የቀድሞው ተጫዋችና የአሁኑ የላይቤሪያው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዊሃ በተገኙበትም ሽልማቱን ወስዷል። በመድረኩ ባደረገው ንግግር ላይም «ይህንን ሽልማት ከልጅነቴ ጀምሮ አልመው የነበረ ነው፤ አሁን ግን በሁለት ዓመታት በተከታታይ አሸናፊ ለመሆን ችያለሁ» ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
ከምርጥ የዓመቱ ተጫዋች ባሻገር በሌሎች ዘርፎችም ሽልማቱ የሚሰጥ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም ደቡብ አፍሪካዊያኑ ቴምቢ ጋትላና እና ዴዚሪ ኤሊስ በምርጥ ሴት ተጫዋች እና ሴት አሰልጣኝ ዘርፍ አሸናፊ ሆነዋል። ሞሮኳውያኑ አክራፍ ሃኪሚ እና ሃርቬ ሬናርድ በወጣት ተጫዋች እና ምርጥ አሰልጣኝ ዘርፍ እንዲሁም በምርጥ ብሄራዊ ቡድን የሞሪታኒያ በሴቶች ደግሞ የናይጄሪያ ቡድኖች ተመራጭ ሆነዋል።
በዕለቱ በዳካር በተካሄደው ሌላ መርሃ ግብርም ግብጽ ደቡብ አፍሪካን በመርታት የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ሃገር በመሆንም ተመርጣለች። የካሜሩንን ደካማ አዘጋጅነት ተከትሎ ካፍ ዕድሉን ነጥቆ ፍላጎት ያላቸው ሃገራት እንዲወዳደሩ ማድረጉ ይታወሳል። ስድስት ወራት ብቻ ላሉት የዝግጅት ጊዜም ሁለት ሃገራት ብቻ የቀረቡ ሲሆን የካፍ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በሰጡት ድምጽ 16ቱን በማግኘት ግብጽ የ32 ኛው አፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ሃገር መሆኗን አረጋግጣለች። ምርጫውን ተከትሎም የሃገሪቷ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዚዳንት ሃንይ አቡ ሪዳ «ኮሚቴው እምነቱን ስለጣለብን እንዲሁም መንግስት ላደረገልን ድጋፍ ምስጋና እናቀርባለን» ብለዋል።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ አህመድ ሾቢር አክለውም «ከመንግስት ያገኘነው መተማመኛ አግዞን ደቡብ አፍሪካን ለማሸነፍ ችለናል። ይህ ደግሞ ጥሩ ውድድር እንድናዘጋጅ ያግዘናል፤ በደጋፊዎች በኩልም መልካም ነገር እንደሚኖር ቃል እገባለሁ» ማለታቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል። የሰባት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ግብጽ እአአ በ2006 ውድድሩን ማዘጋጀቷ ይታወሳል። ለዚህ ውድድርም በአምስት ከተሞቿ የሚገኙ ስምንት ስታዲየሞችን እንደምታዘጋጅ ታውቋል። የዘንድሮውን ውድድር ለየት የሚያደርገው ደግሞ የተሳታፊ ብሄራዊ ቡድኖቹ ቁጥር ወደ 24 ማደጉ ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 2/2011
ብርሃን ፈይሳ