የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በቶኪዮ ኦሊምፒክ ተሳታፊ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞችን ስም ዝርዝር አስታወቀ። ፌዴሬሽኑ በቅርቡ ወደ ዝግጅት ምዕራፍ እንደሚገባም ይጠበቃል።
በጃፓን አስተናጋጅነት የሚካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ የወራት እድሜ ብቻ የቀረው መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ወደ ዝግጅት ለመግባት የሚያስችለውን የአሰልጣኞች ምርጫ ማድረጉን አስታውቋል። ፌዴሬሽኑ ምርጫውን ባዘጋጀው መስፈርት መሰረት አወዳድሮ ያከናወነ መሆኑንም በድረ ገጹ አስነብቧል።
ፌዴሬሽኑ በአፋጣኝ ወደ ስልጠና ለመግባት በሚያስችሉ ሁኔታዎች ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅርቡ ምክክር ማድረጉ የሚታወስ ነው። ከስድስት ወራት ያነሰ ጊዜ ብቻ ለቀረው ውድድር ካለፉት የሪዮ ኦሊምፒክና የዶሃ ዓለም ሻምፒዮና ተሞክሮ በመውሰድ ስልጠና እንዲታቀድና በአፋጣኝ ወደ ትግበራ እንዲገባ ሁኔታዎች እንዲመቻቹም አቅጣጫ አስቀምጧል። ለተግባራዊነቱም ፌዴሬሽኑ በሚያወጣው የምልመላና የስልጠና ዝግጅት ሚናውን እንደሚወጣ ባስታወቀው መሰረት የአሰልጣኞችን ምርጫ ያከናወነ ሲሆን፤ በቅርቡ አትሌቶችን በመምረጥ ወደ ስልጠና እንደሚገባም ይጠበቃል።
ምርጫው እርምጃን ጨምሮ ኢትዮጵያ በምትታወ ቅባቸው አምስት ርቀቶች ተደርጓል። በዚህም መሰረት በመካከለኛ ርቀት አሰልጣኝ ብርሃኑ መኮንን፣ ሃብታሙ ግርማ፣ ኢሳ ሽቦ እና ጉዲሳ ታሱ ተመርጠዋል። አሰልጣኝ አብርሃም ኃይለማሪያም እና ስንታየሁ ካሳሁን ደግሞ በተጠባባቂነት የሚቆዩ ይሆናል። በ3ሺ ሜትር ደግሞ አሰልጣኝ ተሾመ ከበደ እና ዶክተር ብዙአየሁ ታረቀኝ ሲመረጡ አሰልጣን ከፍያለው አለሙ ተጠባባቂ ሆነዋል።
ሃገሪቷ በኦሊምፒክ መድረክ በተለይ ውጤታማ በሆነችባቸው የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ርቀቶችም አራት አሰልጣኞች ተመራጭ ሆነዋል። አሰልጣኝ ሁሴን ሸቦ፣ ቶሌራ ዲንቃ፣ ንጋቱ ወርቁ እና ኃይሌ እያሱ ሲመረጡ፤ አሰልጣኝ ተፈሪ መኮንን እና በሪሁን ተስፋይ ደግሞ የተጠባባቂነት ስፍራን ይዘዋል። በረጅሙ የአትሌቲክስ ውድድር ማራቶን በማናጀር አሰልጣኝነት ስኬታማ የሆኑት አሰልጣኝ ሃጂ አደሎ ከሌላው አሰልጣኝ ገመዶ ደደፎ ጋር በመሆን የርቀቱን እንደሚመሩም በዝርዝሩ ተመልክቷል። አሰልጣኝ ጌታነህ ተሰማ እና ይረፉ ብርሃኑ ደግሞ ተጠባባቂ ሆነው ተመርጠዋል። የእርምጃ ቡድኑም በሻለቃ ባየ አሰፋ አሰልጣኝነት ወደ ቶኪዮ የሚያመራ ይሆናል።
ፌዴሬሽኑ ምርጫውን ያሳወቀው ከትናንት በስቲያ ሲሆን፣ በምርጫው ላይ ቅሬታ ያለው አካል እስከ ዛሬ ድረስ ጉርድ ሾላ በሚገኘው ጽህፈት ቤቱ በመገኘት ማሳወቅ እንደሚችልም ተጠቁሟል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 11/2012
ብርሃን ፈይሳ