የሰሞኑ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
ከሁለት ሳምንት በፊት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአንድ የወንጀል መዝገብ ላይ ውሳኔ አሳልፏል። ይህንኑ ተከትሎ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የፌስቡክ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ የበቃው የችሎት ዘገባ እንዲህ ይላል- ንጉሴ ይርጋና ሰብለ ተረፈ የተባሉ ባለትዳሮች የገንዘብ እጦት ገጥሟው “እጅ ሲያጥራቸው” አበዳሪ ፍለጋ ከላይ ከታች ሲሉ ይበልጣል ታሪኩን ያገኛሉ።
ይበልጣል ደግሞ ምናለ ዘውዴና ኤልሳ ምናለ የተባሉትን አባትና ልጅ ለባለትዳሮቹ ያገናኛቸዋል። ምናለም ለጥንዶቹ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በ12 ፐርሰንት ወርሃዊ ወለድ አራጣ ያበድራቸዋል፤ ይበልጣልም የአገናኝነቱን ድርሻ ይቀበላል።
ባልና ሚስት ግምቱ 15 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር የሆነውን በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘውንና በ500 ካሬ ሜትር መሬት ላይ ያረፈውን የጋራ ንብረታቸው የሆነውን ባለሁለት ፎቅ መኖሪያ ቤት ለአራጣው መያዣነት አደረጉ።
በአራጣ ብድር ውሉ መሰረት ተበዳሪዎቹ የብድር ገንዘቡን ከነወለዱ ከሶስት ወር በኋላ ለመመለስ ባለመቻላቸው አራጣ አበዳሪው ምናለና ልጁ ኤልሳ ለአራጣ ብድር ውሉ ሽፋን ለመስጠት “አስደናቂ” ተግባር ይፈጽማሉ።
የተበዳሪዎቹን የ15 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር መኖሪያ ቤት በብድሩ ገንዘብ እና በሶስት ወሩ ወለድ በድምሩ በሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ኤልሳ የገዛችው በማስመሰል በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽህፈት ቤት ከጥንዶቹ ተበዳሪዎች ጋር በመቅረብ የሽያጭ ውል ይፈራረማሉ።
የኋላ ኋላ ተበዳሪዎች በነበራቸው በዕምነት ላይ የተመሰረተ የቃል ስምምነት መሰረት ብድሩን ከነወለዱ መልሰው ቤታቸውን እንዲመልሱላቸው አበዳሪዎቹን ቢጠይቁም “አፍንጫችሁን ላሱ” ይሏቸዋል። ተበዳዮቹም መብታቸውን በሕግ ለማስከበር ወደ ፍትህ አካላት ያመራሉ።
በፍጻሜውም ዓቃቤ ሕግ በአበዳሪዎቹና በደላላው ላይ በአራጣና በወንጀል የተገኘን ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ወንጀሎች ክስ መሰረተባቸው። ፍርድ ቤትም ጥፋተኝነታቸውን በማስረጃ አረጋግጦ ከሰሞቹ የጽኑ እስራትና የገንዘብ ቅጣት ውሳኔን አስተላልፎባቸዋል።
እኛም ይህንን ጉዳይ እንደመነሻ ይዘን በዚህ ጽሁፋችን በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ከማቅረብ ወንጀል ጋር በተያያዘ ንቃተ-ሕግን የሚያዳብሩና የወንጀሉን አስከፊ ገጽታ የሚያሳዩ መሰረታዊ ጉዳዮችን እናብራራለን።
በወንጀል የተገኘን ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ወንጀል በጥቅሉ
በእንግሊዝኛ ቋንቋ Money Laundering የተሰኘው ድርጊት ሰፊ ጉዳዮችን የያዘ ነው። በአገራችን የመኒ ላውንደሪንግ ድርጊት ወንጀል ተደርጎ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕግ የተደነገገው በ1996 ዓ.ም. በወጣው የወንጀል ሕግ ነው፤ በአንድ አንቀጽ ብቻ ማለት ነው።
ይሁንና ድርጊቱ እየተወሳሰበና የአስጊነቱ ጥላ እየከበደ በመምጣቱ በ2005 ዓ.ም. በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያለመ አዋጅ ቁጥር 780/2005 ወጥቷል።
በአዋጁ መግቢያ ላይ ሰፍሮ እንደምናነበው ይህ ወንጀል የደህንነት ሥጋት ከመሆኑም በላይ የፋይናንስ ሥርዓቱ የተረጋጋ፣ ግልጽነት ያለው፣ ጤናማና ቀልጣፋ እንዳይሆን የሚያደርግ ከባድ ወንጀል ነው። በዚሁ መነሻ ነው እንግዲህ የተለያዩ አካላትን ድርሻና ኃላፊነት ባካተተ መልኩ የተሟላና ሁሉን አቀፍ የህግ ማዕቀፍ በአዋጅ መልክ ሊዘጋጅ የቻለው።
በአዋጁ መኒ ላውንደሪንግ ለሚለው ቃል በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ በሚል የተሰጠው ትርጓሜ በአንዳንዶች ትችት ሲሰነዘርበት ይስተዋላል። በተለይ ለእንግሊዝኛው ቃል በቀጥታ ትርጉም “ንብረት ማጠብ ወይም ንብረት ማጽዳት” የሚል አቻ ቃል ከመስጠት ይልቅ ረዥም የሆነ ሀረግ በትርጓሜነት መያዙ አግባብነት እንደሌለው ይገለጻል።
ከሁሉም በላይ ድርጊቱ በወንጀል የተገኘን የወንጀል ፍሬ የሆነን ንብረት መደበቅ፣ ማስተላለፍ፣ መረከብ፣ በይዞታ ማድረግ፣ መጠቀምና የመሳሰሉትን የወንጀል ድርጊቶች የሚያካትት ሰፊ ጉዳይ ሆኖ ሳለ በአዋጁ የተሰጠው የትርጓሜ ሀረግ ግን የወንጀሉን ምንነት በከፊል የሚገልጽ መሆኑን በማንሳት የሰላ ትችት የሚሰነዝሩ ልሂቃነ-ሕግ አሉ።
አዋጁ መኒ ላውንደሪንግን በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ወንጀል በሚል ትርጓሜ ቢሰጠውም “በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ወንጀል” ማለት በራሱ ምን ማለት ነው ለሚለው ግን ሕጋዊ አንድምታ አላስቀመጠለትም። ከዚህ ይልቅ ይህንን ወንጀል የሚያሟሉ ናቸው ያላቸውን የወንጀል ድርጊቶች መዘርዘርና መተንተንን ነው የመረጠው።
ቢኒያም ሺፈራው “በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ምንነትና አተረጓጎም በኢትዮጵያ ሕግና ዓለም አቀፍ መለኪያዎች ተነጻጻሪ እይታ” በሚል በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በሚታተመው የሕጋዊነት መጽሔት ላይ ባሰናዳው ጽሑፉ መኒ ላውንደሪንግን እንደሚከተለው ተርጉሞታል፡-
“መኒ ላውንደሪንግ ማለት ገንዘብ የሚያስገኝ ወንጀል በመፈጸም የተገኘን ገንዘብ ከሕጋዊ ድርጊት የተገኘ ለማስመሰል እና ያለምንም ስጋት በሕጋዊው ገበያ አስገብቶ ለሚፈልጉት ነገር ለመጠቀም የሚያስችሉ የተለያዩ ድርጊቶችን መፈጸም ነው”
ከዚህ ትርጉም የምንረዳው ታዲያ በአጭሩ መኒ ላውንደሪንግ ከወንጀል የተገኘንና በወንጀል የቆሸሸን ገንዘብ ወይም ንብረት ንጹህ የማድረግ ድርጊት መሆኑን ነው። ይህ የማጽዳት ድርጊት ደግሞ ማሸሽ፣ መደበቅ፣ ማስተላለፍ እንዲሁም ምንጩን፣ ስፍራውንና የባለቤትነት መብቱን መደበቅ፣ መለወጥ፣ መረከብ፣ መጠቀም ወዘተ ሊሆን ይችላል።
የንብረቱን ሕገወጥ አመጣጥ የማጽዳቱ ድርጊቶች ደግሞ በባንኮች፣ በኢንሹራንሶች፣ በወጭና በገቢ ንግዶች፣ ድንበሮችን በማሻር፣ የብድር ወይም ሌላ ውል በመዋዋል፣ ሎተሪ የደረሰ ለማስመሰል ከዕድለኞች በመግዛት፣ ቅርጻቸውን፣ ይዘታቸውንና ዓይነታቸውን በመለወጥና በመሳሰሉት ዓይነት መንገዶች ሊፈጸሙ ይችላሉ።
በአዋጁ መሰረት በመኒ ላውንደሪንግ ወንጀል ሥር ከሚካተቱት ድርጊቶች ውስጥ የመጀመሪያው ንብረቱ የወንጀል ፍሬ መሆኑን በማወቅ ወይም ማወቅ እየተገባ በቸልተኝነት የንብረቱን ሕገ-ወጥ ምንጭ ለመደበቅ ወይም ለመሸፈን ወይም አመንጪውን ወንጀል የፈጸመውን ሰው ከሕግ ተጠያቂነት እንዲያመልጥ ለማድረግ ንብረቱን መለወጥ ወይም ማስተላለፍ ነው።
ከላይ በተገለጸው የአራጣ ጉዳይ ምናለ የተባለው ግለሰብ በአራጣ ምክንያት የተገኘውን ቤት ይህንን ሕገ-ወጥ ምንጩን ለመደበቅ ወይም ለመሸፈን በሚል ልጁ ኤልሳ ምናለ ቤቱን ከተበዳዮቹ የገዛች እንዲመስል በማድረግ የሽያጭ ውል እንዲፈራረሙ አድርጓል።
ኤልሳ የተባለችው ልጁ በበኩሏ የመኖሪያ ቤቱ ከአራጣው ጋር በተያያዘ የተገኘ የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቀች ይህንኑ ሕገ ወጥ ምንጭ ለመደበቅ ወይም አመንጪ የሆነውን የአራጣ ወንጀል የፈጸመውን አባቷን ከሕግ ተጠያቂነት ለማስመለጥ የቤቱ ገዥ በመምሰል በሽያጭ ውል ላይ በመፈራረም የመኒ ላውንደሪንግ ወንጀል ፈጽማለች።
ሁለተኛው ደግሞ ንብረቱን ወይም የንብረቱን ትክክለኛነት፣ ምንጩን፣ ቦታውን፣ ዝውውሩን ወይም የባለቤትነት መብቱን መደበቅ ወይም እንዳይታወቅ ማድረግ ነው። ቢኒያም ሺፈራው የጠቀሰውን አንድ ማሳያ ተውሰን እነዚህን ድርጊቶች እናብራራቸው።
አንድ ለፖለቲካ ተጽዕኖ ተጋላጭ የሆነ ሰው (በአገር ውስጥ ወይም በዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ባለው ኃላፊነት የተነሳ ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ወይም ተሰጥቶት የነበረ ሰው ወይም ቤተሰቡ ወይም የቅርብ ግንኙነት ያለው ሌላ ሰው) አምስት ሚሊዮን ብር ጉቦ ይቀበላል።
ብዙም ሳይቆይ መርካቶ ከሚገኝ አንድ ነጋዴ ጓደኛው ገንዘብ የተበደረ ለማስመሰል በማሰብ ገንዘቡ በነጋዴው የባንክ ሂሳብ ውስጥ እንዲገባ ካደረገ በኋላ የአንድ ሚሊዮን ብር ብድር ውል በማዘጋጀት መልሶ መበደር የሚባለውን የመኒ ላውንደሪንግ ዘዴ በመጠቀም የገንዘቡን ሕገ-ወጥ ምንጭ ይደብቃሉ።
ፖለቲከኛው በብድር አገኘሁት የሚለውን ገንዘብ በመጠቀምም በባለቤቱ ሥም የልብስና የጫማ መሸጫ ሱቅ በመክፈት ወደ ንግድ ሥርዓቱ ውስጥ ይገባል። ንግዱ በትክክል ባይከናወንም ለገቢ ሰብሳቢ መስሪያ ቤት ወርሃዊና ዓመታዊ ሪፖርት በማቅረብ የንግድ ሥራ የትርፍ ግብር ይከፍላሉ።
ከዚያም ባልና ሚስት ቀሪውን አራት ሚሊዮን ብር የሱቁ ትርፍ በማስመሰል በተለያየ ጊዜ ጥቅም ላይ ያውሉታል። በዚሁም መሰረት መኪናና ቤት በመግዛት ኑሯቸውን እጅግ ከፍ ወዳለ ደረጃ አሸጋገሩት።
በመጨረሻ ግን የፖለቲከኛው የባንክ ሂሳብ የጥርጣሬ ግብይት (ዝውውር) በፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል ምርመራ ይደረግበታል። በምርመራውም ወቅት ፖለቲከኛው የብድር ውሉን በማቅረብ የገንዘቡና የሀብቱ ምንጭ ትክክለኛ ነው በሚል ይሞግታል።
ይህንኑ መነሻ በማድረግም የአበዳሪው ነጋዴ የገንዘብ ፍሰት በተመሳሳይ ይመረመራል። በውጤቱም አበዳሪው ነጋዴ ገንዘቡን አበደረ በተባለበት የግብር ዘመን ለግብር ሰብሳቢው መስሪያ ቤት የኪሳራ ሪፖርት በማቅረቡ ግብር ለመክፈል ያልቻለ ስለመሆኑ ይረጋገጣል።
“የኪሳራ ሪፖርት ያቀረበ ነጋዴ እንዴት አንድ ሚሊዮን ብር ሊያበድር ይችላል?” የሚለውን ጥርጣሬ በመያዝ በተካሄደው ሰፊ ምርመራም ነጋዴው ገንዘቡን እንዳላበደረና ፖለቲከኛውም ገንዘቡን በብድር ሳይሆን በጉቦ ያገኘ መሆኑ ሊረጋገጥ ችሏል።
ከዚህ ማሳያ የምንረዳው ታዲያ አንድን ንብረት ወይም የንብረቱን ትክክለኛነት፣ ምንጩን፣ ቦታውን፣ ዝውውሩን ወይም የባለቤትነት መብቱን መደበቅ ወይም እንዳይታወቅ ማድረግ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ወንጀል መሆኑን ነው።
ሶስተኛው በመኒ ላውንደሪንግ ወንጀል ሥር የሚመደብ ድርጊት ንብረቱን መረከብ፣ በይዞታ ሥር ማድረግ ወይም መጠቀም ነው። እነዚህን ተግባራት በመፈጸም መሳተፍ፣ ለመፈጸም ማደም፣ መሞከር፣ መርዳት፣ ማመቻቸት ወይም እንዲፈጸም ማማከርም እንዲሁ ወንጀል ነው።
በአጠቃላይ ከእነዚህ የአዋጁ ድንጋጌዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ታዲያ የመኒ ላውንደሪንግ ወንጀል በቁሙ ትርጓሜ የተሰጠው ባይሆንም ቅሉ፤ የተጠቀሱት አድራጎቶች የመኒ ላውንደሪንግ ወንጀሎች ተብለው እንደሚያስቀጡ ነው።
የአመንጪው ወንጀል ፍርድ ማግኘት ወይም ያለማግኘት እሰጥ አገባ
ከላይ በተብራሩት የመኒ ላውንደሪንግ ወንጀል አድራጎቶች ውስጥ “የወንጀል ፍሬ” እና “አመንጪ ወንጀል” የሚሉ ሁለት ፍሬ ነጥቦችን እናገኛለን።
በአዋጁ በተሰጠው እንድምታ መሰረት የወንጀል ፍሬ ማለት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከአመንጪ ወንጀል የተገኘ ማንኛውም ገንዘብ ወይም ንብረት ማለት ነው። አመንጪ ወንጀል ማለት ደግሞ ማንኛውም ለወንጀል ፍሬ ምንጭ የሆነና ቢያንስ አንድ ዓመት ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል ነው።
በዚሁ መነሻ አንድ ሰው በመኒ ላውንደሪንግ ወንጀል የሚጠየቀው በአንድ በኩል አንድ ዓመትና ከዚያ በላይ እስራት የሚያስቀጣ አመንጪ ወንጀል ሲፈጽምና ከዚሁ ወንጀልም የገንዘብ ወይም የንብረት ጥቅም ሲያገኝ ነው።
ከላይ በመግቢያችን በጠቀስነው የወንጀል ጉዳይ አመንጪ ወንጀል የሚባለው አራጣው ሲሆን፤ የወንጀሉ ፍሬ ደግሞ የመኖሪያ ቤቱ ነው። የአራጣ ወንጀል በወንጀል ሕጉ እስከ አምስት ዓመት እስራት የሚያስቀጣ በመሆኑ እና የወንጀል ፍሬ ለሆነው ቤት የመገኛ ምንጭ በመሆኑ ተከሳሾቹ ከአራጣው በተደራቢነት በመኒ ላውንደሪንግ ወንጀልም ተቀጥተዋል ።
እዚህ ላይ አከራካሪው ጉዳይ የንብረቱ ምንጭ ሕገ-ወጥ መሆኑን ለማስረዳት በተከሳሹ ላይ በአመንጪው ወንጀል የጥፋተኝነት ፍርድ መስጠቱ የግድ እንደማያስፈልግ በአዋጁ መደንገጉ ነው። ይህ ማለት ለማሳያነት በተነሳንበት ጉዳይ በመኒ ላውንደሪንግ ክስ ምንጩ የተደበቀውን መኖሪያ ቤት ሕገ-ወጥ ምንጭ ለማስረዳት በተከሳሾቹ ላይ በአራጣው ወንጀል የጥፋተኝነት ፍርድ እንዲሰጥ አይጠበቅም እንደማለት ነው።
ሕግ አውጪው ይህንን ድንጋጌ በሚያካትትበት ወቅት በአመንጪው ወንጀል የጥፋተኝነት ፍርድ የማይሰጥባቸውን ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት እና ፍርድ ባለመሰጠቱ ምክንያትም በወንጀል ፍሬው ምክንያት በግለሰቦች መብትና በኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው።
ለማሳያነት አመንጪው ወንጀል በይርጋ ቢታገድና ክስ መስርቶ የጥፋተኝነት ፍርድ ማሰጠት ባይቻል የመኒ ላውንደሪንግ ወንጀል ክስና ቅጣት በይርጋ የማይታገድ ወንጀል በመሆኑ ክሱ ራሱን ችሎ ተመስርቶ እንዲቀጥል እድል የሚሰጥ ድንጋጌ ነው። በተጨማሪም በአመንጪው ወንጀል የተከሰሰ ሰው ቢሞትና ክሱ ቢቋረጥ በግብረ-አበሩ ላይ የቀረበው የመኒ ላውንደሪንግ ክስ ግን ራሱን ችሎ እንዲቀጥል ይደረጋል።
በመኒ ላውንደሪንግ ክስ የንብረቱ ምንጭ ሕገ-ወጥ መሆኑን ለማስረዳት በተከሳሹ ላይ በአመንጪው ወንጀል የጥፋተኝነት ፍርድ መሰጠቱ የግድ አይደለም ሲባል ግን የንብረቱ ምንጭ ሕገ-ወጥ ስለመሆኑ ማስረጃ አይቀርብም ማለት እንዳልሆነ ልብ ይሏል። ማስረጃ በማቅረብና የንብረቱ ምንጭ ሕገ-ወጥ መሆኑን በማሳየት በመኒ ላውንደሪንግ ወንጀል ጥፋተኛ ማስባል ይገባል እንጂ።
ለምሳሌ በመግቢያችን በጠቀስነው ጉዳይ ለአራጣው ወንጀል በሕግ የተቀመጠው ክስ የማቅረቢያ ጊዜ (ይርጋው) አልፏል እንበል። በዚህ ሁኔታ በአራጣው ወንጀል ክስ መስርቶ ተከሳሾቹን ጥፋተኛ ማስባል እንደማይቻል እሙን ነው። ይሁንና የመኒ ላውንደሪንግ ክሱን ብቻ በመመስረትና የንብረቱን ሕገ-ወጥ ምንጭ (አራጣውን) በማስረጃ በማረጋገጥ ተከሳሾቹን ጥፋተኛ ማሰኘት ይቻላል።
ነገር ግን አንድ ሰው በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ወንጀል ሲከሰስ የክሱ መነሻ ሆኖ የሚቀርበው አመንጪ ወንጀል መኖሩና ከዚህም ወንጀል ገንዘብ መገኘቱ ተጠቅሶ ይህ የተገኘው ሕገ-ወጥ ገንዘብም ሕጋዊ እንዲመስል በአዋጁ የተጠቀሱት እነዚህ እነዚህ ድርጊቶች ተፈጽመዋል በሚል ነው። እናም በአመንጪው ወንጀል ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ሳይሰጥ እንዴት በመኒ ላውንደሪንግ ወንጀል ሊከሰስ ይችላል የሚል ክርክር መነሳቱ አይቀርም።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከመሰረቱ ሕገ-ወጥ ምንጭ አለው የተባለው “የወንጀል ፍሬ” ተብሎ የሚጠቀሰው ንብረት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከአመንጪው ወንጀል የተገኘ ንብረት ስለመሆኑ አዋጁ ትርጉም አስቀምጦለታል። ከዚህ የምንረዳው አንድ ንብረት የወንጀል ፍሬ ነው ለመባል በቅድሚያ “ወንጀልና ወንጀለኛ” የተፈረጁበት የአመንጪ ወንጀል የጥፋተኝነት ፍርድ ሊኖር እንደሚገባም የሚሞግቱ አሉ።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 11/2012
ገብረክርስቶስ