የአገር ውስጥ ምርቶች ለህብረተሰቡ ሲቀርቡ ከጤንነት ከደህንነት አንጻር ጥራታቸው የተረጋገጠ እንዲሆን ማድረግ ምርትና አገልግሎቶቹ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪና ተፈላጊ እንዲሆኑ ማስቻል ለዚህም አሰራር መዘርጋትና አገልግሎት መስጠት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ አክሪዲቴሽን ጽህፈት ቤት የተሰጡት ስልጣንና ኃላፊነቶች ናቸው፡፡ እነዚህን ኃላፊነቶች ከመወጣት አንጻር ያለበትን ደረጃ አስመልክተን ከዋና ዳይሬክተሩ ከአቶ አርአያ ፍሰሃ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደዚህ አቅርበነዋል፡፡
አዲስ ዘመን፦ ጽህፈት ቤቱ ምን ያህል ኃላፊነቱን እየተወጣ ነውማለት ይቻላል?
አቶ አርዓያ ፦ጽህፈት ቤቱ አክሪዴት የሚያደርገው ተቋማትን ሳይሆን የሚሰሩትን ስራ ነው፤ እነዚህን አገልግሎት ሰጪዎች አለም አቀፋዊ መስፈርት በተከተለ መልኩ በመስራታቸው ዙሪያ ግን የብቃት ምስክርነት በመስጠት እናረጋግጣለን።
ከዚህ አንጻር እስከ አሁን ሜካኒካልና ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግን በተመለከተ ለመፈተሽ የሚችል መሳሪያን ተጠቅመን አገልግሎቱ ብቃትና ጥራት ያለው መሆኑን እያረጋገጥን ነው። ሌላው ኬሚስትሪ ላይ የፍተሻ ላብራቶሪ ኦዲቱ ምን ይመስላል? የሚለውን ለማረጋገጥ ላብራቶሪም መፈተሽ ስላለበት ለዚህም የብቃት ማረጋገጫ እንሰጣለን።
አዲስ ዘመን፦ በተለይም የህክምና ላብራቶ ሪዎችን በመፈተሽ በኩል ሚናችሁን እየተወጣችሁ ነው?
አቶ አርአያ ፦ በባዮሎጂ ዘርፍ የከብት ህክምናን ጨምሮ በየትኛውም የላብራቶሪ ስራ ላይ የተሰማሩ አካላት በዓለም አቀፋዊ መስፈርት ማለትም አይሶ አይ ኤ ሲ እና ኤሌክትሮ ቴክኒካል ኮሚቴ የሚባሉትን በማቀናጀት 17025 የሚባለውን መስፈርት በመጠቀም የአክሪዲቴሽን አገልግሎት እንሰጣለን።
አዲስ ዘመን፦ ካልተሳሳትኩ ይህንን አገልግሎት ላለፉት ስድስትና ከዚያ በላይ ዓመታት ሰጥታችኋልና ያገኛችሁት ተጨባጭ ውጤት እንዴት ይገለጻል?
አቶ አርዓያ ፦ አዎ መጀመሪያ የእኛ ብቃት በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተረጋግጦ እኤአ ከ 2017 እስከ 2023 የሚቆይ የብቃት ማረጋገጫ አግኝተናል።ይህ አለም አቀፋዊ ተቀባይነታችን ደግሞ ጎረቤት አገሮች ድረስ ሄደን አገልግሎቶቻችንን እንድንሰጥ የሚያስችለን ነው።ሆኖም እየሰራን ያለነው የአገር ውስጥ ምርቶች በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖራቸውና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ነው።
በህክምና ላብራቶሪ በኩል ሊሟሉ የሚገባቸው መስፈርቶች ተሟልተዋል አልተሟሉም በማለት እየፈተሽንና ዓለም አቀፋዊ የሆነውን አይሶ 15189 የአክሪዴቴሽን ማረጋገጫ እየሰጠን ነው።ይህ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከተሰሩ ስራዎች መካከል ተጠቃሹ ነው።
በቁጥጥር ስራ ላይ ለተሰማሩ አካላትም የአክሪዲቴሽን አገልግሎት ሰጥተናል፤ ዘርፉን ኢንስፔክት የሚያደርገው አካል እውቀት ብቃት እንዳለውና የሚጠቀምባቸው የመቆጣጠሪያ መሳሪያዎች ብቃት ሊኖራቸው እንደሚገባ ህጉ ያዛል በመሆኑም ይህንን አይሶ 17020 በተሰጠው መስፈርት መሰረት በመመዘን አሟልተው ለተገኙ የአክሪዲቴሽን አገልግሎቱን እየሰጠን እንገኛለን ።
እስከ አሁን ግን አክሪዴት ያደረግናቸው አካላት በሙሉ በምርት ላይ ያተኮሩ ናቸው።አገልግሎት ሰጪና ሌሎች ዘርፎች ላይ ግን አልሰራንም።
አዲስ ዘመን፦ ሌሎቹን አክሪዴት ማድረግ ያልተቻለው ስላልመጡ ፤ ወይንስ እናንተ የመስጠት አቅሙ ስለሌላችሁ ?
አቶ አርአያ፦ አገልግሎቱ ለሁሉም አንድ አይነት ነው።እኛም አለም አቀፍ እውቅናና አቅም ያለን ነን፤ ግን የአሰራር ስርዓቱ ገና የዳበረ ባለመሆኑ አልመጡም።
አዲስ ዘመን ፦ተቋማት ወደ ጽህፈት ቤቱ ላለመምጣታቸው ምክንያቱ ምንድን ነው?
አቶ አርአያ፦ የሚያስገድዳቸው አካል ባለመኖሩ ነው።እንደ አገር የቅንጅት ችግራችንም እዚህ ጋር ሊነሳ ይችላል። ሁሉም በየመስሪያ ቤቱ እንደ መንግስት እንጂ እንደ አንድ አገር ተባብሮና ተሳስሮ ተናብቦ የመስራትና በስራው ዙሪያም ፎረሞች እየተካሄዱ የምንገማገምበት አግባብ የለም።’
ጥራትን የሚለኩት አካላት በሙሉ ያውቁናል ገበያንም መፍጠር የሚችሉት እነርሱ ናቸው ፤ ስለዚህ እኛ አንታወቅም ማለት አንችልም።ምክንያቱም ገዢዎቹ የጥራት ተቆጣጣሪዎቹ በመሆናቸው፤ ስለዚህ ስራውን ከማገዝ አኳያ እነሱ ሚና ሊኖራቸው ይገባል።የተለመደ ከሆነው አካሄድ የሚወጣበትን እይታ መፍጠር ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ዘመናዊ ወደሆነው አሰራር ለመምጣት ታሳቢ ሊደረጉ የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉም እናምናለን።ግን ሙከራዎች ተጠናክረው ካልሄዱ እኛም እንደ ጽህፈት ቤት ተውጠን ከመቅረታችንም በላይ የምናያቸው ምልክቶች አስገዳጅ ስለሆኑ ወይም ስለተለጠፈ ጥራት አለው ማለት ላይሆን ይችላል፤ በመሆኑም መርሆውን ሙሉ የማድረግ ስራ መሰራት አለበት።
አዲስ ዘመን፦ ስለዚህ በየምርቶቹ በላይ የሚለጠፉት የጥራት ደረጃ ምልክቶች ምንም ትርጉም የላቸውም ማለት ነው?
አቶ አርአያ፦ ጥራቱን የጠበቀ ነው ማለት አንችልም።ምክንያቱም ያ እንዲለጥፍ ያደረገው አካል ብቃቱ ተለክቶ እስካልተረጋገጠ ድረስ እርግጠኛ መሆን በጣም አስቸጋሪ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ጽህፈት ቤቱ ከላብራቶሪ በተጨማሪ ሰዎችንም አክሪዴት ያደርጋልና ይህ ስራ ውጤታማ ነው ማለትስ ይቻላል?
አቶ አርአያ፦ አሁን ለምሳሌ ሰዎች በሲኦሲ ብቃታቸው እንዲለካ ይሆናል ፤ አንዳንድ መስሪያ ቤቶችም የባለሙያዎቻቸውን ብቃት በየጊዜው ያስለካሉ።ለምሳሌ የኢንጂነሪንግና የህክምና ባለሙያዎች የሙያ ፍቃዳቸውን በተወሰነ ጊዜ ልዩነት ያሳድሳሉ፤ ግን እዚህ ላይ ለእድሳት በሚመጡበት ወቅት የሰዎቹን የቀደመ የስራ አፈጻጸም የሚያሳይ መረጃ የለም፤ ምናልባት መረጃው በስነ ስርዓት ተደራጅቶ የሚቀመጥበት አግባብ ቢኖር ማን ውጤታማ ነው? የትኛው ደግሞ ስራው ላይ እንዝላልነት አሳይቷል? በዛ ምክንያት በአገርና በተጠቃሚው ላይ ምን ዓይነት ጉዳት ደርሷል? የሚለው ቁልጭ ብሎ ይታይ ነበር።በዚህ መነሻነትም ምን ሲያሻሽሉ ነው ሙያዊ ፍቃዳቸው መታደስ የሚችለው የሚለውን ለመወሰን ያስችል ነበር። ይህ አሰራር ስለሌለ የሙያ ብቃት አረጋጋጭ ተብለው ለተቀመጡ አካላት እኛ የሲኦሲ ስልጠናዎችን እንሰጣለን እንጂ እስከ አሁን መዝኑኝ ብሎ ማመልከቻ የላከልን የለም። ግን የአክሪዲቴሽን አገልግሎት ለመስጠት ከተዘጋጀን አራት ዓመት አስቆጥረናል።
አዲስ ዘመን፦ እነሱ ወደእናንተ ካልመጡ እናንተ መሄድ አትችሉም?
አቶ አርአያ ፦ እኛ ግንዛቤን ከመፍጠር ውጪ ልንመዝናችሁ ኦዲት ልናደርጋችሁ ነው በማለት ስርዓት ልንዘረጋ አንችልም። ይህንን ካደረግን የጥቅም ግጭት ከሌሎች አካላት ጋር ይፈጠራል። ስለዚህ እኛ የምና ደርገው ኦዲት መስፈርቶቻችንና ሊሟሉ የምንፈልጋቸውን ነገሮች እናሳውቃለን እንጂ እገዛ ማድረግና የማማከር ስራ ለመስራት ስርዓቱ አይፈቅድልንም።
አዲስ ዘመን፦ እናንተ ይህንን ማድረግ ካልቻላችሁ ተቋማቱን አክሪዴት ሁኑ ብሎ ማስገደድ የሚችለው ታዲያ ማነው?
አቶ አርአያ ፦ ይህንን ሊያስደርግ የሚችለው መንግስት ወይንም ሌላ አካል ነው።ለምሳሌ ትምህርት ቢሮ የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ( ሲኦሲ) መመዘን ከፈለጋችሁ የእናንተ ብቃት አክሪዴት አድርጉ ብሎ ማዘዝ ይችላል።ጽህፈት ቤቱ ግን ማስገደድ አይችልም።ካስገደደ ተቆጣጣሪ ሊሆን ነው ፤ ስለዚህ እኛ ተቆጣጣሪ አይደለንም የሚቆጣጠር ሌላ አካል አለ ።
አዲስ ዘመን ፦ ወደ እናንተ ጽህፈት ቤት የመጡት ምን ያህል ተመዘኑ ያልመጡትስ ያሉበት ደረጃ ምን ይመስላል?
አቶ አርአያ ፦ እየመጡ ያሉትን እናበረታታለን፤ ግን ሲመጡ በውስን ስራቸው ነው ፤ አክሪዴትድ ሆኗል ይህ ላብራቶሪ ስንል የትኛው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፤ በመሆኑም ተቆጣጣሪው አካል ተቋማት መስፈርቱን አሟልተው እንዲመጡ ክትትል ድጋፍ ቁጥጥር ማድረግ ይገባቸዋል ። ይህንን ማድረግ ባልቻልን ልክ በአንድ አገር ላይ ሁለት አይነት አሰራር ይፈጠራል ።በአገር ውስጥ መስፈርቱን ማለፍ ያቃታቸው ውጪ ሄደው ፍተሻውን አድርገው አክሪዴት ሊሆኑ ነው ።ይህ የምንልበት ተቋማቱን ከገበያ ውጪ ሊያደርጋቸውም ይችላል።
አዲስ ዘመን፦ እዚህ ላይ ግን ውጪ አገር ያሉት በደንብ ስለማይመዝኗቸው ነው ወይስ ሌላ ምክንያት አለው ውጪ ሄደው መመዘናቸው ችግር የሆነው?
አቶ አርአያ ፦ ከውጪ አክሪዴት መሆን ለምርት ሰርተፊኬሽን አጋዥ አይደለም፤ ምክንያቱም ምርት ማለት ሂደቱ ከጥሬ እቃው እስከ ስርጭቱ ነው ፤ የውጪው ይህንን የመከተል እድል የለውም ።በተሰጠው አይነት (ሳምፕል) መሰረት ፍተሻ ብቻ ነው የሚያደርገው፤ ይህ በክትትል እየተሞላና እየተስተካከለ ካልሄደ ውጤቱ እምብዛም ነው።
በሌላ በኩልም እኛ ይህንን ስር ተጠንቅቀን ባልሰራን መጠን የውጭ ምንዛሪ የማምጣት ስራችን ጥላ ያጠላበታል።ምክንያቱም የምንፈልገው የውጭ ምንዛሪ በደመነፍስ የሚመጣ ባለመሆኑ። በሌላ በኩልም ውጪ አይነት (ሳምፕል) መላክ ጊዜ ይወስዳል ፣ ገንዘብ ይፈልጋል ይህ ደግሞ ለኪሳራ ዳርጎ ከገበያ ያስወጣል።በዚህ መልክ ተወዳዳሪነታችንን ደካማ የሚያደርገው በመሆኑ ተከታትሎ ማስተካከል ያስፈልጋል።
ሌላው ችግር ግን ምርታቸውንም ሆነ ላብራቶሪ እቃዎችን አክሪዴት ለማድረግ የማይመጡ አሉ፤ ለምን ቢባል አክሪዴሽን ሳይንሳዊ ስራ ከመሆኑ አንጻር በአግባቡ መስራት ይፈልጋል ፤ ከዚህ አንጻር ደግሞ ለምን እጨቃጨቃለሁ ገንዘቤንም ለምን አወጣለሁ በሚልና አስገዳጅም ባለመሆኑ አይመጡም።
የአሰራር ስርዓት ቢኖር ችግር ሲያጋጥም በጊዜ እየታረመ የጥራት ችግር ያለባቸው ምርቶች በጤና ላይ ጉዳት ሲያስከትሉም በጊዜ ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል።በመሆኑም አክሪዲቴሽን ለህብረተሰቡ በተለይም ደግሞ ለመንግስት ወሳኝ ነው።ለምሳሌ ለአርሶ አደሩ በፊት ዩሪያና ዳፕ ማዳበሪያ ይሰጠው ነበር፤ አሁን ግን ስሌት ተሰርቶ በጎደለው ነው ማዳበሪያ እየተሰጠ ያለው እዚህ ላይ አፈሩን የሚመረምረው አካል ከጎደለ ወይም አሰራሩ ችግር ካለው የተሳሳተ ውጤት ይመጣል ፤ ያን ጊዜ ደግሞ ገበሬው 12 ወራት የለፋበት ከንቱ ስለሚቀር በቴክኖሎጂ መተማመን ይተዋል ።
አዲስ ዘመን፦ አክሪዲቴሽንን ተጠቅመንበት ቢሆን ኖሮ ግን የምናስገባቸውን ቴክኖሎጂዎች በአግባቡ ለማሸጋገር ይረዳን ነበር ማለት ይቻላል?
አቶ አርአያ ፦ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በአግባቡ ለማካሄድና አመኔታን ለማሳደግ አክሪዲቴሽን ጠቃሚ ቢሆንም በዛው ልክ ደግሞ እየተጠቀምንበት አይደለም ።ለዚህ ዋናው ምክንያት ቅንጅት አለመኖር ነው፤ በመሆኑም እንዴት ባለው መልኩ በፖሊሲ ማዕቀፍ ተያይዞ በየትኛው ፕላት ፎርም ተገናኝቶ ነገሮችን እየመረመረና ቴክኒካል ኮሚቴዎችን አዋቅሮ ችግር ሲፈጠርም እያጣራና የመፍትሔ አቅጣጫ እያመላከተ መሄድ አለበት የሚለው በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት የተሰጠው አካሄድን ይፈልጋል።አልያ በየቦታው በጥራት ዙሪያ ስራዎች ቢኖሩም የሚመጣው ለውጥ በጣም አናሳ
ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፦በተለይም በጣም አንገብጋቢ የሆኑት የህክምና መሳሪያዎች ብቃት ላይ ያለው የጥራት ቁጥጥርና ምርመራ ምን ይመስላል? አለስ ለማለት ያስደፍራል?
አቶ አርአያ ፦ ህክምና በጣም ሰፊ ዘርፍ ነው፤ እኛ አሁን እየሰራን ያለንው የሽንት፣የሰገራ፣ አክታ እና የደም ምርመራ (ክሊኒካል ኬሚስትሪ) ላይ ነው። ግን እንደ አልትራሳውንድ፣ራጅና ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶች ብቃት የሚረጋገጥበት አግባብ አልተፈጠረም።
ሌላው ደም ስጡ፣የዓይን ብሌን ለግሱ ይባላል ግን የባንኮቹ ይዘት አልተረጋገጠም ፤ በዚህም ምክንያት ምን ያህሉ ይበላሻል? ምን ያህሉ ደግሞ ጥቅም ላይ ይውላል? የሚለው መረጃ የለም ፤ በመሆኑም አግባብነታቸውና ጥራታቸው መፈተሽ ይኖርበታል።
ሆስፒታል ውስጥ የሚያገለግሉ ባለሙያዎችም በየጊዜው ብቃታቸው እየተረጋገጠ ስልጠናዎች የሚወስዱበት አግባብ የለም። ይህ ሁሉ ሲደመር ደግሞ አሁን ያለንበት ደረጃ የለም የሚያስብል ነው።ማጋነነን ባይሆን ይህ ተቋም እየለመነ አገልግሎቱን እየሰጠ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፦ ግን እኮ በህክምናው ዘርፍ አብዛኞቹ ሆስፒታሎች “የጥራት ደረጃው ተፈትሾ በተረጋገጠ ላብራቶሪ “ አገልግሎት እንሰጣለን እያሉ ነው የሚያስተዋውቁት እርስዎ ደግሞ በዘርፉ ገና ብዙ እንዳልተሰራ ነው እየተናገሩ ያሉት አይጋጭም ?
አቶ አርአያ ፦ ትንሽ ሞክረው ብዙ እንደሰሩ ያወራሉ ፤ ወደዛ ቁጥጥር ከገባን ይህች በጭላንጭል ያለችው ጅምር ትጠፋለች ብለን ስለምንሰጋ ነው እየተንከባከብን ነው የያዝናቸው።ሆኖም አሁን ዘመኑ የቴክኖሎጂ ከመሆኑ አንጻር አብዛኛው ማህበረሰብም ተጠቃሚ ነው ከዚህ አንጻር በይነ መረብ ገብቶ የተቋማቱን ስም አስገብቶ በየትኛው የስራ ዘርፋቸው ላይ ብቃታቸው እንደተረጋገጠ ቢፈትሽ በግልጽ ተቀምጦ ይገኛል። እስከ አሁንም በአገሪቱ ላብራቶሪውን ሙሉ በሙሉ አክሪዴት ያደረገ ሆስፒታል የለም።
አዲስ ዘመን፦ ችግሩ ግን የግንዛቤ ማጣት ወይስ አክርዴት ብንደረግም ባንደረግም የሚጨምርልን ነገር የለም ብሎ ማሰብ?
አቶ አርአያ ፦ ተቆጣጣሪ ባለስልጣናት ማስገደድ ስላልቻሉ ብቻ ነው።በእኛ በኩል ዶክመንተሪ በመስራት በየክልል ላሉ ጤና ቢሮዎች ልከናል።ከዚህ በተጨማሪም ከለውጡ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሆነ የአመራር ሹም ሽረት ስላለ በተቀያየሩ ቁጥር በቶሎ በመሄድና ስለ ጽህፈት ቤቱ በማስረዳት ክፍተት እንዳይፈጠር እየሰራን ነው። ግን 10 በመቶ የሚሆን ውጤት እንኳን አልተገኘም።
እዚህ ላይ ግን መታወቅ ያለበት ነገር ወደ አንድ ተቋም ሄደን ስለ ጽህፈት ቤቱ ስለተናገርን አክሪዴት መሆን ስላለው ጠቀሜታ ስላወራን ብቻ የሚሆን አይደለም።ምክንያቱም አንድ ተቋም በቃ እራሴን አክሪዴት አደርጋለሁ ብሎ ቢነሳ የአሰራር ስርዓቱን ለመዘርጋት በትንሹ ዘጠኝ ወር ይፈልጋል። በመሆኑም የመሪዎች ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ ያስፈልገዋል።ይህ ካልሆነ በለመድነው የአሰራር ስርዓት የሚመጣ አይደለም።
አዲስ ዘመን፦ ከህክምና መሳሪያዎች ሳንወጣ የደም ዓይነት (ሳምፕል) መመርመሪያ (ፒቲ) በአገር ውስጥ አቅራቢዎች አለመኖራቸውና ከውጭ ለማስመጣት ደግሞ ብዙ የውጭ ምንዛሪ መጠየቁ ተቋማት ላብራቶሪዎቻቸውን እንዳያስፈትሹ አድርጓቸዋል ይባላልና እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ አርአያ፦ ይህ ትክክል ነው ፤ ፒቲ ሁለት ዓይነት ነው ስራው። ውስጣዊና ውጫዊ የጥራት መቆጣጠሪያ።ይህ ማለት እቃዎቹ አንድ ሳምፕል ይሰጣቸዋል በዚህም ውስጣዊ ጥራቱን ማረጋገጥ ይቻላል።ውጫዊ ጥራቱን ለመለካት ደግም አንድ ሳምፕል ተሰጥቶ ይሰራ ይባላል ከዛ በኋላ ስራው ተጠናቅቆ ሲገባ በትክክል አስፈላጊው ደረጃ ላይ ከተገባ ውጤቱ ጥሩ ይሆናል አልያም በተቃራኒው ይሆናል ማለት ነው።
ይህንን ነገር እንደ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጥተናቸዋል ለምሳሌ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (ፓስተር) ወደዚህ ስራ እንዲገባ ጠቁመናል፤ በነገራችን ላይ ኢንስቲትዩሽኖች እኮ ተቋቁመዋል። ግን ጥራትን ከማስጠበቅ አንጻር ራቅ አድርገው አያስቡም ፤ አሁን ያሉት በመጠኑም ቢሆን ይሰጣሉ ግን ወደፊት እንዳንወድቅ መጠንቀቅ አለብን ።በመጀመሪያ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ። ናሙናዎች በሚጓጓዙበት ወቅት እንዳይቀየሩ መጠንቀቅ ተጓጉዘው የሚቀመጡበት መመቻቸት አለበት።ይህ ከሆነ በኋላ ደግሞ ግብዓቱን ወደማምረትና ማከፋፈል ይገባል።ይህ ሲሆን በብዙ መጠን ወጪ ይቀንሳል።ኤልሲ አከፋፈት ያስቀራል።
አዲስ ዘመን ፦ ይህ ግብዓት ግን በአገር ውስጥ ሊመረት አይችልም? ይህንን ማድረግ የሚችሉ ኢንስቲትዩሽኖችስ የሉም?
አቶ አርአያ ፦ ለምሳሌ ኬሚካል ኢንስቲትዩሽን ፣ የምግብ ማቀነባበሪያ ፣ የቴክስታይልና ሌዘር፣ ሜዲካል ላብራቶሪ የሚያቀርብ ኢንስቲትዩሽኖች አሉ።እነዚህ ይህንን ስራ መደገፍ አለባቸው። ግን ሲያደርጉ አይታዩም ። እነዚህ ቢተሳሰሩ ቢቀናጁ የበለጠ ጥሩ ይሆናል።
በሌላ በኩል ግን ጥራት ላይ የሚሰሩ አካላት በሙሉ ፖለቲካዊ ተሿሚ መሆናቸው ዘርፉን ጎድቶታል፤ በአንጻሩ ግን በእውቀት በስራው ላይ ብዙ ልምድ በማካበት ቢሾሙ ነው ለአገሪቷም ለስራውም መፍትሔ የሚሆነው።ይህ ደግሞ የአለም ተሞክሮ ነው።
አዲስ ዘመን፦ አክሪዲቴሽን እንደዚህ በሁሉም ዘርፍ አስፈላጊ ከሆነ አገልግሎቱን ለምንድን ነው እየለመነ የሚሰጠው?
አቶ አርአያ ፦ አዎ አክሪዲቴሽን ጽህፈት ቤት በኢትዮጵያ አገልግሎቱን እየለመነ የሚሰጥ ብቸኛ ተቋም ነው።እባካችሁ ምን እናግዛችሁ፣ ስልጠና እንስጣችሁ እንላለን፤ ይህንን ሰምቶ አንድ ተቋም ወደእኛ ማመልከቻ ሲልክ በደስታ ነው የምንቀበለው።የችግሩ መንስኤ ግን አስገዳጅ ያለመሆኑ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ጽህፈት ቤቱ ይህንን ኃላፊነት በብቃት ሊወጣለት የሚችል ባለሙያስ አለው? ይህንን የምለው ከፍተኛ የሆነ የሰራተኞች ፍልሰት አለ የሚባል ነገር ስለሰማሁ ነው፤
አቶ አርአያ ፦ ሰራተኞችን ብቁ ለማድረግ ረዘም ያለ ስራ እንሰራለን። መጀመሪያ በአክሪዲቴሽን መስፈርት መሰረት ይሰለጥናሉ ፤ ካለፉ ቴክኒካሊ ኦዲት ይማራሉ። ይህንን ካለፉ ደግሞ ሞኒተር ይደረጋሉ ቀጥሎም ሞኒተር ተደርገው ብቁ ከሆኑ በኋላ ወደ ስራው ይገባሉ። ሆኖም እንዳልሽው ስራውን ከለመዱት ወይም ብቁ ከሆኑ በኋላ ግን ከእኛ ጋር አይቀመጡም።
አዲስ ዘመን ፦ ለመውጣታቸው ምክንያቱ ምንድን ነው?
አቶ አርአያ ፦ የደመወዝ በቂ ያለመሆን ነው። እንዳይወጡ ከፍተኛ የሆነ ጥረት እናደርጋለን ግን በዛ መልኩ ማቆም ካልቻልን ባሉበት ሆነው እንዴት እንጠቀምባቸው የሚለውን በማሰብ አሁን ላይ የውጭና የውስጥ ሰራተኛ በሚል ከፍለን እየተጠቀምንባቸው ነው።በሌላ በኩል ብቁ ከሆኑ ጽህፈት ቤቱን በትርፍ ጊዜያቸው እንዲያገለግሉ ከዚያም ሲያልፍ ደግሞ ያሉበትን ተቋም ለአክሪዲቴሽን ምዘና እንዲያበቁ በማድረግ እንዲያግዙን እናደርጋለን።
አዲስ ዘመን ፦ ጽህፈት ቤቱ አንድ ስራ ሲሰራ የመገናኛ ብዙሀንን ጠርቶ መግለጫ ከመስጠት ባለፈ ራሱን ለማስተዋወቅ የሄደበት መንገድ አጥጋቢ አይደለም ፤ የሚሉ አሉና እርስዎ የሚመለከታቸውን አካላት ጨምሮ ሌሎችም ያውቁናል ብለው ያስባሉ?
አቶ አርአያ ፦ ልክ ነው በዚህ ላይ ክፍተት አለብን ። ግን ደግሞ ስንጠራቸው የተለያየ ሰው ነው የሚልኩት፤ በዚህ ምክንያት የመጣው ሁሉ ለተቋሙ ስራ አዲስ ይሆናል።በመሆኑም አንድ ተቋም ወርክሾፕ ላይም ይሁን ሌላ ተልዕኮ ሰጥቶ ሰራተኛ ሲልክ ለምን እንደላከ ማሳወቅና ሲመለስም ለሌሎች መረጃ የሚሰጥበት አግባብ አለመዘርጋቱ የእኛም ተቋም እንዳይታወቅ እንቅፋት ፈጥሯል።
የራሴን ተሞክሮ ብነግርሽ አንድ ቦታ ሄጄ ስብሰባ ስሳተፍ ወደ ተቋሜ ስመለስ መጀመሪያ የማደርገው ለማኔጅመንቱ ስለነበረው ሁኔታ አጭር ሪፖርት ማቅረብ ነው።ማኔጅመንቱ ደግሞ በስሩ ላሉ ሰራተኞቹ የሰማውን ያካፍላል ።ይህ ሁኔታ የበታች ሰራተኞችም ሲሄዱ በተመሳሳይ ተግባራዊ የሚደረግ አሰራር ነው።ከዚህ በኋላ በዛ ስብሰባ ላይ ዳግም የሚሄድ ሰው የቀደመ ታሪኩን ስለሚያውቅ ለጉዳዩ አዲስ አይሆንም። ስራዎችም ይሳለጣሉ ማወቅና መተዋወቅ ካለብን ተቋማትና ሰራተኞች ጋር የቅርብ ግንኙነት ይኖረናል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፦ ምናልባት ይህ ተቋማት ለተቋማት ለሚያደርጉት ግንኙነት ይጠቅም ይሆናል፤ ግን ማንኛውም ሰው ስለጽህፈት ቤቱ ማወቅ የለበትም?
አቶ አርአያ ፦ አዎ ሁሉም ሊያውቀው ይገባል እኛም በዚህ ልክ መንቀሳቀስ አለብን። መገናኛ ብዙሀንንም በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል። ይህንንም እንደ እጥረት ወስደን እናስተካክላለን።
አዲስ ዘመን፦ እዚህ የእናንተ ጽህፈት ቤት ባለበት ግቢ ውስጥ እንኳን ደረጃዎች ኤጀንሲ፣ተስማሚነት ምዘና፣ስነ ልክ አለ ፤ ይህ እንደው የሀላፊነት መደራረብ እያስከተለ አይደለም፤ ተናበን እየሰራንስ ነው ትላላችሁ?
አቶ አርአያ ፦ አዲስ ለሆነ ሰው ሁሉም ተቋማት ተመሳሳይ ስራ የሚሰሩ ሊመስል ይችላል ።ግን ሁሉም የራሳቸው የስራ ድርሻና ሀላፊነት አላቸው ።ደረጃዎች ኤጀንሲ በሚያወጣላቸው የመገምገሚያ መስፈርት መሰረት ደግሞ ስራቸውን እየቃኙ ሀላፊነታቸውን ይወጣሉ።
በነገራችን ላይ ሁሉም ስለ ጥራት የሚያወሩ በመሆኑ የተወራረሰ አሰራር አላቸው ግን ከውሳኔ ሰጪነትና ከስራ ተሳትፎ አንጻር የየራሳቸው ግዴታ አላቸው።
አዲስ ዘመን ፦አክሪዲቴሽን ግን ምን ያህል በስራው ውጤታማ ነው ? ጽህፈት ቤቱንስ የሚገመግመው አካል አለ ?
አቶ አርአያ፦ አክሪዲቴሽን በበላይ ሆኖ ብቃትን ይቆጣጠራል። ግን የእሱ የመገምገም ብቃት አይታይም ማለት አይደለም። እሱንም የአፍሪካ አክሪዲቴሽን በሰጠው መስፈርት መሰረት እየሰራ መሆኑን ያየዋል፤ እነሱን ደግሞ አለም አቀፉ አክሪዴቴሽን ያየዋል።በዚህ መልክ ዓለም አቀፍ ግንኙነቱ አለ።
አዲስ ዘመን፦ አንዳንዶች ተቋሙ የተጣለበትን ኃላፊነት እየተወጣ ስላይደለ አስፈላጊ አይደለም ይላሉና ጽህፈት ቤቱ እንደ አገር አስፈላጊነቱ እንዴት ይገለጻል?
አቶ አርአያ ፦ በጣም አስፈላጊ ነው። አክሪዴትድ ያልሆነ ምርት አለም አቀፍ ገበያ መሄድ አይችልም።አክሪዲቴሽን ከውጭ እንጠይቅ ከተባለ ደግሞ በጣም ውድ ነው። ይህ ድርጅት ባይኖርና እያንዳንዱ ተቋም ከውጭ አገር አክሪዲቴሽን ላስመጣ ቢል አገሪቱ ከማትወጣው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ውስጥ ትገባለች።ከዚህ አንጻር ድርጅቱ በጣም ወሳኝ ነው።
ሌላው ከውጭ አክሪዴት ሆኖ የመጣ ምርት ዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተቀባይነት ቢያጣ ይግባኝ ብሎ የሚቆምለት የሚሟገትለት አይኖርም ፤ ስለዚህ ፖለቲካሊም ሆነ ኢኮኖሚካሊ ለአገሪቷ መሰረታዊ ነው።አክሪዲቴሽን ተጨባጭ እውነታን በአንድ ነገር ላይ ያቀርባል ፤ የሚጨበጥ መረጃም ያለው በመሆኑ ያንን ወስዶ ፖሊሲ ለማሻሻል፣ ህግ ለማስተካከል፣ አዲስ ህግ ለማርቀቅ ተጨባጭ የሆነ መረጃን ስለሚያቀብል ለመንግስት በስራው መተማመን ይፈጥራል።
አዲስ ዘመን፦ በዚህ ደረጃ አስፈላጊ ከሆነ ከማን ምን ይጠበቅ?
አቶ አርአያ ፦ በመጀመሪያ የቅንጅት ስራ ይሰራ ፤ ይህ የሚጀምረው ደግሞ ሁሉም ተቆጣጣሪ አክሪዲቴሽን ለስራችን ጠቃሚ ነው ብለው ማመን መቻል አለባቸው።አሁን ግን ይህ ሁኔታ ስለሌለ ክፍተቱ የሰፋ ነው።
አዲስ ዘመን፦ጽህፈት ቤቱ ባይኖር ኖሮ ይህ ይጎድል ነበር፤ በመኖሩ ደግሞ እንደዚህ ያለውን ችግር ቀርፏል የሚሉት አለ?
አቶ አርአያ ፦ ጽህፈት ቤቱ ሳይፈጠር ጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ውጤቶች አምራቾች የተሳተፉበት አንድ መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር፤ በመድረኩ ላይ አክሪዲቴሽን የሚባል ተቋም አገር ውስጥ አለመኖሩ እየጎዳን ነው፤ ከገበያ እየወጣን ነው ሲሉ ዋሉ ፤ ከዛም ጽህፈት ቤቱ ተቋቋመና ወደ ስራ ገባ ሆኖም እንደዛ ሲጮሁ የነበሩት ሁሉ ብቅ አላሉም።ተቀስቅሰው እንኳን መምጣት አልቻሉም።
በመሆኑም ተቋሙ ባይኖር ኖሮ በየመድረኩ ለንግድ ስራችን መዳከም እንደ ምክንያት ተደርጎ ሲወራ ይኖር ነበር። ስለዚህ አሁን መፈጠሩ የንግድ መሰረታዊ ችግር የቱ ጋር ነው የሚለውን ለመለየት አስችሏል።
አዲስ ዘመን፦ እንደ አገር በጥራት ቁጥጥር ስራችን የት ላይ ነን ማለት ይቻላል?
አቶ አርአያ ፦ ገና ዳዴ ላይ ነን።
አዲስ ዘመን ፦ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ አርአያ፦ እኔም በጣም አመሰግናለሁ!
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 11/2012
እፀገነት አክሊሉ