ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ ፋይናል ኤግዛም ስላለኝ በጠዋት ተነሳሁ፡፡ አንዳች ነገር ጸሎት እንዳደርግ ገፋፋኝ፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ጸሎት ያደረኩት ከሁለት ወር በፊት ሚድ ኤግዛም ስንፈተን ነው፡፡ በገዛ እጄ ፈተናውን ሳልፈተን እንዳልቀር ሰግቼ ‹‹አባታችን ሆይ …›› ስል ‹‹ወደፈተናም አታግባን›› የምትለዋን ክፍል ዘለልኳት፡፡ በሶ ሳልበጠብጥ ሆዴ እየተበጠበጠ ከዶርም ወጣሁ፤ ለማጥናት፡፡
ለፈተና ዝግጅት ማድረግ የምጀምረው ፈተናው በሚሰጥበት ዕለት ነው፡፡ የሲሳይ ንጉሱ ‹‹ሰመመን›› ላይ እንዳለው ድብርት የተባለ ገጸ ባህሪ ፈተና እስኪጀመር ድረስ ያሉትን ደቂቃዎች እጠቀማለሁ፡፡ ደግሞ የትም ቦታ ማጥናት እችላለሁ፡፡ ነገር ግን ከተቀሩት ተማሪዎች ለመስተካከል ላለመለየት ቤተ መጻሕፍት ገብቼ ማጥናት ጀመርኩ፡፡ ብዙም ሳልቆይ የቤተ መጻሕፍቱ ጩኸትና ‹‹ንጹህ አየር›› ምቾት ነሳኝ፡፡ ወጣሁ፡፡ የተማሪ መማሪያ ክፍሎች ወደ ሆኑት አዳራሾች (በተማሪዎች አጠራር ስፔስ) ሄጄ ለማጥናት ወስኜ ጎራ አልኩ፡፡ በየወንበሩ ላይ ተማሪ ሳይሆን ጭንቀት ተቀምጧል፡፡ ጨነቀኝ፡፡ ወጣሁ፡፡
አገልግሎት ለመስጠት ሳይሆን ለግቢው ውበት ከተተከሉት የህዝብ ስልኮች አንዱን ተደግፌ አሰላሰልኩና ዶርም ለማጥናት ወሰንኩ፡፡ ለአራት ሰዎች ተበጅታ ስድስት ሆነን ተንደላቀን የምንኖርባት ዶርማችን ራሷን ጥላ ጠበቀችኝ፡፡ ቁጢጥ ከማለቴ ዕረፍት ላይ ያሉ ጫማዎችና ያልታጠቡ ካልሲዎች ጠረን ጠራኝ፡፡ በወንዶች ዶርም ሊገኝ የሚችለው ብቸኛው የታጠበ ነገር ፎቶ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እዚህም አልተሳካም፡፡ ብቻዬን ልሆን የምችልበትን ቦታ ሳስብ ቆየሁ፡፡ መጸዳጃ ቤት ምቹ ቦታ ሆኖ ታየኝ፡፡ ተነሳሁ፡፡ ጊዜያዊ በሚል ማጽናኛ ወደሚጠራው ቋሚ የቆርቆሮ መጸዳጃ ቤታችን አመራው፤ ለማጥናት፡፡
አዲሱ ቤተ መጻሕፍታችን ሥራ የጀመረ ሰሞን ከምሥራቅ አፍሪካ አንደኛ ነው የሚል ወሬ ሰምቼ ስስቅ አመሸሁ፡፡ እንደ እኔ ዩኒቨርሲቲያችንን ከምሥራቅ አፍሪካ አንደኛ የሚያሰኘው ዘጠኝ ዓመት ሙሉ ጊዜያዊ እየተባለ የሚጠራው ቋሚ የቆርቆሮ መጸዳጃ ቤታችን ነው፡፡ በእርግጥ አዲሱ ቤተ መጻሕፍት ግሩም ነው፡፡ ነገር ግን ከምሥራቅ አፍሪካ አንደኛ ሊሆን አይችልም፡፡ ምሥራቅ አፍሪካ እኮ ሰፈር አይደለም፡፡ በትንሽ ትልቁ ከእነ ኬንያ ጋር መወዳደሩ እንደ አምስት ሺና አስር ሺ ሜትር ሩጫ ቀላል አይደለም፡፡
መጸዳጃ ቤት ተቀምጬ ከአጎራባች ተቀማጮች የሚሰሙ ለየት ያሉ ድምፆችን እንደ ማጀቢያ ሙዚቃ ተጠቅሜ ማጥናት ጀመርኩ፡፡ ‹‹መልካም መዓዛውን›› ተቋቁሜ ትንሽ ካነበብኩ በኋላ መሰናክሎች በዙብኝ፡፡ ከጉድጓዱ የሚወጣው እንፋሎት ቀቀለኝ፡፡ ይህን እንፋሎት በአግባቡ መጠቀም ቢቻል የከተማዋን የኃይል አቅርቦት ችግር መቅረፍ ይቻል ነበር፡፡ እዚህ መጸዳጃ ቤት ገብቶ የወጣ ሰው ጠረን ፣ ተቀምጦ ሳይሆን ተጠምቆ ወጣ ያሰኛል፡፡ ከመግባቱ በፊት የነበረውን ጠረን ለመመለስ ወይራ መታጠን አለበት፡፡ አብዛኞቹ በከተማው የሚገኙ ዶደራንትና ሽቶ ቸብቻቢ የኮስሞቲክስ ሱቆች የተከፈቱት ከዚህ መጸዳጃ ቤት በኋላ ነው፡፡
በየደቂቃው የሚያንኳኳው ተማሪ ሌላኛው እልህ አስጨራሽ አደናቃፊ ነው፡፡ ምላሽ ፈላጊ ማጀቢያ ሙዚቃ እንዳለ የገባኝ ይህን ጊዜ ነው፡፡ በተንኳኳ ቁጥር ሰው አለ እያልኩ ቆየሁ፡፡ በታከተኝ ሰዓት ከጣቶቹ ይልቅ በድምፁ የተማመነ ሽንተኛ መጣ፡፡ ከፍ ባለ ድምፅ ‹‹ሰው አለ?›› ሲል የለም አልኩት፡፡ አንኳኪው በሩን ገፍቶ ሊገባ ታገለኝ፡፡ በኋላ ወደ ቀልቡ ሲመለስ ነው መሰል ትቶኝ ሄደ፡፡
የመፀዳጃ ቤት ቆይታዬ እንዳሰብኩት ባለመሆኑ እየተማረርኩ ወጣሁ፡፡ ብርድ ብርድ ስላለኝ ፀሐይ ለመሞቅ ልብስ አስጥተው ፀሐይ ላይ የተሰጡ ተማሪዎችን ተቀላቀልኩ፡፡ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ እያለሁ እነዚህ ተማሪዎች ከተሰጣ ልብሳቸው ጋር አብረው የሚደርቁበት ምክንያት አይገባኝም ነበር፡፡ አንድ ዕለት በአካባቢው ሳልፍ በስልክ የሚያወራ ተማሪ ‹‹አሁን መምጣት አልችልም ልብስ አስጥቼ እየጠበኩ ነው›› ሲል ሰማሁት፡፡ ስልኩን እስኪጨርስ ጠብቄ ሌባ አለ እንዴ አልኩት፡፡ ገርመም አደረገኝና ‹‹አይ የፍሬሽ ነገር›› አለ፡፡ ቀጠለ፡፡ ‹‹እዚህ እኮ የተማረ ማህበረሰብ ነው ያለው፡፡ አየህ ተማሪው አርስ በርሱ ይተሳሰባል፡፡ አብዛኞቻችን እንደልብ የምንቀያይረው ልብስ የለንም፡፡ ስለዚህ አንዳችን የአንዳችንን እንለብሳለን፡፡ አንተ አንድ ልብስ አጥበህ ስታሰጣ የወደዳት ሌላ ተማሪ እስክትደርቅ ጠብቆ ይወስዳታል፡፡ አንድ ሳምንት ለብሶ አጥቦ እዚያው ያገኘበት ቦታ ያሰጣታል፡፡ አሁን እኔ ልብሴን ማን እንደሚወስድ እያየሁ ነው፡፡ እግረ መንገዴንም በቀጣዩ ሳምንት የምለብሰውን ሸሚዝ ሌሎች አጥበው ከሚያሰጡት እየመረጥኩ›› አለኝ፡፡
ፀሐዩ ሲበቃኝ በከተማው ካሉት ካፌዎች በአንዱ ለማጥናት መንገድ ጀመርኩ፡፡ መንገድ ዳር የቆመ የማስታወቂያ ሰሌዳ ጋር ደረስኩ፡፡ በርከት ያሉ ተማሪዎች እንደ ንብ ወረውት ያነበንባሉ፡፡ የወራሪዎቹ ቁጥር እስኪቀንስ ጠብቄ ጠጋ ብዬ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ በተማሪዎች ላይ የዲሲፕሊን ዕርምጃ መወሰዱን የሚያትት ጽሑፍ ነው፡፡ የዲሲፕሊን ዕርምጃው ለምን እንደተወሰደ የሚገልጸው ዓረፍተ ነገር ለግቢው ውበት የተተከለውን ሳር በመደቅደቃቸው ብሎ ይጀምራል፡፡ መደቅደቅ የሚል ቃል መደበኛ ቋንቋ ውስጥ መኖሩን ተጠራጠርኩ፡፡ የመደቅደቅን ፍቺ ባለመረዳቴ ኮብልስቶኑን ደቀደቅህ ተብዬ እንዳልከሰስ በጥንቃቄ እየረገጥኩ መንገዴን ቀጠልኩ፡፡
ዋናው በር ላይ ስደርስ አራት ጥበቃዎች ተመለከትኩ፡፡ ጥበቃዎቹ አዲስ በወጣ ደንብ የተማሪዎችን ስነ ምግባር በመቆጣጠር ረገድ ከፍ ያለ ስልጣን እንደተሰጣቸው ይነገራል፡፡ አዲስ ስለወጣው ደንብ ተማሪው ምንም አያውቅም፡፡ ክልክል ነው እየተባለ ከነሱ አፍ ከሚወጣው በቀር በውል የታወቀ ነገር የለም፡፡ የግቢያችን ጥበቃዎች በምን ምክንያት እንደሚቆጡና መታወቂያ እንደሚቀበሉ አይታወቅም፡፡ አንዳንዶቹ ዘና ያለ አሊያም የዘነጠ ተማሪ ሲያዩ ዓይናቸው ይቀላል፡፡ ስለዚህ ብዙ ተማሪዎች በር አካባቢ ምስኪን ለመምሰል አንገት ሰብሮ መሬት እያዩ መጓዝን ልማድ እያደረጉ ነው፡፡
ከሳምንት በፊት ከበግ ተራ ትንሽ ከፍ ብሎ ወንድና ሴት ተማሪዎች እጆቻቸውን ቁልቁል ወርውረው የመጨረሻዋን ጣታቸውን አቆላልፈው ወክ ሲያደርጉ ነበር፡፡ ግቢውን እየቃኙ ከነበሩት ጥበቃዎች አንዱ ቁሙ አላቸው፡፡ ጥንዶቹ ተገርመው ‹‹ምን አጠፋን?›› አሉ፡፡ ጥበቃው በቁጣ ‹‹ኮንታክት አድርጋችኋል›› አለ፡፡ እንግዲህ አዲስ በወጣው ደንብ ኮንታክት አታድርጉ የሚል ሕግ ይኑር አይኑር የማያውቁት ተማሪዎች ጥበቃውን ተለማምጠውና ይቅርታ ጠይቀው ‹‹ኮንታክት›› ሳያደርጉ ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡
በሩን አልፌ ባጃጅ ለመያዝ ረጅሙን ሰልፍ ተቀላቀልኩ፡፡ ባጃጅ ነጂዎቹ ሰልፍ የያዘው ሰው የትም አይሄድብንም፤ ቆሞ ይጠብቀናል፡፡ ይልቅስ ሰልፉ ተስፋ አስቆርጧቸው መንገድ የጀመሩት ሰዎች እንዳያመልጡን እያሉ ሰልፈኛውን ትተው ዞረው ይለቅሟቸዋል፡፡ ሰዓቴን ተመለከትኩ፡፡ መፈተኛ ሰዓቴ እየደረሰ ነው፡፡ ፊቴን ወደ ዩኒቨርሲቲያችን መለስኩ፡፡ ፈተናው እስኪ ጀመር ድረስ መፈተኛ ክፍላችን ውስለ ማጥናት፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 2/2011
የትናየት ፈሩ