ከኤዞፕ ተረቶች አንዱ እንዲህ ይላል።በአንድ የገጠር መንደር ውስጥ የሚኖሩ ድሃ ባልና ሚስት ገበሬዎች ነበሩ።ከዕለታት አንድ ቀን ከሚያረቧቸው ዶሮዎች መካከል አንዷ የወርቅ እንቁላል ጣለች።ገበሬዎቹ ባልና ሚስቶች በሆነው ነገር እየተደነቁ እንቁላሉ የወርቅ መሆኑ እንዲመረመር የመንደሩ ሊቅ ወደ ሆኑ አዛውንት ዘንድ ወሰዱት።አዛውንቱም እንቁላሉ ንጹህ ወርቅ እንደሆነ ነገሯቸው፡፡
ባልና ሚስቱ እንቁላሉን ለወርቅ ነጋዴዎች በውድ ዋጋ ሸጡት።በማግስቱም ዶሮዋ ሌላ የወርቅ እንቁላል ጣለች፤ በቀጣዮቹ ቀናትም እንዲሁ።ገበሬዎቹ ባልና ሚስቶች በገጠማቸው እድል እየተደሰቱ በየቀኑ አንድ የወርቅ እንቁላል እያገኙ በሀብት ደረጁ።ከቀን ቀን ሀብታቸው እየጨመረ ሲመጣ አባወራው በየቀኑ አንድ አንድ እንቁላል ከመልቀም ይልቅ በአንድ ቀን ብዙ የወርቅ እንቁላል ማግኘትን ተመኘ።
እንዲህም አለ “ይህች ዶሮ በአንድ ቀን የምትጥለው አንድ የወርቅ እንቁላል ብቻ ነው።ባርዳት ግን ሆዷ ውስጥ ያለውን የወርቅ እንቁላል በሙሉ በአንድ ጊዜ ማግኘት እችላለሁ”።ሚስቱን ጠርቶ ሀሳቡን አካፈላት።ባለቤቱ ዶሮዋን እንዳያርዳት አጥብቃ ብትለምነውም አሻፈረኝ አለ።በመጨረሻም የወርቅ እንቁላል የምትጥልላቸውን ዶሮ አረዳት፣ ነገር ግን ከሆዷ አንድም እንቁላል አላገኘም።
አባወራው ገበሬ የወርቅ እንቁላሉን ማግኘት የሚችለው ዶሮዋ ስትኖር ብቻ መሆኑን ዘንግቷል።ቅጥ ያጣ የገንዘብ ፍቅር በአንድ ቀን የመክበር ጉጉቱ ውስጥ ዘፍቆት ማመዛዘን እንዳይችል ስላደረገው ዶሮዋን አረደ።አሁን ምን ይውጠዋል ? እጁ ላይ ያለችው ጥሪት ስታልቅ ወደ ቀደመ ህይወቱ ሊመለስ ነው።ግና እንደ ቀድሞ የድህነት ህይወቱን አሜን ብሎ ተቀብሎ መምራት አይችልም።ምቾትን፣ ባለጸግነትንና ማዘዝን ለምዷላ።መውረድ ወደ ላይ እንደመውጣት ቀላል አይደለም።ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “መሰላል” በተሰኘ ግጥማቸው ወጥቶ ስለመውርድ አንዲህ ይላሉ፡፡
ዘርግተው የጨበጡትን መርገጥ፤
የመውጣት ሕግ ነው የማይለወጥ፤
ሲወርዱ ግን ያስፈራል፤
የረገጡትን ያስጨብጣል፡፡
የወቅቱ የአገራችን ሁኔታም ይሄው ነው።በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች መቶ በመቶ በአንድ ፓርቲ በተሞላ ፓርላማ በሚወጡ አፋኝ ሕጎች ተጠርንፈው፣ ሀሳባቸውን በነጻነት መግለጽ ሳይችሉ አባላቶቻቸው እየታሰሩ፤ እየተሰደዱና እየተገደሉባቸው ተሸማቀው ይኖሩ ነበር።የአገሪቷ ህዝቦችም አፈናና አድሎ እንዲቆም መሰዋትነት እየከፈሉ ይታገሉ ነበር።ከእለታት አንድ ቀን አገሪቱን እየገዛ ካለው ፓርቲ ውስጥ የወጣ አንድ ቡድን የህዝቡን ጥያቄ አድምጦ ከዚህ በኋላ በመጣንበት መንገድ መጓዝ የለብንም ብሎ መሪውን ያዘ፡፡
ቀን ሄዶ ቀን መጣ።ጭቁኖቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን በነጻነት መግለጽ ቻሉ።ገሚሶቹ በየጨለማ ቤቱ የታሰሩት ሰዎቻቸው ተለቀቁላቸው።ኑሯቸውን በዱር በገደል ያደረጉም አገራቸው ገብተው በነጻነት መንቀሳቀስ ጀመሩ።የሚደግፋቸው ህዝብም በነቂስ ወጥቶ ሆ ብሎ ተቀበላቸው።
ውሎ ሲያድር ከሕዝብ እያገኙት ያለው ድጋፍ በሂደት እንዳይቀዘቅዝ የሰጉት እነዚህ ፖለቲከኞች እንደጋለ ቀጥቅጠው ወንበር ሊያደርጉት ቋመጡ።ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብታቸውን “ተጠቅመው” ለተከታዮቻቸው የሚባለውንም የማይ ባለውንም አሉ። እኒህ በስልጣን ፍቅር የታወሩ ፖለቲከኞች በሕጋዊ ሂደቶች ስልጣን ከማግኘት ይልቅ በአንድ ጀንበር ወንበሩ ላይ ጉብ ለማለት ሲሉ የወርቅ እንቁላል የምትጥልለትን ዶሮ እንዳረደው ገበሬ አገሪቱን ለማፍረስ አስፍስፈዋል።ተዉ የሚሏቸውን ለመስማት ፍቃደኛ አይደሉም።የአገር መሪ መሆን የሚቻለው አገር ስትኖር ብቻ መሆኑን ዘንግተዋል።በአጭሩ “መጀመሪያ የመቀመጫዬን” ካለችው ዝንጀሮ አንሰዋል።አገሪቱ ከፈረሰች በኋላ አሁን ያላቸውን አይነት ሚና እንኳን ሊኖራቸው እንደማይችል አልተረዱም።እንደ ቀድሞ ጭቁን ሆኖ የመኖር ዕጣም አይገጥማቸውም።
ሲወርዱ ግን ያስፈራል፤
የረገጡትን ያስጨብጣል።ይሆናል ነገሩ።
የትናንቶቹ ጭቁኖች ገና ስልጣን ላይ ሳይወጡ የነበረውን የሚያስንቁ ጨቋኞች መሆናቸው ያስገርማል።ዛሬ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ማህበራዊ መሰረት አለን ብለው በሚያምኑበት አካባቢ ሌሎች ፓርቲዎች ተንቀሳቅሰው ሀሳባቸውን በነጻነት እንዳይገልጹ አባላቶቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን እያሰማሩ የሽብር ተግባር እየፈጸሙ ነው።ምርጫው ከመካሄዱ በፊት አሸናፊዎች መሆናቸውን እያወጁ ነው።ከእነርሱ የተለየ ሀሳብ የሚያቀርቡትን “ባንዳ” እያሉ በመጥራት ከህዝብ ለመነጠል እየሰሩ ነው።
“እዚህ አካባቢ ድርሽ ትሉና ወየውላችሁ” እያሉ የሚዝቱ በዝተዋል።“በዚህ አካባቢ ላካሂድ የነበረውን የህዝብ ስብሰባ እከሌ የተባለ ፓርቲ አባላቶቹንና ደጋፊዎቹን በመላክ አስተጓጎለብኝ” የሚል ክስ የሚያቀርቡ ፓርቲዎች ቁጥር ጨምራል። አንዱን የፖለቲካ ድርጅት ከአንድ አካባቢ ያባረረው ፓርቲ ከሌላ አካባቢ በሌላ የፖለቲካ ድርጅት ተባረርኩ እያለ ክስ ሲያቀርብ እየሰማን ነው።የመንግስት አካልም አባሪ በመሆን “ወደ አካባቢው መጥታችሁ ችግር ቢፈጠር ለደህንነታችሁ ማረጋገጫ መስጠት አልችልም” የሚል ምላሽ እስከመስጠት ደርሷል፡፡
ይሄ ሁሉ ውዥንብር ከክርስቶስ ልደት በፊት የኖረው ኤዞፕ የጻፈውን የወርቅ እንቁላል የምትጥል ዶሮ ታሪክ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ገቢር ለማድረግ የሚደረግ ጉዞ ነው።የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ክፍል 2 አንቀፅ 32 (1) ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወር መብት እንዳለው በግልጽ አስቀምጧል። በተመሳሳይ ሁኔታ በሕገ መንግሥቱ ክፍል አንድ አንቀጽ 14 እና ክፍል 2 አንቀፅ 29 (1) እንደተደነገገው ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈር የአካል ደኅንነትና የነጻነት መብት አለው፣ ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል። እንዲሁም ይህ ነጻነት ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በህትመት አሊያም በመረጠው በማንኛውም የማሠራጫ ዘዴ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሠራጨት ነጻነቶችን እንደሚያካትት በሕገ መንግሥቱ ሠፍሯል።
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 30(1) ለማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብትን አጎናጽፏል። ኢትዮጵያ የተቀበለችው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም ዓቀፍ ቃል ኪዳን በአንቀፅ 19 ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የራሱ አስተያየት ሊኖረውና አስተያየቱን የመግለፅ መብት፣ እንዲሁም በዚሁ ቃል ኪዳን አንቀፅ 21 ማንኛውም ሰው ሰላማዊ ስብሰባ የማድረግ መብት እንዳለው በመግለጽ ይህንንም መብት የቃል ኪዳኑ ፈራሚ ሐገራት እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ ያስገድዳል።
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለችው የአፍሪካ የግለሰብና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር አንቀፅ 11 ማንኛውም ሰው ሐሳቡን ለመግለጽ በነጻነት መሰብሰብ እንደሚችል በመግለጽ እነዚህንም መብቶች የማክበርና የማስከበር መብቶቹ የሚከበሩባቸውን ሁኔታዎች የማሟላት ግዴታ በአባል አገራት ላይ ይጥላል። እነዚህን የዜጎችን የአካል ደኅንነትና ነጻነት መብቶች የመጠበቅ ኃላፊነት በግንባር ቀደምትነት የተጣለበት መንግሥት ነው። አገሪቱ የወርቅ እንቁላል ጣይዋ ዶሮ እጣ እንዳይገጥማት መንግስት የህግ የበላይነትን በማስከበር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ኃላፊነቱን ለመወጣት መንቀሳቀስ አለበት።
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 11/2012
የትናየት ፈሩ