በታላቅ መድረክ የደመቀችው ኢትዮጵያዊት

ኢትዮጵያ በፋሽንና ሞዴሊንግ ኢንደስትሪ ውስጥ ኋላ ከቀሩ ሀገራት አንዷ ብትሆንም በዘርፉ ያልተነካ እምቅ አቅም እንዳላት ይታመናል። ይህን እምቅ አቅም ጥቂቶች በግል ጥረታቸው አልፎ አልፎም ቢሆን አበረታች ውጤት ሲያስመዘግቡ ይታያል። በሞዴሊንግና ፋሽን ኢንደስትሪው ዘርፍ ደፍረው በመግባት ብዙ መሰናክሎችን አልፈው ከራሳቸው አልፈው ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ያስተዋወቁና ስሟን ያስጠሩ ወጣቶች በየዘመኑ ይፈጠራሉ።

ከነዚህ አንዷ በቅርቡ በትልቅ ዓለም አቀፍ የቁንጅና ውድድር ማንፀባረቅ የቻለችው ወጣት ሞዴል ሐሴት ደረጄ የዘመኑ ፈርጥ መሆን ችላለች። በቅርቡ በሕንድ በተካሄደው 72ኛው “ሚስ ወርልድ” የቁንጅና ውድድር ኢትዮጵያን የወከለችው ሐሴት ደረጄ ከዓለም ሁለተኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ አንደኛ በመሆን ወደ ሀገሯ ተመልሳለች። ባለፈው ሐሙስ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ስትደርስም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ በርካቶች የክብር አቀባበል አድርገውላታል።

“ኢትዮጵያን የመሰለች ታላቅ ሀገር መወከል ከባድ ኃላፊነት አለው” የምትለው ሞዴል ሐሴት ደረጄ፣ ብርቱ ፉክክር በሚደረግበት ዓለም አቀፍ ውድድር ሀገርን መወከል ክብር እንደሆነ ትናገራለች። “ኢትዮጵያን የመሰለች ብዙ ባህልን ከተለያዩ እሴቶች ጋር የያዘች ሀገርን መወከል ትልቅ ክብር ነው፤ ከከባድ ኃላፊነት ጋር የሚሰጥም ነው” ስትል ትገልጻለች።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ2ኛ ዓመት የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ የሆነችው ሐሴት፣ “ሀገርን በመወከል ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ተግባር በጥንቃቄ መከወን አለበት፣ ምንም ባደርግ ‘ሐሴት አደረገች’ ሳይሆን ኢትዮጵያ ነው የሚባለው፤ ከስሜ ይልቅ ሚስ ኢትዮጵያ የሚሉኝም ይበዛሉ። ሀገርን እንደመሸከማችን የኢትዮጵያን ስም የሚመጥን፣ ክብሯንም ከፍ የሚያደርግ ተግባራትን መፈፀም ግድ ይለኝ ነበር” በማለት ተናግራለች።

በስፋት ስለ ኢትዮጵያ የምታብራራው ሐሴት፣ ከውድድሩ በኋላም ኢትዮጵያ ለዓለም የምታስተዋውቃቸው በርካታ ፀጋዎች ያሏት ሀገር መሆኗን ጠቅሳ አብዛኛው ዓለም የሰው ዘር እንዲሁም የቡና መገኛ ምድር መሆኗን እንኳን አያውቅም ብላለች። ተስፋ ሳትቆርጥ በመሥራቷ ሕልሟን እንዴት ማሳካት እንደቻለች የምታስረዳው ሐሴት፣ “ለችግሮች እጅ ባለመስጠት ሕልማችንን እንዴት ማሳካት እንደምንችል ምስክር ነኝ” ብላለች።

ሐሴት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥራዎች የነቃ ተሳትፎ እንዳላት ገልጻ ይህንን ተግባሯን ሕፃናትን ማዕከል ባደረጉ ጉዳዮች አጠናክራ እንደምትቀጠል በውድድሩ ላይ ተናግራለች።

የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሣ፣ ሐሴት ደረጄ በውድድር ቆይታዋ የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት እና መልካም ገፅታ በማስተዋወቅ ላደረገችው ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በቀጣይም ያገኘችውን ዓለም አቀፍ እውቅና እና ተፅዕኖና በመጠቀም የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብቶች ለማስተዋወቅ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በጋራ የሚሠሩ ሥራዎች ላይም ተወያይተዋል:: የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሣ ሐሴት ደረጄ ባስመዘገበችው ውጤት የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው በዓለም መድረክ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ በኩል ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባትና ይህንንም ለመፈፀም በምታደርገው ጥረት የተቋሙ ድጋፍ እንደማይለያት ተናግረዋል::

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም ሐሴት ደረጄን የባህል አምባሳደር አድርጎ ሾሟል። የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማሃዲ በአቀባበል መርሐ ግብሩ እንደገለፁት፤ በሞዴሊንግ ዘርፉ በዓለም መድረክ ይህን ዓይነት ውጤት ሲመጣ የመጀመሪያው ነው። እውቅና መስጠት ላይም ውስንነት አለ ብለዋል። ሐሴት በዓለም መድረክ ያመጣችው ውጤት ለሌሎች ታዳጊዎች ምሳሌ እንደሚሆንም አክለዋል። በሞዴሊንግ ዘርፉ የተሰማሩ ወጣቶች በዘርፉ ተስፋ እንዳለ በማሰብ በቀጣይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን መሥራት እንደሚኖርባቸውም ገልፀዋል ።

“አምባሳደር ሆኜ በማሳልፈው ጊዜ ሙሉ ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ እሠራለሁ” ስትል ሐሴት ገልጻለች። ወደፊት ከሞዴሊንጉ ባላፈ የእናቶችና ሕጻናት ጤና ላይ ማኅበራዊ ኃላፊነቷን ለመወጣት እንደምትሠራ ተናግራለች።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You