
18ኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና በአዲስ አበባ መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ አድርጎ ተካሂዷል። ለሁለት ዓመት ተቋርጦ ትናንት በተካሄደው ሀገር አቀፍ የሃያ አንድ ኪሎ ሜትር ፉክክር በዓለም አቀፍ ውድድሮች ልምድ ያካበቱ አትሌቶች በሁለቱም ፆታ አሸናፊ ሆነውበታል።
156 ሴቶች በተፎካከሩበት ውድድር የቀድሞዋ የ1500 ሜትር ተወዳዳሪ አትሌት ፋንቱ ወርቁ አሸናፊ ሆናለች። እኤአ በ2016 የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና የ1500 ሜትር የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ የኢትዮ ኤሌክትሪክ አትሌት ፋንቱ የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን አሸናፊ ለመሆን ርቀቱን በ1:13.30 ሰዓት አጠናቃለች። ዓይናለም ደስታ ከመቻል ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ ያስመዘገበችው ሰዓት 1:13.40 ሆኗል። የሸገር ከተማዋ አትሌት ብዙ አገር አደራ በ1:13.43 ሰዓት ውድድሩን ሦስተኛ ሆና ያጠናቀቀች አትሌት ነች።
389 አትሌቶች በተሳተፉበት የወንዶች ውድድር በተለያዩ ዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ ውድድሮች በጠንካራ ተፎካካሪነቱ የሚታወቀው የኦሮሚያ ፖሊስ አትሌት ሌሊሳ ፉፋ አሸናፊ ሆኗል። ውድድሩን ቀዳሚ ሆኖ ለማጠናቀቅ 1:03.46 ሰዓት ፈጅቶበታል። ነጋሳ ደቀባ ከኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ 1:03.49 ሰዓት በማስመዝገብ ሁለተኛ ሆኖ ፈጽሟል። ሌላኛው እውቅና ብዙ ልምድ ያለው አትሌት ሰይፉ ቱራ በግሉ ተወዳድሮ 1:03.58 ሰዓት በማስመዝገብ ሦስተኛ ደረጃን ይዟል።
ሦስት ክልሎች፣ ሃያ አንድ ክለቦችና ተቋማት አትሌቶቻቸውን ባፎካከሩበት የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና በወንድ ሸገር ከተማ በ31 ነጥብ አጠቃላይ የውድድሩ አሸናፊ በመሆን የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል። ኦሮሚያ ፖሊስ በ51( በዘጊ ነጥብ ) ሁለተኛ፣ ኦሮሚያ ኮንስትራክሽን በተመሳሳይ 51 ነጥብ ሦስተኛ ሆነው አጠናቀዋል። በሴቶች ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ29 ነጥብ አጠቃላይ አሸናፊና የዋንጫ ተሸላሚ ነው። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ89፣ ኦሮሚያ ፖሊስ 98 ነጥብ ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነው ያጠናቀቁ ክለቦች ናቸው።
በውድድሩ ለአሸናፊ አትሌቶች የ150 ሺ ብር ሽልማት ሲበረከትላቸው፤ ሁለተኛ ሆነው ላጠናቀቁ የ100ሺ ብር እና 3ኛ ደረጃን ይዘው ለፈፀሙ የ75 ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በውድድሩ ላይ በመገኘት ከአንድ እስከ ስድስት በመውጣት አሸናፊ ለሆኑ አትሌቶች የሜዳሊያ እና የገንዘብ ሽልማት የሠጡት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስኅን፣ ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት መሠረት ደፋር ሲሆኑ፣ የሜክሲኮ እና የኖርዌይ አምባሳደሮች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም ለአሸናፊዎች ሽልማት አበርክተዋል።
ውድድሩ የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች፣ የክለቦችና ተሳታፊ ተቋማት አትሌቶች የጎዳና ላይ የውድድር ዕድል እንዲያገኙ፣ አትሌቶች የሀገር ውስጥ የውድድር ልምድ እንዲያዳብሩ፣ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራትና በውድድሩ የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ አትሌቶችን በሽልማት ማበረታታትን ዓላማ አድርጎ ነው የተካሄደው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም