
የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ‹‹ፅዱ ኢትዮጵያን ባህል ማድረግ›› በሚል መሪ ሀሳብ ከትናንት ጀምሮ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የአካባቢ ብክለት ንቅናቄ አስጀምሯል። እያንዳንዱ ወራት የየራሳቸው ርዕሰ ጉዳይ አላቸው። የሰኔ ወር የፕላስቲክ ብክለትን መከላከል፣ የሐምሌ ወር የአፈርና ውሃ መሸርሸርን መከላከል፣ የነሐሴ ወር የአየር ብክለትን መከላከል፣ የመስከረም ወር የቆሻሻ አያያዝ አወጋገድ፣ የጥቅምት ወር የድምፅ ብክለትን የመከላከል ዘመቻ ሆነው፤ በዚህኛው ዙር የመጨረሻውና 6ኛ የሆነው የኅዳር ወር አጠቃላይ ግምገማና የሕግ አፈፃፀሞች የሚታዩበት ይሆናል። በዚህ አጋጣሚ ኅዳር ሲታጠን የሚል ቆሻሻን የማፅዳት ባህል እንዳለን ልብ ይሏል።
በዚህ በሰኔ ወር የሚጀመረውን የፅዱ ኢትዮጵያ ዘመቻ ‹‹ኅዳር ሲታጠን›› ከሚለው አባባል ወስደን ‹‹ሰኔ ሲታጠን›› ብለነዋል። የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ባወጣው መርሐ ግብር የሰኔ ወር የፕላስቲክ ብክለትን የመከላከል ንቅናቄ የሚደረግበት ወር ነው። እዚህ ላይ ሁለት ዐቢይ ጉዳዮች አሉ። አንደኛው፤ የፕላስቲክ አወጋገድን የተመለከተ ሕግ ሰሞኑን ፀድቆ መነጋገሪያ ሆኗል። መነጋገሪያ የሆነበት ምክንያት በተለምዶ ‹‹የአንድ ብር›› የሚባለው ፕላስቲክ (ፌስታል) መከልከሉ ነው። አንድ ብር የተባለው በተለምዶ እንጂ በአሁኑ ጊዜ የአንድ ብር ፌስታል የለም። አጀንዳ የሆነበት ምክንያት ‹‹ምን አማራጭ ኖሮ ነው የተከለከለው?›› በሚል ነው። አፈፃፀሙን እና ችግሮቹን ወደፊት ከምናያቸው ጉዳዮች ተነስተን እንታዘባለን።
የሰኔ ወር የፕላስቲክ ብክለትን የመከላከል ንቅናቄ የሚሆንበት ሌላኛው ምክንያት ግን የፕላስቲክ ብክለት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ መሆኑ ነው። ባለፈው ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን (ጁን 5) በኮሪያ ሪፐብሊክ አዘጋጅነት የተከበረው ዓለም አቀፍ የአካባቢ ቀን መሪ ቃሉ ‹‹የፕላስቲክ ብክለትን ማስወገድ›› የሚል ነበር። በዕለቱ የጀመረው የኢትዮጵያ ‹‹ፅዱ ኢትዮጵያን ባህል ማድረግ›› ንቅናቄ የሰኔ ወርን የፕላስቲክ ብክለትን የመከላከል ንቅናቄ አድርጓል።
‹‹ፅዱ ኢትዮጵያን ባህል ማድረግ›› የሚለው ንቅናቄ ይሳካ ዘንድ ለመሆኑ ምን አይነት የፅዳት ባህል አለን የሚለውን እንታዘብ።
ብዙ ነገሮችን የምናደርገው ዓመት እና ሁነት ጠብቀን ነው። ለምሳሌ ዕቅድ የምናወጣው አዲስ ዓመት (መስከረም) ሲደርስ ነው። መስከረም ካለፈ በኋላ እንኳን አዲስ ዕቅድ ማውጣት የታቀደውም ይረሳል። የበጎ አድራጎት ሥራዎችን (ለምሳሌ ሕሙማንንና አቅመ ደካሞችን መርዳት) የምንሠራው እንደ እንቁጣጣሽ፣ ገና፣ ፋሲካ፣ መውሊድ ወይም አረፋ ያሉ በዓላት ሲመጡ ነው። እነዚህ በዓላት ሲያልፉ ይረሳል፡፡
ልክ እንደነዚህ ሁሉ ፅዳትም የሚፀዳው ኹነት ተጠብቆ ነበር። ከዚህ በፊት በነበሩት ዓመታት ከተሞች የሚፀዱት በከተማዋ ውስጥ የሆነ ዝግጅት የሚደረግ ከሆነ ነው። ለምሳሌ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን፣ የከተሞች ሳምንት ወይም ሌላ መንግሥታዊ በዓላት ሲኖር ነበር። የዚያን ሰሞን ቀለሞች ይቀባሉ፤ ቆሻሻዎች ይፀዳሉ። ያ ዝግጅት ሲያልፍ ግን አይቀጥልም፤ እንዲያውም ይባስ ብሎ በዝግጅቱ ምክንያት የወዳደቁ ተረፈ ምርቶች የሚያቆሽሹት ይበልጣል፡፡
‹‹ኅዳር ሲታጠን›› የሚባል ባህል ግን አለን። በዚህ ቀን በየቦታው ቆሻሻ ይቃጠላል (ሌላ ቀን አይደረግም እንጂ) ዋና ዓላማውም ቆሻሻን ማቃጠልና ፅዱ አካባቢ መፍጠር ነው። የኅዳር ወር የመኸር ወቅት ስለሆነ ከጭቃም ከአቧራም የፀዳ ነው። የክረምት ወቅት ጭቃ አለበት፤ የበጋ ወቅት አቧራ አለበት፤ የበልግ ወቅት ደግሞ የጭቃውም የአቧራውም ቅልቅል ነው። የመኸር ወቅት የፀዳ ነው። ለዚህ ሳይሆን አይቀርም ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው ልማድ ‹‹ኅዳር ሲታጠን›› የተባለው።
እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች የማንቂያ ምክንያት መሆን ነበረባቸው። ቢያንስ በእንዲህ ዓይነት አጋጣሚ እንኳን አስታውሰን መነቃቃት ቢፈጠር ማለት ነው። ልቦና ቢሰጠን በዚያው ቢለምድብን ጥሩ ነበር። ግን ባህል ሳይሆን ቀርቶ እነሆ ዛሬ ድረስ ስለአካባቢ ንፅሕና እያወራን ነው። ቆሻሻን ለማስወገድ እና ንፁሕ አካባቢ ለመፍጠር ከምንም በላይ ዋናው ጉዳይ ባህል ማድረጉ ነው። ለዚህም ይመስላል የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን መሪ ቃሉን ‹‹ፅዱ ኢትዮጵያን ባህል ማድረግ›› ብሎ የሰየመው።
በነገራችን ላይ አዲስ አበባ ንፁሕ የምትሆነው በማፅዳት ሳይሆን ባለማቆሸሽ ነው። የከተማዋ ነዋሪ በነቂስ ወጥቶ ሁሉንም ቆሻሻ ጠራርጎና አፅድቶ ቢገባ የአስተሳሰብ ለውጥ ከሌለ በአንድ ቀን ማበለሻሸት ይቻላል። ከኮሪደሩ ልማት በፊት የነበሩት እና አሁንም ቢሆን የኮሪደር ልማት ባልተሠራባቸው አካባቢዎች ያሉት የወንዝ ዳርቻዎች እኮ ጥሩ ምሳሌ ይሆኑናል። የወንዞች ዳርቻ በክረምት ጎርፍ ጠራርጎ ሲወስደው ወንዙ ንፁሕ ይሆናል፤ ወዲያውኑ ግን ረፋድ እንኳን ሳይሆን አፍንጫ ተይዞ የሚታለፍበት ይሆናል። በግንብ እና በአጥር ዙሪያ ያለው አፍንጫ የሚበረቅስ መጥፎ ሽታ አብሮ የተገነባ አልነበረም፤ በሰዎች ሽንት እና የቆሻሻ መጣያነት ነው እንዲያ የሚሆነው።
መቼም እንግዲህ ገና ለገና ይቆሽሻል ተብሎ ዝም መባል የለበትም። የሚያቆሽሸውን ያህል በዚያው መጠን ደግሞ ቶሎ ቶሎ የሚያፀዳ ቢኖር ችግሩ ይቀንሳል። ኧረ እንዲያውም በጣም ይቀንሳል። ልብ ብላችሁ ከሆነ ብዙ ጊዜ ሰዎች ሽንት የሚሸኑት ከዚህ በፊት የተሸናበት ቦታ ላይ ሲደርሱ ወይም ቆሻሻ በዝቶበት የሚያዩት ቦታ ላይ ነው፤ ቆሻሻ የሚጣለውም ቆሽሾ የሚታይ ቦታ ላይ ነው። የያዝነውን ሶፍት እንኳን ንፁሕ ቦታ ላይ ለመጣል ይከብደናል። ቆሻሻ ቦታ ከጠፋ ብዙ ሰው ሊጥለው ያሰበውን ነገር በኪሱ ይከተዋል፤ ቆሻሻ ያለበት ቦታ ለመጣል ማለት ነው። እንግዲህ ከዚህ የምንረዳው ሁሉም አካባቢ ንፁሕ ቢሆን ሁሉም ለንፅሕና እንደሚበረታታ ነው።
የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ልብ ብላችሁ ታውቃላችሁ? የፕላስቲክ ውሃ ማሸጊያ በነበረበት ጊዜ የታሸገበትን ወረቀት ለመጣል ዘወር ዘወር ብለው ያያዩ ነበር። የተጣለ ካለ ሁሉም ይጥላል። የተጣለ ከሌለ ግን ፕላስቲኩ ወገብ ላይ ካለው ሽፋን ውስጥ ያደርጉታል፤ ወይም ኪሳቸው ይከቱታል (እኔ ብዙ ቀን ኪሴ ከትቻለሁ)። እንግዲህ መሬት ላይ በመጣል የሚጀምረው አንድ ሰው ነው ማለት ነው፤ ከዚያ በኋላ መቼም አንዴ ተጥሎበታል በሚል ሁሉም እየጣለ ወለሉ የፕላስቲክ ፋብሪካ ይመስላል፡፡
ምናልባት በኅዳር ሲታጠን ስም በዘመቻ ብዙ አካባቢዎች ፀድተው ይሆናል፤ ግን እንዲህ አይነት ዓመታዊ ነገሮች መፍትሔ አያመጡም። ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣው ባህል ማድረጉ ነውና ‹‹ፅዱ ኢትዮጵያን ባህል ማድረግ›› በሚል የተጀመረውን ንቅናቄ ትኩረት እንስጠው!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም