የኢትዮጵያ ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ወጣት እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ ኃይል በትምህርትና በእውቀት እንዲበለጽግ፤ በስርዓት እንዲገራ በማድረግ ለአገሩ የድርሻውን እንዲያበረክት ዕድል መስጠት ተገቢ ነው፡፡ በተለይም ዛሬ አገራዊ ለውጥና የልምላሜ ተስፋ በሚስተዋልበት ልዩ ዘመን አዕምሮን ከጉልበት አቀናጅቶ መሥራት የወጣቶች ግዴታ መሆን አለበት፡፡
ወጣቱ በተሥፋ መቁረጥ እየዋለለ ከተዘፈቀበት የተለያዩ የሱስ ወጥመዶች ራሱን ነፃ ማውጣት ይጠበቅበታል፡፡ በሱስ የናወዘ አዕምሮ ባለቤት ከቶም ጠያቂና ምክንያታዊ ሊሆን አይችልም፡፡ የተሻለ ነገን አስቦና አልሞ ለመሥራት አቀበት ይሆንበታል፡፡ የሀገራዊው ለውጥ መሪ ዶክተር አብይ አህመድ ‹‹ያገሬ ወጣት ሆይ በእጅህ ያለውን ጉልበትና በአዕምሮህ ያለውን የአስተሳሰብ ጉልበት አቀናጅተህ ያለ ከልካይ ለምርታማነት አውለው›› ሲሉ የተደመጡትም ከወጣቱ የሚመነጨው እምቅ አቅም ለለውጡ የሚያበረክተውን ጉልህ ድርሻ ተገንዝበው ነው፡፡
አዎ ወጣቱን ነፃነት ሰጥቶ አገርና ወገን ተስፋ እንዲጥልበት ማድረግ እንጂ እርስ በእርሱ እየተቆራቆዘ በተፈጠረለት የአስተሳሰብና የድርጊት ሽክርክሪት ልክ አዙሪት ውስጥ እንዲኖር መፍረድ ከአገር ክህደት አይተናነስም፡፡
በመላው አገሪቱ የሚገኙ ወጣቶች ወጥ በሆነ አወቃቀር ተሰቅዘው ኖረዋል፡፡ በወጣትነታቸው ልክ ማሰብ እንዳይችሉ ሆነዋል፡፡ በጉልበታቸው ልክ ሠርተው ሀብትና ንብረት እንዳይፈጥሩ ተደርገዋል፡፡ ይህንን እውንት የሚያጎሉ ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደሉም፡፡ የነበሩት አደረጃጀቶች ግብራቸውና ተግባራቸው ለየቅል ነበር፡፡ ለይምሰል የተፈጠሩና እስትንፋሳቸው በሪሞት የተያዘ ነበር የሚሉም ሰዎች ገጥመውኛል፡፡ በሥጋቸው እንጂ እኮ በተግባራቸው ጃጅተዋል በሚል የሚጠይቁም ነበሩ፡፡ ምክንያቱን ሲገልጹም ራሳቸውን ችለው መቆም አይችሉም፤ ራሳቸውን ችለው መወሰንም ጭምር ይላሉ፡፡
ከወጣት አደረጃጀት እስከ መንግሥታዊ ተቋም፤ ከግል ድርጅቶች እስከ በጎ አድራጎት መስሪያ ቤቶች በሌብነት የደነደኑ ናቸው፡፡ ስለዚህ የሥልጣን ወንበር ማፍረስ ሳይሆን የበሰበሰውን ግድግዳም አፍርሶ መቀየር ያስፈልጋል ሲሉም ይደመጣል፡፡
የወጣት አደረጃጀቶች አሁን ከመጣው የለውጥ ኃይል ጋር አብረው መለወጥ ይችሉ ይሆን ? ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንዳሉት በዚህ ወቅት ‹‹የሚቦኑ አቧራዎች ማወካቸው የግድ ነው፡፡ ተደልድለው እስኪጠብቁ ድረስ፡፡›› የወጣት አደረጃጀቶች በየአካባቢው የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አስተውሎ ላጤናቸው ለውጥ ማካሄዳቸው አይቀሬ ይመስላል፡፡ በተለያዩ መድረኮች አስተሳሰብ ሲሟሽ ትታዘባላችሁ፡፡
ሴቶችና ሕፃናት ወጣቶች ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን በቅንጅት ርብርብ ላይ መሆናቸውን በማህበራዊ ሚዲያዎቻቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹አሁን ያለውን ለውጥ አስጠብቆ በማስቀጠልና ምክንያታዊ ወጣቶች በመፍጠር ለሀገር ሰላም የበኩላችንን እንወጣ›› ሲሉ ጆሮ ላለው አደራ ሰጥተዋል፡፡ አዎ አደራን በሚያከብር፤ በሚፈራና በሚጠብቅ ማህበረሰብ ውስጥ ላደገ ኢትዮጵያዊ፤ ሐፍረትና ይሉኝታ ብሎ ነገር ያልፈጠረበት፤ ከእናቱ መቀነት የሚፈታ ሌባ፤ አገርን የሚሰርቅ ከሃዲ በዓይን ከማየት በላይ የሚያሳፍር ነገር የለም፡፡
ለዚህ ነው ትውልዳችንን በእውቀት መገንባት፤ ባሕልና ጨዋነት ማስተማር፤ ከስህተቶቹና ከጉድለቶቹ እንዲታረም ማድረግ የህብረተሰቡ ኃላፊነት የሚሆነው፡፡ ይህች አገር እንክርዳዱ አይብዛባት ማለታቸው ተገቢ ነው፡፡ ለዘመናት የአባቱ ወግ የሆነውን መቻቻልና አብሮነት ሊክድ የሚቃጣው ፈር የለቀቀው ወጣት በራሱና በአቻዎቹ መድረክ ሊታረቅና ሊቃና ይገባዋል፡፡
ወጣት አባይነህ አስማረ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት ነው፡፡ ወጣቱ ከዚህ አገራዊ ለውጥ ጋር እንዴት እራሱን አዋህዶና አስተሳስሮ የመዋቅሩን ቁመና እንዴት ቃኝቶ እየሠራ እንደሆነ ጠይቀነዋል፡፡ ባለፉት ወቅቶች ወጣት ማህበራት ብቻ ሳይሆን አብዛኛው የወጣት አደረጃጀቶች በፖለቲካ የተጠመዘዙ ናቸው በሚል የሚነሳው ትክክል ነበር ወይ? ለሚለው ሃሳብ፤ ወጣት ማህበሩ የተቋቋመበት ራሱን የቻለ ተልዕኮና ተግባር አለው፡፡ የአገሪቱ የዴሞክራሲ ሂደት ግልጸኝነት ይኖር ዘንድ ገለልተኛ ሆኖ በታዛቢነት ጭምር አገልግሏል፡፡
ፓርቲዎች ወጣቶችን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ፕሮግራም በስትራቴጂዎ ቻቸው አካተው እንዲቀርቡ ታግሏል ሲል ይገልጻል፡፡ በሥራ ሂደት ውስጥ የማህበሩን ሚና ለአንድ ፓርቲ አድርጎ የማየት አስተሳሰቦችና ድርጊቶች ታይተዋል ብሏል ወጣት አባይነህ፡፡ የኢህአዴግ ተላላኪ አድርጎ የማየት ዝንባሌዎች መታየታቸውን አብራርቷል፡፡
ማህበሩ ከለውጡ በፊትና ከለውጡ በኋላ ያለውን ልዩነት አስመልክቶ ሲናገር አገራዊ ለውጡን ማህበሩ በጽኑ ይደግፋል፡፡ አሁን አገሪቱንም ሆነ ከተማዋን በመምራት ላይ የሚገኙ አዲስ አመራሮች ለወጣቱ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ሰጥተዋል፡፡ ሃሳቡንም በተገቢው አድምጠው በማወያየት ፈጣን ምላሾች እየሰጡ ነው፡፡ ወጣቶች ካሉባቸው በርካታ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ጥያቄ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ራሳቸውን የቻሉና ነፃ የሆኑ አደረጃጀቶች የሚሉ ጥያቄዎችም ነበራቸው፡፡ ይህ ማህበር የወጣቶችን ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች ሊፈታ የሚችል ቁመና ላይ አይደለም፡፡ ቁመናውን ካላስተካከለ ተበታትኖ አቅም አይኖረውም በሚል ሁለት ወራት የወሰደ ጥናት በአዲስ አበባ ማካሄዳቸውን ተናግሯል፡፡
በጥናቱ የተገኘው ውጤት የወጣት የማህበሩ ቁመና አሁን ላለው የወጣቶች ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚችል አለመሆኑን ያረጋግጣል፡፡ የአሠራርና የአመራር ለውጥ መደረግ አስፈላጊ መሆኑ ታመነበት፡፡ የምንሠራው ሥራ ‹‹ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ›› እንዳይሆን ታስቦበታል ሲል ተናግሯል፡፡ የመንግሥት ቢሮዎችን ተሞክሮ ለማየት ሞክረን ነበር ሆኖም የአመራርም የአሠራርም ለውጥ ተደርጎባቸው ሕዝብን ከማማረር ያልተላቀቁ አሉ፡፡ የዚህ ዓይነት ችግሮች እንዳይገጥሙን ከስሜት በጸዳ መንገድ፣ በጣም በተረጋጋና በማስተዋል ለመሥራት ታስቦበታል፡፡
የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ችግር ሊፈታ የሚችል ግዙፍ የወጣ ቶች ዋስትናና ጠበቃ የሆነ ማህበር ሆኖ እንዲሠራ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ማህበሩ ትናንት የነበረውን ስህተት መድገም የለበትም፡፡ በራሱ እግር መቆም መቻል ይኖርበ ታል፡፡
ማህበሩን መልሰን ሥናደራጅ ትኩረታችን ሰብእና ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ በማሕበረሰቡ ጥሩ ሥም ያለው፣ የተወደደና ሰው አክባሪ ትሁት ቅቡልነት ያለው በበጎ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነ ወጣት ማህበሩን መምራት አለበት የሚል አቋም ይዘናል፡፡ በሕይወቱና በትምህርቱ አርዓያ የሆነ ወጣት መሆን አለበት አመራር ሆኖ የሚመጣው ወጣት፡፡ ከዚህ በፊት ወጣቶች በሚፈልጉት መንገድ ለመደራጀት ሁኔታው አይፈቅድላቸውም ነበር፡፡ አሁን ተቀይሯል፡፡ በየሙያው የተሰማሩ ወጣቶች በሙያቸው እንዲደራጁ በማድረግ በርካታ ክንፎች እንዲፈጠሩ ሆነዋል፡፡ በኃይልም፣ በአሠራርም በአመራርም ብዙሃኑን ወጣት እንዲያሳትፍ የተደረገ አደረጃጀት ነው የተፈጠረው፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች በየደረጃውና በየስርዓቱ ሕይወታቸውን እየገበሩ የመጡ ናቸው የሚለው ወጣት አባይነህ አስማረ፤ አሁን ላይ የለውጣቸውን ፍሬ አገሪቱ ባላት አቅምና ሀብት ልክ መቋደስ አለባቸው ሲል ይሞግታል፡፡ ወጣቱ ምክንያታዊና ሞጋች ትውልድ ሆኖ በውይይትና በድርድር የራሱንም ሆነ የአገሩን ጥቅም ማስከበር አለበት ሲል መክሯል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 2/2011
ሙሀመድ ሁሴን