ሀገር ሀገር ሆና እንድትቀጥል ጠንካራ መንግስታዊ ሕግና ስርአት ያስፈልጋል፡፡ የሀገር ሰላም የሚከበረው ብርቱ ሕግና ደንብን የማስከበር ስራ ሲሰራ ብቻ ነው፡፡ በዴሞክራሲና በነጻነት መከበር ስም ሀገር እንድትታመስ ሰላሟ እንዲናጋ የሚፈቅድ መንግስትም ሆነ ሕዝብ የለም፡፡ የሕግ የበላይነትን የማስከበሩ እርምጃ በይደር የሚታለፍ አይደለም፡፡ የመንግስት አብይና ቀዳሚ ስራ የሀገርና የሕዝብን ሰላም ዳር እስከዳር ማስከበር ነው፡፡
በአሁኑ ሰአት በሀገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ሁሉም ተቃዋሚ የነበሩ በውጭ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች በሰላም ገብተው ሀገራቸው ላይ ሰላማዊ የፖለቲካ ውድድር እንዲያደርጉ የተመቻቸ ቢሆንም መሬት ላይ ያለው እውነት ግን ከዚህ በተጻራሪ ነው፡፡
መንግስት በምህረትና በይቅርታ ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ካደረጋቸው ውስጥ አብዛኞቹ ይሄን ድል ያመጣነው እኛ ነን በሚል አታሞ ደላቂ ሆነዋል፡፡ አንዳንዶችም ሽምቅ ኃይላቸውን አሰልፈው ውጊያ ከፍተው ሕዝቡን እያመሱት ይገኛሉ፡፡ ከተቀበሩበት ተቆፍረው የወጡ፤ ስማቸው በትውልዱ የተረሱ ፓርቲዎች ሁሉ በትንሳኤ ሙታን እንዲነሱ ተደርገው የድሉ ባለቤት እኛ ነን ሲሉ ያሳፍራል፡፡ በኦሮሚያም ሆነ በአማራው ክልል ሕዝብ ያደረገውን መራራ ትግል ክደው እኛ ነን ይሄንን ድል ያመጣነው ለማለት የሞራል ብቃቱ የላቸውም፡፡ የፖለቲካ ነጋዴዎችና ሸቃጮች በሕዝቡና በለውጥ ኃይሉ መራራና ፈታኝ ትግል የተገኘውን ውጤት የራሳቸው አድርገው ሊሰብኩ መሞከራቸው በእጅጉ ያስተዛዝባል፡፡ አልተገናኝቶም ያስብላል፡፡
ይህ ሕዝብን መድፈር መናቅና መርገጥ ነው፡፡ የዴሞክራሲ መኖርና ልእልና ለሕዝብ መብትና ነጻነት መከበር ወሳኝ ቢሆንም፤ በዴሞክራሲ ይስፈን ስም ስርአተ አልበኝነት፤ የሕግና ስርአት ጥሰት፤ የዜጎች የተረጋጋ ሰላም መደፍረስ ሲሰፍን መቀበልም ሆነ ማስተናገድ ከቶውንም አይቻልም፡፡ የለውጡ ኃይልና የእነዚህ ስብስቦች አስተሳሰብ ጭርሱን አልተገናኘም፡፡ አልተገናኝቶም እንዲሉ፡፡
ፍጹም ዴሞክራሲ የሚባል ነገር በአለማችን ላይ የለም፡፡ ዴሞክራሲ ከሕግና ከስርአት በጥብቅ መከበር ጋር ብቻ ነው ተቆራኝቶ መሄድ የሚችለው፡፡ የለም የተባለው የዴሞክራሲ ስርአት መስፋት፤ የነጻነቶች መከበር፤ በሕግና በስርአቱ ሊራመድ ካልቻለ የመጨረሻው ውጤት የስርአተ አልበኝነት መስፈንና መንሰራፋት በመጨረሻም ሀገሪቱ የማትወጣው ውስብስብ አረንቋ ውስጥ መውደቅ ይሆናል፡፡ይህ እንዲሆን መንግስትም ሆነ ሕዝብ አይፈቅድም፡፡
የተመዘገቡት የለውጥ እርምጃ ሂደቶች በምንም መልኩ በዚህች ምድር ላይ ሊታሰቡም ሆነ ሊታለሙ የማይችሉ ግን በተግባር የታዩ አለምንም ያስደመሙ ናቸው፡፡ ይህንን ጠብቆ የበለጠ ለውጥ ለማምጣት መንግስትና ሕዝብ እጅና ጓንት ሆነው ከመስራት ውጭ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ሶስተኛ መንገድም አይኖርም፡፡ የሀገራችን ቀደምት የፖለቲካ ሕይወት በውስብስብ ሴራዎች የተዋቀረ በመሆኑ በየትውልዱ ፈረቃ እጅግ ከፍተኛ መስዋእትነቶች ተከፍሏል፡፡ ወጣቶች አልቀዋል፡፡
ከዚህ ሀገራዊና ትውልዳዊ ውድቀት መማር ያልቻሉ አንጋፋ የፖለቲካ ሰዎች ዛሬም ጥልፍልፍ ሴራ ውስጥ ገብተው እየዳከሩ ይገኛሉ፡፡ አሁን የተፈጠረው አይነት የፖለቲካ ምህዳር መስፋት ከዚህ ቀደም በነበረው ሁኔታ ተፈጥሮ አያውቅም፡፡ ሕዝብና አለም የመሰከረለትን ፖለቲካዊ ለውጥ ለማደናቀፍ ሴራዎች በየመስኩ እየተሸረቡ ግጭቶች እንዲበራከቱ እየተደረገ በተለያዩ አካባቢዎች ህዝብን ሰላም የመንሳት ጸጥታውን የማደፍረስ ስራዎች በፖለቲካ ድርጅቶች ስም እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡
መንግስት የቱንም ያህል ሰላማዊ መንገድ ቢመርጥም ጭርሱንም አቅም የሌለውና ደካማ ነው ብለው መደምደሚያ ላይ የደረሱም ይመስላል፡፡ ሀያ ሰላሳና አርባ አመታት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ያልቻሉ ያዝነው ባሉት ትግልም ድል አድርገው ለፍሬ ያልበቁ ለመብቃትም ያልቻሉና የማይችሉ የነበሩ ዛሬ በተሰጣቸው የሰላም እድል በቦሌ ሰተት ብለው ገብተው ለሰላም መቆም ሲገባቸው ሀገሪቱን በብዙ መልኩ በማተራመስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለሰላም የተዘረጋው እጅ መልሶ እንዲታጠፍ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
በመላው ሀገሪቱ የተሻለ ሁኔታን ለመፍጠር በስደት ሁነው በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ ተቃዋሚ ድርጅቶች በሰላም ወደ ሀገራቸው ገብተው በሳል እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ በሩን ከፍቶ በክብር የተቀበላቸውን ሕዝብና መንግስት አስመርረው መልሶ አንቅሮ እንዲተፋቸው እያደረጉ ነው፡፡ ምነው ባልመጡ እዛው በቀሩ ኖሮ እስኪል ድረስ ደርሷል ሕዝቡ፡፡
ሕዝቡ የደመቀ አቀባበል አደረገ ማለት ወገኖቻችን ናችሁ ከስደት እንኳን ወደ ሀገራችሁ መጣችሁ ማለቱ የነበረና ጥንትም የኖረ ባህሉ ነው እንጂ ሙሉ በሙሉ እንደግፋችኋለን ማለቱም አይደለም፡፡ ይህንንም መረዳትና መገንዘብ አልቻሉም፡፡
የሕዝብ ድጋፍ አለን ስለዚህም መንግስትነት ይገባናል ለዛውም በፍጥነት ሀገራዊ አመራር ላይ መቀመጥ አለብን የሚሉ የፖለቲካ ቀልደኞች በስፋት ሰፍነዋል፡፡ አንዳቸውም ታግለው አሸንፈው አልገቡም፡፡ የድል አድራጊነት ብቃቱ አቅሙ ችሎታውም አልነበራቸውም፡፡እነሱን ወደ ሀገር እንዲገቡ ያደረጋቸው የሕዝብ ትግልና መስዋእትነት እንዲሁም በኢሕአዴግ ውስጥ የነበረውና ያለው የለውጡ መሪ ኃይል ነው፡፡ ዛሬ ከእውነታው አፈንግጠው እውነቱንም ክደው እየዳከሩ ይገኛሉ፡፡ አልተገናኝቶም፡፡
በሰላም ሀገር ወስጥ ገብተው ለመስራት የገቡትን ቃል በማጠፍ ትጥቅ ፈተናል በሰላም ገብተናል የሚሉት ሁሉ በስውር ሰራዊት የማደራጀት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ገብተዋል፡፡ በየቦታው ያለማቋረጥ የሰላም መደፍረስና አለመረጋጋት የሚታይበት፤ሕዝብን መዝረፍ፣ መግደል የተከሰተበት ሁኔታም ጭምር ነው ያለው፡፡ሕዝብ ምን አደረገ ለምንስ በችግር ይፈተናል ብለው ማሰብ አልቻሉም፡፡
ጠቅላይ ሚነስትሩ በሰላም ተባብረን ሀገራችንን እናልማ እናቅና ተመካክረን ተወያይተን ልዩነቶቻችንን ጠብቀን ይህቺን ሀገር ወደ ታላቅነት እናሸጋግራት ሲሉ በተደጋጋሚ ያስተላለፉት መልእክት ጆሯቸውን በደፈኑ አክራሪ ፖለቲከኞች ተጥሷል፡፡ለሰላም የተዘረጋላቸውን እጅ ነክሰዋል፡፡ አልተገናኝቶም ማለትም ይኸው ነው፡፡ በሰለጠነው ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን በኋላ ቀር ፖለቲካ ውስጥ ከመባጀት የከፋ ነገር የለም፡፡ ሲስሟት ቀርቶ ሲስቧት አይነት መሆኑ ነው፡፡ በፍቅር ሲጋበዙ ጉልበትና ኃይል ናፋቂዎች ሆነው ብቅ አሉ፡፡ ጠመንጃ አፍቃሪና ነካሽ ሆነው የትም አይደርሱም፡፡ መንግስትና ሕዝብ ለሰላሙ ሲል ታግሎ ያሸንፋል፡፡
እኛው ለምነን እኛው ወደ ሀገራችሁ ግቡ ብለን በሰላም አስገብተን ልንወጋ አይገባም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የገለጹትም ይሄንኑ አመላካች ነው፡፡ በሰላም ንገስ ቢባል ምንም በሌለበት ሳልዋጋ አልነግስም ያለው አይነት መሆናቸው ነው፡፡ በበርካታ ታጋሽነት ሆደ ሰፊነት ለሰላም እጁን ዘርግቶ የአበባ እቅፍ ይዞ የተቀበላቸውን ሕዝብና መንግስት የግድ ገፋፍተው ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዲሄድ እያደረጉት ነው፡፡ የበዛ ትእግስት ይመራል ወይንም ይጎመዝዛል እንዲሉ በብዙ አቅጣጫና መልኩ ሰፊ ትእግስት ያሳየው መንግስት በቃኝ ወደማለቱ ሊያዘነብል ይችላል፡፡ ለዚህ ነው የኢትዮጵያ መንግስት አምባገነን ሊሆን ጫፍ ላይ ደርሶአል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ፡፡
ሀገር ሲተራመስ ሕዝብ በሴረኛ ፖለቲከኞች እርስ በእርስ እንዲጋጭ ሲደረግ ግጭት በየቦታው ሲዛመት በምንም መልኩ መታገስ ዳር ቆሞ መመልከት አይቻልም፡፡ የመንግስት ዋነኛው ተግባር የሀገርና የሕዝብን ሰላምና መረጋጋት ማስከበር ነው፡፡
ሰማንያና ዘጠና ፓርቲ የተቀፈቀፈባት የአለማችን ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ ነች፡፡ ረብ የለሽ የሕዝብን ቀልብና ልቦና መሳብ ያልቻሉ በአላማ ሳይሆን በቅርብ ትውውቅ በዝምድና በመንደርና ጎጥ ልጅነት የተሰባሰቡ ፓርቲዎች ለዚህ ታላቅ ሕዝብና ታላቅ ሀገር አይመጥኑም፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከጎጥና መንደር ከዘረኝነት በላይ ነው፡፡ አንድም ሕዝባዊ መሰረት ሳይኖራቸው ባሕር ማዶ ተሻግረው ወይንም ጎረቤት ሀገር ሆነው ሕልም ሲያዩ የነበሩት ሁሉ ዛሬ ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ ማየት ያሳፍራል፡፡ አይደለም ታላቋን ሀገር ኢትዮጵያን ራሳቸውን ለመምራት አይመጥኑም፡፡ ሀገር መምራት እንደ ወሬና ፕሮፓጋንዳም አይቀልም፡፡ በቅንጡ ሕይወት ሲንፈላሰሱ የኖሩ ፓርቲዎች፤ ዜግነታቸውን ለውጠው የተለያዩ ሀገራትን ዜግነት በቃለ መሀላ የተቀበሉ መሪዎችና ተመሪዎች ምንም እንኳን ኢትዮጵያዊ ቢሆኑም እንዴት አድርገው ሀገር እንምራ የማለት ሞራል እንዳገኙም ለማሰብ ይከብዳል፡
ከስንትና ስንት አመት በፊት የተለዩትን ሕዝብ ግማሹ ባሕሉን ጭምር የረሳ በጥንታዊ ያረጀና ያፈጀ ፖለቲካ ውስጥ የሚዳክር ዛሬም ከስም ማጥፋት ከውንጀላ ከሀሰት ወሬና ፕሮፓጋዳ ያልተላቀቁ ሰዎች ባልተለወጠው ኋላ ቀር አስተሳሰባቸው ሀገር መምራት ሕዘብ ማስተዳደር አይችሉም፡፡ትውልዱም ዘመኑም ተለውጧል፡፡ የጥለኸው እለፍ የሴራ ፖለቲካ ቀመር ቁንጮዎች በጠመዝማዛው መንገድ በመጠቀም የስልጣን ጥማቸውን ለማርካት እየተክለፈለፉ ይገኛሉ፡፡ አልተገናኝቶም፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቅን ተነሳሽነትና ሰፊ ትእግሰት የዚህንም ሕዝብ ሰላም አፍቃሪነትና ከልብ ሀገር ወዳድነት በቅጡ ሊረዱ አልቻሉም፡፡ ልቅ ዴሞክራሲ ሕግና ስርአትን ያልጠበቀና ያላከበረ ዴሞክራሲ በየትም ሀገር የለም፡፡ ሕገወጥነትን ስርአተ አልበኝነትን የሚያበረታታ እኔ ብቻ ልደመጥ ልሰማ ሌላው ‹‹ውጉዝ ከመአሪዎስ›› የሚል ዴሞክራሲም ሆነ ፍጹም የሚባል ዴሞክራሲ በምድር የለም፡፡
ዛሬ ላይ በተጨባጭ እየታዩ ያሉት ሀገራዊ ሁኔታዎች የተፈቀዱትንና የተከፈቱትን የዴሞክራሲ በሮች ዳግም እንዲከረቸሙ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ሕዝብን ማእከል ያላደረገ የፖለቲካ አላማውን ለማራመድ በጭፍን ጥላቻ ተውጦ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት በስፋት እየዘመተ ያለው ስመ ብዙ ነጋዴ ሚዲያ የሚያሰላው ወሬ ሸጦ ስንት ገንዘብ እንዳተረፈ እንጂ ሀገራዊ መግባባት ሰላምን መረጋጋት እንዲመጣ አይሰራም፡፡ አያስበውም፡፡ በሚቆሰቁሰው እሳት አብሮ እንደሚነድም አያስተውልም፡፡ እልቂትና ጥፋትን እየደገሰ ግጭት እንዲዛመት የማድረግ ሀገራዊ ኃላፊነት የጎደለው ስራውን ገፍቶበታል፡፡ አክቲቪስት የተባሉትም ነጋ ጠባ የጦርነት ነጋሪ እየጎሰሙ ሕዝብን በሕዝብ ላይ ማነሳሳት ጥላቻ የመዝራት ሰፊ ስራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
የዴሞክራሲ መገኘት ልቅነትን ሕገወጥነትን ስርአተ አልበኝነትን የሚያሰፍን ከሆነ ገና ዴሞክራሲ አልገባንም ማለት ነው፡፡
የዴሞክራሲ መገኘት መጠፋፋትን የሚያስከትል ሕግና ስርአት እንዲጣስ በር የሚከፍት፤ ሰላምና መረጋጋት የሚያደፈርስ ሕዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ ከሆነ ከዴሞክራሲ እሳቤ ጋር አልተዋወቅንም ማለት ነው፡፡ ዴሞክራሲ በጋራ መግባባት ላይ አንዱ የሌላውን መብትና ነጻነት ልዩነትም በማክበር ሰላምን መሰረት አድርጎ የሚቆም መርህ ነው፡፡ ዴሞክራሲን በስም እንጂ በተግባር የማናውቀው በመሆኑ ሀገርንና ሕዝብን ከጥፋት ለማዳን የሕዝቡንም ሰላምና መረጋጋት ለመጠበቅ ሕግና ሕግን በኃይል የማስከበር አማራጭን መከተል ግድ የሚልበት ግዜ ላይ እየተደረሰ መሆኑን ሁሉም ማስተዋል ይገባዋል፡፡
አሁንም ባለው የጠበበ ሰአት ተፎካካሪ ፓርቲውም ሆነ ሚዲያው ሕግና ስርአትን አክብሮ ታጣቂውም ትጥቁን አስቀምጦ በሃሳብ የበላይነት በውይይትና በንግግር አሸናፊ ለመሆን ቢሰራ ይመረጣል፡፡ በተረፈ የበዛን ትእግስት ከአቅም ማነስ ተርታ የሚመድቡት አላዋቂዎች ገፍተው ገፍተው የሚያመጡት ውጤት የማያፈናፍን ሕግ እንዲሰፍን ማድረግ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ከእኛም በፊት ነበረች፡፡ ከእኛም በኋላ ትቀጥላለች፡፡ በፖለቲካ ቡድኖች ጩኸትና ሴራ አትፈርስም፡፡ በብዙ ሺህ ዘመናት ታሪኳ ውስጥ የትየለሌ የሆኑ ፈተናዎችን መከራዎችን ውጣ ውረዶችን መውደቅና መነሳቶችን አሳልፋ ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡ የማይደናቀፈው ሀገራዊ ጉዞዋም ይቀጥላል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 2/2011
መሐመድ አማን