‹‹ማረሚያ ቤት ወይስ እስር ቤት?›› የሚለው ጥያቄያዊ ዐረፍተ ነገር ለብዙ ዘጋቢ ፊልሞችና መጣጥፎች ርዕስ ሆኗል። በአንዳንድ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ዘጋቢ ፊልም፤ እንዲያውም ‹‹እስር ቤት›› የሚለው አልመጥን ብሎ ‹‹ማሰቃያ ቤት›› በሚል ተተክቷል። የብሮድካስትም ሆነ የህትመት መገናኛ ብዙኃን ይሄን ጥያቄያዊ ርዕስ ለመጠቀም የተገደዱት ስሙንና ምግባሩን ለማግናኘት ነው። ሁለቱም ስሙ ነው። ማረሚያ ቤት ይባላል፤ እስር ቤት ይባላል። ማረሚያ ቤት የሚሉት መንግሥትና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ናቸው። እስር ቤት የሚሉት ደግሞ ታሳሪዎች፣ የታሳሪ ቤተሰቦች፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ልሳኖቻቸው ናቸው። ሁሉም ምክንያት አላቸው። ምንም ተባለ ምን ሁለቱም ስም ያግባባናል።
ማረሚያ ቤት በሚለው እናውራ። ማረሚያ ቤት ማለት ጥፋት አጥፍቶ የታሰረ ሰው ከድርጊቱ የሚታረምበት ማለት ነው። ይሄ ብቻ አይደለም። ማረሚያ ቤት መማሪያ ቤትም ነው። ይሄንን ስል ምናልባት የቅንጦት ቦታ እያስመሰልኩት አይደለም። ‹‹የሰው ልጅ ከሁለት ነገሮች ይማራል፤ አንድም ከፊደል ሀ ብሎ አንድም ከመከራ ዋ ብሎ ›› የሚለው የጸጋዩ ገብረመድህን አገላለጽ ግልጽ ያደርግልናል። ማረሚያ ቤት ውስጥ የገቡ ሰዎች የሚማሩት ከብዙ ነገር ነው። ብዙ አይነት ገጠመኝ አለ፤ ብዙ አይነት ታሪክ አለ። እርስበርሳቸው ብዙ አስገራሚ ክስተት ይጨዋወታሉ። የሚታሰሩበትን ጉዳይ ውስብስብ ድርጊቶች ይሰማሉ። የተለያየ አይነት ባህሪ ያለው ሰው ያያሉ፤ ‹‹እንዲህም አይነት ጉድ አለ!›› የሚያሰኙ ነገሮችን ይሰማሉ።
ከዚሁ ሁሉ በላይ ግን በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኘው ትልቁ ነገር ንባብ ነው። ማንበብ ማለት እንግዲህ ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው። ማንበብ ማለት ሁሉም ነገር ነው። ይልቅ ስለማንበብ ጥቅም ሳይሆን ስለማንበቢያ ጊዜ እናውራ።
ካለው የኑሮ ውጣ ውረድና ትንቅንቅ አንፃር ብዙ ሰው በቂ የማንበቢያ ጊዜ የለውም። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ይሄ የሰነፎች ማሳበቢያ እንጂ ሰው ለማንበብ ጊዜ አያጣም ይላሉ። በተደጋጋሚ እንደማሳያ የሚጠቀሰው ደግሞ ፈረንጆች በየባቡሩና በየታክሲው ውስጥ ያነባሉ የሚል ነው። እውነት የእኛ አገር ባቡር የሚነበብበት ነው? እንኳን በእጅ መጽሐፍ ወይም ጋዜጣ ዘርግቶ ለማንበብ እጃችንን ከኪሳችን የምናስገባበት ክፍተት አለ? እንኳን ባቡር ውስጥ ታክሲ ውስጥ ራሱ ማንበብ ይቻል ይሆን? ከወንበሩ ልክ በላይ ተቀምጠህ ላለመውደቅ አንዴ የታክሲውን ጣሪያ ፤ አንዴ የታክሲውን ግድግዳ ፤አንዴ የታክሲውን ወንበር እያፈራረቅክ ትደገፋለህ እንጂ መጽሐፍ ወይም ጋዜጣ ዘርግተህ የምታነብበት አይደለም።
እነዚህ ውጫዊ ጫናዎች (ግላዊ ስንፍናችን እንዳለ ሆኖ) የማንበብ ባህላችንንም አዳክመውታል። አሁን አሁን በንባብ ከቤተ መጻሕፍት ይልቅ ማረሚያ ቤቶች ስማቸው እየተነሳ ነው። ብዙ ሰዎችም የንባብ ልምዳቸውን ሲያካፍሉ የማረሚያ ቤት ቆይታቸውን ይጠቅሳሉ። ብዙ ሰዎችም ማረሚያ ቤት ውስጥ ሆነው ጽፈዋል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ታራሚ ለመጠየቅ ሲሄዱ መጽሐፍ መያዝ እየተለመደ መጥቷል፤ መሰልጠን ይሏል ይህ ነው። አወንታዊ ኩረጃ ማለት ይሄ ነው። ማረሚያ ቤት ውስጥ ላለ ሰው መጽሐፍ መስጠት ማለት ከማረሚያ ቤት ውጪ ያለውን ዓለም መስጠት ማለት ነው። በቃ ከእስር ማስፈታት ማለት እኮ ነው!
ታራሚዎች ብዙ ችግር ነው ያለባቸው። አንዳንዶቹ በሠሩት ሥራ የሚጸጸቱ ይሆናሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ባልሠሩት ሥራ በሀሰት ምስክር የታሰሩ ይሆናሉ፤ አንዳንዶቹም ባላወቁት መንገድ ወደ ስህተት የገቡ ይሆናሉ። እነዚህ ሁሉ ይበሳጫሉ ማለት ነው። መጽሐፍ መስጠት ማለት እንግዲህ እነዚህን ችግሮቻቸውን ማቃለል ማለት ነው። አንዳንዱ ያ የደረሰው ችግር በእሱ ላይ ብቻ የደረሰ ይመስለዋል፤ ከዚያ በኋላ ሕይወት የሌለው ይመስለዋል። በመጽሐፍ ውስጥ ግን የዓለምን ምስጢር ያውቅበታል። ዓለም ምን እንደሆነች ያያል፤ ያኔ ይረጋጋል፤ ሕይወት ምን እንደሆነች ያውቃል። አዕምሮው ባህር ይሆናል።
ባነበበ ቁጥር ብስል ሰው ይሆናል፤ አገናዛቢ ይሆናል። እንኳን የሠራውን ስህተት ሊደግም ያለጥፋቱ እንኳን ቢታሰር አገናዛቢ ሰው ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባል። ይሄ ሰው ከማረሚያ ቤት ሲወጣ ምሁር ሆኖ ሊወጣ ይችላል። በፊት ይጠጣ የነበረው እርግፍ አድርጎ ይተወዋል፤ በፊት ይሠርቅ የነበረው የስርቆት ነውርነት ይታየዋል። ያለጥፋቱ የታሰረው ደግሞ በራሱ ትዕግስት ይኮራል። ከወጣ በኋላ አድሎአዊ አሠራርን ይቃወማል፤ የፍትሕ ሥርዓት እንዲሰፍን ይታገላል።
እንግዲህ ይሄ ሁሉ ይሆን ዘንድ መጻሕፍት ታራሚዎች ጋ መድረስ አለባቸው። ይሄ ደግሞ በሳምንት አንድ ቀን ከሚመጡ ጠያቂዎች ተጠብቆ አይዘለቅም፤ ለዚያውም የሚመጡ ጠያቂዎች ሁሉ ‹‹መጽሐፍ ይይዛሉ ወይ?›› የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።
መጻሕፍትን ለታራሚዎች በመስጠት ከመንግሥት ተቋማት ብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲን ልናመሰግን ይገባል። በተለያዩ የክልልና የዞን ከተሞች የንባብ ሳምንት ያካሂዳል። ኤጀንሲው በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከትምህርት ቤቶች በተጨማሪ ወደ ማረሚያ ቤቶች ጎራ ማለት ጀምሯል። እስከአሁንም በብዙ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ መጽሐፍ ሰጥቷል፤ በማረሚያ ቤቶች ውስጥ መድረክ በማዘጋጀት ታራሚዎችን ከደራሲዎችና ከታዋቂ ሰዎች ጋር አገናኝቷል። ባለፈው ወር መጨረሻ ያደረገውን እንደ ምሳሌ እንውሰድ።
ብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጄንሲ ‹‹በንባብ እንታረም›› በሚል መሪ ሃሳብ ለቦንጋ ማረሚያ ቤት መጻሕፍት ሰጥቷል። መጻሕፍት መስጠት ብቻ ሳይሆን ማረሚያ ቤቱ ውስጥ መድረክ በማዘጋጀት ታራሚዎችን ከደራሲያንና ከታዋቂ ሰዎች ጋር አገናኝቷል። በማረሚያ ቤት ውስጥ ቆይተው የተፈቱ ሰዎች የንባብ ልምዳቸውንና የማረሚያ ቤት አጋጣሚዎቻቸውን ለታራሚዎች አጋርተዋል። ከእነዚህም አንዱ ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል ነበሩ። የማረሚያ ቤት ሕይወታቸውን ብቻ ሳይሆን የንባብ ልምዳቸውንም አጋርተዋል። ማንበብ ምን ያህል እንደሚያንጽ ከሕይወት ልምድ ያገኙትን ለታራሚዎች ነግረዋቸዋል።
ከታዋዊ ሰዎች ድምጻዊት ብሩክታዊት ጌታሁን (ቤቲ ጂ) ተገኝታለች። ቤቲ ጂ አህጉራዊ ሽልማት ያገኘችና ዓለም አቀፋዊ እውቅና ያላት ናት። በቅርቡ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል ሽልማትን ሲቀበሉ የዓለም ህዝብ በቀጥታ ስርጭት በሚከታተለው መድረክ ላይ በመዝፈን ተጨማሪ ዝናን አግኝታለች።
ታራሚዎች እንዲህ ዓይነት ታዋቂ ሰዎችን የማግኘት ዕድል የላቸውም። ኮንሰርት አይገቡም፤ መድረክ አይከታተሉም። የፈለጉትን የመገናኛ ብዙኃን አይከታተሉም፤ እናም እንዲህ ዓይነት ታዋቂ ሰዎችን ሲያገኙ ትልቅ ደስታ ይሰማቸዋል። ብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጄንሲ፣ የከተማ አስተዳደሮችና የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ይህን በማድረጋቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ታራሚዎችን ከመጽሐፍ ጋር ለማገናኘት ከግለሰቦች አልፎ እንዲህ በመንግሥት ሲታገዝ ተደራሽነቱ ሰፊ ይሆናል።
‹‹መጻሕፍትን ለታራሚዎች›› በሚል በሦስትና አራት ወጣቶች የተጀመረ አንድ መርሐ ግብር አለ። መድረኮችን እያዘጋጁ ታዋቂ ሰዎችን በመጋበዝ መጻሕፍት ያሰባስባሉ። የመድረኩ የመግቢያ ዋጋ ሁለትና ከዚያ በላይ መጽሐፍ መያዝ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በማህበራዊ ገጾች በሚደረግ ቅስቀሳ (ማህበራዊ ገጽ እንዲህ ለበጎ ነገር ቅስቀሳም ይውላል) መጻሕፍትን ያሰባስባሉ። ከዝግጅቱ አስተባባሪዎች አንዷ የሆነችው ሰላም በለጠን እንዴት እንደጀመሩት ጠይቀናታል።
ሃሳቡ የተጀመረው በ2010 ዓ.ም ክረምት ላይ ነው። ሃሳቡን ያመነጨውም የገጣሚ ደበበ ሰይፉ ወንድም አዶናይ ሰይፉ ነው። አዶናይ 60 ያህል መጻሕፍት ነበሩት። እነዚህ መጻሕፍት ተደራሽ እንዲሆኑ ይፈልጋል። አዶናይ ከጋዜጠኛ ሙሉጌታ አንበርብር ጋር የፌስቡክ ጓደኛሞች ነበሩና በጉዳዩ ላይ አወሩ፤ ሙሉጌታም ለሰላም ነገራት። እንዲህ እንዲህ እያሉ ሌሎችም ተቀላቀሉና መጻሕፍትን ማሰባሰብ ጀመሩ።
ጋዜጠኛ ሙሉጌታ በወቅቱ ሃዋሳ ስለነበር እዚያው ሃዋሳ መጻሕፍትን ማሰባሰብ ጀመረ። እነ ሰላም ደግሞ አዲስ አበባ ማሰባሰብ ጀመሩ። ይህን እያደረጉ አዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የሚዘጋጀው ንባብ ለሕይወት ተጀመረ። የንባብ ለሕይወት አስተባባሪውን ቢኒያም ከበደን አነጋግረው ከንባብ ለሕይወት ዓውደ ርዕይ ላይ አንድ ሺህ መጻሕፍትን መሰብሰብ ቻሉ። የሰባሰቧቸውን መጻሕፍት ለሃዋሳ ማረሚያ ቤት ሰጡ።
ቀጥሎ ደግሞ ለጅማ ማረሚያ ቤት ሰጥተዋል። ይህም የሆነው መጽሐፍ የማሰባሰብ ሥራቸውን አስፍተው በመቀጠላቸው ነው። ይህን ሲያደርጉም የጅማ ዞን የመጓጓዣ አገልግሎትን ጨምሮ ትብብር አድርጎላቸዋል።
እንቅስቃሴያቸው እየሰፋ መጥቶ መድረኮችን ማዘጋጀት ጀመሩ። መስከረም 23 ቀን 2011 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር ባዘጋጁት የስነ ጥበብ ምሽት አንድ ሺህ 550 መጻሕፍት ተሰበሰበ። ይሔኛው ደግሞ ለባህርዳርና ለፍኖተ ሰላም ማረሚያ ቤቶች ተሰጠ። በብሔራዊ ቴአትር በተዘጋጀው መድረክ ላይ ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የተጋበዙ ሰዎችም ተገኝተዋል። በግንቦት ወር በተዘጋጀ መድረክ ደግሞ ከአንድ ሺህ 650 በላይ መጽሐፍ መሰብሰብ ተችሏል። ከፕሮግራሙ ውጪ ደግሞ ብዙ መጻሕፍት ተሰብስቧል። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ በተሰበሰቡ መጻሕፍት፤ ሃዋሳ፣ ባህርዳር፣ ፍኖተ ሰላም፣ ጅማ፣ ደብረብርሃን፣ አሶሳና የመሳሰሉት ከተሞች ለሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ለታራሚዎች መጻሕፍት ሰጥተዋል።
ይህን እንቅስቃሴ የሚያደርጉት መደበኛ ሥራቸውን እየሠሩ ነው። በዚህም ምክንያት በፈለጉት ፍጥነት አልሄደላቸውም። አሁን ላይ ያለውን እንቅስቃሴ የምታስተባብረው ሰላም በለጠ ብትሆንም እሷም ‹‹ከመደበኛ ሥራዬ ጋር ስለሆነ ያስቸግራል›› ትላለች። ቢሆንም ግን ይህን በጎ እንቅስቃሴ ወደ ማህበር ለማሳደግ በሂደት ላይ ናቸው።
ይህ በማረሚያ ቤቶች የሚደረግ የመጽሐፍ ስጦታ በማህበር፣ በመንግሥትም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ሊጠናከር ይገባል። ምግብ ይዘን እንደምንሄደው ሁሉ መጽሐፍም የመንፈስ ምግብ ነውና በማንበብ አዕምሯቸውን ሊገነቡ ይገባል። ማረሚያ ቤት ውስጥ ያለ ሰው ሌላ የመዝናኛም ሆነ የእግር ጉዞ አማራጭ ስለሌለው መጽሐፍ ለታራሚ ምን እንደሆነ ግልጽ ነው። እያነበቡ ከሆነ እንደታሰሩ ሳይሆን እየታረሙ እንደሆነ ያስባሉ። በተለይም ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጄንሲ እንደሚያደርገው ታዋቂ ሰዎችና ደራሲዎች እየሄዱ ሲያዝናኗቸውና ልምድ ሲያካፍሏቸው ደግሞ እስር ቤት የሚለው ቀርቶ ማረሚያ ቤት ይሆናል ማለት ነው። ማንበብ በራሱ ደግሞ ከብዙ ነገሮች ስለሚያርም ታራሚ ያደርጋቸዋል።
ታራሚዎችን ከመጻሕፍት ጋር እናገናኛቸው!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 7/2012
ዋለልኝ አየለ