
በኢትዮጵያ በኢኮኖሚው መስክ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ ስለመሆኑ በርካታ ተጨባጭ መረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። በማህበራዊ ግንኙነት ረገድም ጠንካራ ትስስር ለመኖሩ ዘመናትን ያሳለፈው ብዝሃነታችን አንዱ ቋሚ ምስክር ነው። በፖለቲካው ረገድ ግን ብዙ የሚጠበቁብን ሥራዎች እንዳሉ የአደባባይ ምስጢር ነው። በአንድ ሀገር ውስጥ ያሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተደጋግፈው የሚሄዱና አንዱ በአንዱ ውስጥ የሚታይ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ።
ዛሬም ድረስ ብልጭ ድርግም የሚሉት አለመስማማቶች የሚመነጩት ከእዚሁ ከፖለቲካው መንደር ነው። አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩም ሆነ ነጋዴው፣ እንደማህበረሰብ የትኛውም ብሔረሰብ ሆነ ሃይማኖተኛ ኢትዮጵያ ሀገሩ እንደሆነች ያምናል። በፖለቲከኛውና በምሁራኑ ረገድ ግን ኢትዮጵያዊነትን እየተቀበሉ በሀገራዊ አጀንዳዎች ልዩነትን ማጉላት፣ አንዳንድ ጊዜም ልዩነትን መፈብረክም የጉብዝና መለያ እየተደረገ ሲወሰድ ማየት የተለመደ ሆኗል። እነዚህ አካላት ከአፋቸውም ሆነ ከግብራቸው አንድ ስለሚያደርጉን ነገሮች መስማት ይናፍቀን ጀምሯል። ብዙዎቹ አንድ በሚያደርጉን በሚያስማሙን ጉዳዮችም ለሀገር መሥራት ሽንፈት ይመስላቸዋል።
ሁላችንም የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት እና የእምነት መስመር ሊኖረን ይችላል። ነገር ግን በሃሳብና በተግባር ምንም ይሁን ምን በኢትዮጵያ ሰላም፣ በሉዓላዊነታችንና በብሔራዊ ጥቅሞቻችን ጉዳይ ልዩነት ልንፈጥር አይገባም። ለምሳሌ ምንም ዓይነት የሃሳብ ልዩነት ቢኖረን በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የሰላም እጦት እንዲፈጠር በር ልንከፍት አይገባም። ይህ በየትኛውም አካባቢ ቢሆን እንታገልለታለን የምንለውን ሕዝብ ጭምር ለጥፋት የሚያጋልጥ መሆኑ ግልጽ ነው።
በእዚህ ረገድ ታሪካችን እንደሚነግረን ትናንትም ዛሬም ምን አልባትም ነገም በኢትዮጵያ ውስጥ የሰላም እጦት ተፈጥሮ ሞት መፈናቀልና ውድመት ሲከሰት የትኛውም ኢትዮጵያዊ ጥቅም ተጠብቆ አያውቅም። በአንጻሩ የጎረቤት ሀገራትን ጨምሮ በርካታ ጠላቶቻችን ግን አትርፈውበታል።
ስለዚህ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን ከማንም ጋር ተስማምቶ ቢሠራ በውጤቱ ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ አንሆንም። በመሠረተ ሃሳብ ደረጃ የእዚህ ጉዳይ በሰላም መጠበቅ የማይስማማ ያለ አይመስለኝም። የሕዝብ ሰላም እንዲጠበቅ ገዢው ፓርቲ ከተፎካካሪ ፓርቲ ጋር አጀንዳ ቀርጾ እቅድ አውጥቶ መርሃ ግብር አስቀምጦ ቢሠራ የጋራ ተጠቃሚነት ይረጋገጣል። በኢኮኖሚውና በሀገር ሉዓላዊነት መጠበቅ ረገድም ሊሆን የሚገባው ይኸው ነው።
አንዳንዶች በተለይም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ወገን በገዥው መንግሥት የሚሠሩ ሥራዎችን በሙሉ ጥቅምን ለማስጠበቅና የእድሜ ማራዘሚያ ብቻ አድርገው ሲመለከቱ እናያለን። ለእዚህ እንደ ማሳያ በቅርቡ መቋጫውን የሚያገኘው ታላቁ የሕዳሴ ግድብና እንደ አዲስ እየተቀጣጠለ ያለው የባሕር በር ጥያቄን ማንሳት እንችላለን።
የትናንቱ ኢህአዴግ የሕዳሴውን ግድብ ሲጀምር ብዙ ተብሎ ነበር። ሁሌም እንደምንለው ኢህአዴግ ዛሬ የለም የሕዳሴው ግድብ ግን ለኢትዮጵያውያን ጥቅም መስጠት ብቻ ሳይሆን አንድ የመደራደሪያ አካል እና በራሳችን አቅም ሠርተን መለወጥ እንደምንችል ሕያው ምስክር ሆኖ ተቀምጧል።
የባሕር በር ጥያቄውም ምላሽ ሲያገኝ አንድን ማህበረሰብ ወይንም በአንድ ዘመን የነበረን ሥርዓት ብቻ ተጠቃሚ እያደረገ ሊቀጥል የሚችልበት እድል የለም። ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታገኝ አሁን ያለውን መንግሥት መደገፍ ሌሎች የፖለቲካ ልዩነቶችን መተው ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም።
ዛሬ ይህን መንግሥት የሚቃወም የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ግለሰብ ነገ ሀገር የመምራት እድሉን ቢያገኝ ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆኗ ሥራውን ያቀልለታል እንጂ የሚጎዳው ነገር አይኖርም። ደጋፊን ላለማስቀየም በሚመስል አካሄድ በአረንጓዴ ዐሻራ ዛፍ ሲተከል ሳይቀር ተቃውሞ ማሰማት የተለመደ ሆኗል። እዛ ቤት ደግሞ ይህንን ተከትሎ አጋጣሚውን ጉዳያቸው አድርገው ያራግቡታል።
በእዚህ ረገድ በቅርቡ ከኢዜማ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የተነሳው ሃሳብ ይበል ይቀጥል የሚያሰኝ ነው። ሌሎችም ከእዚህ ብዙ ሊማሩ ይገባል። ዛሬ እንኳን የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ይቅሩና የተለያየ ሃይማኖት እምነት ተከታዮች በሀገርና በሰብአዊነት ጉዳይ በአንድ የሚቆሙበት ዘመን ነው። ሀገርን መዳረሻው አድርጎ ከተቋቋመ አካል በሀገራዊ ጉዳይ አልስማማም አልያም በኅብረት አልሠራም ሲል መስማት አሳፋሪ ነው።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በሚያስማሙን ጉዳዮች ለሀገራችንና ለሕዝባችን ለራሳችንም ስንል ተስማምተን ከመሥራት ባለፈ፤ በማያስማሙን ጉዳዮችም ላይ ሃሳባችንን ልናራምድ የሚገባን በሰላማዊ መንገድ ብቻ ሊሆን ይገባል። በብዙ ፖለቲከኞችና ምሁራን ዘንድ ልዩነት የሚገለጽበትም ሆነ የሚተገበርበት መንገድ ስህተት ብቻ ሳይሆን ብዙ የሚያስከፍለንም ነው። ትንንሽ ልዩነቶቻችንን እየፈለጉ ጥቂት መሣሪያና ጥይት በመላክ የቤት ሥራ የሚሰጡን ዛሬም በሥራ ላይ ናቸው። ለእዚህ ደግሞ በትንሽ በትልቁ የሚያኮርፉና እኔ ያልኩት ብቻ መሆን አለበት የሚል ምልከታ ያላቸው ዋናዎቹ ናቸው። የእነዚህን አካላት ስህተት የበለጠ የሚያደርገው ሃሳባቸው ተቀባይነት ሲያጣ መሸሸጊያ መከታ የሚያደርጉት የቆሙለትን ሕዝብ ሳይሆን ርዳታ የሚቸሯቸውን የውጪ ሀገራት መሆኑ ነው።
ይህ የሃሳብ ልዩነትን ነፍጥ በማንገብ ጥይት ተኩሶ መፍትሔ ለማፈላለግ በየዱሩ ያሉትን ብቻ የሚመለከት አይደለም። በሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉትንም ያካትታል። ለምሳሌ በ1997ዓ.ም የተካሄደው ሦስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ብዙ ጉዶች የታዩበት ነበር። አብሮነታችን የዲሞክራሲ ባሕላችን መከባበርና መዋደዳችን ሁሉ የተፈተሸበት ነበር። በወቅቱ የነበረው ጥያቄና ልዩነት በፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ ብቻ የተገደበ አልነበረም። የምርጫውን ውጤት በተመለከተ የአውሮፓ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን እና ምርጫ ቦርድ በየፊናቸው እጅግ የተራራቀ መግለጫ ያወጡ ነበር።
ከምርጫ በፊት ውጤቱን በሰላም በጸጋ ለመቀበል ሲምሉ ሲገዘቱ የነበሩት አካላትም ማፈግፈግ ጀመሩ። በመንግሥትም በኩል የሕዝብን ሰላም የማስጠበቅ ኃላፊነት አለብን በሚል ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና ከቤት ውጪ የመሰብሰብ እገዳ ተጣለ። 25 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሕዝብ የተሳተፈበት በብዙ ተስፋ ሲጠበቅ የነበረውም ምርጫ እኛ ብቻ የምንረዳውን ጥቁር ጠባሳ አስቀምጦ አለፈ። የዜጎች ሞት ተከሰተ… ንብረት ወደመ … የዲሞክራሲ ግንባታ ጅማሯችን መደነቃቀፍ ጀመረ… የሀገር ገጽታ ተለወጠ። በእዚህ ሂደት ግን ኤርትራውያን፤ ግብጻውያን ወይንም ሱዳናውያን የችግሩ የጉዳቱ ተቋዳሽ ሲሆኑ አልታዩም።
ዛሬም በየቦታው ያሉት የሰላም እጦቶች የጎረቤት ሀገራትን ወይንም የአውሮፓና የእስያ ዜጎችን ለችግር አይዳርጉም። ራሳችንን እና የራሳችንን ዜጋ ብቻ ነው። አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ በጋራ ስንሠራ ግን ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ማድረግ እንችላለን። በእዚህ ሂደት የእኛ ብለን የለየነው የምንታገልለት ማህበረሰብም ጥቅም መጠበቁ የማይቀር ነው።
በሀገራዊ ጉዳይ አንድ ለመሆን አንድ ዓይነት መሆን አይጠበቅብንም። ቢገባንና ብናስተውል አይደለም በፈረሰች ሀገር ውስጥ ይቅርና ጥቅሟ ባልተረጋገጠበት ሀገር ውስጥ ሆነን የምንታገልለት ሕዝብ ሊኖር አይችልም። የምንደግፈውም ሆነ የምንመራው የፖለቲካ ፓርቲ ከሀገርና ከሕዝብ ጥቅም ሊበልጥብን አይገባም።
ቸር እንሰንብት።
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
በተስፋይ መንግስቱ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም