የኩሩ ህዝቦች መኖሪያ፣ የህብረ ብሄር ቡቃያ
የሰላም ተምሳሌት ዓርማ፣ የቀለሞች ኅብር ኢትዮጵያ
በደም አሻራሽ አትመው ህዝቦች ለሰጡን አደራ
ለህገመንግስታችን ክብር ታጥቀን ቆመናል በ ጋራ…
በሀገሩ የሚኮራ ሀገሩንም የሚያኮራ፣ ለዘመናት ጀግንነቱን እየደጋገመ ያስመሰከረ፣ የሀገሩን ሉዓላዊነት በማስከበር ፈጽሞ ግንባሩን የማያጥፍ፣ ድል ማድረግ ዜማው፣ ማሸነፍ ቋንቋው የሆነ፣ የአፍሪካ ኩራት የኢትዮጵያ መከታ፣ የራሱን የማይሰጥ የሰውም የማይነካ፣ ሰላምን ከፍ ለማድረግ ራሱ ዝቅ የሚል፣ ህዝቡን በነፃነት ለማኖር የደም ዋጋ የሚከፍል፤ ይህ ኃይል ማነው ተብሎ ቢጠየቅ አገር ሁሉ ተስማምቶ የኢትዮጵያ ወታደር ነው ማለቱ አይቀርም።
ከድሆች ጓዳ እስከ ገበሬው አጨዳ ድረስ ተሰማርቶ ሰላም የሚያስከብር ብቻ ሳይሆን ልማት የሚያሳልጥ የመከላከያ ኃይላችን የአገር ፍቅሩ ረቂቅ፣ ዲስፕሊኑ ጥብቅ፣ ተልዕኮው ትልቅ ርዕዩ ሩቅ ነው። የዚህ ጀግና ሰራዊት አካል ሆነው ሺዎች ግዳጃቸውን በላቀ ክብር ፈጽመው አልፈዋል። እሳት እሳት እየተካ፣ ኮከብ ኮከብን እየወለደ የኢትዮጵያ ማሕፀን ጀግና ማፍራቱን ቀጥሏል፤ ወደፊትም ይቀጥላል።
የኢትዮጵያን የነፃነት ታሪክ ስናስብ ይህንን ለመጠበቅና ለማስከበር የተሰውትን የኢትዮጵያ ልጆች በፅኑ እናስባቸዋለን። ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛች ሀገር ናት ስንል የቅኝ ግዛትን ቀንበር የሰበሩትን ኢትዮጵያውያንን ማሰብ ይኖርብናል። እንደ እሳት ወላፈን በሚጋረፉ የኢትዮጵያውያን አጥንቶች የታጠሩትን ድንበሮቿን ስናስብ አጥር ቅጥር ሆነው የወደቁትን ኢትዮጵያውያንን ማሰብ አለብን።
ኢትዮጵያውያን ሁሉ በተፈጥሮ ወታደሮች ናቸው። የኢትዮጵያ ወታደሮች ደግሞ የተፈጥሮ ወታደርነትን ከዘመናዊ ስልጠናና ከዲስፕሊን ጋር ያዋሀዱ ምርጦች ኢትዮጵያውያን ናቸው። ይህ ነው የዘመናት የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት የማሸነፍ ጥበብ”።
ከላይ በሰፊው ያቀረብነው መልዕክት የኢትዮጵያን መከላከያ አስመልክቶ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር ዓብይ አህመድ በአንድ ወቅት የተናገሩት ነው። እውነት ነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለዘመናት ለአገር ከከፈለው ክቡር መስዋዕትነት አንጻር ውለታውን በቃላት ድርደራ መግለጽ አዳጋች ነው።
አገርን ከወራሪና ከአሸባሪ ለ24 ሰዓት ነቅቶ መጠበቅ፣ ወገን ለተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ አደጋ በተጋለጠበት ወቅት ፈጥኖ ደርሶ መታደግ፣ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሁሉ የላቀ የቦንድ ግዢ ድጋፍ ማድረግ፣ ባልተጠበቀ የአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ የአርሶ አደሩ ሰብል አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ ጽኑ ክንድ መሆን ከአገር አልፎም ለአፍሪካ ህዝቦች የሰላም ዋስትና በመሆን በላብና በደሙ ወርቃማ ታሪክ የጻፈ ነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት! የዚህ ታላቅ ሰራዊት ክቡር ውለታ በገንዘብና በቁሳቁስ እንደማይከፈል ለማንም ግልጽ ነው። የመ ከላከያችን ከፍያ የአገርና የህዝብ ሰላም ውሎ ሰላም ማደርና የኢትዮጵያ ሉዓላ ዊነት ለዘላለም ተጠብቆ መኖር ነው። ይሁንና ለዚህ ታላቅ የመከላከያ ውለታ መንግሰት የአቅሙን ያህል ልዩ ትኩረት በማድረግ የሰራዊቱን ኑሮ ለማሻሻልና በአቅምና በብቃትም ከፍተኛ ደረጃ እንዲይዝ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
በተለይም የለውጥ አመራሩ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ አንስቶ ተምሳሌታዊ ሪፎርም በማካሄድ መከላከያን ኢትዮጵያዊ መልክ የማስያዝና በሁሉ መስክ ግዳጅ የመወጣት አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ የማሳደግ ሥራዎች ተሰርተዋል። ይህንን ምቹ ሁኔታ በመጠቀምም መከላከያችን ዛሬም እንደትናንቱ የአገሪቱን ሰላምና የህዝቦቿን ደህንነት በማረጋገጥ የኢትዮጵያ ወሳኝ ክንድነቱን እንደሚያረጋግጥ አይጠረጠርም!
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2012