“ኦግዚሞሮን” የግሪክ ቃል ነው። አቻ እስኪገኝለት ድረስ “ኦግዚሞሮን” እያልን እንቀጥላለን። ኦግዚሞሮን ዘይቤ (figure of speech) ነው። ቃሉን በምጥን ስናስቀምጠው ሁለት አብረው የማይሄዱ፤ ተቃራኒ ነገሮችን ልክ ተመሳሳይ ትርጉም እንዳላቸው አድርጎ በመጠቀም መልእክት ማስተላለፊያ መንገድና በንግግርም ሆነ በጽሁፍ (በፈጠራም ሆነ ኢ-ፈጠራ) አገልግሎት የሚሰጥ የአፃፃፍ ስልት ነው። (የበለጠ ለመረዳት ተቃራኒውን “Tautology”ንም መመርመር አይከፋም።)
በሌላው ዓለም የጥበብ ስራዎችን ለመመዘን ይሁን ሙያዊ አስተያየት ለመስጠት ስራዎቹን በፀጉር ስንጠቃ ደረጃ ማየት የተለመደና የሙያው አካል ነው። እዛ አንድን የኪነጥበብ ስራ ዝም ብሎ “ፐፐፐ…” ማለት ነውር ነው። በመሆኑም ሁሉንም ነገር በልኩና በመስመሩ፤ በተገቢ መስፈርትና መለኪያ መመዘን በመጀመራቸው ዜጎች ጥበብን ማጣጣምና ከጥበብ ማግኘት የሚገባቸውን እንዲያገኙ፤ የፈጠራ ባለሙያውም የበለጠ እንዲተጋና የተሻለ እንዲሰራ፤ ጥበብም እንድታድግ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።
ወደ እኛ ጋር ስንመጣ ያለውን ሁኔታ ከፀሀፊው የበለጠ አንባቢያን ስለምታውቁት ወደ ዝርዝር ውስጥ አንገባም።
ኦግዚሞሮን በጽሁፍ ስራዎች ውስጥ፤ ያለው ቦታ ከዚህ በመለስ የሚባል አይደለም። በግጥም ይሁን ልቦለድ፣ በታሪክ ይሁን በፍልስፍና፣ በሃይማኖትም ይሁን ፖለቲካው እየገባ የማገልገል ብቃት ያለው ዘይቤ ነው።
በፈጠራ ስራዎችና ከእነሱም ውጪ ከፍተኛ አገልግሎትን በመስጠት የሚታወቁ በርካታ የኦግዚሞሮን “ቤተሰቦች” ያሉ ሲሆን Act naturally, Alone together, Amazingly awful, Bittersweet, Clearly confused, ark light, living dead, darkly lit, sweet sorrow, Deafening silence, Definitely maybe እና የመሳሰሉት ተዘውታሪ ናቸው።
ስለ አንዳች ጥበባዊ ፋይዳ ሲባል ቴክኒኩን አብዝተው ከሚጠቀሙት ሰዎች ስንጀምር በቀዳሚነት የምናገኘው ያንኑ ዘመን አይሽሬ፤ የእንግሊዙን ዊሊያም ሼክስፒር ነው።
ሼክስፒር ኦግዚሞሮንን ይሁነኝ ብሎ በመጠቀም የሰራ ሲሆን ይህም ለከፍታ እንዳበቃው ስራና ህይወቱን ያጠኑ መስክረውለታል። በ”ሮሜዎና ጁሊየት” ሮሜዎ “Why, then, O brawling love! O loving hate! O anything, of nothing first create!” በማለት የተናገረውም ተዝወትረው ከሚጠቀሱለት ስራዎቹ አንዱ ነው (መስመር የተጨመረ)።
ወደ እኛ ስንመጣም አይብዛ እንጂ ቃሉ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ለማየት ተችሏል። በተለይም በፈጠራ ስራዎች ውስጥ እየተዘወተረ ስለ መምጣቱ የሚጠቁሙ የአሁኑ ዘመን ስራዎች ያሉ ሲሆን በተለይም በድምፃውያኖቻችን በኩል ኦግዚሞሮን እንደ አንድ የመልእክት ማጉያ ቁልፍ ብልሀት ሆኖ እናገኘዋለን። ቀደምት ፀሃፍትም ይህ ቀረሽ በማይባል ብቃት አገላብጠው ተጠቅመውባታል። ለዚህ ቀዳሚው “ተወርዋሪው ኮከብ” ሲሆን፤ እንዲህ ሲል ተቀኝቶም እናነብለታለን፤
አወይ የኔ ነገር እንዳው ተለባብሶ፣
መስቀል ተሰላጢን ዘፈንና ለቅሶ።
ሀገሬ ተባብራ ካረገጠች እርካብ፣
ነገራችን ሁሉ የእንባይ ካብ የእንቧይ ካብ። (ዮፍታሄ ንጉሴ፤ መስመሮች የተጨመሩ)
ይህ የዮፍታሄ “መስቀል ተሰላጢን” ስራ ተፅእኖ ፈጣሪ ሲሆን በድምፃዊ ቴዲ አፍሮ አማካኝነትም ወደ እዚህኛው ትውልድ ተሻግሮ ተደማጭነትን ያገኘ ስራ ነው።
ሌላው የኦግዚሞሮን ዘይቤ ተጠቃሚ ደማሙ ብእረኛ መንግስቱ ለማ ሲሆኑ ከበርካታ ስራዎቻቸው መካከልም “ባለ ካባና ባለ ዳባ”ን (ርእሱ ራሱ) ጠቅሶ ማለፉ በቂ ነው። (አንድ ሰው ባንዴ ባለ ዳባም፤ ባለካባም ሊሆን ስለማይችል።)
ወደ አሁኑ ዘመን ስንመጣ ኦግዚሞሮን በተለያዩ ዘውጎች ለተለያዩ ኪናዊ ፋይዳዎች አገልግሎት ላይ ውሎ የምናገኘው ሲሆን ከእነዚህ ዘውጎችም አንዱ ሙዚቃ ነው። ቴዲ አፍሮ አንዱና ምናልባትም ከዚህ ዘመን ድምፃውያን ኦግዚሞሮንን አብዝቶ የሚጠቀም ሲሆን የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል።
“ … የበደል አበባ . .”፤ “… እያነቡ እስክስታ …” (ድምፃዊው ይህን “Oxymoronic speech” መጠቀም ለምን አስፈለገው? የሚለውን ላንባቢ/አድማጭ ትተነዋል።)
ኦግዚሞሮን ከጥበብ ስራ ባሻገር በእለት ተእለት ንግግርና ማህበራዊ ህይወትም ሲዘወተር ለዚህም አንድ ሰሞን በፖለቲካው አውድ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው “ትሁት ነፍሰ ገዳይ” ተጠቃሽ ነው።
ይህንን ኦግዚሞሮን በአንድ ወቅት ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚ/ተከራካሪ ክርክር በሚያደርጉበት ወቅት የገዥውን ፓርቲ ወክለው ከሚሟገቱት አንዱ የነበሩት አቶ ሽመልስ ከማል ተቃዋሚዎችን (ለማሸነፍ?) በተደጋጋሚ ይጠቀሙበት እንደነበር ይታወሳል።
ወደ ኋላ፤ ወርቃማው ዘመን ስንሄድ ደግሞ ሙሉቀን መለሰን እናገኘዋለን።
እፍ ብለው ጠፋ ባነደው ከሰለ
ብፈልግ አጣሁኝ አንችን የመሰለ። (መስመር የተጨመረ)
ወደ ማጠናቀቁ እንሂድ። ከዛ በፊት ግን ይህ የኦግዚሞሮን ዘይቤ ለኛ አዲስ እንዳልነበረ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አንዱ ቃል ግጥም ነው። የሚከተለውን እንይ፤
ከማይሆን ሰው ጋራ ፍቅር መጀመር፣
ውሃን በብርሌ ወዝቶ ማደር
ንብን በገለባ አህያን በማር። (መስመር የተጨመረ)
አልተገረማችሁም።? በጥበብ መራቀቅ፣ መጥበብ መጠበብ ለኢትዮጵያውያን አዲስ አይደለም የሚባለውን የሚያረጋግጥስ አይደለምን??
ለማጠናቀቅ፤ በሌላው አገር ስራዎችን፤ በተለይም የፈጠራ ስራዎችን በመላ የማሄስ፤ ዝም ብሎ ማድነቅና መደናነቅ፣ ፐፐፐፐ … ብሎ ማለፍ ወዘተ ከቀረ ቆየ። በእይታ/Perspective ያልተደገፈ፣ መስፈርት የሌለው፣ አቅጣጫው የማይታወቅ፣ በፈርጅ በፈርጁ የማያይ አሂያሂያስ ጉዳቱ፣ ጥበብ ገዳይነቱ፣ የፈጠራ ሰዎችን ላልተፈለገ ስንፍናና ቅጥፈት የመዳረጉ ጉዳይ ግንዛቤ በመያዙ ወግድ ከተባለ ሰነባበተ። በምትኩም በፀጉር ስንጠቃ ደረጃ ማየቱ እየተዘወተረ፣ እየተወደደ፣ ከጉዳቱ ጥቅሙ እያየለ፣ ጥበባዊ ፋይዳው እየናረ በመመጣቱ ተወዳጁና ተደናቂው የአሂያሂያስ መንገድ ይሄው ብትንትን አድርጎ የማየቱ ጉዳይ ሆነና እየተሰራበት ይገኛል።
እኛስ ጋር? “የኛን ዝም ነው” የሚሉ መኖራቸው ሁሌ እየተሰማ ነው። በእርግጥም እውነታቸውን ይመስላል። አንዳንድ ሂሶች ሲሰሙና ሲነበቡ ተስፋ የሚያስቆርጡ ብቻ ሳይሆኑ ጥበብና ጥበበኛውን ይዘው ወደ ገደል በመንደርደር ላይ ሁሉ ያሉ ይመስላሉ። ከነፈሰው ጋር የሚነፍሱ አስተያየቶች መአት ናቸው። ከጥቂት ዓመታት በፊት “ሰንደቅ” እንዳስነበበን ከሆነ “ባይበላስ ቢቀር” ሁሉ የሚያስብሉ ሂስ መሳይ ሂሶች እየተሰሙ ነው። “አሁን በኢትዮጵያ የሥነጽሁፍ ታሪክ አንደኛ አዳም ረታ፣ ሁለተኛ አዳም ረታ፣ ሶስተኛም አዳም ረታ” ይሉ ጥናታዊ ጽሑፍ/ሂስን ምን ይሉታል? እሱ ራሱ እንዲታዘብ እድል ይፈጥርለታል እንጂ ምን ፋይዳ አለው – ለሱም፣ ለስራውም፣ ለአገሪቱ ሥነጽሑፉም።? (ሂሱ ቢያንስ አስተያየቱን በዘመን ከፋፍሎ ቢያቀርብልን ኖሮ እኛም ይህን ባላልን ነበር። ከላይ በፀጉር ስንጠቃ ደረጃ … ያልነው ሆኖ ቢሆን ሃያሲ ተብየው ቢያንስ ለእንደዚህ አይነቱ ትዝብትና አስቂኝነቱ ላመዘነ ስራ አይዳርግም ነበር።
(ይህ ጽሁፍ ቃሉን በማስረጃ ከማስተዋወቅ ያለፈ እንዴት? ለምን ኪናዊ ፋይዳ ሲባል? ወዘተ የሚሉትን እንደማይመልስ እየጠቆምኩ ጠለቅ ብሎ ለማወቅ የፈለገ እዚሁ በተሰጡት ምሳሌዎች ላይ ብቻ ተመስርቶም ቢሆን ምላሽ ማግኘት ይችላል፡፡)
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2012
ግርማ መንግሥቴ