የአገራችን ወጣቶች ለለውጥ ምክንያት የመሆን ታሪካዊ ዳራቸው በርከት ያሉ ቢሆንም የ1960ዎቹ እና የ1997ቱ ግን በታሪክ ፍፁም የሚዘነጉ አይደሉም። ከእነዚህም በኋላ ባሉ የለውጥ ጊዜያትም የወጣቱ ሚና የጎላ ነው። በአሁኑ ወቅት ሁለት ዓመት እየሞላው ለሚገኘው አገራዊው የለውጥ ሁኔታ የወጣቱ ሚና የሚዘነጋ አይደለም።
ይሁን እንጂ አሁን ባለንበት በዚህ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች ዋና ተዋናይ ሆኖ የሚታየው ወጣቱ ቢሆንም ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ‹‹ወጣቱን የሚሰበስበው ማህበር ባለመኖሩ ነው›› የሚል በአንድ ወገን ‹‹አይደለም አገር እንዳትረጋጋ የሚፈልጉ ሃይሎች የሚነዙት ተንኮል ድምር ውጤት ነው›› የሚሉ ደግሞ በሌላ ወገን ይነሳል ሐቁ የቱ ነው? የሚለው የዚህች ጽሁፍ ማጠንጠኛ ነው።
ወጣት እዮብ ብርሃኑ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሲሆን በጅቡቲ መስመር የከባድ መኪና አሽከርካሪ ነው። የሥራው ባህሪም በተለያዩ አካባቢዎች ስላሉ ወጣቶች መጠነኛ ግንዛቤ እንዲጨብጥ አስችሎታል። እርሱ እንደሚለው ህጋዊ የወጣት ማህበራት አደረጃጀቶች በሚፈለገው ደረጃ ሚናቸውን ባለመወጣታቸው ወጣቱ ርዕስ በርዕሱ እየተነጋገረ ችግሮችን የሚፈታባቸው ምህዳር ጠቧል ይላል።
70 በመቶ የሚሆነው ወጣት የተበታተነ እንጂ የተደራጀ አይደለም፤ የሚያሰባስበው የመንግሥት አደረጃጀት ባለመኖሩ ግለሰቦችና የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚፈልጉት መንገድ እያሰባሰቡ የመሰላቸውን ተግባር ማስፈፀሚያ አድርገውታል ይላል። በዚህም የተነሳ አንዳንድ ወጣቶች ሳይገባቸው አገራቸውንና ወገናቸውን የሚጎዳ ተግባር ሲፈፅሙ ይታያሉ። እራሳቸውንም ችግር ውስጥ በመክተት የወደፊት ህይወታቸውን ያበላሻሉ። አላስፈላጊ መስዋዕትነትንም ይከፍላሉ ይላል።
ወጣቱ የሚደግፈው የፖለቲካ ፓርቲ ሊኖር ቢችል እንኳን ከስሜት ነፃ ሆኖ እራሱንም አደጋ ላይ ሳይጥል ሌሎች ወገኖቹንም ሳይጎዳ በሰላማዊ መንገድ ሐሳቡን ማራመድ ይገባዋል ይላል። እውነተኛ የአገር ተቆርቋሪነትና ፍትሐዊ አመለካከት ያለው አንድ ወጣት ነገሮችን በጥበብ ተመልክቶ አገሩን ወደ ሚፈልገውና ወደ ሚመኘው ዕድገት ማሻገር እንደሚገባው እዮብ ጠቅሷል።
ከምንም በላይ ወጣቱ ህይወቱን አደጋ ውስጥ ከሚያስገቡ ተግባሮች ታቅቦ በማህበራት በመደራጀት ሰላማዊ የመነጋገሪያ መድረኮችን በመፍጠር ችግሮቹን ተወያይቶ የመፍታት ልምድ ሊያዳብር ይገባል ይላል። አሁን ላይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች የተለያዩ አስተሳሰቦችን እንዲያራምዱ ክፍተት የሆነው አንድ ዓይነት አጋራዊ እሳቤ ላይ የተመሰረተ የወጣት አደረጃጀት ባለመኖሩ እንደሆነ እዮብ ያስረዳል።
ወጣት ህዝቅኤል አያሌው በአዲስ አበባ ከተማ የመሰናዶ ትምህርት ተማሪ ነው። ወጣትነቱን ከታላላቆች የሚማርበት፣ ክፉና ደጉን የሚለይበት፣ ለመጪው ዘመን መሰረት የሚጥልበት፣ የእድሜ ክልል እንደሆነ ያምናል። እንደ ህዝቅኤል ገለፃ አሁን ላይ በአንዳንድ ወጣቶች የሚፈፀመው አላስፈላጊ ተግባር በወጣቱ ንቃተ ህሊና ላይ ጠንክሮ ካለመሥራት የመጣ ነው። ወጣቶችን ማደራጀት፣ ማንቃትና በአስተሳሰብ ማበልፀግ በርካታ ችግሮችን ለማስወገድ አቅም ይፈጠራል። ነገሮችን በግብታዊነት ከመፈፀም ይልቅ ምክንያታዊ ወይም ተጠይቃዊ ለመሆን ያስችላል፤ ትዕግስትና የማሰላሰል ፋታን ይሰጣል፤ ኃላፊነትንም ያጎናጽፋል። ስለሆነም ወጣቶች በተለያዩ አጋጣሚዎች እየተገናኙ ሐሳብ የሚለዋወጡባቸውን እና የሚተራረሙባቸውን መድረኮች መፍጠር ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን በሐሳብ ልዕልና የማመን ልምድ ይዳብራል።
እንደ ህዝቅኤል በየትምህርት ቤቱ ክበቦችን በማቋቋም በተለይም ወጣቱን ስለ አገሩ ጉዳይ በቂ እውቀት ማስጨበጥ፣ ማወያየትና ማነጋገር ኃላፊነትና አደራን እንደመስጠት ነው። የጋራ አገራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ ሁሉን አቀፍ የጋራ መድረኮችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል። በተለይም የወጣት ማህበራት መስፋፋትና መደራጀት ይህን ችግር ለመፍታት ብቸኛው አማራጭ በመሆኑ ትኩረት የሚያስፈልገው ጉዳይ እንደሆነ ያምናል።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ዋና ጸሐፊ ወጣት ይሁነኝ መሐመድ እንደሚያስረዳው አሁን በአገሪቱ እየተስተዋለ ያለው ችግር ወጣቱ በመበታተኑና የሚያሰባስበው ሕጋዊ የመንግሥት አደረጃጀት ባለመኖሩ ነው የሚለውን አስተያየት አይቀበልም። ይልቁንም የብሔርም ይሁን የሃይማኖት ችግሮች መነሻቸው የወጣቶች መበታተንና ያለመሰባሰብ ጉዳይ ሳይሆን አገሪቱ እንዳትረጋጋ የሚያደርጉ አጀንዳዎች ተቀርፀው በወጣቱ ውስጥ እንዲያደጉና እንዲበለፅጉ በመደረጉ ነው።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ቀደም ሲልም ይሁን አሁን ባለው አሠራሩ ማንኛውም ወጣት አባል በመሆን ሐሳቡን በነፃነት መግለፅ የሚችልበትን አሠራር ይከተላል። ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችንም ማዕከል ያደረጉ የውይይት መድረኮችን ያካሂዳል። ወጣቱ አሉታዊ ከሆኑ እንቅስቃሴዎች እራሱን ጠብቆ ምክንያታዊ እይታውን በማስፋት የሐሳብ ደጋፊና ነቃፊ ብቻ መሆን እንዳለበት ግንዛቤ እየተሰጠው መሆኑን ተናግሯል። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን በየአካባቢው ለራሳቸው ስያሜ የሰጡ ወጣቶች መኖራቸውን ጠቅሶ እነዚህ ወጣቶች በአገራቸው ጉዳይ አንድ የሚያደርጋቸውን የጋራ ጥያቄ አንግበው መነሳት ሲገባቸው በየፊናቸው የሚከተሉት አካሄድ ጥሩ ያለመሆኑን አስረድቷል። ወጣቶች በቋንቋ ፣ በብሔርና በሃይማኖት እኩልነት ላይ የሚፈለገውን ግንዛቤ እየያዙ አለመምጣታቸው ዛሬ በዩኒቨርሲቲና በተለያዩ መድረኮች ላይ ሲገናኙ ተመሳሳይ ዕይታ እንዳይኖራቸው አድርጓቸዋል ይላል።
ይሁንና ማህበሩ ግን አገራዊ ገጽታ ያላቸው የሰላም ኮንፈረንሶችን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር በመሆን በጋራ ማዘጋጀታቸውን ጠቅሷል። በመድረኮቹም ስለ ማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምና ሐሰተኛ መረጃን አስመልክቶ ልምድ መለዋወጥ ተችሏል። ከሰላም ሚኒስቴር ጋር ተመሳሳይ መድረኮችን ለማዘጋጀትም በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ወጣቱ ይገልፃል።
በመጨረሻም የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ወቅታዊ ችግሮችን ከመፍታት በዘለለ ዘላቂ መፍትሄን ሊያስገኙ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንዳለባቸውም ይመክራል። እያንዳንዱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማትና ትናንሽ ስብስቦች ሁሉ ወጣቶችን ወደ ትክክለኛ መንገድ በማምጣት በኩል መንግሥትን ማገዝ እንደሚገባቸው ጥሪ አስተላልፏል።
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2012
ኢያሱ መሰለ