ፍርድ ቤቶቻችንን በወፍ በረር
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
መንግሥትን ሦስት አካላት ናቸው አምዶች ሆነው የሚያቆሙት – ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ። ሕግ ተርጓሚዎቹ ፍርድ ቤቶች ናቸው። እነዚህ አካላት አንዱ ከሌላው ሳይልቁ ወይም ሳያንሱ በእኩልነት፤ እንደ ሞሰብና እንደ እፊያው ተጠባብቀው አገርን ያስተዳድራሉ።
የመንግሥት ሥልጣን በእነዚህ አካላት የተከፋፈለበት ሁነኛ አመክንዮ ለግልጽነት፣ ለተጠያ ቂነትና ለፍትሐዊነት ነው። ሦስቱም በየራሳቸው ነፃና ገለልተኛ ሆነው ራሳቸውን የቻሉ አካላት ቢሆኑም ቅሉ፤ በሕግ አግባብ አንዱ የሌላውን ሥራ ይመዝናል፣ ይገመግማል፣ እርምት እንዲወሰድ ያደርጋል።
ከሦስቱም አካላት ታዲያ በተለይም ፍርድ ቤቶች በአደረጃጀትም ሆነ በአሠራራቸው ብርቱ ጥንቃቄን የሚጠይቁ ተቋማት ናቸው። ሕዝብ ንብረቱን ቢዘረፍ፣ መብቱን ቢገፈፍ “አቤት!” የሚለው ለፍርድ ቤት ነው። ተራውም ዜጋ ሆነ ልሂቅ ሹመኛው እኩል የሚቆምበት ቦታ የፍርድ አደባባይ ነው።
እናም ፍርድ ቤቶች በአገር ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ሚና አላቸው። ለሕግ የበላይነት መከበር፣ ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መረጋገጥ ከፍርድ ቤቶች በላይ ጠበቃ የለም። ይሁንና ፍርድ ቤቶች ለሥም ብቻ ሕንፃቸው አምሮና አጊጠው ስለታዩ ሚናቸውን ይጫወታሉ ማለት አይደለም።
በተለይም ከተጽዕኖ ነፃና ከወገንተኝነት የጸዱ ካልሆኑ የከፋ ጉዳት እንደሚያስከትሉ ሩቅ ሳንሄድ ከቅርብ ጊዜ ታሪካችን የምንማረው ሐቅ ነው። የአገራችን ፍርድ ቤቶች የፖለቲካውን በትረ-ሥልጣን በሚጨብጠው የአስፈጻሚው ፈርጣማ ክንድ ውስጥ ገብተው የመገልገያ መሳሪያ ሆነው ሕዝብን ያስለቀሱባቸው ታሪኮች ጥቂት አይደሉም። ከሕዝቡም ተዓማኒነትን ማትረፍ ተስኗቸው ኖረዋል።
ከዚህም ሌላ በየዓመቱ በአደረጃጀትና በአሠራር ብልሹነት እንዲሁም በመልካም አስተዳደርና በሙስና ከሚታሙ ተቋማት በቁንጮነት የሚያስቀምጧቸውን ሪፖርቶች ደጋግመን አንብበናል። በየጊዜው የጉዳዮች መበራከትና የውስብስብነታቸው መጨመር እንደተጠበቀ ሆኖ እልባት ሳያገኙ ለዓመታት የሚንከባለሉ መዛግብት የትየለሌ ናቸው።
በተለያዩ ጊዜያት በተወሰዱት የማሻሻያ ዕርምጃዎች እፎይታን የሚሰጡ ውጤቶች ተገኝተዋል። ጥቂት የማይባሉ ጉዳዮች በወቅቱ እልባት ያገኛሉ። ሕግንና ማስረጃን መሰረት አድርገው ፍትሐዊ ውሳኔዎች የሚተላለፉባቸው መዛግብት ቀላል አይደሉም። እፍኝ ቢሆኑም ዘመናዊ አሠራሮችና ቴክኖሎጂዎችም በሥራ ላይ ውለዋል።
ይሁንና በሕግ ማዕቀፍ፣ በተቋማዊ አደረጃጀት፣ በአሠራር፣ በዘመናዊነትና በሰው ኃይል ያሉት ችግሮች እስከአሁንም አልተቀረፉም። ከመንግሥቱ መናገሻ ከአዲስ አበባ ጀምሮ እስከ ወረዳዎች ድረስ ያሉ ፍርድ ቤቶች በአብዛኛው የሕዝብን ዕንባ በስፍር የሚያጠጡ የብሶት ተቋማት ናቸው አሁንም።
ከጥንቱና ከባህላዊው የዛፍ ሥር የዳኝነት ሥርዓት ባልዘመነ መልኩ በተለይም በዞንና በወረዳ ከተሞች የሚገኙ የፍርድ ቤቶች እንኳን ሊገቡባቸው ሊያዩዋቸው የሚያስፈሩ አሮጌ “ሕንፃዎች” ናቸው። አብዛኞቹ ፍርድ ቤቶች የአጥሮቻቸው ዙሪያ በፍትሕ ደላሎች የተሞላ ስለመሆኑ መንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልጽ አድምጠነዋል። በዳኝነት ነፃነት ሽፋን ተጠያቂነት፣ ውጤታማነት፣ ቅልጥፍናና ተገማችነት ስጋት ውስጥ መውደቃቸውም ይነገራል።
ይህንን መነሻ በማድረግ ታዲያ መንግሥት ባለፉት ሁለት ዓመታት ለውጥ አመጣባቸዋለሁ ብሎ ከተንቀሳቀሰባቸው ተቋማት ውስጥ ፍርድ ቤቶች ግንባር ቀደሞቹ ናቸው። በተለይም በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የአሠራርና የአደረጃጀት ችግሮችን ለማስወገድ እየተሠራ ይገኛል። ጎን ለጎንም የፍርድ ቤቶችን የሕግ ማዕቀፍ ለማሻሻል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ቀርቧል።
አሁን በሥራ ላይ ለሚገኘው የፍርድ ቤቶች የሕግ ማዕቀፍ መሰረቱን የጣለው በ1988 ዓ.ም የወጣው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988 ነው። አዋጁ እስከአሁንም በሥራ ላይ ያለ ቢሆንም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ቁጥራቸው 138/1991፣ 254/1993፣ 321/1995 እና 454/1997 የሆኑ የማሻሻያ አዋጆች ወጥተውለታል። በተጨማሪም የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በክልሎችም እንዲደራጅ ያደረገ አዋጅ ቁጥር 322/1995 አለ።
አዋጆቹ እንዲህ መብዛታቸውና መበታተናቸው በአሠራር ላይ እንቅፋት ፈጥረዋል። ከዚህ በመነሳትም ወጥና የነባሮቹን አዋጆች ጉድለቶች በማረም አዳዲስ ጉዳዮችን አካትቶ ፍርድ ቤቶችን የተሻሉ ተቋማት ለማድረግ ያለመ አዲስ አዋጅ ተሰናድቷል።
እኛም በዚህ ጽሑፍ ከአዲሱ አዋጅ ጉዳዮች ውስጥ የሰበር ሰበር እና መሰረታዊ የሕግ ስህተት የሚሉትን ጉዳዮች መዝዘን እናብራራለን።
“የመጨረሻ ውሳኔ”
አገሪቱ በክልሎች የተዋቀረውን የፌዴራል ሥርዓት መተግበር ከጀመረች ጊዜ አንስቶ መሰረታዊ የሕግ ስህተት እና የመጨረሻ ውሳኔ የሚባሉት ጉዳዮች በዳኞች፣ በሕግ ልሂቃን፣ በአስተማሪዎች፣ በተማሪዎችና በፖለቲከኞች ሳይቀር እስከአሁንም ጎራ አስለይተው እንዳነታረኩ ይገኛሉ። በተለይም ሁለቱም ጉዳዮች ትርጓሜ ያልተ ሰጣቸው በመሆኑ የክልልና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ጸሐይ አይሙቀው እንጂ በብርቱ ሲጠዛጠዙ ነው የኖሩት።
በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 80 ላይ ሰፍሮ እንደም ናነበው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፌዴራል ጉዳዮች ላይ የበላይና የመጨረሻ የዳኝነት ሥልጣን አለው። የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም በበኩሉ በክልሉ ጉዳይ ላይ የበላይና የመጨረሻ የዳኝነት ሥልጣን አለው።
ከዚህ ሌላ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበትን ማንኛውንም የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም በሰበር ችሎት የማየት ሥልጣን ሲኖረው የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም በተመሳሳይ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበትን በክልል ጉዳዮች የተሰጠ የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም በሰበር የማየት ሥልጣን ተሰጥቶታል።
ከዚሁ ጋር አይይዞ ታዲያ አዋጅ ቁጥር 25/1988 የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠበትን መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበትን ጉዳይ በሰበር እንዲያይ ሥልጣን ሰጥቶታል።
ይሁንና መሰረታዊ የሕግ ስህተት የሚለውንም ሆነ የመጨረሻ ውሳኔ በሚል የተገለጸውን ጉዳይ ትርጓሜ ሊያስቀምጡለትና መከራከሪያ እንዳይሆን ሊያደርጉት የሚገባቸው አዋጅ ቁጥር 25/1988ም ሆነ ተከታትለው የወጡት ማሻሻያዎቹ በዝምታ አልፈውታል። በዚሁ መነሻ የጉዳዩ አከራካሪነት ሦስት አስርት ዓመታትን ተሻግሯል።
የክርክሩ ማጠንጠኛ ደግሞ ወዲህ ነው – ከላይ እንደተገለጸው ሕገ-መንግሥቱ በአንድ በኩል “የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፌዴራል ጉዳዮች ላይ የበላይና የመጨረሻ የዳኝነት ሥልጣን አለው” ይላል። ጥቂት እልፍ ብሎ ደግሞ “የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበትን ማንኛውንም የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም በሰበር ችሎት የማየት ሥልጣን አለው” ይላል።
ከዚህ ነው እንግዲህ የክርክሩ እሰጥ-አገባ የሚቀዳው። ይህ የሕገ-መንግሥቱ “የመጨረሻ ውሳኔ” የሚለው አገላለጽ በክልል ሰበር ችሎቶች ውሳኔ ያገኙ ጉዳዮችንም ይጨምራል ወይስ አይጨምርም የሚለው ነው ዓይነተኛው መከራከሪያ። “መሰረታዊ የሕግ ስህተት” የሚባለውስ መለኪያው ምንድን ነው የሚለውም አከራካሪ ነው።
የፌዴራል ሰበር ችሎት በአገሪቱ “የመጨረሻው የዳኝነት አካል ነው” በሚል የሚሞግቱ ወገኖች “የመጨረሻ ውሳኔ” የሚለው ሀረግ በፌዴራልም ሆነ በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተቋጬ የትኛውንም የመጨረሻ ውሳኔ ያጠቃልላል ባይ ናቸው። በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የታዩ ጉዳዮችንም ጨምሮ ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ “የሰበር ሰበር (Cassation over cassation)” በፍርድ ቤቶች ሥርዓት ውስጥ ያለ መሆኑን ያሳያል።
በተቃራኒው የሙግት ዋልታ ላይ የቆሙት ደግሞ “የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፌዴራል ጉዳዮች ላይ የበላይና የመጨረሻ የዳኝነት ሥልጣን አለው” የሚለውን የሕገ-መንግሥቱን ሀረግ መዝዘው የፌዴራል ሰበር ችሎት በፌዴራል ጉዳዮች ላይ እንጂ በክልሎች ጉዳይ ላይ ሥልጣን እንደሌለው ይከራከራሉ። አያይዘውም የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልሉ ጉዳይ ላይ የበላይና የመጨረሻ የዳኝነት ሥልጣን እንዳለው ሕገ-መንግሥቱ መደንገጉን ያወሳሉ።
በተለይም ከፌዴራል ሥርዓቱ በመነሳት የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች በየራሳቸው ያላቸውን ጣምራነትና መሳ የዳኝነት ስልጣን (Dualism) በማንሳት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከፌዴራል ጉዳዮች ውጪ በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት የተወሰኑ የክልል ጉዳዮችንም የማየት የመጨረሻ ሥልጣን ሊኖረው እንደማይችል ይሞግታሉ። ከዚህ ውጪ የሰበር ሰበር የሚኖር ከሆነ የማዕከላዊውን መንግሥት የበላይነት የሚያመጣ ስለመሆኑም ይገልጻሉ።
ይህ የሰበር ሰበር ጉዳይ የሕገ-መንግሥት ክርክር በመሆኑ እልባት ማግኘት ያለበት በሕገ-መንግሥቱ ተርጓሚ አካል ማለትም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው። ይሁንና ሕገ-መንግሥቱን ያረቀቁትን የያኔዎቹን ሰዎች ሃሳብና አመክንዮ ከሕገ-መንግሥት ጉባዔው ቃለ-ጉባዔና ከአገሪቱ መሰረታዊ የፌዴራሊዝም አምዶች አንጻር ተመዝኖ እስከአሁን እልባት ሊሰጠው አልተቻለም።
ያም ሆነ ይህ በአሁኑ ወቅት የሰበር ሰበር አለ የሚለው አመለካከት ሚዛን ደፍቷል፤ እየተተገበረም ያለው ይኸው ነው። በተለይም የሰበር ችሎቱ የሚሰጠው የሕግ ትርጉም በየትኛውም ደረጃ ላይ በሚገኝ የፌዴራል ወይም የክልል ፍርድ ቤት ላይ አስገዳጅነት እንደሚኖረው በአዋጅ ቁጥር 454/1997 በግልጽ በመደንገጉ የሰበር ችሎቱ የመጨረሻው የዳኝነት አካል ነው ለሚለው ሙግት የሕግ ድጋፍ ሆኗል።
በዚሁ መነሻ በፌዴራል ደረጃ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደርሶ ውሳኔ ያገኘም ሆነ ከየትኛውም ክልል እስከ ክልል ሰበር ደርሶ የተዘጋ ዶሴ ሁሉ በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመታየትና በመወሰን ላይ ይገኛል፡፡
ከሽሬም ሆነ ከሞያሌ፣ ከጎዴም ሆነ ከጋምቤላ ከእያንዳንዱ ቤተሰብና መንደር የሚመጣ ሙግት በየደረጃው ያሉ የክልል ፍርድ ቤቶችን አልፎ እስከ ክልል ሰበር ደርሶ ውሳኔ ቢያገኝም የመጨረሻውን መጨረሻ ለማስወሰን በሚል ተሟጋቾች ከዓመት ዓመት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት መዝገብ ቤትን እስከጣሪያው እየሞሉት ይገኛሉ።
ለፓርላማው የቀረበው የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ እንደሚያመለክተውም በተለይም የገጠር መሬት ይዞታንና አላባን የተመለከቱ አያሌ ክርክሮች እስከ ክልል ሰበር ውሳኔ ካገኙ በኋላ ለፌዴራል ሰበር አቤቱታ ለማቅረብ ከሩቅ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ባለጉዳዮች ለከፍተኛ ወጪና እንግልት እየተዳረጉ ይገኛሉ።
ጉዳዮቹም ከጊዜ ወደጊዜ በዓይነትና በብዛት እየጨመሩ መምጣታቸው የሰበር ችሎቱ በሚሰጠው የህግ ትርጉም ጥራት ላይ ዓይነተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል። ይህንኑ መነሻ በማድረግ ታዲያ ረቂቅ አዋጁ በክልል ሰበር ችሎት የታዩ ጉዳዮች ሁሉ ለፌዴራል ሰበር ችሎት እንዳይቀርቡ ከሚያደርግ አዲስ ሥርዓት ጋር ብቅ ብሏል።
ረቂቅ ሕጉ ጉዳዮች በክልል ሰበር ችሎት እልባት ካገኙ በኋላ ለፌዴራል ሰበር የሚቀርቡበትን የማጣሪያና የመለኪያ መስፈርት አስቀምጧል። በዚሁም መሰረት አንድ የመጨረሻ ውሳኔ ለፌዴራል ሰበር የሚቀርበው የሕገ-መንግሥቱን ድንጋጌዎች የሚቃረን ሲሆን፤ የፌዴራል ሰበር ችሎት የሰጣቸውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞች የሚቃረን ሲሆን እንዲሁም የሕግ ስህተቱ የተፈጠረበት ጉዳይ ሰፋ ያለ የህብረተሰብ ክፍልን በሚነካ መልኩ ሀገራዊ ፋይዳ የሚኖረው ሲሆን ነው።
ይሁንና የማጣሪያ መስፈርቶቹ ለትርጉም የተጋለጡና መግባባት ላይ የማያደርሱ (Subjective) መመዘኛዎች ናቸው። በክልል ሰበር የተወሰነ የመጨረሻ ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት እስከተገኘበት ድረስ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ከሕገ-መንግሥቱን ድንጋጌዎች የሚቃረንበት ዕድል ሰፊ ነው። ከዚህም ሌላ “የሕግ ስህተቱ የተፈጠረበት ጉዳይ ሰፋ ያለ የህብረተሰብ ክፍልን በሚነካ መልኩ ሀገራዊ ፋይዳ የሚኖረው ሲሆን” የሚለው በራሱ ለትርጉም የተጋለጠና በተግባር ላይ በሚውልበት ጊዜ አስቸጋሪ እንደሚሆን ግልጽ ነው።
በዚህም መነሻ የሰበር ችሎቱ በመዛግብት ላይ ውሳኔ ለመስጠት ከሚያደርገው ጥረት ባልተናነሰ መልኩ ጉዳዩ ለሰበር መቅረብ አለበት/የለበትም የሚለውን በማጥራትና በመመዘን ሰፊ ጊዜና ጉልበት ሊወስድ እንደሚችል ከወዲሁ መገመት አያዳግትም።
በመሆኑም ረቂቅ አዋጁ በደንብ ተፈትሾ መስተ ካከል ይኖርበታል። የመለኪያ መስፈርት ከማስቀመጥ ይልቅ የሰበር ችሎቱን ለ110 ሚሊዮን ሕዝብ የሚመጥን ማድረግ የተሻለ ነው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አንድ የሰበር ችሎት ብቻ በመኖሩ በጉዳዮች ተጨናንቆ ኖሯል። እናም ችሎቶችን ማብዛት፣ የዳኞችን አቅም ማጎልበት፣ ቴክኖሎጂ መጠቀምና ችሎቱን በመላ አገሪቱ ተደራሽ ማድረግ የተሻሉ አማራጮች ናቸው።
እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው የረቂቅ ሕጉ በጎ ጎን በሕግ የመዳኘት ሥልጣን የተሰጠውም ይሁን ሌላ አካል የሚሰጡት የመጨረሻ ውሳኔ በሰበር ሊታረም እንደሚችል መደንገጉ ነው። ይህም ወታደራዊ ፍርድ ቤቶችም ሆኑ ሌሎች አካላት የሚሰጧቸው የመጨረሻ ውሳኔዎች ለሰበር ይቀርባሉ/አይቀርቡም የሚለውን የዓመታት ሙግት እልባት ይሰጣል።
“መሰረታዊ የሕግ ስህተት”
ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የቀረበ የመጨረሻ ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለበት የሚባለው ምን ዓይነት ስህተት ሲኖርበት ነው ለሚለው እስከአሁን በሕግ ምላሽ አልተሰጠውም።
በተዘረጋው አሠራር ግን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር አጣሪ ችሎት ላይ የሚሰየሙ ሦስት ዳኞች ለሰበር የቀረበው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለው/የለውም በሚለው ላይ ወስነው ትዕዛዝ እንዲሰጡበት ነው የሚደረገው።
ሦስቱ ዳኞች መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለበት በማለት ያስቀርባል የሚል ትዕዛዝ ከሰጡ ጉዳዩ አምስት ዳኞች ለሚሰየሙበት የሰበር ችሎት ይቀርባል። አምስቱ የሰበር ዳኞችም ጉዳዩ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለበት ካሉ ያርሙታል፤ ከሌለበት መሰረታዊ ስህተት አልተፈጸመበትም በማለት ይወስናሉ።
ከዚህ የምንረዳው በአጣሪ ዳኞች መሰረታዊ የሕግ ስህተት ስላለባቸው ለሰበር ያስቀርባሉ ከተባለ በኋላ በአምስቱ የሰበር ዳኞች ታይተው መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለባቸውም ተብለው ውድቅ የሚደረጉ ጉዳዮች የመኖራቸውን ያክል በአጣሪዎቹ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለባቸውምና አያስቀርቡም የተባሉ ነገር ግን የሕግ ስህተት ያለባቸው ጉዳዮች እንደሚኖሩ ነው። ይህም በሰበር መታየት የሚገባውን ጉዳይ አጣሪ ዳኞቹ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት ይግባኝ የማይባልበት ትዕዛዝ የሚሰጡበት ሰፊ አጋጣሚ መኖሩን ያሳያል።
ይህንን መሰረታዊ ችግር ለማስወገድ ረቂቅ አዋጁ አንድ የመጨረሻ ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለበት ለማለት የሚያሰኝ ሁኔታን ተርጉሞታል። በዚሁ መሰረት አንድ የመጨረሻ ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለበት የሚባለው በውሳኔው ላይ የተጠቀሰው የሕግ አንቀጽ ስህተት ስለሆነ፣ አላግባብ ስለተተረጎመ፣ ጭብጥ አላግባብ ስለተያዘ ወዘተ ብቻ ሳይሆን ስህተቱ በውሳኔው ላይ ፍትህን የሚያዛባ ጉልህ ውጤትን አስከትሎ ከሆነ ነው።
ትርጓሜው መቀመጡ በመንደርደሪያና በሐተታቸው ላይ ስህተት ኖሮባቸው በውጤት ደረጃ ፍትሕ የማያዛቡ ውሳኔዎችን ወደ ሰበር ከመድረስ የሚከለክል ነው። ይህም በዳኞች የውሳኔ የአጻጸፍና የሕግ አጠቃቀስ ስህተት ብቻ በውጤት ደረጃ ለውጥ የማያመጡ መዛግብትን ለሰበር እንዳይቀርቡ በማድረግ የጉዳዮችን መግበስበስ እንደሚቀንስ ይጠበቃል።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 4/2012
ገብረክርስቶስ