ኢትዮጵያና ካናዳ ያላቸው የብሔር ብዝኃነት እንዲሁም የፌዴራል ሥርዓት መከተላቸው ያመሳስላቸዋል፡፡ አገራቱ በንግድ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በኢነርጂ፣ በግብርና ውጤቶች ማቀነባበር፣ በመድኃኒትና በግብአት አቅርቦት፣ በቀጣናዊ ሰላምና ደህንነት፣ በፖለቲካ፣ በምሥራቅ አፍሪካ ሰላምና ደኅንነት እንዲሁም በሽብርተኝነትና በስደተኞች ጉዳይ ላይ በጋራ በመሥራት አምስት አስርት ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡
ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ የተያዘውን ግብ ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የካናዳ ድጋፍ ትርጉም ያለው እንደሆነም ይነገራል፡፡ መጪው ጊዜ የሰላምና የብልፅግና እንደሚሆን ተስፋ ሰንቀን በምንገኝበት በዚህ ወቅት በ33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ከመሳተፍ በተጓዳኝ በአገሪቱ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ መኖሩን በመገንዘብ የካናዳ የግል ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ የልዑካን ቡድናቸውን መርተው ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመሪነቱን ኃላፊነት ከተረከቡ ወዲህ ኢትዮጵያ ተስፋ ያላት አገር እንድትሆን የበኩላቸውን ተግባር እንዳከናወኑ ወደፊትም የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚያደርሱዋት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
ባለፉት 50 ዓመታት ካናዳን የመሩት መሪዎቿ አገራቱ ግንኙነታቸው በንግድና ኢንቨስትመንት ታጅቦ አሁን ካለበት የወዳጅነት ደረጃ ላይ እንዲደርስ በጎ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ ያ የመልካም ወዳጅነት ዘመን ዛሬ ላይ በአንድ ደረጃ ከፍ ያለ ትርጉም እንዲኖረው ሰሞኑን ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ጉብኝት ትልቅ ሚና ይኖረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ማጠቃለያ ባስተላለፉት መልዕክት በንግድና ኢንቨስትመንት ፣ የፆታ እኩልነትን በማስተዋወቅ ፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመታገል ላይ ያተኮረው የኢትዮጵያ ጉብኝታችንን አጠቃለናል ። አጋሮች ብቻ አይደለንም – ጓደኞች ነን ፡፡ እናም አብረን መስራታችንን እንቀጥላለን።ማለታቸውም መጪው ዘመን ለኢትዮጵያና ካናዳ ግንኙነት ብሩህ እንደሆነ ያመላከተ ነው!
አዲስ ዘመን የካቲት 4/2012