በፈረንጆቹ 2019 መጨረሻ አካባቢ ሁዋን በተሰኘችው የቻይናዋ ከተማ የተከሰተው ኮሮና የተሰኘው አዲስ ቫይረስ ዓለምን እያነጋገረ ይገኛል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ቫይረሱ እስከ አሁን በትንሹ አስራ ስድስት በሚሆኑ አገራት ተዛምቷል፤ በቻይና ብቻ ከ900 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት መንስኤ ሆኗል። ቫይረሱ በፍጥነት በመዛመት በርካታ ሰዎችን መያዙም በቻይና ተከስቶ ከነበረው የሳርስ ቫይረሰ የከፋና በገዳይነቱም ወደር ያልተገኘለት ተብሏል።
የዓለም ጤና ድርጅት ገና ከመነሻው ‹‹ቫይረሱ የዓለም ትልቅ ሥጋት ነው›› ሲል አስገንዝቧል።በቫይረሱ የሰጉ አገራትም ወደ አገራቸው የሚገቡ ቻይናውያንና በሌሎች ዜጎች ላይ ጥብቅ ምርመራ ለማድረግ ተገደዋል።
አፍሪካን ብቻ ብንመለከት ኬንያን ጨምሮ አንዳንድ አገራት ደግሞ ወደ ቻይና የሚያደረጉትን የአውሮፕላን በረራ ጭምር እስከ ማቋረጥ ደርሰዋል። አውሮፕላኖቿ በሳምንት ከሃያ ጊዜ በላይ ወደቻይና የሚበሩባት ኢትዮጵያም፣በተርሚናሎች አካባቢ በመንገደኞች ላይ ከምታደርገው ጠበቅ ያለ የጤና ፍተሻ ውጭ እያደረገች ትገኛለች።
ቫይረሱ አለባቸው የተጠረጠሩ አስራ አንድ ኢትዮጵያውያን መገኘትም በሀገሪቱ ላይ ሥጋት አሳድሮ የቆየ ሲሆን፣ በምርመራ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጧል።ለተጨማሪ ምርመራም የደም ናሙናቸው ደቡብ አፍሪካ ተልኮ የስምንቱ ነፃ መሆኑ ሲታወቅ የሦስቱ ውጤት እየተጠበቀ ይገኛል።ሀገሪቱ ሰሞኑን ደግሞ የኮሮና ቫይረስ የላቦራቶሪ ምርመራ ማድረግ ጀምራለች።
በኮሮኖ ቫይረስ ዙሪያ ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ብዙ ያሉ ቢሆንም፣ቫይረሱ እንዴት ሊከሰት ቻለ በሚለው ዙሪያ ግን ጥልቅ መረጃዎች በስፋት ሲወጡ አልታዩም። ሰሞኑን ግን ቢቢሲ በጤና ገፁ ኮሮና ቫይረስ የመከሰቱን ሚስጥር በተመለከተ ዝርዝር ዘገባ ይዞ ወጥቷል።
በአዳዲስ የጤና ጠንቆች ላይ የሚመራመሩት ፕሮፌሰር ቲም ቤንተን ዋቢ በማድረግ የቀረበው ይህ ዘገባ፣ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በተለይ በኢንፌክሽን የሚተላለፉ በሽታዎች ከእንስሳት ወደ ሰዎች እየተላለፉ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። በሽታዎቹ በአዝጋሚ ሂደት እንደሚተላለፉ ገልፀው፣ በፍጥነት ሲዛመቱ መቆየታቸውን ይገልፃሉ።
ፕሮፌሰሩ የ1980 ኤች አይቪ ኤድስ ቀውስ ምንጭ ዝንጀሮ መሆኑን፣ ከ2004 እስከ 2007 የተከሰተውና ዓለምን ያሸበረው ‹‹በርድ ፍሉ›› የተሰኘው ቫይረስ መነሻ ወፎች መሆናቸውንና በ2009 የተከሰተው ‹‹ስዋይን ፍሉ›› በአሳማ ምከንያት መፈጠሩን በአብነት ይጠቅሳሉ። የሳርስ ቫይረስ መነሻም የሌሊት ወፍ እንደሆነና ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሌሊት ወፎች ኢቦላ የተሰኘውን አደገኛ ገዳይ በሽታ ሊፈጥሩ እንደቻሉም አስታውሰዋል።
ሰዎች በአብዛኛው በሽታ የሚይዛቸው ከእንስሳት መሆኑንም ፕሮፌሰሩ ይጠቅሳሉ። ‹‹በሽታ እንዴት ከእንስሳት ወደ ሰው ሊተላለፍ ይችላል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው›› ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ አብዛኛዎቹ እንስሳት ‹‹ፓቶጂንስ›› የተሰኘና ለሞት የሚያበቃ ባክቴሪያና ቫይረስ እንደሚሸከሙ ይገልፃሉ።
የአየር ንብረት ለውጥ ደግሞ በሽታው ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍበትን ሂደት በእጅጉ እንዳፋጠነው ይናገራሉ። በተለይ በከተማ የሚኖሩ ህዝቦች ቁጥር እየጨመረ መምጣትና የሰዎች ዓለም አቀፍ ጉዞዎችና እንቅስቃሴዎች መጨመር ለእነዚህ በሽታዎች መፈጠርና በፍጥነት መዛመት አይነተኛ ሚና መጫወታቸውን ያብራራሉ።
እንደ ፕሮፌሰሩ ገለፃ፤ የሰዎች የአኗኗር ሁኔታም በእጅጉ እየተለወጠ ነው። ከሃምሳ ዓመት በፊት በከተሞች ውስጥ የሚኖረው 35 በመቶ የሚሆነው የዓለም ህዝብ በአሁኑ ወቅት ወደ 55 በመቶ ከፍ ብሏል። ይህ ሁኔታም በተለይ የከተሞች መስፋፋትን በማስከተሉ እነዚህ ትላለቅ ከተሞች የያዟቸው አረንጓዴ ቦታዎች በተለይ በፓርኮችና መናፈሻዎች ውስጥ መኖር ለሚችሉ አይጦች፣ ፍልፈሎች፣ ቀበሮዎች፣ ወፎች፣ ተኩላዎችና ጦጣዎች፣ ሌሎችም እንስሳቶች ሁነኛ መጠለያ ለመሆን በቅተዋል።
የዱር እንስሳትም በአብዛኛው ምግብ እንደ ልብ በማግኘታቸው ከዱር ህይወት ይልቅ በከተሞች ይበልጥ ስኬታማ እየሆኑ መጥተዋል። በዚህም ምክንያት ከተማዎች የበሽታዎች መራቢያ ማዕከል በመሆን ላይ ይገኛሉ።
ኮሮና ቫይረስም የዚሁ ክስተት ውጤት ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉም ነው ያመለከቱት።
እንደ ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ፤ ለበሽታው በዋናነት የሚጋለጡት ድሀ በሚባሉ ከተሞች የሚኖሩና በፅዳት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች የተመጣጠኑ ምግቦችን እንደልብ ባለማግኘታቸው፣ ለተበከለ አየር ተጋላጭ በመሆናቸውና በቆሻሻ አካባቢዎች ላይ በመኖራቸው ምክንያት ደካማ በሽታ የመከላከል አቅም ነው ያላቸው።
አዳዲስ ኢንፌክሽኖች ሰዎች በጥግግት በሚኖሩ ባቸውና ተመሳሳይ አየር በሚተነፍሱባቸው ትላልቅ ከተሞች ላይ ሊስፋፉ እንደሚችሉም ፕሮፌሰሩ የጠቆሙ ሲሆን፤ አንዳንድ ሰዎችም በባህላቸው የከተማ የዱር እንስሳቶችን ለምግብነት መጠቀማቸውም የቫይረሱን ስርጭት ከፍ እንደአደርገው ተናግረዋል።
የኮሮና ቫይረስ የሰዎችን ባህርይ እንደቀየረም ፕሮፍሰሩ ይገልፃሉ። በዚህም ምክንያት ልዩ ልዩ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የሰዎች ጉዞዎች መታገዳቸውን፣ ወቅትን ጠብቀው ድምበር የሚሻገሩ ሠራተኞች ጉዞም መስተጓጎሉን ለአብነት በመጥቀስ ያብራራሉ።
አዲሱን የኮሮና ቫይረስ ክስተት ለመቀነስም ፕሮፌሰሩ መፍትሄ ናቸው ያሏቸውን ምክረ ሐሳቦችንም ሰጥተዋል። ቫይረሱ በግለሰብ ደረጃ ቀውስ እያስከተለ የመሆኑን ያህል ህብረተሰቡና መንግሥታት እያንዳንዱን አዳዲስ ኢንፌክሽን ማከም እንደሚጠበቅባቸው ያሳስባሉ።
አብዛኛዎቹ የከተማ ነዋሪዎች ለከተማ የዱር ህይወት ዋጋ እንደሚሰጡ ሁሉ አንዳንድ እንስሳት በሰዎች ጤና ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉም ማወቅ እንደሚኖርባቸው ያስገንዝባሉ። የትኛው እንስሳ በቅርቡ ወደ ከተማ እንደገባ መገንዘብና የትኞቹን እንሳሰት መመገብ እንደሚገባም ጥንቃቄ መውሰድ ይኖርባቸዋል።
እንደ ፕሮፌሰር ቲም ቤንተን ማብራሪያ፤ የአካባቢ ንፅህናን፣ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትንና የፀረ ተባይ ቁጥጥርን ማሻሻልም እንዲህ አይነቱ ቫይረስ እንዳይከሰትና እንዳይስፋፋ ለማድረግ ይረዳል። ሰዎች አካባቢያቸውን የሚይዙበትን መንገድና ከአካባቢዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማስተካከል ይገባቸዋል።
በዋናነት መታየት የሚገባው ጉዳይ ደግሞ በከተሜነትና በሰዎች መካከል የኑሮ ልዩነት እየሰፋ በሄደና የአየር ንብረትም እየተለወጠ በመጣ ቁጥር በቀጣይ የአካባቢ ሥነምህዳር እየተረበሸ እንደሚመጣና ኮሮናን የመሳሰሉና ሌሎችም ቫይረሶች እየተፈጠሩ እንደሚሄዱና አደጋቸውም እየጨመረ ሊመጣ እንደሚችል ያላቸውን ሥጋት ፕሮፌሰሩ ይጠቁማሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2012
አስናቀ ፀጋዬ